Sunday, 24 July 2022 00:00

“አይቅርብኝ!” - በበጎም በክፉም፣ ከብራና እስከ ኢንተርኔት ዘመን!

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(1 Vote)

   ይላል። ያለ መንግሥት ሞግዚትነት፣ ውለን ማደር የምንችል አይመስለውም። አዎ፣ ሕግና ሥርዓትን የሚያስከብር መንግሥት ከሌለ፣ በሰላም ወጥቶ መግባት አይኖርም። ከትክክለኛ የስራ ድርሻው በተጨማሪ፣ “ምንም አይቅርብኝ” ወደ ማለት ካልሄደ፣ አገር “አማን” ይሆናል። ችግሩ፣ በዚህ የማይረካ ፖለቲከኛ ሞልቷል። “ሁለ-ገብ”፣ “ሁሉን-ቻይ” መሆን ያለበት ይመስለዋል። “መንግሥት የሕዝብ እረኛ ነው” ብሎ ያስባል። መንግሥት እረኛ ከሆነ፣ ሕዝብስ ምን ሊሆን ነው? በዚያ ላይ፣ “አይቅርብኝ” ብሎ ሁለገብ ለመሆን ሲሻማ፣ የስራ ድርሻውን ትቶ ሃላፊነቱን ያዋርዳል። ህግና ሥርዓትን ይረሳዋል። በሌላ በኩል ደግሞ፣ አንዳንዱ ጋዜጠኛና ተዋናይ፣ ዘፋኝና ገጣሚ፣ ወይም የእግርኳስ ኮከብ… ድንገት ሙያውን ትቶ ፖለቲከኛ ካልሆንኩ ይላል።
በእርግጥ፣ የፖለቲካ ፍላጎቱ ድንገተኛ ካልሆነና፣ ቀስ በቀስ አብሮት ያደገ ከሆነ፣ በጎ ነው። የእድሜ ልክ ዝንባሌ ከሆነ፣ ከሙያ አይተናነስም። ድንገተኛ
ሲሆን ግን፣” አይቅርብኝ” ይመስልበታል፤ ሙያ አይሆንለትም። ከቀድሞ ስራው ያዘናጋዋል፤ ሙያውን ያስረሳዋል። እንዲያም ሆኖ፣ ለመፍረድ
ያስቸግራል። ብዙዎቹ ወደ ፖለቲካ ረግረግ የሚገቡትና የሚጨቀዩት፣ ሳይታወቃቸው እየተንሸራተቱ ነው። ጎትጓችና ተንኳሽ ሞልቷል። ጠብ ያለሽ በዳቦ በዝቷል። አጨብጫቢ ተከታይም እንዲሁ። ተላካፊ ነገረኛ የመበርከቱ ያህል፣ አይዞህ ባይ አሳሳችም እንደ ልብ ይገኛል። ታዲያ፣ ታዋቂ ሰዎች የአጃቢ እልልታ ቢማርካቸውና ቢሳሳቱ፣ ዝነኞች በትንኮሳ ሰበብ የእልህ ስሜት ቢጋልባቸውና ቢሰናከሉ ይፈረድባቸዋል? ከቀሽም ቲፎዞዎች ግፊት ጋር እየተንፏቀቁ፣
በብሽሽቅ እልህ እየተጎተቱ፣ ሳያስቡት ወደ ፖለቲካ ረግረግ ይገባሉ። ከተነከሩበት በኋላ ደግሞ፣ ተመልሰው ለመውጣት ይቸገራሉ። እርም ብለው ለመላቀቅ ማሰባቸው፣ እርግፍ አድርገው ለመተው መሞከራቸው አልቀረም። “ምለው የሚገዘቱ” ጥቂት አይደሉም። ምን ያደርጋል? ገና አስበው ሳይጨርሱ፣ ለመራመድ ገና እግራቸውን ሳያነሱ፣… እዚያው እያባበለ የሚያዘናጋ የደጋፊዎች ውትወታ አስሮ ይይዛቸዋል። ህሊናቸውን ጠልፎ ይወስድባቸዋል። ስንዝር ለመነቃነቅ ጊዜ የማይሰጥ የውዝግብ መዓት፣ እዚያው አንቆ ያስቀራቸዋል። በየቀኑ በእልህ የሚያንተከትክ የብሽሽቅ ሰበብ ጠፍቶ አያውቅማ። አንዱ እየተነኮሰ፣ ሌላኛው እያሞካሸ፣ እየጎተተም እያዳለጠም፣ እጥፍ አድርጎ ይዘፍቃቸዋል። ተሳዳቢና ተላካፊ ብቻ አይደለማ ችግሩ። አይዞህ ባይና አሳሳች ቲፎዞም ጉልበተኛ ነው። ለቲፎዞ የመታዘዝ እዳ አለባቸው። አለበለዚያ፣ ጭቃውን ያዞርባቸዋል። ለደጋፊያቸው እልልታ ጆሮ ካልሰጡና እህ ብለው ካልሰሙ፣ ለቲፎዞ ውትወታ ካልተሸነፉና እሺ ብለው ካልተሳተፉ፣ ጉዳቸው ሊፈላ ይችላል። የዛሬ ተከታያቸው ነገ እየተከታተለ ስድብ ያወርድባቸዋል። ቀላል ሸክም አይደለም። እዚያ ከፍታ ላይ ያልደረስንና መዘዙ ያልደረሰብን ሰዎች፣ ነገሩን አቅልለን ልናየው እንችላለን። ግን በጣም ከባድ ነው። የምታውቁት
ሰው ሁሉ የጠመመባችሁ የጠመዳችሁ ቢሆን አስቡት። ለነገሩ፣ ደጋፊዎቹ በኩርፊያ ባይዞሩበት፣ አጃቢዎቹም ለስድብ ባይዘምቱበት እንኳ፣ እንደ
ወትሯቸው ካልሆኑለት፣ በጭንቀት ይናወጣል። ያስለመዱትን እልልታ ካስቀሩበት፣ ከዙሪያው ከራቁ፣ አጀቡ ከሳሳ፣ ዓለም ሁሉ ኦና የሆነችበትና ከመዝገቧ የሰረዘችው ሊመስለው ይችላል። በእርግጥ፣ ችግር የለውም። እንዲህ እስኪሆን ድረስ ማን ይጠብቃል? ገና፣ ከፖለቲካው ረግረግ ለመውጣት ሲያስቡ፣ ከማጡ ገለል ለማለት ሲሞክሩ፣ የቲፎዞዎች ውትወታ ያስደነብራቸዋል። “ምነው ዝም አልክ?” እያለ ትንፋሽ ያሳጣቸዋል። የሆነ ነገር መተንፈስ አለባቸው። ያሰቡትን ትተው፣ ያስለመዱትንና የሚጠበቅባቸውን ነገር መናገር መፃፍ ይኖርባቸዋል። ወደ ዳር ለመሄድ ያነሱትን እግር፣ አጃቢያቸው  ጎትቶ ይወስድባቸዋል። የተቀናቃኝ ስድብና ብሽሽቅም፣ እልህ እያስያዘ ወደ አዘቅቱ መሃል ይገፋቸዋል። እንዴትና በየት በኩል ማምለጫ ያገኛሉ? ማምለጫ መንገድ ቢገኝስ፣ በየትኛው አቅም? በአንዳች ተዓምር ኃይለኛ ፅናትና ብርታት አግኝቶ፣ የእልህ ስሜትን ተቋቁሞ፣ ብሽሽቅን ችላ ብሎ፣ ስድባቸውንም በዝምታ ቢያሳልፍ፣… አይለቅቁትም። እንዲያውም ይጠምዱታል። የጭቃ መዓት እጥፍ ድርብ ያወርዱበታል። በአዲስ የእልህና የብሽሽቅ ስሜት፣ በአዲስ ጉልበት
ተመልሶ ይገባበታል። አንዳንዱ ዝነኛ ግን ብልጣብልጥ ነው። ይጠነቀቃል። ዘው ብሎ ሳይገባ፣ በእግር ጣት ብቻ እየተጠነቀቀ ዳር ዳሩን እየነካካ ለመቆየት
ይጥራል። ግን፣ በእግር ጣት ላይ ቆመው እስከመቼ ይዘልቁታል? ያኔም፣ “እስከ ቁርጭምጭሚት ብቻ ከሆነ ችግር የለውም” ብለው ራሳቸውን ለማሳመን
