Saturday, 16 July 2022 18:14

ኮሮና የለም? ወይንስ ተዘነጋ፡፡

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ
Rate this item
(0 votes)


         በአለም አቀፍ ደረጃ በየጊዜው እንደሚወጣው መረጃ ከሆነ የኮሮና ቫይረስ መልኩን ለውጦ እንደሆን እንጂ ተወግዶአል የሚል ዜና የለም። በኢትዮጵያም ቢሆን ከ January 2020 እስከ June 2022 ድረስ የወጣው መረጃ የሚያሳየው  የሚከተለውን ነው፡፡
በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር  489,846
የሞት መጠን     7,548
ክትባት የወሰዱ   49,686,694 መሆኑን ያሳያል፡፡
በአለም አቀፍ ደረጃ ዛሬም በየቀኑ መረጃዎች በአለም የጤና ድርጅትም ሆነ በኢትዮጵያ እንዲሁም በመላ የአለም ሀገራት  ለህብረተሰቡ ይቀርባል፡፡ በዚህም መሰረት የአለም የጤና ድርጅት ከኢትዮጵያ ጋር ተመሳሳይ በሆነ ጊዜ ባወጣው መረጃ በአለም ላይ ያለው የኮሮና ቫይረስ ስርጭት የሚከተለውን ይመስላል፡፡


            ከላይ የተመለከታችሁት ኮሮና ቫይረስን በተመለከተ የአለም የጤና ድርጅት ያወጣው መረጃ ነው፡፡ ከታች በተመለከተው አድራሻ የበለጠ ስለሁኔታው መረዳት እንደሚል ለአንባቢዎች እንጠቁማለን፡፡
https://www.worldometers.info › coronavirus
የኮቪድ-19 ቫይረስን ስርጭት በተመለከተ የአለም የጤና ድርጅትም ሆነ የኢትዮጵያው የጤና ሚኒስቴር የሚያሳዩት መረጃ እንደተጠቆመው ሲሆን በይፋ የሚታየው ጥንቃቄ ግን ቫይረሱ ጭርሱኑ ከአገር ተወግዶአል የተባለ ይመስላል፡፡
በብዙ ስፍራዎች ማለትም ሰዎች በሚንቀሳቀሱባቸው ወይንም አገልግሎት በሚያገኙባቸው ስፍራዎች የፊት መሸፈኛ የማይጠቀሙ እንዲሁም እርቀትን የማይጠቀሙ ለእጃቸው ማጽጃ አልኮሆል ወይንም ሳኒታይዘር የሌላቸው በርካታ ናቸው፡፡ ይህ ደግሞ ተገልጋዮቹ ብቻ ሳይሆኑ አገልግሎት ሰጪዎችም ጭምር ጥንቃቄ ሲያደርጉ አይታዩም፡፡
የኮሮና ቫይረስ እንደመጣ ይታይ የነበረው በየድርጅቱ ደጃፎች ተቀምጠው የነበሩ የእጅ መታጠቢያዎች ዛሬ የሉም፡፡ አብዛኞቹ የተነሱ ሲሆን አንዳንዶቹ ደግሞ ባዶአቸውን ተመልካች አጥተው ተቀምጠዋል፡፡


የእጅ ማጽጃው አልኮሆል ወይንም ሳኒታይዘር እንደከአሁን ቀደሙ በየስፍራው ከሚገኙ የጎዳና ግብይቶች አይገኝም፡፡ ሰዎች ወንዶች በሱሪያቸው ሴቶች በቦርሳቸው በየደረሱበት ይጠቀሙበት የነበረ ሲሆን ዛሬ ግን አይታይም፡፡
የህዝብ ማመላለሻ ትራንስፖርቶች ከአሁን ቀደም የፊት መሸፈኛ ያላደረገ አይሳፈርም ይሉ የነበሩ ሲሆን አሁን ግን ችላ ብለውታል፡፡
ባጠቃላይም የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የተሰጠው ማሳሰቢያ እና አፈጻጸሙ በሁሉም መስክ ችላ የተባለ ይመስላል የሚለውን ጠቆም ለማድረግ ያህል ያነሳነው ሲሆን ከዚሁ ጋር በተያያዘ ያገላበጥነው መረጃ ከቫይረሱ ጋር በተያያዘ የእናቶችን ወይንም በእርግዝና ላይ ያሉ ሴቶችን የሚመለከትበትን ነጥብ በመጠኑ እስነብባችሁ፡፡


የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ መንገድ የእናቶችን ጤንነት ሊጎዳ የሚችል እና የሚያደርሰው ጉዳትም አንዱ ከአንዱ የተሳሰረ ሊሆን እንደሚችል መረጃዎች ያስረዳሉ፡፡ በዚህም መሰረት በአለም አቀፍ ደረጃ ያለውን እውነታ በትክክል ለማስረዳት የተጠናከረ ሁሉንም ያካተተ ጥናት ባይካሄድም ነገር ግን የዳሰሳ ውጤቶች የሚያሳዩት እውነታ አለ፡፡ በዚህም በአካላዊ ፤አእምሮአዊ እና ኢኮኖሚያው እንዲሁም በማህበራዊ አቅጣጫ በእርግዝና ላይ ያሉ ሴቶችን ደህንነትን የሚመለከቱ እውነታዎች አሉ፡፡
ሴቶች በተለይም በእርግዝና ላይ ያሉ ሴቶች በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ጉዳት ሊደርስባቸው ይችላል ሲባል ከሌሎች ወይንም በእርግዝና ላይ ካልሆኑ ሴቶች በተለይ ያላቸውን ስሜት የሚመለከት ነው፡፡ ስለጡት ማጥባትና በማህጸን ውስጥ ሊኖር ስለሚችለው ነገር በተለይም ይህ ምንጭ ያደረግነው ጥናት አለመመልከቱን ይጠቅሳል፡፡
በእርግዝና ላይ የነበሩ እና የኮቪድ-19 ቫይረስ ያላቸው ሴቶች በምጥ ወቅት፤ ልጅ ሲወለድ፤ እና ጡት በማጥባት ወቅት ምን ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባቸው የሚገልጽ መመሪያ ከአሁን ቀደም የተሰራጨ ሲሆን ለአጠቃቀሙ ግን ሁኔታውን ለመቀበል ደረጃ ሊወሰን እንደሚችል ይህ መረጃ ይጠቁማል፡፡ እናቶች ከአእምሮአቸው ጋር በተያያዘ ያለውን ጤንነት በሚመለከት በህክምና ተቋማት የሚገኙ ሪፖርቶች እንደሚያስረዱት ድብርት፤ጭንቀት የመሳሰሉት መመዝገባቸውን የዳሰሳው ጥናት ያሳያል፡፡ በኮሮና ቫይረስ ተይዘው የነበሩ ሴቶች ልጅ ከወለዱ በሁዋላም በቤተዘመድ የመጎብኘት እድላቸው በእጅጉ እንደሚቀንስም ተረጋግ ጦአል፡፡ የጤናው መሰረተ ልማት ውጥረት ውስጥ መውደቅም ሌላው አስቸጋሪ ነገር ሲሆን የአለም የጤና ድርጅት እንደሚገልጸው በአንዳድ ሀገራት አስቸጋሪ የሆኑ ፖሊሲዎችን ተግባራዊ ማድረግ ለእናቶች ምቹ አለመሆኑ ተስተውሎአል፡፡
በኮቪድ-19 ምክንያት ሴቶች ከወንዶች ይበልጥ በገቢያቸው ስለሚዳከሙ ኑሮአቸውን ለመደገፍ በተለይም ልጆቻቸውን ለመንከባከብ ከፍተኛ ትግል ሲያደርጉ ይስተዋላሉ፡፡     
