Print this page
Saturday, 13 October 2012 11:37

የጀርባ ህመም የበርካቶች የጤና ችግር

Written by  መታሰቢያ ካሣዬ
Rate this item
(34 votes)

የጀርባ አጥንቶች መላው ሰውነታችንን ተሸከመው ከመያዛቸውም በላይ የእያንዳንዳችን አቋቋም አካሄድ፣ አቀማመጥና አተኛኘት ይወስናሉ፡፡ በዚህ የሠውነታችን ክፍል ላይ የሚደርስ ጉዳት ለብዙ የጤና ችግሮች መንስኤ ለሆነው ችግርና ለጀርባ ህመም መነሻ ምክንያት ይሆናል፡፡ በአገራችን የሚገኙ የመንግስትና የግል የጤና ተቋማትን መሰረት አድርገው የሚወጡ መረጃዎች እንደሚያረጋግጡት፣ ከህመማቸው ለመፈወስና እፎይታን ለማግኘት ወደ ጤና ተቋማት ከሚሄዱ አሥር ህሙማን መካከል፣ ሶስቱ የወገብና የጀርባ ህመም ተጠቂዎች ናቸው፡፡ የጀርባ ህመም በጀርባ አካባቢ ብቻ ተወስኖ የሚቀር ሳይሆን ቀስ በቀስ ወደ አንገት፣ እጅ፣ እግርና ወደ ፊኛ አካባቢ በመተላለፍ የችግሩ ተጠቂ የሆነው ሰው እንደልቡ ለመንቀሳቀስ፣ ዕቃ ለማንሳትና እንደፈለገ ለመዟዟር እንዳይችል ያደርጉታል፡፡