ይሞክራሉ። ትንሽ ቆይተው እስከ ጉልበት ድረስ ወደ ረግረጉ ይራመዳሉ። ሁለመናቸው ለመነከር፣ ጭቃ ውስጥ ለመንከባለል፣ ብዙ ጊዜ አይፈጅባቸውም።
ለነገሩ፣ “ዳር ዳሩን ብቻ!” ብለው ቢቆሙ እንኳ፣ የፖለቲካ ረግረግ ዝም ብሎ አይጠብቅም፤ ባለበት ረግቶ አይቀመጥም። የምን እርጋታ? ወዲህ ወዲያ
ይምቦራጨቃል። ጭቃ የሚወራወሩ ጀማሪና ነባር የረግረግ ቤተኞች አካባቢውን ሁሉ ይበክሉታል። በግማሽ ልብ ዳርዳሩን የሚያመነቱና የተነካኩ ሰዎች፣ ከፍንጥርጣሪው አይመልጡም። ጭቃ በጭቃ ይሆናሉ። አንደኛውን ከአካባቢው ርቀው ካልጠፉ በቀር፤ አንደኛውን ብንገባበት ይሻላል ብለው ይቀላቀላሉ።
ወደ ፖለቲካ ረግረግ ጠጋ ጠጋ ማለት፤ ዳርዳሩን ማንዣበብ፣ ጎራ እያሉ በዙሪያው እግር ማብዛት ተጠልፎ ለመግባት ነው። ከጭቃው ግድም ዞር ዞር
ማለት ካዘወተሩ፣ መነካካት አይቀርም። ከተነካካ አይቀር ደግሞ፣ “ሌላውን የማጨቅየት እድል ለምን ያምልጠኝ!”፤ “ጭቃ እየተወረወረብኝ፤ አፀፋው መመለስ እየቻልኩ ለምን ዝም እላለሁ!” በሚል ስሜት ተጎትቶ ይገባና ይለይለታል። የኑሮ መተዳደሪያውንና ሙያውን ረስቶ፣ የፖለቲካ ረግረግ ምርኮኛ ይሆናል። ትንሽ በትንሽ፣ እየተንሸራተተ እየተነካካ። በእርግጥ፣ አንዳንዶቹ በዝላይ ነው ዘው ብለው የሚገቡበት። በየሙያ መስካቸው ስኬታማ
ከዋክብት ለመሆን የቻሉ ሰዎች፣ የፖለቲካ ሜዳ ውስጥ ገብተው ጨለማውን የሚያደምቁ አብሪ ከዋክብት ለመሆን የሚችሉ ይመስላቸዋል። ሰናይ እድል ይሁን ጠማማ እድል ይሁን ለይቶ ለመናገር ያስቸግራል። የዩክሬኑን ዜለንስኪ ተመልከቱ። ከአዝናኝ ኮመዲ ተነስተው፣ ዛሬ የጦርነት መሪ ሆነዋል። እድል ነው ወይስ ፍዳ? የሆኖ ሆኖ፣ አንዳንዶቹ ሰዎች፣ ከንግድና ከቢዝነስ ሙያቸው፣ ከተዋናይነት ወይም ከሂሳብ አስተማሪነት፣ ከእግርኳስና ከዘፈን፣ ከጋዜጠኝነትና
ከሃይማኖት ሰባኪነት፣ ከእርሻ ወይም ከሰራተኛ ማህበር አባልነት፣… “ከእንስሳ መብት ጠበቃ” ሳይቀር፣ ከኮሜዲም ጭምር፣… ለፖለቲካ ሜዳ
የሚያመች ዝንባሌና እውቀት ያለው ባለሙያ ይገኛል። ከአንድ ሺ፣ ከመቶ ሺ ተዋናይ፣ አንድ ስኬታማ ፕሬዚዳንት አይጠፋም። ታዲያ ድንገት ብልጭ ስለሚልለት አይደለም። ቀድሞውንም፣ ዝንባሌው ይኖረዋል። በሙያው ተዋናይ ቢሆንም፤ የፖለቲካ ጉዳዮችንም መከታተል ያዘወትራል። ከማንነቱ ጋር ያዋህደዋል። የዚህ ወይም የዚያ ፓርቲ ቲፎዞ ከመሆን ያለፈ እውቀት እያዳበረ ይቆያል። የሆነ ጊዜ ላይ እንደ ሮናልድ ሬገን፣ ተወዳጅና ስኬታማ ፖለቲከኛ ለመሆን ይበቃል። ይህ ግን፣ ከስንት ጊዜ አንዴ የሚያጋጥም ነው። ብዙዎቹ አይሳካላቸውም። እንዲያ ሆኖ፣ ከጥበብ መድረክ እየተወረወሩ ወደ ፖለቲካ
