Saturday, 13 October 2012 10:54

የቴዎድሮስ ጥይቶች…ዒላማ!!

Written by  ምንተስኖት ገላግሌ
Rate this item
(5 votes)

ፍልስምና 2…ወተት ወይስ አጥንት?

የዛሬ አራት ዓመት ገደማ ቴዎድሮስ ተክለ አረጋይ ለየት ያለ ማለትም በኛ ሃገር ያልተለመደ ዓይነት መፅሃፍ ይዞ ብቅ ብሎ ነበር፡፡”ፍልስምና” በሚል ርዕስ የተለያዩ ታዋቂ ሰዎችን ኢንተርቪው አካትቶ በመጽሃፍ መልክ ሲያስጠርዘው” የምንፈልጋቸውን ሰዎች ይዞልን መጣ “ብለን ተደስተን ነበር፡፡ እንደ ከረሜላ የጣፈጡን፤ አኞ ሆነው ችክ ያሉብንም ነበሩ-ጥቂት (ለዛቸው ሳይሆን ያልሆኑትን ለመሆን የሞከሩት) ፍልስምና ቁጥር 1 በርግጥም ደስ የሚሉ ሃሳቦችን የሚያንሸራሽርና ለዛ ያለው ጥራዝ ነበር፡፡ የህይወት ፍልስፍናቸውን በርብሮ በማውጣቱ ብዙ አዳዲስ ነገሮችን ያየን ይመስለኛል፡፡እንዲህ ስንል ግን ሁሉም ጥሩ ነበሩ ማለት አይደለም፡፡አንዳንዶቹ አስገራሚ የሃሳብ መልካቸውን ሲያሳዩ ሌሎቹ ያልሆኑትን ለመምሰል ሲሞክሩ ዥንጉርጉር መልካቸውን ታዝበናል፡፡ የተውሶና የራስ ነገር ያሥታውቃል፡፡ ጋሽ ስብሃትን የመሳሰሉት ግን ከተፈጥሮ የተቀዳ ትክክለኛ ማንነታቸውን፣ሳይደበደቁ ፣አስገራሚ አተያዮችን አሳይተዋል፡፡ጋሽ ስብሃት የሚለየው የሌለውን ነገር ለመሆንና ለመምሰል ባለመሞከሩ ነው፡፡  ግልጽነቱ ደስ ይላል፡፡

 

በሁሉም ግልጽነቱ ባልስማማም፡፡ሌላው ቀርቶ ቴዎድሮስ ሲጠይቀው የሚናገረው ከሁላችንም ለየት ይላል፡፡ ለምሳሌ እንዲህ፡-“ጋሽ ስብሃት ኑሮ እንዴት ነው?” ይለዋል፡፡ጋሽ ስብሃት ሲመልስ፡-“እንደምታየው ነው፡፡ ሌላ ጫፍ ያለው ጥያቄ ስጠኝ እንጂ ገና ከመጀመራችን ድፍን ጥያቄ ምንድነው?…ኑሮ እንዴት ነው ብሎ ጥያቄ …ያው እንደሚኖሩት ነው፡፡እንደምታየኝ ነው፡፡ይህን እመስላለሁ አሁን፡፡” ጋሽ ስብሃት ልዩነቱ እዚህ ላይ ነው፡፡እኛ ሰው ደስ እንዲለው ተጨንቀን ተጠብበን የምናወራበትን ጉዳይ እርሱ በሚገርም ሁኔታ ይገላግለናል፡፡ቴዎድሮስ ሌላም ጥያቄ ጠይቆታል ፤እኔን ያስገረመኝ መልስ ያለው፡፡እንዲህ ጠየቀው፡-“የሰው ልጅ ከውልደቱ እስከ ሞቱ ቀድሞ በተቆጠረለት ዕጣ ፈንታ ከሆነ የሚጓዘው ጥረትና ድካሙ ታዲያ ምኑ ላይ ነው ትርጉም የሚሰጡት?”