Saturday, 23 July 2022 14:09

የክልሎች መዝሙር ሕጋዊ መሠረት አለው?

Written by  ከአብዱራህማን አህመዲን፤ የቀድሞ የፓርላማ አባል)
Rate this item
(2 votes)

    እኛ ኢትዮጵያውያን መቼም ትንሽ እርግማን ብጤ ሳይኖርብን አይቀርም፡፡ ጡር ሳንሰራ አይቀርም፡፡ መስቃ ሳንፈጽም አይቀርም፡፡ ያ ካልሆነ በትንሽ በትልቁ መጨቃጨቅን፣ በየእለቱ መነታረክን፣ አጀንዳ እየፈበረክን እሰጥ አገባ ውስጥ መግባትን የእለት ከእለት ስራችን አናደርገውም ነበር፡፡ ሰሞኑንም ብዙ የመነታረኪያ አጀንዳዎች ተለቀውልናል፡፡ አንዷን ወስጄ የዚህ መጣጥፍ ርእሰ ጉዳይ ላደርጋት ወደድሁ፡፡
ባለፈው ሳምንት የአዲስ አበባ ከንቲባ የምክር ቤት አባላት ላቀረቡላቸው ጥያቄዎች በሰጡት መልስ፤ የኦሮሚያ ክልል መዝሙር በአዲስ አበባ ት/ቤቶች እንዲዘመር የተደረገበትን ምክንያት አብራርተዋል፡፡ ያንን ማብራሪያ ከሰማሁ በኋላ ስለ ብሄራዊ መዝሙር ትንሽ ንባብ አደረግኩና ይህቺን ማስታወሻ ከተብኩ፡፡
በዚህ መጣጥፍ ስለ የህዝብ መዝሙር ትርጉም፣ ስያሜ፣ ታሪካዊ ዳራ፡- ማለትም የህዝብ መዝሙር መቼ እንደተጀመረ፣ የት ሀገር እንደተጀመረ፣ የክልል የህዝብ መዝሙር ስላላቸው ሀገሮች፣… የመሳሰሉትን አጠቃላይ ሁኔታዎች በወፍ በረር እንቃኛለን፡፡ ወደ ሀገራችን የህዝብ መዝሙር በመመለስ ታሪካዊ ዳራዎችን ጨምሮ ሂደቱን እናወሳለን፡፡ አሁን በስራ ላይ ያለው የኢትዮጵያ ህዝብ መዝሙር እንዲሁም ኢትዮጵያን የረሳው የክልሎች መዝሙር ሕጋዊ መሠረት ያለው ስለመሆን አለመሆኑ እናያለን፡፡ ከትርጉሙ እንጀምር…
ብሄራዊ መዝሙር በተለያዩ ምሁራን በተለያየ መንገድ የሚገለጽ ሲሆን ለምሳሌ ኬለን (2003፣ 166) ብሄራዊ መዝሙር ማለት “ሁልጊዜ መዘመር ያለባቸው፣ ሁልጊዜ የሚዘመሩ ቃላት ናቸው። እነዚያ ቃላት እና ዜማዎች ቋሚ ምልክቶች ተደርገው የሚወሰዱት ለዚህ ነው። በዚህ መንገድ ነው ሀገራት ቋሚ መሆናቸውን የሚገልጹት” በማለት ትርጓሜ ሰጥቶታል፡፡
ብሔራዊ መዝሙር የአንድን ሀገር ወይም ሕዝብ ታሪክና ወግ የሚያመለክትና የሚያሞካሽ፣ አርበኝነት የሚገለጽበት፣ ግጥምና ዜማን ያካተተ ሙዚቃዊ ቅንብር ነው። አብዛኛዎቹ የህዝብ መዝሙሮች በወታደራዊ ሰልፎች የሚቀርቡ ህብረ ዝማሬዎች መሆናቸው ይስተዋላል። የላቲን አሜሪካ፣ የመካከለኛው እስያ እና የአውሮፓ ሀገራት ያጌጡና የኦፔራ ገጽታ ያላቸው የህዝብ መዝሙሮችን የማቅረብ ዝንባሌ አላቸው፡፡ የመካከለኛው ምስራቅ፣ የኦሽንያ፣ የአፍሪካ እና የካሪቢያን ሀገራት ደግሞ ይበልጥ ቀለል ያሉ “ፋንፋር” መዝሙሮችን ይጠቀማሉ። በብዙ ግዛቶች የተከፋፈሉ እንደ ዩናይትድ ኪንግደም፣ ሩሲያ እና የቀድሞዋ ሶቪየት ኅብረት ያሉ አንዳንድ ሀገሮች፣ የተለያዩ ይፋዊ ብሔራዊ ህብረ ዜማዎች አላቸው። የእነዚህ ሀገሮች አካል በሆኑ ክልሎች አካባቢያዊ ዜማዎች ያላቸው ሲሆን ግዛቶቹ ሉዓላዊ መንግስታት ባይሆኑም ብሔራዊ መዝሙሮች ተብለው ይጠራሉ።
የብሔራዊ መዝሙር ታሪካዊ ዳራ