በጀርባ ህመም መንስኤነት የሚጠቀሱ በርካታ ጉዳዮች ቢኖሩም ከእያንዳንዱ ሰው የዕለት ተዕለት ተግባራት ጋር ቀጥተኛ ቁርኝት ያላቸው ጭንቀት፣ ድብርትና የሥራ ጫና የጡንቻ መወጣጠር እንዲፈጠር ያደርጋሉ፡፡ ይህ ደግሞ በጀርባ አካባቢ የሚገኙ ጡንቻዎችና ነርቮች እንዲኮማተሩ ያደርጋል፡፡ በዚህ ሣቢያም ከቀላል እስከ ከባድ ደረጃ ያላቸው የወገብ ህመሞች ይፈጠራሉ፡፡ በዘርፉ የተካሄዱ በርካታ ጥናቶችና ምርምሮች እንደሚጠቁሙት ያልተስተካከለ አቋምና በቂ እንቅስቃሴ ማድረግ አለመቻል የጀርባ ህመም፣ የአንገት ህመም እና ሌሎች ተያያዥ የጤና ችግሮች ይፈጥራል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ለወገብ ህመም በዋንኛ መንስኤነት ከሚጠቀሱት መካከል የጨጓራ ህመም፣ የዲስክ መንሸራተት፣ የአፈጣጠር ችግር፣ የአካሄድ፣ የአቀማመጥና የአተኛኘት ችግሮች፤ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት፣ የምግብ መፈጨት ሥርዓት መስተጓጐል፣ ጡንቻዎችን በአካላዊ እንቅስቃሴ አለማጠንከር፣ እጢዎች፣ የኩላሊት፣ የማህፀን፣ የዳሌ፣ የሪህና የስኳር በሽታዎች እንዲሁም የጨረር ህክምናዎች ተጠቃሾች ናቸው፡፡ አካላዊ ውፍረት ከመጠን በላይ መጨመርና የአጥንት መሸርሸር ችግርም ለወገብ ህመም መንስኤ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ የጀርባ ህመም ሲከሰት የተለያዩ ምልክቶች የሚኖሩ ሲሆን ምልክቶቹ እንደ የሰው ሁኔታና የበሽታ መከላከል ብቃት ሊለያዩ ይችላሉ፡፡ ሆኖም የጀርባ ህመም ዋንኛ ምልክቶች እንደሆኑ ከሚታወቁት መካከል ራስ ምታት የራስ ማዞርና መደንዘዝ፣ አንገት ለማዟዟር መቸገር፣ የእጅ መደንዘዝና እንደልብ አለመታዘዝ፣ ወገብ ላይ ቁርጥ የሚያደርግ ህመም መሰማት፣ የጡንቻዎች መወጣጠር ስሜት፣ ቁርጥማት፣ ለመተንፈስ መቸገር፣ ሠገራና ሽንት መቆጣጠር አለመቻል፣ የእግርና የእጅ መሸማቀቅና እንደ ኤሌክትሪክ የሚነዝር ህመም ይገኝበታል፡፡ ማንኛውም ሰው እነዚህን ምልክቶች በተደጋጋሚ ያስተዋለ እንደሆነ ወደ ባለሙያ ዘንድ በመሄድ ለችግሩ መፍትሔ መፈለግ ይኖርበታል፡፡ እ.ኤ.አ በየዓመቱ ጥቅምት 16 ቀን የሚከበረውን አለም አቀፉን የአከርካሪ አጥንት ቀን አስመልክቶ ባለፈው ማክሰኞ በተዘጋጀ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ፤ 1ኛ ካይሮፕራክቲክና ሪሃብሊቴሽን ዌልነስ ክሊኒኮች ዳይሬክተርና ከይሮፕራክተር ዶ/ር ሰላም አክሊሉ ሲናገሩ፤ አከርካሪ አጥንት መሃል ላይ ያሉ ነገሮች (ዲስክ) ስፓይናል ኮርድ ጫና ላይ ፈጥሮ ከባድ ችግር ሊፈጥር ይችላል ብለዋል፡፡ ለጀርባ ህመም ከሚያጋልጡ ነገሮች መካከል በግዴለሽነት አካልን ያለ አግባብ በማጠማዘዝ፣ ከባድ ዕቃን ሰውነትን ከጉልበት አጠፍ ሳይሉ በቀጥታ አጐንብሶ ለማንሳት መሞከር አንዱ ሲሆን ተንሸራቶ በወገብ መቀመጥና በመኝታ ጊዜ በጀርባ ተንጋሎ መተኛት ለከፋ የጀርባ ህመም ያጋልጣል ብለዋል፡፡ ወንዶች ከኋላ ኪሳቸው ውስጥ ተለቅ ያለ የኪስ ቦርሳ ይዘው ሲቀመጡ፣ በዳሌ አጥንታቸው ላይ መዛባትን በማስከተል ለጀርባ ህመም እንደሚዳርጋቸውም ዶ/ር ሠላም ይናገራሉ፡፡ የጨጓራ ህመም ከጀርባ ህመም ጋር ግንኙነት ያለው መሆኑን የሚጠቅሱት ዶክተሯ፤ 26% የሚሆኑ ጨጓራችን ታሟል ብለው የሚያስቡ ሰዎች ችግራቸው የጨጓራ ሳይሆን የነርቭ ችግር መሆኑንም ገልፀዋል፡፡ የአከርካሪ አጥንትና ተያያዥ የጤና ችግሮች መንስኤና መከሰቻ ቦታዎቹን መነሻ በማድረግ በሚሰጥ ህክምና ችግሩ ሙሉ በሙሉ መፍትሔ ያገኛል፡፡ ከመድሃኒት ህክምናና ከቆዳ ህክምና ሌላ በሙያተኛ የታገዘ ጅምናስቲኮች፣ ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ የሚሰጡ ፊዚዮቴራፒዎች፣ የአኮንፓክቸር ህክምናዎች