Saturday, 16 July 2022 17:40

ሚሊኒየም አዳራሽ ዛሬ ለባለቤቶቹ ይመለሳል

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(0 votes)

• ከ7ሺ በላይ የኮቪድ ህሙማን ህክምናቸውን በአዳራሹ ተከታትለዋል
     • ዛሬ በአዳራሹ የምስጋናና የርክክብ ፕሮግራም ይካሄዳል
      
            ከሁለት ዓመታት በላይ በኮቪድ 19 ወረርሺኝ የተያዙ ህሙማን ህክምናቸውን ሲከታተሉበት የነበረው ሚሊኒየም አዳራሽ ዛሬ ለባለቤቶቹ ሊመለስ ነው። አዳራሹ ከዛሬ ጀምሮ ወደ መደበኛ አገልግሎቱ እንደሚገባም ታውቋል።
በአዲስ ፓርክ ዴቨሎፕመንትና ማኔጅመንት ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ስር ሲተዳደር የነበረውና ንብረትነቱ የባለሃብቱ የሼህ መሀመድ ሁሴን አሊ አልአሙዲ የሆነው ሚሊኒየም አዳራሽ፣ ከግንቦት ወር 2012 ዓ.ም ጀምሮ የኮቪድ 19 ህሙማን መታከሚያ ሆኖ ቆይቷል። አዳራሹ ባለፈው ሰኔ ወርም ሙሉ በሙሉ አገልግሎት መስጠቱን አቁሞ የማፈራረስና የማስተካከል ስራ ሲሰራ የቆየ ሲሆን ዛሬ ከቀኑ 10 ሰዓት በሚከናወን የምስጋናና የርክክብ ስነ-ስርዓት አዳራሹ ለባለቤቶቹ ይመለሳል።
 በአንድ ሺ መደበኛና በ40 የጽኑ ህሙማን አልጋዎች በግንቦት 2012 ዓ.ም አገልግሎት መስጠት የጀመረው ሚሊኒየም አዳራሽ፤ የኮቪድ ወረርሺኝ ከፍተኛ ደረጃ ላይ በደረሰበት ባለፈው ዓመት ሚያዚያ ወር 100 ተጨማሪ የጽኑ ህሙማን አልጋዎችን አዘጋጅቶ ህሙማንን ሲቀበል ነበር።
የህክምና ማዕከሉ ከ3 ሳምንት በፊት ሙሉ በሙሉ ስራውን ያቆመ ሲሆን አንዳንድ የማስተካከል ስራዎቹ ተጠናቀው ለባለቤቶቹ ለመመለስ ዝግጁ ተደርጓል ተብሏል።
በአዳራሹ ከ7ሺ በላይ የኮቪድ 19 ህሙማን የታከሙ ሲሆን አገሪቱ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ በወደቀችበት ጊዜ ማዕከሉን ለህሙማን ህክምና መገልገያ እንዲሆን መፈቀዱን ትልቅ እፎይታን አስገኝቶ እንደነበር ይታወሳል። በአሁኑ ወቅት አዳራሹን ለባለቤቶቹ ለመመለስና ወደ መደበኛ ስራው እንዲመለስ ለማድረግ የተወሰነው በኮቪድ 19 ወረርሽኝ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ በመቀነሱና ህሙማኑን በመደበኛ የኮቪድ 19 ወረርሺኝ ህክምና ተቋማት ተቀብሎ ማስተናገድ በሚቻልበት ደረጃ ላይ በመደረሱ እንደሆነ ተገልጿል።
ዛሬ ከቀኑ 10 ሰዓት ላይ የጤና ሚኒስትሯ ዶ/ር ሊያ ታደሰ በሚገኙበት የርክክብና የምስጋና ፕሮግራም እንደሚካሄድና አዳራሹ ለባለቤቶቹ እንደሚመለስ ተገልጿል።

Read 1266 times