Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 13 October 2012 11:20

‘አገር በቀል ዘመናዊነት…’

Written by 
Rate this item
(7 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!

እንደ ድሮው በሠላሳ ብር ሽንኩርት የሆነ ኪሎ ሥጋ  በሚገዛበት ዘመን ቢሆን “በጥቅምት አንድ አጥንት እንዴት እያደረጋችሁ ነው…” ምናምን እንባባል ነበር፡፡ (ከጥቂት ዓመታት በፊት እንኳን “ድሮ” እየተባለ መጠቀስ ሲጀምር “ይሄ ነገር እንዴት እንዲህ ሊሆን ቻለ!”  ምናምን የሚል ያገባኛል ባይ መጥፋቱ አያሳዝናችሁም!) እናላችሁ… ዘንድሮ ስለ ‘አንድ አጥንት’ ምናምን ነገር ብታነሱ…አለ አይደል… “የምን አጥንት ነው የምታወራው? የሉሲን አጥንት ማለትህ ነው!” ምናምን የሚባል መልስ ልታገኙ ትችላለችሁ፡፡ እናላችሁ…‘የጓዳችንን ጉድ’ እያወቅን በአደባባይ  ‘ሁሉም ሙሉ፣ ሁሉም ዝግጁ’ አይነት ነገር እንደሆነ ማስመሰሉ ‘ናሽናል አይዴንቲቲ’ ምናምን ነገር እየሆነ መምጣቱ የምር ያሳዝናል፡፡ ሀሳብ አለን…በዚህ ጉዳይ ላይ ‘አንዳንድ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች’ ይጠየቁልንማ!እኔ የምለው…የሉሲን ነገር ካነሳን አይቀር… እሷ ሴትዮ ግሪን ካርድ ምናምን ነገር አገኘች ወይስ እዛው ሚዩዚየም ውስጥ ካገኘችው ‘ሌላ አጥንት’ ጋር “ሀብትሽ በሀብቴ…” ምናምን ተባብላ ሦስት ጉልቻ ነገር ሠራች! ዘንድሮ እንደሁ ውጪ ለመሄድ ወይም ውጪ ለመቅረት እትናዬዎቻችን ‘የማያገቡት ፍጡር’ ያለ አይመስልም፡፡

ልክ ነዋ…አገሮቹ የትኛው የዓለም ክፍል እንዳሉ የማናቃቸውን ዜጎች እያገቡ መሆኑን እንሰማለና! እናላችሁ…የአገርና የህብረተሰብ መሰረት ሲናጋ እንዲህ ነው የሚያደርገው! ‘ያገባኛል ባይ’ ይጥፋ! ምኞት አለን…እኛን ልክ ልካችንን ከሚነግሩን አንደበቶች ጋር የሚያዳምጥ ጆሮዎች የመረቀላቸውን በርከት አድርጎ ይስጠንማ! እናላችሁ…የዚች አዲስ አበባችን ‘አገር በቀል ዘመናዊነት’ ግራ እያጋባን ነው፡፡ ሀሳብ አለን…“የአዲስ አበባ አገር በቀል ዘመናዊነት…” ምናምን የሚል ኮንፍረንስ ይዘጋጅልንማ፡፡ ዘመናዊነት የሚባሉት ነገሮች የትኞቹ እንደሆኑ ከተነገረን ‘ቁርጣችንን እናውቃለና!’ ‘ቁርጡን ያወቀ’ ደግሞ…አለ አይደል… “ፈቀቅ ለማይል ነገር…” ጊዜውንም ጉልበቱንም አያጠፋም፡፡ (እነ እንትና…አሁንም ቁርጣችሁን አላወቃችሁም እንዴ! ቂ…ቂ…ቂ…) እናማ…እዚቹ መቶ ሀያ ምናምን ዓመት የሞላች አዲስ አበባ ውስጥ ለምንም ይሁን ለምን ‘ከተማ’ ወጣ ብላችሁ እስክትመለሱ እኮ አንድ ሺህ አንድ ‘ጉድ’ ነው የምታዩት፡፡ (‘ጉድ’ የምንለው የእኔ ቢጤዎች እንደሆንና፣ የዘመኑ ‘ሙቨርስ ኤንድ ሼከርስ’ ግን ሁሉንም ነገር ከዘመናዊነት ጋር እንደሚያዩት ልብ ይባልማ!)