ለወገብ ህመም ህክምና ይረዳሉ፡፡ ማንኛውንም አይነት ህክምና ለማድረግ ከመሞከር በፊት ግን የህክምና ባለሙያን ማማከርና ምርመራ ማድረግ ተገቢ ነው፡፡ ለጀርባ ህመም ከሚደረጉ ምርመራዎች መካከል ከበሽተኛው ከሚሰጥ ጠቋሚ ምልክቶች በመነሳት፣ የነርቭና የአካል ምርመራ ማድረግ፤ በየደረጃው ያሉ የአከርካሪ አጥንቶች ያሉበትን ሁኔታ ለማየት የራጅ፣ የሆሮሞግራፊ፣ የሲቲስካንና የኤም አይ አር ምርመራዎች ማድረግ፣ የስኳር፣ የኩላሊት፣ የማህፀን፣ የዘር ፍሬዎች ፊኛ፣ እና መሰል በሽታዎች መኖር አለመኖራቸውን ማረጋገጥ ዋንኞቹ ናቸው፡፡ በቲቢ በሽታ፣ በኩላሊት፣ በሪህ፣ በደም ግፊት፣ በስኳር፣ በጨጓራ፣ በጭንቀትና በውጥረት እንዲሁም በእርግዝናና አካላዊ ውፍረት ምክንያት የሚከሰቱ የጀርባ ህመሞች በህክምና መፍትሔ ያገኛሉ፡፡ የአከርካሪ አጥንት በአደጋ፣ በመውደቅና መሰል በሆኑ ችግሮች ጉዳት በሚደርስበት ወቅት፣ ለተጐዳው የአከርካሪ ክፍል ድጋፍ በማድረግ በደረቅ አልጋ በማስተኛትና መድሃኒት በመስጠት፣ የአከርካሪ አጥንቱን ማከም ይቻላል፡፡ በአከርካሪ አጥንቱ ላይ የደረሰው ጉዳት ከፍተኛ ከሆነና ህብለሰረሰር ድረስ የደረሰ ከሆነ በዚህም ሳቢያ እጅና እግር ከሰነፉ ብሎም መንቀሳቀስ ካቆሙ በቀዶ ጥገና መፍትሔ ያገኛል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በዲስክ መንሸራተትና በትርፍ አጥንት መብቀል ምክንያት የሚከሰተው የጀርባ ህመምም በቀዶ ጥገና ሊስተካከል ይችላል፡፡ ከላይ በዝርዝር ከተገለፁት ውጪ በሆነ የህክምና ዘዴ ማለትም በካይሮፕራክቲክ ህክምና ዘዴ ለአከርካሪ አጥንት ችግሮች መፍትሔ ማግኘት ይቻላል፡፡ ይህንኑ አስመልክተው ዶ/ር ሠላም ሲናገሩ የካይሮፕራክቲክ ህክምና ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባና መድሃኒትም ሆነ ቀዶ ጥገና ምርጫ ሲታጣ ጥቅም ላይ ሊውል የሚገባው የህክምና ዘዴ ነው ብለዋል፡፡ ይህንን ህክምና የሚሰጡ ሰባት ክሊኒኮችን ከፍተው በመንቀሳቀስ ላይ መሆናቸውን የተናገሩት ዶክተሯ አራቱ ክሊኒኮች በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ቀሪዎቹ ሶስቱ ደግሞ በጅማ፣ በድሬዳዋና፣ በጐንደር ከተሞች መከፈታቸውን ገልፀዋል፡፡ አገልግሎታቸውን በማስፋፋት ዘመናዊ ሆስፒታል ለመክፈትና በምሥራቅ አፍሪካ ደረጃ የካይሮፕራክቲክ ህክምና ትምህርት የሚሰጥበት ኮሌጅ ለማቋቋም ዕቅድ እንዳላቸውና ለዚህም መንግስት 4500 የግንባታ ቦታ የሰጣቸው መሆኑን ዶክተር ሠላም ተናግረዋል፡፡ ህብረተሰቡ በአከርካሪ አጥንት ጤንነት ቅድመ ጥንቃቄ ችግሮችና መፍትሔዎች ላይ ግንዛቤ እንዲኖረው ለማድረግም ለአንድ ወር የሚቆይ ነፃ የስልጠና ፕሮግራም መዘጋጀቱንም ዶክተር ሠላም በዚሁ ጊዜ ተናግረዋል፡፡ ከእያንዳንዱ ሰው የዕለት ተዕለት ተግባራት ጋር  በእጅጉ ቁርኝት ያለውን የአከርካሪ አጥንት የጤና ችግር ከዚህ በታች ለመዘርዘር በሞከርኳቸው መንገዶች ልንከላከለውና ለወገብ ህመም ከሚደረገው ችግር ልንድን እንችላለን፡፡ የመከላከያ መንገዶቹ አቀማመጣችንንም ሆነ ለሥራ የምናደርገውን እንቅስቃሴ አካላዊ ቅርፃችንን በሚያዛባ መልኩ  እንዲሆን ማድረግ፡፡ ከባድ እቃዎችን አለማንሳት በጀርባ አለመተኛት፣ በጐን በኩል መተኛትን መልመድ፤ ውፍረትን መቀነስ፤ ሲጋራ አለማጨስ፤ አካላዊ እንቅስቃሴ ማድረግ፤ የሥራ አካባቢን ምቹ ማድረግ የተመጣጣነ ምግብ መመገብ ለረጅም ጊዜ አለመቆምና አለመቀመጥ የረዥም ርቀት አሽከርካሪዎች እረፍት እያደረጉ ማሽከርከሩን ልማድ ማድረግ ሲሆኑ ሁልጊዜም በምንቀመጥበትም ሆነ በምንራመድበት ወቅት ቀጥ ብለን መሆን እንደሚኖርበት የህክምና ባለሙያዎቹ ያስገነዝባሉ፡

Read 36290 times Last modified on Saturday, 13 October 2012 14:37