ባጠቃላይ ግን በእርግዝና ላይ ያሉ ሴቶች በእርግዝና ላይ ካልሆኑት ሴቶች በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ይበልጥ ተጋላጭ እና ታማሚ ናቸው የሚል ምንም መረጃ የለም፡፡ ቢሆንም ግን በእርግዝና ላይ ያሉ ሴቶች የኮሮና ቫይረስ ከያዛቸው የኮሮና ቫይስ ካልያዛቸው ሴቶች ይበልጥ በህመሙም ሆነ በስሜታቸው ሊጎዱ እና በማህራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮችም ይበልጥ ሊቸገሩ ይችላሉ፡፡ ገቢያቸው ከፍተኛ የሆነ፤ መካከለኛ ገቢ ያላቸውና ገቢያቸው ዝቅተኛ ባልሆኑ ሀገራት የሚኖሩ ሰዎች የሚደርስባቸው ጉዳት የተለያየ ቢሆንም ይህንን ችግር ሁሉም በየደረጃው ይጋሩታል፡፡
ቫይረሱ የያዛቸው ሰዎች የሚያሳዩት ምልክት ከአሁን ቀደምም ለንባብ ያልነው ቢሆንም አሁንም ማስታወስ እንወዳለን፡፡
የኮሮና ቫይረስ የተለያዩ ሰዎችን በተለያየ መንገድ ሊያጠቃ የሚችል ሲሆን በአብዛኛው በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ግን የሚከተሉት ምልክቶች ይታዩባቸዋል፡፡
በጣም የተለመደው ምልክት፡-
ትኩሳት፤ ሳል፤ ድካም፤
የጣእም ወይንም የማሽተት ስሜት ማጣት፤ ሲሆን በአነስተኛ ሁኔታ የሚኖሩት ምልክቶች ደግሞ
የጉሮሮ ህመም፤ የእራስ ምታት፤
አጠቃላይ የሰውነት ህመምና ስቃይ፤
ተቅማጥ፤ በቆዳ ላይ ሽፍታ፤
የአይን መቅላት ወይንም መታመም የመሳሰሉት ናቸው፡፡ በእርግጥ እነዚህ የህመም ስሜቶች ከኮሮና ጋር በተያያዘ ብቻ የሚሰሙ አለመሆናቸውን መረጃው ይጠቁማል፡፡
የኮሮና ቫይረስ አሁንም ስርጭቱ ቢቀንስም አለመገታቱን የሚያመላክቱ መረጃዎች አሉ። በመላው አለም ኢትዮጵያን ጨምሮ በየቀኑ የሚሰጠው የጥንቃቄ መልእክት አልተቋረጠም፡፡
በእርግዝና ላይ ያሉ ሴቶች በእርግዝና ላይ ካልሆኑት ሴቶች ይበልጥ ለኮሮና ቫይረስ  ይጋለጣሉ የሚል መረጃ ባይኖርም እርግዝና በራሱ የሚያስትከለው የሰውነት ለውጥ እና የአቅም መዳከም ሁኔታ ስለሚኖር መጠንቀቅ ይበጃል፡፡ በአሁኑ ወቅት በየቦታው እንደሚታየው ስለቫይረሱ ምንም ጥንቃቄ አለማድረግ ተገቢ አይደለም፡፡ የኮሮና ቫይረስን ክትባት መውሰድም ተገቢው የጥንቃቄ እርምጃ መሆኑ መዘንጋት አይገባውም፡፡
እራስን ከቫይረሱ ለመከላከል አካላዊ እርቀትን መጠበቅ፤ በተቻለ መጠን እራስን ከሌሎች ማራቅ፤ አየር እንደልብ በሚዘዋወርበት ቦታ መሆን፤ ሳል ወይንም ማስነጠስ ቢኖር በቀጥታ ወደአየር ከመልቀቅ ይልቅ ፊትን ዞር ማድረግና ሸፈን በማድረግ ማሳል፤ እጅን መታጠብ፤ ያልታጠበ እጅን ከፊት ማራቅ የመሳሰሉት በቤት ውስጥ ወይንም በማናቸውም ቦታ ሊደረጉ የሚገባቸው ጥንቃቄዎች ናቸው፡፡ በተጨማሪም በተለይም ከቤት ውጭ ሰዎች በሚኖሩባ ቸው ቦታዎች ሁሉ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ (face mask) ማድረግ ቫይረሱ እንዳይ ተላለፍ ይረዳል፡፡
ምንጭ፡- BMC reproductive health

Read 10479 times