ጋሽ ስብሃት ተቀበለ፡-“ይሄንን …ለብፁእ አባታችን አቡነ ጳውሎስ ነው የምታቀርበው፡፡ እሳቸውም ግን መልስ የላቸውም፡፡መጽሐፍ ይጠቅሱልሃል እንጂ እሳቸውም ፣ማንም አያውቀውም፡፡ልደትህን አልመረጥክ፣ሞትህን አትመርጥም፡፡ ሁላችንም የምናውቀው መምጣታቸውንና የማይቀሩ መሆናቸውን ብቻ ነው፡፡ መሃል ያለው ነው የእኛ፡፡ እያለ ይቀጥላል፡፡ የዳንኤል ሃሳብም ግራ-ግብት የሚያደርግ ነው፡፡ ብዙዎቹ ጥመውኛል፡፡ ጀማነሽም በዚያ እትም ድንቅ የተሰኘች ነበረች፤ እዚህ ፍልስምና ሁለት ላይ ግን በጣም ወረደች፤ ሰባኪ መሰለች፤ ለዚያውም ያልተዘጋጀ፡፡ ርዕሷ ብቻ ነው-የተመቸኝ፡፡ እውነት ለመናገር ለጀማነሽ ያለኝ ፍቅርና አክብሮት ለየት ይላል፡፡ ተዋናዮቹ ሰፈር ፈርጠም ያለ ብስለት ያላትም እርሷ ናት!! ቁጥር ሁለት ፍልስምና ላይ ወደ ስብከት ስትገባ የሚያምረው ውስጣዊ መልኳ ረገፈ፡፡ ምናልባትም እግዚአብሄርን ይሁን ማንን ባላውቅም የሚታይ ፍርሃት ተነበበባት፡፡ እዚህ ጋ የቴዎድሮስ ጥይትም ዒላማ አልመታም፡፡ እንደኔ እንደኔ ቢዘልላት ነውር አልነበረውም፡፡ መንፈሳዊ መሆንና ለመፍራት መፍራት ይለያያል፡፡ሃሳብ አለ፤እምነት አለ፡፡…ሁለተኛው ፍልስምና ወደ ሃይማኖት ሰዎች ያነጣጠረ ነው፡፡አንዳንዴም ከፍልስፍና ጋር የሚነጻጸር ሆኖ ቀርቧል፡፡እዚህ ላይ እኔ በግሌ በጣም የምወደው ዶክተር ዳኛቸውን ማየቴ ብቻ በደስታ ሞልቶኛል ፤መቸም ሰውየው የሚናገረው አያጣም፤ ለዚያውም አጣፍጦ ነዋ!! ሰዉየውን በሬዲዮ ይሁን በወረቀት ሳየው ደስታዬ ልክ የለውም፡፡ እንዲሁ አይደለም የወደድኩት፡፡በሚጣፍጥና በዕውቀት በተሰባጠረ ሃሳብ እንጂ!! የዘመናችንን የጥበብ ጭርታ ለመግፈፍ መጽናኛ አድርጎ ፈጣሪ የሰጠን ይመስለኛል-ዶክተርን፡፡መቸም ዶክተሮቻችን ብዙ ቢሆኑም ዶክተር ከዶክተር እንደሚለይ ፣ምናልባት መቶ እጥፍ እንደሚለያይ ማሳያ ነው-ዶክተር ዳኛቸው፡፡ቴዎድሮስ ዶ/ር ዳኛቸውን ከጠየቀው ጥያቄዎች አንዱ፡-“ሶስቱ የፍልስፍና ጠላቶች ምንድናቸው?” የሚል ነው፡፡ዶክተር ዳኛቸው ሲመልስ፡-“አንደኛው እርግጠኝነት ነው፡፡እርግጠኝነት ወደ ዶግማ፣ ቀኖና ይወስዳል፡፡ በርትራንድ ራስል እንደሚለው፡- ፍልስፍና ያነሳቸው ጥያቄዎች እርግጠኛ መልስ ከተገኘላቸው ፍልስፍና መሆኑ ይቀርና ሌላ ዘርፍ ውስጥ ይገባል፡፡እርግጠኛ ካለመሆን የሚንቀሳቀስ የዕውቀት ዘርፍ ነው -ፍልስፍና፡፡…”እያለ ይቀጥላል፡፡ ቴዎድሮስ “ሃይማኖትና ፍልስፍና ተቀራራቢ ናቸው ወይስ ተገፋፊ?” ሲል ዶክተር ዳኛቸውን ጠይቋል፡፡ እንዲህ መልሷል ዶክተር፡-በዚህ ዙሪያ የላቀ ጥናት ያቀረቡት የ20ኛው ክ/ዘመን እውቁ አሜሪካዊ ፈላስፋ ፕሮፌሰር ሊዎ ስትራውስ እንዳሉት “ኃይማኖትና ፍልስፍና ሊዋሃዱ አይችሉም፡፡ነገር ግን ሁለቱም ዘርፎች በመቻቻል እንዲኖሩ ከተደረገ አንዱ ለሌላው አስተዋጽኦ ሊያደርግ ይችላል፡፡በመሆኑም ምክንያታዊነት ከኃይማኖት የመነጨ የሞራል አስተምህሮት ካልታከለበት ወደ ስታሊንና ጉላጉልና የሂትለር concentration camp ይወስደናል፡፡በሌላ በኩል ደግሞ ኃይማኖትም የምክንያታዊነት ግብዐት ከሌላት ወደ አክራሪነትና Spanish inquisition  ይወስዳል፡፡በመሆኑም በታሪክ እንዳየነውሁለቱን አቻችለው መሄድ የቻሉ ስልጣኔዎች ትልቅ ቦታ መድረስ ችለዋል፡፡” ከዚህ ሌላም ስለ ሃይማኖት ሲናገር “ኃይማኖትና ፍልስፍናን ስናነጻጽር ኃይማኖት  ለማመን ከፈለግህ ተቀበል የሚል መርህ ሲኖረው፣ ፍልስፍና ደግሞ “ለማወቅ ከፈለግህ መርምር”የሚል መርህ ላይ የተመሰረተ ነው፡፤ወይም በሌላ አባባል ቃሉን እንዳለ ተቀበል”ሲል ሀለተኛው ደግሞ ቃሉን መርምረህ ተቀበል” ነው የሚለው፡፡ ፍልስፍና ኃላፊነቱን ሰው ልጅ ትጋት ላይ ይጥላል፡፡ ኃይማኖት ላይ ሰው ተቀባይ…. ሲሆን ፣ፍልስፍና ግን መርማሪ…. ነው፡፡ ለምሳሌ ሁለቱን የቃል ( …..›) አስተምራዎች ብንወስድ ክርስቶስ “እኔ እውነትና መንገድ ነኝ፡፡” ብሎ እንድትቀበለው ሲነግርህ፣ ከክርስቶስ አምስት መቶ ዓመት በፊት የነበረው ትልቁ ፈላስፋ ሄራክሊላይተስ ደግሞ” እኔን አትስሙ፤ ቃሉን ስሙ” ነው ያለው፡፡ እንግዲህ ቃልን (……) በሚመለከት የሁለቱ አመለካከት የተለያየ ሆኖ እናገኘዋለን፤ የመጀመሪያው ቃሉን ተቀበል(ኃይማኖታዊ ) ሲሆን፣ ሁለተኛው (ቃሉን መርምር) ፍልስፍናዊ ነው፡፡   ፍልስምና 2 ሌላው ታላቅ እንግዳ አርክቴክቱ ሚካኤል ሺፈራው ነው፡፡ ሺፈራው ቃላቱ ያበዱና በዘይቤ ሰማይ የነኩ ናቸው፡፡የንባብ አቅሙም ልክ -የለሽና ጉድ የሚያሰኝ ነው፡፡አቤት ጥፍጥና!! ቴዎድሮስ ስለ ተስፋ ጠይቆታል፣ ሚካኤል ሲመልስ ”ተስፋ የምታደርገውን ነገር ካየህማ ምኑን ተስፋ ታደርገዋለህ?