መድረክ፣ ከእግርኳስ ሜዳ እየዘለሉ ወደ ፖለቲካ ሜዳ ለመግባትና ኮኮብ ለመሆን የሚሞክሩ ጥቂት አይደሉም። ዛሬ ዛሬማ አይፈረድባቸውም። ዝነኛውና
ታዋቂው ብቻ ሳይሆን፣ ተራ ተርታውም አይቅርብኝ ማለት ይችላል። ለመግባት የማይሞክር ስንት ቢሆን ነው? ፌስቡክ፣ ትዊተር፣ ቲክቶክ፣ ዩቱብ፣… የመግቢያ በሮቹ ቢሊዮን ሰዎችን በየእለቱ ማስተናገድ የሚችሉ ናቸው። ባይሳካ እንኳ፣ መሞከር አያስቸግርም። በእርግጥ፣ እዚያው ደፍቆ የሚያስቀር
ረግረግ መሆኑን አስቀድመው የማያውቁ ሰዎች ሕይወታቸው ድንገት ሲበጠበጥ፣ ነገር ዓለሙ ይጨልምባቸዋል። ሕይወታቸው የአዳሜ መጫወቻና ማገዶ ሲሆንባቸው፣ ማንን እንደሚረግሙ እንጃ። የአይቅርብኝ መዘዝ ከባድ ነው። ቢሆንም ግን፤ ጥሩ ነገሮችን ለማግኘትና ለመጨመር መሞከር መጥፎ አይደለም። ጥሩ ነገሮች በቂ አይደሉም። ሁሌም ማደግ መበርከት አለባቸው። አንድ ጥሩ ነገር ብቻ ይዞ ሌላው ሁሉ ይቅርብኝ ማለት አያዋጣም። በሕይወት
መቆየት አይቻልም እንጂ። ጥሩ ነገሮችን ሟሟላት፤ በአይነትና በመጠን እንዲበረክቱ ማድረግ ነው፤ መልካም ህይወት ማለት። ጥሩ ነገሮችን ከሟሟላት በተጨማሪ፣ እርስ በእርስ ማዋደድና ማዋሃድ ያስፈልጋል። በልክ ማጣጣም፣ እንዲሁም አንዱ ሌላውን እንዲያበለፅግና ወደ ከፍታ እንዲወስድ መጣርን
ይጠይቃል። በዚህ በዚህ ስናየው፤ “አይቅርብኝ” ማለት ተገቢ ነው። በሌላ በኩል ግን፣ “አይቅርብኝ” ብሎ ሁሉም ነገር ውስጥ ለመግባትና፣ “ሁሉንም ነገር ለመሆን” መሞከር፣… “ቢቀርብህ”፣ “ቢቀርብሽ” ያስብላል። ሁለት ባለ ታሪኮችን እንደመልከት። አንደኛዋ፣ “ኢሽታር” ነው ስሟ። የሆነ ጊዜ ምን
እንደነካት፣ ድንገት ተነሳባትና፣ “በሁሉም ነገር አንደኛ ካልሆንኩ” አለች። የተፈጥሮ ህግን ማወቅ፣… ምንነታቸውንና ዑደታቸውን መገንዘብ፣ ከአፈርና ከድንጋይ ሕንጻ መገንባት፣ ከአፈሩን ማሳውን ማለምለም፣ የአዝመራውንም ሲሳይ ማብዛት፣ ፍሬውን ማበርከት፣ አንድ ነገር ነው። “የተፈጥሮ ጌታ”፣