በጥንት ዘመን አንዳንድ የአውሮፓ ነገሥታት ንጉሣዊ መዝሙሮች ነበራቸው፡፡ ከእነዚህ መዝሙሮች መካከል አንዳንዶቹ በሕይወት ተርፈው አሁንም ጥቅም ላይ ናቸው፡፡ “እግዚአብሔር ንግስቲቷን ይጠብቃት” የሚለው መዝሙር ለመጀመሪያ ጊዜ የተዘመረው እ.ኤ.አ በ1619 ዓ.ም ሲሆን እስከ አሁን ድረስ የዩናይትድ ኪንግደም እና የኮመንዌልዝ ግዛቶች ንጉሣዊ መዝሙር ሆኖ ያገለግላል። እ.ኤ.አ. በ 1770 ዓ.ም የስፔን ንጉሣዊ መዝሙር ተብሎ የጸደቀው “ሮያል ማርች” (La Marcha Real) በ1939 ዓ.ም የስፔን ብሔራዊ መዝሙር ሆኖ ጸድቋል። ዴንማርክ በ1780 ዓ.ም የተዘጋጀውን ንጉሣዊ መዝሙሯን እንደያዘች፣ ከ1835 ጀምሮ ከዚሁ ጎን ለጎን ተጨማሪ ብሔራዊ መዝሙር አጽድቃለች፡፡ ቬትናምም የአውሮፓውያን ገጽታ ያለው ንጉሣዊ መዝሙር በ1802 ዓ.ም አዘጋጅታለች።
ከሐምሌው አብዮት በኋላ የፈረንሳይ ግዛት የሆነቺው ማርሴይ ቀድሞ ወደነበረችበት መመለሷን ለማብሰር የፈረንሳይ ብሔራዊ መዝሙር ተጀመረ፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ አዲስ የተቋቋሙት ሀገራትም ሆኑ ነፃነታቸውን የተቀዳጁት ሀገራት ብሔራዊ መዝሙሮችን ማዘጋጀት የተለመደ ሆነ፡፡ በተለይም በላቲን አሜሪካ የተደረጉ የነጻነት ጦርነቶችን ተከትሎ በአርጀንቲና (በ1813 ዓ.ም)፣ በፔሩ (በ1821 ዓ.ም)፣ በብራዚል (በ1831 ዓ.ም) በቤልጂየም (በ1830 ዓ.ም) የህዝብ መዝሙሮችን መዘመር የተለመደ ሆነ፡፡
በመሆኑም ከ1930ዎቹ በፊት ብሔራዊ መዝሙሮችን የሚያዘጋጁት በአብዛኛው አዲስ የተቋቋሙ ወይም አዲስ ነፃ የወጡ መንግስታት ነበሩ፡፡ በዚህ መሰረት የፖርቱጋል ሪፐብሊክ በ1911 ዓ.ም፣ የግሪክ መንግሥት በ1865 ዓ.ም፣ የፊሊፒንስ ሪፐብሊክ በ1898 ዓ.ም፣ ሊቱዌኒያ በ1919 ዓ.ም፣ ጀርመን በ1922 ዓ.ም፣ የአየር ላንድ ሪፐብሊክ በ1926 ዓ.ም እና ታላቋ ሊባኖስ በ1927 ዓ.ም የየሀገሮቻቸውን የህዝብ መዝሙር አዘጋጅተዋል።
ምንም እንኳን በ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በይፋ ተቀባይነት ያለው ብሔራዊ መዝሙር የተለመደ ቢሆንም፣ አንዳንድ ብሔራዊ መዝሙሮች የህዝብ መዝሙር ሆነው ከመጽደቃቸው በፊት የሀገር ፍቅር መዝሙር ሆነው ያገለግሉ ነበር። በአንዳንድ ሀገሮች ደግሞ ወታደራዊ ማርሽ ሆነው ያገለግሉ ነበር፡፡
አንድ ብሄራዊ መዝሙር ዜማና ግጥሞችን ያካተተ መሆን አለበት ከተባለ ጥንታዊው ብሔራዊ መዝሙር ተብሎ ሊጠቀስ የሚችለው የኔዘርላንድ ብሔራዊ መዝሙር ነው። የጃፓን ብሄራዊ መዝሙር ግጥም ከኔዘርላንድ መዝሙር የቀደመ፣ ከበርካታ ምዕተ-አመታት በፊት ማለትም እ.ኤ.አ ከ794–1185 ባለው ጊዜ የተጻፈ ነበር፡፡ ነገር ግን እስከ 1880 ዓ.ም ድረስ በሙዚቃ የተቀናበረ አልነበረም።
ብሄራዊ መዝሙር ማለት “በይፋ የአንድ የተወሰነ ግዛት ብሔራዊ መዝሙር ነው ተብሎ በከፍተኛ የመንግስት አካል ከጸደቀበት ጊዜ መጀመር አለበት” ከተባለ በዚህ ረገድ በ1796 ዓ.ም በፈረንሳይ ብሔራዊ ኮንቬንሽን በይፋ የፀደቀው የፈረንሳይ “ላ ማርሴይ” የመጀመሪያው ይፋዊ ብሔራዊ መዝሙር ተብሎ ሊወሰድ ይችላል።