እኔ የምለው…እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ… በቀደም አውቶብስ ውስጥ ነገርዬውን ሁሉ ለአደባባይ አብቅተው አንዷን ተሳፋሪ እንትን ሊሉ ሲሉ ተያዙ ተብሎ ሚዲያ ላይ ጉዳቸው የወጣው  አዛውንት ነገር ግርም አይልም፡፡ ኽረ እንዴት ነው ነገሩ! አንድ አዛውንት ያውም በጠራራ ፀሐይ፣ ያውም በህዝብ መጓጓዣ ውስጥ፣ ያውም ያ ሁሉ ሰው ባለበት እንዲህ አይነት እነ ሻሮን ስቶን ፊልም ላይ እንኳን የማይታሰብ ነገር ሲሞክሩ…አለ አይደል… ዘመኑ ምን ያህል እንደዋወጠብን አይታያችሁም! (እኔ ምን ጠረጠርኩ መሰላችሁ…ሰውየው አውቶብስ ላይ ከመሳፈራቸው በፊት ‘ኮሌክሽን ቪዲዮ’ አይተዋል ማለት ነው፡፡ ለእንዲህ አይነት ለልብ ወለድ እንኳን የማይመች ድርጊት የምንሰጠው ምክንያት ስናጣስ!) እናማ…ወዴት እየሄድን እንደሆነ ግራ አይገባችሁም! ለነገሩማ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…  ዓይን ያዝ ሲያደርግ የከተማው ጥጋ ጥግ  ሁሉ እኮ…ካሜራ፣ ዳይሬከተር ምናምን ሳይኖር ‘ፋታል አትራክሽን’ የሚሠራበት አይነት ሆኗል ነው የሚባለው፡፡ ይህም የአዲስ አበባ አገር በቀል ዘመናዊነት አንዱ ምልክት መሆኑ ነው? ወደ ቦሌ ጠጋ ብሎ ያ ሰፈር ተከራይቶ የነበረ ወዳጄ  ሁለት ሰዓት ተኩል ምናምን ለሥራ ሲወጣ በየመኪናው ውስጥና በየሱቁ ጥግ የሚያየው ‘ግብግብ’ (እነ ቮድካ የወተትን ቦታ እየተኩ ግብግብ የማይሆንስ!) እየረበሸው እንትናዬዎች ሳይከናነቡ ወደማይወጡበት እንደ ታሪክ ቅርስነት መያዝ ያለበት መንደር ተዛውሯል፡፡ ልክ ነዋ…ለጸሎት  በዚህ ዘመን ተከናንባ የምትወጣ እንትናዬ የሚገጥማት “እንዴት አደርሽ?” የሚል ሰላምታ ሳይሆን “ምነው፣ ደህና አይደለሽም እንዴ!” የሚል ይሆናል፡፡እናላችሁ… ዙሪያችሁን ታዩና ነገሩ ሁሉ የስልጣኔ መገለጫ ይሁን…የ‘አይ ኪው’ አፈር ድሜ መጋጥ ይሁን…“ስለ ሰው፣ ስለ ሰው ቀድጄ ልልበሰው…” ይሁን ግራ ግብት ይላችኋል፡፡  ኮሚክ እኮ ነው…የአሥራ አምስትና የአሥራ ስድስት ዓመት ወንዶች የቪያግራ ወዳጅ የሆኑበትና…በዛው ዕድሜ አካባቢ ያሉ እንትናዬዎች የ‘ቮድካ ደረቋን’ ወዳጅ የሆኑበት ዘመን ምን አይነት ስልጣኔ እንደሆነ የሚነግረን ነው የጠፋው፡፡ ስሙኝማ…የመጠጡና የሌላው ነገር አቀማምና፣ ‘ስትራቴጂያዊ አፈጻጸም’ (ቂ…ቂ…ቂ…) አደባባይ ቢወጣ ‘ጊነስ’ ምናመን አይነት መጽሐፍ ውስጥ ቦታ አያሰጠንም ትላላችሁ! የምር…‘ከእንትን በፊት ለመጋጋል’ ተብለው የሚደረጉ የመጠጥ፣ የቂማና የሌላ ነገሮች ‘ሚክስቸሮች’…አለ አይደል…“ምን አለ የኖቤል ሽልማት ሰዎች ወደ እኛም አየት ቢያደርጉ…” የሚያሰኝ ነው፡፡ ግርም የሚለኝ ምን መሰላችሁ…ይሄ ሁሉ፣ አንድ  በሚስቱ የተበሳጨ ፈረንጅ አለ እንደተባለው “ፎር ዘ ላውዚ ስሪ ሚኒትስ” ይሄ ሁሉ ከክተት አዋጅ ያልተናነሰ ዝግጅት! እናላችሁ…የአዲስ አበባ አገር በቀል ዘመናዊነት ገና መአት ጉድ ያሳየናል፡፡ ነገሬ ብላችሁልኝ እንደሁ ከአዛውንት እስከ ታዳጊ…እንትናዬዎችን ‘የሚለክፉ’ ወንዶች በጣም በዝተዋል፡፡   የሚገርመው ነገር ደግሞ ምን መሳችሁ… ብዙ እንትናዬዎች ‘ለከፋ’ ነገር ሲገጥማቸው ከመናደድ ወይ ከመቆጣት ፈንታ ጭራሽ ፈገግታ ሲያሳዩ ስታዩ…የአዲስ አበባ አገር በቀል ዘመናዊነት በአምስተኛ ማርሽ እየተንደረደረ እንደሆነ ይታያችኋል፡፡ ስሙኝማ…በፊት ጊዜ እኮ እንዲህ ‘የተለከፈች’ እንትናዬ… ካለ ታላቅ ወንድም፣ አለበለዛ ደግሞ የሰፈር ልጅ አምጥታ ‘ታስጠፈጥፍ’ ነበር፡፡ የዘንድሮ እንትናዬዎች ታላቅ ወንድም የላቸውም ማለት ነው!  