“የተፈጥሮ እመቤት” የሚል ማዕረግ ይስገኛል። የጥበብ የትጋት ውጤት ነው። ኢሽታር፣ “የሰማይ የምድር እመቤት”፣ “የአበባና የአዝመራ፣ የፍቅርና የፍሬያማ ኑሮ አለኝታ” ብለው የሚያሞካሿትም በዚህ እምነት ነው። ነገር ግን፣ ጌታ ወይም እመቤት መሆን ማለት፣… ከልኩ ያለፈ እንደሆነ፣ ተፈጥሮን በዘፈቀደ ወደ ማዘዝ ያዘነበለ ጊዜ፣… ያኔ “በተፈጥሮ ላይ ማመጽ” ይሆናል። ተራሮችን ቆፍሮ መንገድ መስራት፣ የመስኖ ቦይ መዘርጋት ይቻላል። እንደ ኢሽታር ለመሳሰሉ “የተፈጥሮ እመቤቶች”። ግንባታ፣ ለጥበበኛ የተፈጥሮ ጌቶች፣ ይቻላል። ኢሽታር ግን፣ ከዚህም አልፋ፣ “ተራሮች ሁሉ ካላጎነበሱ፣ ሞቼ እገኛለሁ” አለች። “ካልሰገዱ ወዮላቸው” እስከ ማለት ደረሰች። የተራሮች ተፈጥሮ ግን እንደዚያ አይደለም። እና ምን ተሻለ? “በእሳት አጋያቸዋለሁ፤ ልምላሜያቸውን አመድ አድርጌ አራቁታቸዋለሁ” ብላ ዛተች። ዝታም አልቀረችም። “በእብሪት አብጧል” ብላ የጠመደችው ተራራ ላይ ዘመተችበት።
ሰማይ ምድሩን የሚያናውጥ ነጎድጓድ ድምፅዋን ለቀቀችበት። ተሰነጣቀ፣ ግራና ቀኝ ጎኖቹ ተፍረክርከው ተናዱ። የእሳት አውሎ ነፋስ አወረደችበት። ለምለሙ
ተራራ አመድና ከሰል ሆነ። ከዚያስ? ዙፋኗን ተራራው ለይ ተከለች። በየቦታው እየዘመተች የተከለቻቸው ዙፋኖች ብዙ ናቸው። መጀመሪያ ላይ የአንድ ኮከብ (የአንድ ፕላኔት) ገዢ ነበረች። “ኢሽታር ኮከብዋ” ብለው ያከብሯት ነበር። አላረካትም። “የሰማይ ኮከብ” የሚለው ስም ትንሽ ሆነባት።
በሰፊው መንሰራፋትን ፈለገች። ደግሞም፣ የሰማይ ሁሉ እመቤት መሆን አላቃታትም። ብዙም አልተቸገረችም። እረፍት የላትም። ታታሪ ናት። እናም “ኢሽታር የሰማይ ከዋክብት” ተባለች። ግን፣ሰማይ ላይ ተቀምጣ፣ ምድርን በሩቁ እያየች መቆየት አላስቻላትም። ዓለምን አየቻትና፣ በጣም ወደደቻት። የምድርና የሰው ተቆርቋሪ ሆነች። የእርሻ የአዝመራ አምላክ ሆነች። “የፍቅርና የጋብቻ፣ የቤተሰብና የደስታ አለኝታ ናት” ተብላም ታመነባት። በባቢሎንኛ፣ “ኢሽታር ኡማ” ብለው አከበሯት። “ኢሽታር እምነ” ብለው እንደ ተንከባካቢ እናት ቆጠሯት። የፍቅርና የጋብቻ ተቆርቋሪነቷን በማወደስ፣ “ኢሽታር ኡማ እኒስቲ” ብለው አሞገሷት። “ኢሽታር እመ እንስት”… ወይም የሴቶች እናት እንደማለት ነው። ይሁን፣ መልካም ነው። ከልክ ሲያልፍ ነው ችግሩ።
“የልምላሜና የአዝመራ እመቤት” የነበረችው ኢሽታር፤ “ተራራ ካልሰገደልኝ!” ብላ ከልክ ስታልፍ፣… እሳት ለቀቀችበት። “የለምላሜ ጠንቅ የአዝመራ ፀር” ወደ መሆን ወረደች። የመልካምነትን መስመር ጥሳ ከተሻገረች፤ የሁሉም ሥረመሠረት የሆነው “እውኑ ተፈጥሮ” ላይ ካመፀች፣ ዘላለማዊ የልምላሜና የአዝመራ አላማዋን አጽንታ ካልያዘች፣ ሁሉንም ነገር ታጣለች። ሳይታወቃት፣ ማንነቷን ሁሉ ትዘነጋለች። ሳታስበው፣ ተቃራኒውን ትሆናለች። ልምላሜን ታቃጥላለች። ይህም ብቻ አይደለም። የፍቅርና የጋብቻ፣ የቤተሰብና የደስታ እመቤት ናት ተብላለች። እሺ ይሁን። አዎ፣ “የፍቅር ምልክት ናት” ብለው