እ.ኤ.አ. በ1920 ዓ.ም የወጣው የኦሎምፒክ ቻርተር፣ የወርቅ ሜዳሊያ አሸናፊዎች ብሔራዊ መዝሙሮችን የመዘመር ሥነ-ሥርዓትን እንዳስተዋወቀ ይነገራል። ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ብሔራዊ መዝሙሮችን መዘመር በዓለም አቀፍ የስፖርት ዝግጅቶች ላይ ተወዳጅነት እያገኘ መጥቷል፡፡ ይህም ሁኔታ እስከዚያ ጊዜ ድረስ ብሔራዊ መዝሙራቸውን በይፋ ያልገለጹ ወይም ጭራሽ የሌላቸው ሀገሮች ብሄራዊ መዝሙር እንዲኖራቸው ግፊት ፈጥሯል።
ይህን ተከትሎም በርካታ አገሮች ኦፊሴላዊ ተግባራት ላይ ይገለገሉባቸው የነበሩትን የአርበኝነት መዝሙሮች እንደ ብሄራዊ መዝሙር ያስተዋውቁ ጀመር። ሜክሲኮ ከ1854 ዓ.ም ጀምሮ ትገለገልበት የነበረውን መዝሙር በ1943 ዓ.ም አጸደቀች፣ ስዊዘርላንድ ከ1841 ዓ.ም ጀምሮ ትገለገልበት የነበረውን መዝሙር  በ1981 ዓ.ም አጸደቀች። በአፍሪካ እ.ኤ.አ. ከ1960ዎቹ ጀምሮ ከቅኝ ግዛት ነፃ የወጡ ሀገሮች ብሔራዊ መዝሙር ይፋ ማድረግ የተለመደ ነበር። ለምሳሌ ኬንያ ብሄራዊ መዝሙሯን ባቋቋመቺው ብሄራዊ የመዝሙር ኮሚሽ አማካይነት በ1963 ዓ.ም ይፋ አድርጋለች።
በርካታ ሀገሮች ኦፊሴላዊ ብሔራዊ መዝሙር የላቸውም። በዚህም ምክንያት በስፖርት ዝግጅቶች ወይም በዲፕሎማሲያዊ ግብዣዎች ላይ ያልጸደቁ መዝሙሮች ይዘመሩ ነበር። ለምሳሌ፡- ዩናይትድ ኪንግደም “እግዚአብሔር ንግሥቲቱን ይጠብቅ” የሚለው እንዲሁም ስዊድንም እንዲሁ “Du gamla, Du fria” መዝሙር በይፋ የጸደቀ አይደለም፡፡

በዓለማችን ጥንታዊው ብሔራዊ መዝሙር “ዊልሄልመስ” የተሰኘው የኔዘርላንድ ብሔራዊ መዝሙር መሆኑን እድሜ ጠገብ ሰነዶች ያመለክታሉ። ይህ መዝሙር እ.ኤ.አ በ1568 እና 1572 መካከል ባሉት ዓመታት በኔዘርላንድ የአመፅ ጊዜ የተጻፈ ቢሆንም፣ እስከ 1932 ዓ.ም ድረስ ኦፊሴላዊ መዝሙር አልነበረም። ከዓለም ሀገራት ውስጥ 2 ብሔራዊ መዝሙር ያላቸው ኒውዚላንድ እና ዴንማርክ ናቸው፡፡ እነዚህ ሀገራት ሁለት እኩል ደረጃ ያላቸው ኦፊሴላዊ ብሔራዊ መዝሙሮች አላቸው።
ኦስትሪያ በአሁኑ ወቅት ብሔራዊ መዝሙር የሌላት ሀገር ናት። የኦስትሪያ ብሔራዊ መዝሙር እንዲቀር የተደረገው እ.ኤ.አ በ1929 ዓ.ም ነው፡፡ ይህም የሆነበት ምክንያት መዝሙሩ ውስጥ ስድብ አዘል መልእክት አለው ተብሎ ነው፡፡ ግጥሙ የብሪታንያን ቅኝ ገዥነት የሚያሞግስና የማንም መሬት (terra nullius) የሚለውን ጽንሰ-ሀሳብ ለማስቀጠል ነው በሚል ተወንጅሎ ነው። በተለይ “እኛ ወጣቶች እና ነፃ ነን” የሚለው የመዝሙሩ ሁለተኛ መስመር ስንኝ፣ የአውስትራሊያ ተወላጆችን ረጅም ታሪክ የዘነጋ ነው የሚል ትችትም ይሰነዘርበታል።
ጃፓን አጭር ብሄራዊ መዝሙር ያላት ሀገር ናት፡፡ “ኪሚጋዮ” በጃፓን የሄያን ዘመን (እ.ኤ.አ 794 - 1185 ዓ.ም) ባልታወቀ ደራሲ በተፃፈው ጥንታዊ የጃፓን ግጥም ላይ የተመሰረተ የሀገሪቷ ባለ አንድ ስንኝ ብሄራዊ መዝሙር ነው። በሌላ በኩል፤ ግሪክ በዓለም ረጅሙ ብሄራዊ መዝሙር ያላት ሀገር ናት። የግሪክ ብሄራዊ መዝሙር 158 ስንኞች አሉት፡፡