ፀሃይን ወጥታ ካየሃት በኋላ ይነጋል ብለህ ተስፋ ማድረግ ምን ትርጉም ይሰጣል? ተስፋ ማለትማ በጨለማ ሳለህ እንደሚነጋ ማመን፤ አምኖም በእርግጠኝነት በጨለማ ውስጥ ሳለህ ተረጋግተህና እንደሚነጋ ስለምታውቅ ብቻ አስቀድመህ ደስተኛ መሆን ማለት ነው፤ የነገዪቱ ብርሃን የመጀመሪያዪቱ ጨረር የምትፈነጥቀው የዛሬ ብርሃን የመጨረሻ ጨረር በምትሰናበትበት ቅጽበት፤ እኩለ-ሌሊት ላይ ነው፤ ስለዚህ ነው በአውሮፓዊያን አቆጣጠር  ንጋት እኛ መንፈቀ ሌሊት ከምንለው ከሌሊቱ 6፡00 ሰዓት የሚጀምረው፡፡…እኛ ብርሃን ካላየን ነግቷል አንልም፡፡ በእነርሱ አቆጣጠር ፀሃይ ወደ ንጋት ማቅናት ስትጀምር ነግቷል ይላሉ፡፡እንግዲህ ተስፋችን በእውነተኛ ተስፋ ማመናችን፣ እኩለ ሌሊት ላይ ፊታችንን ወደ ምስራቅ ወይም ወደ ንጋት ማዞራችን ላይ ነው፡፡ … ሚካኤል ሌላም የሚላቸው ነገሮች አሉ፡፡ ስለ ተስፋ ...”ከራሴ ህይወት አንድ የተረዳሁት እውነት ቢኖር ተዘጋጅቶ የተጠናቀቀ ህይወት በዚች ምድር ላይ አለመኖሩን ነው ስለዚህ የራስህን ዓለም ‹ራስህ ልትሰራው ይገባሃል፡፡ ተስፋህ ምንድነው ካልከኝ፣ በእምነት የራሴን ዓለም፣ የራሴን ህይወት መልካም ማድረግ መቻሌን ከማወቄ የመጣ ነው እልሃለሁ፡፡ ተስፋህ ምንድነው ካልከኝ ከራሴ እምነትና ከራሴ ጽናት የማገኘው የህልሜ ትርጉም ነው እልሃለሁ፡፡ሚካኤል ስለ ማህታማ ጋንዲ ያወራውን እንካፈል መሰለኝ፡- በታሪክ ከሚመስጡኝ ሰዎች መካከል ማህታማ ጋንዲ አንዱ ነው፡፡ጋንዲ እንግሊዞችን ፍጹም ሰላማዊ በሆነና ለእነርሱ ጨርሶ ሊገባቸው በማይችል እምነትና መንገድ የታገላቸው ነው፡፡ ከምዕተ ዓመታት ቅኝ ግዛታቸው ለማስወጣት የህንድን ህዝብ እያንቀሳቀሰ ስለሚፈታተናቸው ብዙ ጊዜ እስር ቤት ይከቱት ነበረ፡፡ ታዲያ ወደ መጨረሻው አስከፊ እስር ቤት በወረወሩት ጊዜ ምን ይላቸው መሰለህ?”እናንት አውሮፓውያን ወዳጆቼ ሆይ !