Saturday, 16 July 2022 17:46

የነዳጅ እጥረት የእርዳታ አቅርቦትን ማስተጓጎሉ ተገለጸ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(26 votes)

  በድርቅ ሳቢያ 8.1 ሚ. ዜጎች ለተረጂነት ተዳርገዋል
                             
            በኢትዮጵያ ግጭትና ጦርነት አሁንም ለዜጎች መፈናቀልና ተመጽዋችነት ዋነኛው ምክንያት መሆኑን ያመለከተው የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ ድጋፍ ማስተባበሪያ ጽ/ቤት፤ በአማራ፣ ትግራይና ሶማሌ ክልሎች በነዳጅ እጥረት ሳቢያ የእርዳታ አቅርቦት ማጓጓዝ እንዳልተቻለ አስታውቋል።
ተቋሙ ከትናንት በስቲያ ሃሙስ ባወጣው የወቅታዊ ሁኔታ ግምገማ ሪፖርቱ፤ በ2022 ዓ.ም ከ20 ሚሊዮን የማያንሱ ኢትዮጵያውያን በተፈጥሮ አደጋ፣ በድርቅ፣ በጦርነትና ግጭት ምክንያት ለእርዳታ ጠባቂነት መዳረጋቸውን ጠቁሞ፤ አሁንም ድርቅና ጦርነት፣ ግጭትና ጥቃት የሃገሪቱ ዋነኛ ስጋት ሆነው መቀጠላቸውን ተከትሎ፣ በ2023 ዓ.ም የተረጂዎች ቁጥር ሊጨምር እንደሚችል አስታውቋል።
በአሁን ወቅት በትግራይ ከኤርትራ አዋሳኝ እንዲሁም  ከአማራ ክልል አዋሳኝ በሆኑ አካባቢዎችና የፀጥታ ሁኔታቸው አስተማማኝ ባልሆኑ የአማራ ክልል አካባቢዎች በተለይ በሰሜን ወሎ ዋግህምራ፣ በምዕራብ ኦሮሚያ ወለጋ፣ በደቡብ ኦሮሚያ ጉጂ ዞን ለዜጎች እየቀረበ ያለው ድጋፍ በቂ አለመሆኑንና በአንዳንድ አካባቢዎች የጸጥታው ሁኔታ በጭራሽ እርዳታ ለማቅረብ የማያስችል መሆኑን  ሪፖርቱ አመልክቷል።
ከዚህ ተግዳሮት በተጨማሪ በሃገሪቱ የተከሰተውን የነዳጅ እጥረት ተከትሎ በአማራ፣ ሶማሌና ትግራይ ክልሎች በቂ ነዳጅ ባለማቅረቡ ለተረጅዎች እንዲከፋፈሉ የተከዘኑ የእርዳታ ቁሳቁሶችን በየብስ ትራንስፖርት ማጓጓዝ እንዳልተቻለም ነው ሪፖርቱ የጠቆመው።ኢትዮጵያ በቀንና በዓመት ምን ያህል የነዳጅ ምርት ትጠቀማለች? - BBC News አማርኛ
በሃገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በተከሰተው ድርቅ የተነሳ ለተረጂነት የተጋለጡ ዜጎች ቁጥር 8.1 ሚሊዮን መሆኑን የጠቀሰው ይኸው ሪፖርት፤ 3.5 ሚሊዮን በሶማሌ ክልል፣ 3.4 ሚሊዮን በኦሮሚያ፣ 1.1 ሚሊዮን ያህሉ በደቡብ እንዲሁም 2 መቶ ሺህ ያህሉ በደቡብ ምዕራብ ክልል እንደሚገኙም አመልክቷል።






Read 11162 times