በዓለማችን በጣም አስገራሚ የሆነ ብሔራዊ መዝሙርም አለ፡፡ “ሮያል ማርች” የሚባለው የስፔን ብሔራዊ መዝሙር ምንም ቃላት የሌለው በሙዚቃ መሳሪያ የተቀናበረ ብሔራዊ መዝሙር ነው። መዝሙሩ በትራምፔት ብቻ የሚዜም የወታደራዊ ሰልፍ ዜማ ነበር፡፡ ቀደም ባሉ ጊዜያት ዜማው በግጥም የታጀበ እንደነበር ቢታወቅም፣ ከ1970 ዓ.ም ጀምሮ ግን መዝሙሩ ሙሉ በሙሉ ቃል አልባ ሆኗል። “Tiến quân ca” የሚባለው የቬትናም ብሔራዊ መዝሙር ደግሞ በዓለም ላይ ካሉት ሁሉ በጣም አስፈሪው ብሔራዊ መዝሙር ነው ይባላል፡፡ ድምጹ አስፈሪ እንደሆነ ይነገራል፡፡ ትርጉሙ “ተራመድ የቬትናም ወታደር” ማለት ነው።
የህዝብ መዝሙሮች ስያሜ አላቸው፡፡ አሁን በስራ ላይ ያለው የኢትዮጵያ ህዝብ መዝሙር ርእስ “የዜግነት ክብር” የሚል እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ብዙ ሀገሮች በተመሳሳይ ሁኔታ ለየሀገሮቻቸው የህዝብ መዝሙር ስያሜ ሰጥተዋል፡፡ የኢንዶኔዥያ ብሔራዊ መዝሙር “ራያ” ይባላል፡፡ ትርጉሙም “ታላቋ ኢንዶኔዥያ” ማለት ነው፡፡ የኢራቅ ብሔራዊ መዝሙር “ማውቲና” ይባላል፡፡ ትርጉሙም “የምኖርብሽ ቤቴ” እንደማለት ነው፡፡ የሶማሊያ ብሔራዊ መዝሙር “ሶማሊያ ቶሶ” ይባላል፡፡ ትርጉሙም “ሶማሊያ ተነሽ” ማለት ነው፡፡ የእስራኤል ብሄራዊ መዝሙር የተፃፈው በ1948 ሲሆን “ሃቲክቫህ” ወይም “ተስፋ” ተብሎ ይጠራል፡፡ የግብፅ ህዝብ መዝሙር “ቢላዲ ቢላዲ ቢላዲ” ይባላል፡፡ ትርጉሙም “ሀገሬ ሀገሬ ሀገሬ” ማለት ነው፡፡

የብሔራዊ መዝሙር ግጥም ብዙውን ጊዜ በአገሪቱ ብሔራዊ ቋንቋ ወይም በብዙዎች በሚነገር ቋንቋ ይዘጋጃል፡፡ ከአንድ በላይ ብሄራዊ ቋንቋ ያላቸው ሀገሮች ግጥሙን በነዚያ ቋንቋዎች የሚያቀርቡበት ሁኔታ አለ፡፡ ለምሳሌ፡- የስዊዘርላንድ ብሔራዊ መዝሙር በሀገሪቱ አራት ኦፊሴላዊ ቋንቋዎች (ማለትም፡- ፈረንሳይኛ፣ ጀርመንኛ፣ ጣሊያንኛ እና ሮማንሽ) የተለያዩ ግጥሞች አሉት።
“ኦ ካናዳ” የሚለው የካናዳ ብሄራዊ መዝሙር፣ በእንግሊዝኛ እና በፈረንሳይኛ ኦፊሴላዊ ግጥሞች ያሉት ሲሆን፤ እርስ በርሳቸው ያልተተረጎሙ ናቸው፡፡ የሀገሪቱን የሁለት ቋንቋ ተናጋሪነት ባህሪ የሚወክሉ ስንኞችን በመቀላቀል ይዘመራል። መዝሙሩ ራሱ በመጀመሪያ የተፃፈው በፈረንሳይኛ ነው።
የአየርላንድ ብሄራዊ መዝሙር በመጀመሪያ በእንግሊዘኛ ተጽፎ ተቀባይነት አግኝቷል፡፡ ነገር ግን የአይሪሽ ትርጉም በይፋ ተቀባይነት ባይኖረውም ይዘመራል፡፡ የደቡብ አፍሪካው ለየት ያለ ነው፡፡ ደቡብ አፍሪካ 11 ኦፊሴላዊ ቋንቋዎች ያላት ሲሆን፤ ብሄራዊ የህዝብ መዝሙሩ ግጥም በአምስቱ ቋንቋዎች የተጻፈ ነው፡፡ የመጀመሪያው ስንኝ በሁለት ቋንቋዎች የተጻፈ ሲሆን ቀሪዎቹ 3 ስንኞች በሌሎች ቋንቋዎች የተጻፈ ነው፡፡ ሁለት ዘፈኖችን አንድ ላይ በማጣመር እና ግጥሞቹን በማስተካከል፤ እንዲሁም አዳዲስ ዘፈኖችን በመጨመር ነው የተፈጠረው። የቀድሞዋ ቼኮዝሎቫኪያ፣ ኒውዚላንድ እና ፊጂ በመዝሙራቸው ውስጥ የተለያዩ ቋንቋዎችን ተጠቅመዋል፡፡
የአሜሪካ ህዝብ መዝሙር