አክብረዋታል። ነገር ግን፣ የፍቅር አርአያና የጋብቻ ተቆርቋሪ መሆን ማለት፣ በዘፈቀደ መረን የለቀቀ ስሜት ወይም በትዕዛዝ የሚፈጠር ጋብቻ ማለት
አይደለም። ወደ ዚህ ስህተትም ገብታለች - ኢሽታር። መረን የተለቀቀቀ ስሜት፣ ከፍቅር ጋር ያራርቃል። አንድም በወሲብ ንግድ፣ ፍቅርን ያረክሳል። አልያም፣ “የሚሆኑትን ነገር አሳጣቸው” የሚያስብል ይሆናል። በትዕዛዝ ፍቅርን ለመፍጠር፣ በግዴታ ጋብቻን ለመመስረት መሞከርም፣ ምናልባት ባርነትን
እንደሆነ እንጂ ፍቅርን አያመጣም። በሰው የግል ማንነት፣ በመልካም ፈቃድና በነጻነት ላይ የተመሰረቱ ናቸው ፍቅርና ጋብቻ። ነገሩ እንዲህ ነው። የኡሩክ ንጉስ ጊልጋሜሽ፣ በውበቷ ተደንቆ፣ የፍቅር እመቤተነቷንም አውቆ፣ ከልብ የሚወዳት መስሏት ነበር - ኢሽታር። እንዳሰበችው አልሆነም። ለጋብቻ አልፈለጋትም። ኢሽታር፣ በቁጣ ነደደች። ክፉ አውሬ እምጥታ ከተማዋ ላይ ለቀቀችበት። አውሬው አንዴ ሲያጓራ፣ መሬት ተሰነጠቀ። መቶ ሰዎች መሬት ተከፍታ ዋጠቻቸው። አውሬው እንደገና ሲያጋሳ፤ ምድር ተሰንጥቆ ሁለት መቶ ሰዎች እንጦረጦስ ገቡ። ለወትሮ፣ ለከተማዋ ነዋሪዎች ዋና አለኝታቸው
ነበረች። ባልተጠበቀ መንገድ መጥፊያቸው ልትሆን ነው። በእርግጥ፣ የትረካው መነሻ እንደሚነግረን፤ ይሄ ሁሉ ለክፉ ያሰበችው አልነበረም። እንዲያውም፣
ለፍቅርና ለጋብቻ ተቆርቋሪ መሆኗ ነው - መነሻው። ለከተማዋ ነዋሪዎችም አለኝታቸው በመሆኗ ነው - ወደ ከተማዋ የመጣችው። ነዋሪዎች፣ በንጉሡ ላይ በእሮሮ ሲጮሁ ሰምታለች። አመል አመጣ እንጂ፣ ለወትሮው ጊልጋሜሽ፣ ትልቅ ጀግና፣ አዋቂ፣ ጥበበኛ ነበር። በዚህም ብ ዙዎች ያመሰግኑታል። ነ ዋሪዎች ሰ ላም አግኝተዋል። በእርሻና በእጅ ስራ፣ በግዙፍ ግንባታ ጭምር ህይወታቸው በተስፋ እያበበ ነበር። በዚህ በዚህ፣ጊልጋሜሽን ያመሰግኑታል፤ ያደንቁታል።
የሆነ ጊዜ ግን፣ “የሚሆነውን ነገር አሳጣው”። የነዋሪዎች ሕይወት ሁሉ፣ በሱ ትዕዛዝ የመጣ ውጤት መሰለው። የሚያበላቸው የሚያጠጣቸው፣ ከሱ ውጭ ምንም ተስፋ የሌላቸው መሰለው። “የሕዝብ ሞግዚት” ነኝ ብለው የሚያስቡ መንግስታት፣ ቀስ በቀስ የዜጎች ቤትና ጓዳ ውስጥ ገብተን እንዘዝ ይሉ የለ!