ቂ…ቂ…ቂ…. “ገርሌን እነእንትና ለከፉብኝ ተብሎ እኮ ቅምብቢት ከሸራ፣ እነእንትና ከእነእንትና ቡድን ሠርተው ከተማዋ የምትታመስበት ዘመንም ነበር፡፡ ስሙኝማ…ደግሞ ምን አለ መሰላችሁ… ምንም እንኳን አፍ አውጥተው “ስማ ምን ያነጥርሀል…” ምናምን አይነት ቃላት ባይወጣቸውም አንዳንድ የአካል ክፍሎችን…አለ አይደል… ‘በሁለት፣ አንድ ሰባት የማጥቃት ፎርሜሽን’ በማነቃነቅ እንትናዬዎችም  ‘ኮሌክቲቭ ለከፋ’ ነገር እያካሄዱ እንደሆነ ተመዝግቦ ይያዝልንማ! ሀሳብ አለን… ሁኔታዎችን ያላገናዘቡ የአንዳንድ የእንትናዬዎች የሰውነት ክፍሎች እንቅስቃሴ ከትንኮሳ እንደማይተናነሱ የሚያስረዳ ሰርኩለር ምናምን አይነት ነገር ይተላለፍንማ! (ስሙኝማ…አዳም እኮ ዕድለኛ ነበር፡፡ የተታለለው በአንዲት ዕጸ በለስ ነዋ! እኛ አለን እንጂ፣ በአንድ ሺህ አንድ ዕጸ በለሶች እየተታለልንን ያለነው!)እኔ የምለው…እግረ መንገዴን ኤፍ. ኤሞቹ ስለ አዲስ አበባ አገር በቀል ዘመናዊነት ምንም ነገር የማይግሩንሳ! ለነገሩ አንዳንድ የኤፍ. ኤም ፕሮግራሞች ራሳቸው የአዲስ አበባ የአገር በቀል ዘመናዊነት ውጤት ነው የሚመስሉት፡፡ ሀሳብ አለን…ሚዲያ ላይ ያሉ ሰዎች ትንሽ ከአድማጭ፣ ከአንባቢና ከተመልካች አልፈው መሄድ ቢያዳግታቸውም ስለሚያቀርቧቸው ነገሮች የሰዉን ያህል ለማወቅ ቢሞክሩ አሪፍ ነው፡፡ ስሙኝማ…ቡድናችን ነገ ሲጫወት አሪፍ ውጤት ይግጠመውማ! ስሙኝማ…ባለፉት ሳምንታት ብዙ ነገር ሲባል ቆቷል፡፡ ስለ ስፖርታዊ ጨዋነት የተባሉት ነገሮች ሁሉ መልካም ናቸው፡፡ ልጆቹ ምንም እንኳን ወዳጅ አገር ሄደው ቢጉላሉም ዋናው ኳስ ነው፡፡ እነሱ ባህሪያቸው ስለዘቀጠ እኛም እንደነሱ ማሽቆልቆል አይኖርብንም፡፡ በአንድ ወቅት ቡድናችን ናይጄርያ ላይ ተጫውቶ ሲመለስ ዳቦ ምናምን ተወረወረበት ተብሎ… በመልሱ ግጥሚያ አዲስ አበባ ስታዲየም ተረብሾ ነበር፡፡ ያ ዘመን ያለፈ ይመስለኛል፡፡በሌላ በኩል አሪፍ ውጤት ደግሞ ከአሪፍ ጨዋታ ነው የሚመጣው፡፡ ሰሞኑን በየሚዲያው ሲሰጡ ከነበሩት አስተያየቶች አንዳንዶቹ እዛኛው ወገን አሥራ አንድ ተጫዋቾች ያሉበት ቡድን እንዳለ የዘነጉ ይመስላሉ፡፡ በራስ መተማመን እንዳለ ሆኖ ዋናው እስከ መጨረሻ ደቂቃ ያለ ችሎታን ሙሉ ተጠቅሞ ለማሸነፍ መሞከሩ ነው፡፡ አንዳንዶቹ የ“እናሸንፋለን” አስተያየቶች…አለ አይደል…ልክ የእኛ ልጆች ኳሷን ሲጫወቱ ሱዳኖቹ ማጭድ ይዘው የሜዳውን ሳር የሚያጭዱ ነው ያስመሰሉት፡፡፡ እነሱም ጥርሳቸውን ነክሰው እንደሚመጡ ማወቁ ብልህነት ነው፡፡ ዞሮ ዞሮ ኳስ ነው…አራት ነጥብ፡፡ልጆቻችን አሸንፈው ቢያልፉ አሪፍ ነው፡፡ ዘጠና ደቂቃ ጉልበታቸውን ሳይቆጥቡ ተጫውተው ካልተሳካላቸውም ለእኔ እንዳሸነፉ እቆጥረዋለሁ፡፡ ዞሮ ዞሮ ኳስ ነው፡፡ ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 3123 times Last modified on Saturday, 13 October 2012 11:37