የአሜሪካ ህዝብ መዝሙር፣ ከኢትዮጵያ ህዝብ መዝሙር ጋር የሚያመሳስለው ነገር አለው፡፡ ይኸውም ክልላዊ የህዝብ መዝሙር ያለው መሆኑ ነው፡፡ “በከዋክብት ያጌጠ ባንዲራ” የሚል ርእስ ያለው የአሜሪካ ህዝብ መዝሙር የተጻፈው በፍራንሲስ ስኮት ኬይ ሲሆን፤ ጊዜውም እ.ኤ.አ ሴፕቴምበር 14 ቀን 1814 ዓ.ም ነበር፡፡ ከዚህ ግጥም ላይ ተወስዶ “በከዋክብት ያጌጠ ባንዲራ” የሚለው መዝሙር እ.ኤ.አ በ1889 በአሜሪካ የባህር ኃይል በይፋ ስራ ላይ እንዲውል ተደርጓል፡፡ በ1916 ዓ.ም ደግሞ በአሜሪካው ፕሬዝዳንት ውድሮው ዊልሰን እውቅና ያገኘ ሲሆን፤ መጋቢት 3 ቀን 1931 በኮንግሬስ ውሳኔ ብሔራዊ መዝሙር እንዲሆን ተወስኗል፡፡
ከሃምሳው የአሜሪካ ክልሎች አርባ ስምንቱ አንድ ወይም ከዚያ በላይ ክልላዊ መዝሙሮች አሏቸው፡፡ መዝሙሮቹ በእያንዳንዱ የክልል ህግ አውጪ አካል የሚመረጡ ሲሆን፤ የክልሉን የተለየ ሁኔታ የሚያንጸባርቁ መሆናቸው ግምት ውስጥ ይገባል፡፡ ለምሳሌ፣ የአርካንሳስ እና አሪዞና ግዛቶች ሁለት መንግስታዊ መዝሙሮች አላቸው፡፡ አንዳንድ የአሜሪካ ግዛቶች እስከ 10 የሚደርሱ አካባቢያዊ እውቅና የተሰጣቸው መዝሙሮች (ዘፈኖች) አላቸው፡፡ (ይህንን በምሳሌ ላስረዳ፡፡ ለምሳሌ፡- አማራ ክልል የወሎውን “እሪኩም” የክልሉ መገለጫ ዘፈን አድርጎ ሊወስደው ይችላል፡፡ ወይም የአገውኛውን “ጣስካሲምባዋ” የክልሉ መገለጫ ዘፈን አድርጎ ሊወስደው ይችላል፡፡)
ኒውጀርሲ ክልላዊ መዝሙር የላትም፡፡ እ.ኤ.አ. በ2021 ዓ.ም ሜሪላንድ “የእኔ ሜሪላንድ” የሚባለውን በይፋ የሚታወቅ መዝሙር ሰርዛለች፡፡ ኮንፌዴሬሽንን የሚደግፍ ዘረኛ ነው ተብሎ ነው የተሰረዘው፡፡ በምትኩ ግን ሌላ መዝሙር አልተተካም። በ1940 ዓ.ም ተቀባይነት ያገኘው የቀድሞው የቨርጂኒያ ግዛት ዘፈን “ወደ ቀድሞ ድንግልናዬ መልሱኝ” የሚለው መዝሙር፣ በ1997 በቨርጂኒያ ጠቅላላ ጉባኤ ዘረኛ ነው ተብሎ በሚታሰብ ቋንቋ ምክንያት ተሰርዟል። አሁን ደግሞ የኢትዮጵያን ህዝብ መዝሙር ታሪካዊ አመጣጥ እንመልከት፡፡
የኢትዮጵያ ህዝብ መዝሙር
በቀደማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግስት የነበረው የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ህዝብ መዝሙር በ1919 ዓ.ም እንደተጀመረ ሰነዶች ያመለክታሉ፡፡ መዝሙሩ በስምንት ስንኞች የተዋቀረ ሲሆን፤ የግጥሙ ደራሲ ቀኝ ጌታ ዮፍታሄ ንጉሴ ናቸው፡፡ ዜማው በአርመናዊው የሙዚቃ ሰው በኬቮርክ ናልባንዲያን የተሰናዳ ነበር፡፡ ይህ የህዝብ መዝሙር “ኢትዮጵያ ሆይ ደስ ይበልሽ” የሚል ርእስ ነበረው፡፡ ይህ መዝሙር ለመጀመሪያ ጊዜ የተዘመረው ንጉሠ ነገሥቱ በነገሡበት እለት ማለትም፤ ጥቅምት 23 ቀን 1923 ዓ.ም ነበር።
በደርግ ወታደራዊ መንግሥት የአስተዳደር ዘመን ሁለተኛው የኢትዮጵያ ብሔራዊ መዝሙር ተዘጋጅቷል፡፡ ይህ የኢትዮጵያ ህዝብ መዝሙር “ኢትዮጵያ ቅደሚ” የሚል ርእስ ነበረው፡፡ መዝሙሩ ለመጀመሪያ ጊዜ የተዘመረው መስከረም 2 ቀን 1967 ዓ.ም በተከበረው በመጀመሪያው የአብዮት በዓል እለት እንደነበር መረጃዎች ያመለክታሉ። ግጥሙን የጻፈው ገጣሚ አሰፋ ገብረ ማርያም ተሰማ ሲሆን ሙዚቃውን ያቀናበረው አቶ ዳንኤል ዮሃንስ ሀጎስ ነው። ይህ መዝሙር አስር ስንኞች ነበሩት፡፡