የሰው ልጅ እኮ በአራት ግድግዳ የሚታሰር ግዑዝ ነገር አለዚያም እንስሳ አይደለም፡፡” ይላቸዋል፡፡የሰው ልጅ መንፈስ ነው፡፡እዚህ በእስር ሳለሁ ጽናቴና እምነቴ ህንዳውያን ወገኖቼን ያንቀሳቅሳል” ይላቸዋል፡፡ ሚካኤል ብዙ አንብቧል፤ንግግሩ ይጣፍጣል፡፡…ታሪክ ያጣቅሳል፡፡ይመቻል፡፡ዙምራን ብዙ እናውቀዋለን፡፡ በጣም ደስ ያሉኝ ሌላው ሰው መጋቢ ሃዲስ መምህር እሸቱ ዓለማየሁ  ናቸው፡፡ እንዴት ያያሉ? ልበ-ብርሃን ይሏል ይሄ ነው፡፡ከመምህር እሸቱና ቴዎድሮስ ምልልስ ጥቂት ልውሰድ፡፡ መቸም ሁሉ አይቻል ነገር! ሌላውን ለአንባቢ ልተወው፡፡ ጥያቄው እንዲህ ይላል፡-“በአምላክ የመፍጠር ሂደት ውስጥ እሑድ ሰማይና ምድርን ፈጠረ ብለናል፡፡ ፀሐይ መቼ ነው የተፈጠረችው?” መልሱ፡-ረቡዕ፡፡ቴዎድሮስ አሁንም ጠየቀ፡-“ቀደም ሲል የኛ የጊዜ መለኪያ ጸሐይ ናት ካልንና ጸሐይ ደግሞ ረቡዕ ከተፈጠረች፣ ያለ ፀሐይ ቀኑን በምን አውቀን ነው የመጀመሪያ ቀን፣ ሁለተኛ ቀንያልነው?” መምህሩ ሲመልሱ፡”ፀሐይ ረቡዕ ተፈጠረች ሲባል እግዚአብሄር ለብርሃን አምፑል አስገባለት ማለት ነው እንጂ ብርሃን ተፈጠረ ማለት አይደለም፡፡ብርሃን የተፈጠረው እሁድ ነው፡፡ረቡዕ ላይ መግለጫ ሰሌዳ አበጀለት ማለት ነው፡፡ለምሳሌ እዚህ ቤት ኤሌክትሪክ ልትዘረጋ ትችላለህ፡፡አምፑል እስከሌለ ድረስ መቶ ሜትር ብትዘረጋ ጥቅም የለውም፡፡አምፑል የለውም ማለት ግን ኤሌክትሪክ የለውም ማለት አይደለም፡፡በግልባጩ ደግሞ አምፑል አለው ማለት ደግሞ ኤሌክትሪክ አለ ማለት አይደለም፡፡….እያለ ይቀጥላል፡፡…እኔ ትንታኔ እየሰጠሁ አይደለም፤ግን ለንባብ እየጋበዝኳችሁ ነው፡፡ምክንያቱም የተለያዩ አመለካከቶችን ማየት ትችላላችሁና!!...ሁሉም የየራሱ መልክና አተያይ አለው፡፡…ሰለዚህ ጭፍን ከመሆን መርምሮና በርብሮ ማየት ደስ ይላል፡፡   .ቴዎድሮስን ስለ መግቢያው ልወቅሰው ፈልጌ ነበር፡ግን ሌላ ሰው ወቅሶታል፡፡ እንደ እንጀራ የመረጠውን ሊያጎርሰን መፈለጉ ደሜን ባያፈላውም እንዴት በዚህ ሳተ? ብዬ ተገርሜያለሁ፡፡ ብዙው ነገር ላይ ስላስደሰተን ያን ያህል አልተበሳጨሁም፡፡ አዲስ ወግ አሳይቶናል፡፡በመጀመሪያውም ባሁኑም ሸጋ ሸጋ ሰዎች አቅርቦልናል፡፡የተለያዩ አመለካከቶችን ወስዶ የራስን መመዘንም ትልቅ ነገር ይመስለኛል፡፡ ወተት ልጋታችሁ ቢልም ያስጋጠንን አጥንት ውለታ የምንረሳ ውለታ ቢሶች አይደለንም፡፡ ስለፈረንጅ ፍልስፍና ብቻ ከማሰብ አውጥቶናል፡፡ እግዜር ይስጥልን!!

Read 2716 times Last modified on Saturday, 13 October 2012 11:37