“የህዝብ ሞግዚት” ነኝ ብሎ ባሰበ ማግስት፣ “እያንዳንዱ ሰው ለሞግዚት ታዛዥ መሆን አለበት” ብሎ የትዕዛዝና የመመሪያ መዓት መፈብረክ ይጀምራል። ጊልጋሜሽም፤ ወደዚህ አይነት ስህተት ተንሸራተተ። መንግስታት ሃላፊነታቸውን ሲያከናውኑ፣ ህግና ሥርዓትን ሲያስከብሩ፣ ነዋሪዎች በሰላም ሰርተው
ኑሯቸውን ይለውጣሉ። ከተማው ይሟሟቃል፤ ያምራል። ይሄኔ፣ ንጉሶች ይሳሳታሉ። በነሱ ሕግና ትዕዛዝ አማካኝነት የመጣ ለውጥ  ይመስላቸዋል። ማንኛውንም ነገር በትዕዛዝ ለማከናወን ይቃጣቸዋል። ያለኔ፣…. ሰዎች ተስፋ የላቸውም ብለው ማሰብ ይጀምራሉ። “የሕዝብ እረኛ ነኝ” ብለው ራሳቸውን
መሰየም ያዘወትራሉ። ይሄኔ፣… የሚሆኑትን ነገር ያሳጣቸዋል። ይሄኔ፣ ሰዎችን እንደ አገልጋይ፣ እንደ ጭሰኛ፣ እንደ እንስሳት የማየት አመል ያመጣሉ።
መልካም የነበረ መንግስት፣… ሁለገብ ሁሉን ቻይ ሁሉን አቀፍ ካልሆንኩ ይላል። ከእኔ ውጭ ምንም ነገር አይኑር ይላል። ሃላፊነቱን በጀግንነት ያከናውን የነበረው ጊልጋሜሽም፣ ልክ እንደዚህ ተሳሳተ። የነዋሪዎች መኝታና ጓዳ ውስጥ ካልገባሁ አሉ። በጋብቻ እለት፣ሙሽሪት በኔ አልጋ ማለፍ አለባት የሚል
ጉድ አመጣ። በዚህም ነው የነዋሪዎች ቁጣና እሮሮ የተፈጠረው። ፍቅርን የሚያረክስ፣ጋብቻን የሚያዋርድ ክፉ ግፍ ሲመጣ፣ ኢሽታር በዝምታ ማየት አትችልም። የፍቅር እመቤት፣ የጋብቻ አለኝታ ናት። መጣች አየችው። በአንድ በኩል፣ ንጉሡ መንገዱን ስቶ እንጂ፣ የብቃትና የጀግንነት ሰው ነው። በእውቀትም በአካልም በመንፈስም፣ አንቱ የሚያሰኝ፣ ግርማ ሞገስን የሚያቀዳጅ ብዙ ጀግንነት ሰርቷል። የስብዕና ብቃትን ገንብቷል። እውነት ነው። አሁን
መንገድ ቢስትም፣ የእስከ ዛሬ ጀግንነቱን መካድ ተገቢ አይደለም። ግን ደግሞ የቀድሞ መልካም ተግባር፣ ዛሬ ጥፋት እንዲሰራ፣ ግፍ እንዲፈፅም ፈቃድ
አያስገኝለትም። እና ምን ተሻለ? ያሰበውን የጥፋት መንገድ በእንጭጩ ለመዝጋት፣ ለጀግንነቱ የሚመጥን መፍትሔም ለመስጠት የሚችል ማን ነው? የኢሽታር ሃሳብ፣ጥሩ መፍትሄ አይመስልም? ለጋብቻ መረጠችው። ይሄ ለጀግንነቱ ይመጥናል። የሰዎችን ፍቅር የማርከስ የጋብቻ ሕይወታቸውን የማበላሸት ሃሳቡም ለዘላለም ይቀበራል ማለት ነው። ግን የኢሽታር ሃሳብ አልተሳካም። ለበጎ የታሰበ ቢሆንም እንኳ፣ልኩን ከሳተ፣ጥፋት ነው።


Read 10628 times