አሁን ያለው 3ኛው የኢትዮጵያ ህዝብ መዝሙር “የዜግነት ክብር” የሚል ስያሜ አለው። መዝሙሩ በአስር ስንኞች የተዋቀረ ሲሆን፤ የግጥሙ ደራሲ ደረጀ መላኩ መንገሻ ይባላል፡፡ የዜማው ደራሲ ደግሞ ሰሎሞን ሉሉ ምትኩ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ መዝሙርን በተመለከተ የህገ መንግስቱን ዓላማዎች የሚያንጸባርቅ እንደሚሆንና በህግ እንደሚወሰን በህገ መንግስቱ አንቀጽ 4 ላይ ተገልጿል፡፡ ይሁን እንጂ ይህ መዝሙር ህገ መንግስቱ ከመርቀቁ በፊት በ1984 ዓ.ም የተዘጋጀ ነው፡፡ በዚህም መሰረት የህገ መንግስቱን መንፈስ መሰረት አድርጎ የተዘጋጀ አይደለም፡፡
የክልሎች መዝሙር ሕጋዊ መሠረት አለው?
ከደቡብ ክልል ውጪ ያሉት ሁሉም ክልሎች የራሳቸው የህዝብ መዝሙር አላቸው፡፡ በየትምህርት ቤቱም ታዳጊዎች የሚዘምሩት ይህንኑ የየክልሉን የህዝብ መዝሙር ነው፡፡ በተለይ አንዳንድ ክልሎች ሲያዘምሩት የኖሩትና አሁንም ያለው የህዝብ መዝሙር ቁርሾ፣ ቂምና በቀልን የሚያነሳሳ፣ ፀበኝነትን የሚያበረታታ ይዘት እንዳላቸው በግጥሞቹ ይዘት ላይ ትንታኔ የሰጡ ባለሙያዎች ትዝብታቸውን ተናግረዋል፡፡
ታዳጊ ሕፃናት ያሉበትን ክልል ብቻ እንደ ሀገር ቆጥረው ኢትዮጵያን እንዲዘነጉ የሚያደርግ ይዘት እንዳለውም ይነገራል፡፡ ወንድማማችነትና መከባበርንም የሚያመጣ ይዘት የለውም፡፡ አንዳንድ የህግ ምሁራን “ክልሎች የራሳቸው ሰንደቅ ዓላማ እንደሚኖራቸው በህገ መንግስቱ ተደንግጓል፡፡ የክልል መዝሙር እንዲኖር የሚደነግግ አንቀጽ ግን የለም፡፡ ይህ በሆነበት ሁኔታ መዝሙር ማውጣት ኢ-ህገ መንግስታዊ ነው” የሚል አስተያየት ይሰነዝራሉ፡፡ እንደኔ እንደኔ የክልሎች መዝሙር ህጋዊ መሰረት አያጣም፡፡ ይህንንም ያልኩበት ምክንያት፤ ክልሎች የየራሳቸው ክልላዊ ሰንደቅ ዓላማና ዓርማ እንደሚኖራቸው፣ ዝርዝሩ በየራሳቸው ህገ መንግስት እንደሚወሰን፣ በህገ መንግስቱ አንቀጽ 3 ንዑስ አንቀጽ 3 ላይ ተገልጿል፡፡ ሰንደቅ ዓላማው ሊወጣና ሊወርድ የሚችለው  ደግሞ በህዝብ መዝሙር ዝማሬ ነው፡፡ ስለሆነም ክልሎች ክልላዊ መዝሙር ቢኖራቸው ያን ያህል ህግ የጣሰ መስሎ አይታየኝም፡፡
በሌላ በኩል፤ አንዳንድ ሰዎች “በህገ መንግስቱ የማይፈቅድ ቢሆንም በክልሎች ህገ መንግስት ላይ ተደንግጓል” የሚል መከራከሪያ ያቀርባሉ፡፡ ይህ አባባል ግን ውኃ የሚቋጥር ሆኖ አይታየኝም፡፡ ምክንያቱም በህገ መንግስቱ አንቀጽ 9 ንዑስ አንቀጽ 1 ላይ “ህገ መንግስቱ የሀገሪቱ የበላይ ህግ ነው፡፡ ማንኛውም ህግ፣ ልማዳዊ አሰራር፣ … ከዚህ ህገ መንግስት ጋር የሚቃረን ከሆነ ተፈጻሚነት አይኖረውም” የሚል ድንጋጌ አለ፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ መዝሙርን በተመለከተ የህገ መንግስቱን ዓላማዎች የሚያንጸባርቅ እንደሚሆንና በህግ እንደሚወሰን በህገ መንግስቱ አንቀጽ 4 ላይ ተገልጿል፡፡ ይሁን እንጂ የአንዳንዶቹ ክልሎች መዝሙር ይዘት ይህንን ድንጋጌ የሚጥስ፣ ፀበኝነትን የሚቀሰቅስ ነው፡፡ የሚከባበር ሳይሆን የሚገፋፋ ህብረተሰብ የሚቀርጽ መሆኑም ይስተዋላል፡፡
በአሁኑ ወቅት ክልላዊ መዝሙር የሌለው ደቡብ ክልል ብቻ ነው፡፡ ከአዲሶቹ ክልሎች ሲዳማ መዝሙር እንዳለው ሰምቻለሁ፡፡ ከነትርጉማቸው ከሰማኋቸው ውስጥ ፍጅትና ጦርነትን ቀስቃሽ፣ ግጭት ጠማቂ፣ እልቂት ቀፍቃፊ፣… መሆናቸውን ማስተዋል ይቻላል፡፡ ለምሳሌ የአማራን፣ የትግራይንና የኦሮሚያን ክልላዊ መዝሙሮች እንይ፡፡
በስምንት ስንኞች የተዋቀረውና “የታታሪ ህዝቦች” የሚል ስያሜ ያለው የአማራ ክልል ህዝብ መዝሙር፤ ከሞላ ጎደል ተንኳሽ ቃላት አላየሁበትም፡፡ እንዲያውም “ከሌሎች ህዝቦች ጋር እኩል ተከባብረን፤ በፍቅር በአንድነት አብረን እንዘልቃለን” የሚል አብሮነትን ሰባኪ ሃሳብን ያንጸባርቃል፡፡
በአስራ ሦስት ስንኞች የተዋቀረውና “ኦሮሚያ ለምልሚ፣ በልጽጊና ኑሪ!” የሚል ስያሜ ያለው የኦሮሚያ ክልል ህዝብ መዝሙር፤ ጥሩም መጥፎም ሃሳቦችን በውስጡ ይዟል፡፡ ለምሳሌ “የመቶ ዓመት ግፍን በደም አጠብንልሽ… ገዳችን አስመለስን” የሚሉት ሃሳቦች በአንዳንድ ማህበረሰቦች በጥሩ መንፈስ የሚታዩና ተቀባይነት ያላቸው ሆነው አይታዩም፡፡ በሌላ በኩል፤ “ከሌሎች ህዝቦች ጋር፣ በፍቅርና በአንድነት፣… ለመኖር ዋስትና፣ ጽኑ ዓላማ አድርገን…” የሚሉት ሃሳቦች በበጎነት የሚታዩ ናቸው፡፡
ከሁሉም ለየት ያለው የትግራይ ክልል የህዝብ መዝሙር ነው፡፡ ከነ አዝማቹ በሰላሳ ስምንት ስንኞች የተዋቀረው የትግራይ ክልል መዝሙር በጣም ረዥም ነው፡፡ “መስመር ነው ኃይላችን” የሚል ስያሜ ያለው የትግራይ ክልል ህዝብ መዝሙር፤ ከጥሩነቱ ይልቅ መጥፎ ሃሳቦቹ ያመዝናል፡፡ ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻው ስለ ሰላም አያወሳም፡፡ ስለ አብሮነት አይሰብክም፡፡ ስለ ልማት አያነሳም፡፡ ተስፋን አያመላክትም፤ ፍፁም ጨለምተኛ ነው፡፡ ከሞላ ጎደል የትግራይ ክልል መዝሙር በሚከተሉት ቃላትና ሐረጋት የተሞላ ነው፡፡
“የማንወጣው ተራራ የማንሻገረው ወንዝ የለም፣ … ፍፁም ወደ ኋላ የለም፣… በጭራሽ አንሸነፍም፣… ነፍሳችን ውሃ ይጥማት፣ አለት ይሁን ትራሳችን፣ ዋሻ ይሁን ቤታችን፣ ሌትም ቀንም ጉዞ ይድከመንም፣ ይራበንም፣ በጅቦች እንከበብ፣ መሬት ይጥበበን፣ የጠላቶቻችን ጥርስ ስጋችን ውስጥ ይቀርቀር፣ ስጋችን ላሞራ፣ ደማችን እንደጎርፍ ይፍሰስ፣ አጥንታችን ይድቀቅ ዱቄት ሆኖ ይበተን፣ የጦር መሳሪያ መርዝ ፋሽስታዊ ንዳድ፣ ሚሊዮን ጠላቶቻችን ፊታችን ላይ ይጉረፉ፣ መስዋእትነት መቁሰልና ኪሳራም እንከፍላለን፣ የከፋ መከራም ቢመጣ ወደን እንከፍላለን፣…” የሚሉ ቃላትን የያዘ ሲሆን የሚዘጋውም “አሸናፊዎች ነን” በማለት ነው፡፡
የትግራይ ክልል የህዝብ መዝሙር ስለ ሰላም፣ ስለ ፍቅር፣ ስለ አንድነት፣ ስለ ልማት መስበኩም ይቅር፡፡ ስለ ክልሉ የተፈጥሮ ሀብትም ይሁን ስለ ህዝቡ ባህልና ጀግንነት የሚናገረው ነገር የለም፡፡ ሁሉ ነገሩ ስለ ትግል የሚያትት ከመሆኑም በላይ ስለ ታጋዮች ብቻ የሚናገር በመሆኑ የህዝብ መዝሙር ከሚባል የፓርቲ (የህወሓት) መዝሙር ቢባል በጥሩ ሁኔታ ይገልጸዋል፡፡
ወደ ማጠቃለያው እናምራ…
ከላይ ለማየት እንደሞከርነው፤ ከአንድ ሀገር ብሄራዊ ምልክት መገለጫዎች ውስጥ የህዝብ መዝሙር አንዱ ነው። የህዝብ መዝሙር ጠንካራና ግልጽ በሆነ መልኩ የአንድን ሀገር ታሪክ፣ ባህል፣ ጀግንነት፣ ነጻነትና ማንነት ከሚተላለፍባቸውና ከሚንጸባረቅባቸው መንገዶች በዋናነት የሚጠቀስ ነው።
ብሄራዊ መዝሙር የአንድ አገር ኦፊሻል የአርበኝነት ምልክት (Partiotic Symbol) በመሆኑ ዜጎች ለጋራ ግብ፣ ልማትና ሰላም እንዲነሳሱ ያደርጋል፡፡ ሀገር በጠላት ስትደፈር ዜጎችን በአንድነት ጥላ ስር ያሰባስባል፡፡ ለሰንደቅ አላማችን እና ለብሄራዊ መዝሙራችን በሰጠነው ከፍታ ልክ ኢትዮጵያዊነትን ከፍ እናደርጋለን፡፡ ሰንደቅ አላማችንን እና ብሄራዊ መዝሙራችንን ዝቅ ባደረግን ቁጥር ሀገራዊ አንድነታችንንም እንሸረሽራለን።
አንድ የህዝብ መዝሙር ለሀገረ መንግሥት እና ለብሄረ መንግሥት ግንባታ የሚኖረው እና ሊኖረው የሚችለው ፋይዳ በበርካታ መመዘኛዎች መመዘን ቢቻልም፤ በመሰረታዊነት ያለፈውን ትውልድ ታሪክና ጀግንነት በማስታወስ አሁን ያለው ትውልድ ለሀገሩ ቀናኢ እንዲሆን አንድነቱን እንዲያጠናክር በሚያስተላለፈው መልእክትና መጪው ትውልድም ያለበትን ኃላፊነትና አደራ በማስገንዘብ ደረጃው መመዘን አለበት።
አንድ ብሄራዊ መዝሙር አገራዊ አንድነትን የሚያጠናክር፣ የሁሉንም ማህበረሰቦች ባህልና እሴት የሚገልጽ፣ ዜጎች ያለባቸውን ሀገራዊ ሉዓላዊነትን የመጠበቅ ግዴታ፣ ጀግንነትንና ለአገር የተከፈለው የደምና የአጥንት መስዋእትነት፣ ነጻነትና እኩልነትን፣ ብሄራዊ ኩራትን፣ ወዘተ የመሳሰሉ ጉዳዮችን መያዝ ይኖርበታል።
የህዝብ መዝሙር ልክ እንደ ሰንደቅ አላማ በህዝብ ልብ ውስጥ የሰረጸ፣ ዘመን ተሻጋሪ መሆን ይኖርበታል፡፡ መንግሥታት ሲቀያየሩ አገረ መንግሥቱ እንደማይቀየር ሁሉ የአንድ አገር ብሄራዊ መዝሙር የሚቀየር መሆን የለበትም። በሌሎች ሀገሮች የታየውም ይኸው ነው፡፡ በአገረ መንግሥት እና በብሄረ መንግሥት ግንባታ የተሳካላቸው አገራት፣ ለበርካታ አስርት አመታት መንግሥታት ሲቀያየሩ፣ ብሄራዊ መዝሙራቸውን ሲቀይሩ አይታዩም። በአንጻሩ በሀገራችን መቶ ዓመታት ባልሞላ ጊዜ ሦስት መንግሥታት ሲቀያየሩ ብሄራዊ መዝሙራችን አብሮ ሶስት ጊዜ ተቀይሯል። እንዲህ ያለው ሁኔታ አንድ ቦታ ላይ መቆም አለበት፡፡
እንደኔ እንደኔ ክልሎች የየራሳቸው ክልላዊ የህዝብ መዝሙር ቢኖራቸው ችግር ያለው ሆኖ አይታየኝም፡፡ ይሁን እንጂ የየክልሉ ህዝብ መዝሙር ይዘት ፌዴሬሽኑን የሚያጠናክር፣ ሀገራዊነትን የሚያጎላ፣ ስለ ኢትዮጵያ የሚያወሳ፣ ስለ ህዝቧ አንድነትና ጀግንነት፣ ስለ ልማትና እድገት የሚሰብክ፣ ብሩህ ተስፋን የሚያመላክት መሆን ይጠበቅበታል፡፡  
**
ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻው፡ This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ወይም This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡


Read 2258 times