Saturday, 30 July 2022 13:39

ባቲያ ድል ወንበራ ማን ናት?

Written by  (ከአብዱራህማን አህመዲን፤ የቀድሞ የፓርላማ አባል)
Rate this item
(2 votes)

  ብዙ ጊዜ የምጽፋቸው መጣጥፎች ፖለቲካ ቀመስ ናቸው፡፡ የሰው ልጅ ህይወት ግን ፖለቲካ ብቻ አይደለም፡፡ በአንድ ጉዳይ ላይ ደጋግሞ መጻፍ ራሱ ይሰለቻል፡፡ መሰልቸቱ ብቻ ሳይሆን ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ባህላዊ ጉዳዮቻችን ጭምር ሊጻፍባቸው እንደሚገባ አምናለሁ፡፡ ከዚህ ሌላ በባህሪዬ በአንድ ጉዳይ ላይ መቸከል አልወድም፡፡ እናም በዛሬው መጣጥፌ ለየት ባለ ጉዳይ ላይ ለማተኮር አሰብኩ፡፡ እንዲያው ለየት ያለ ጉዳይ አነሳለሁ አልኩ እንጂ ነገሩ ከዚያው ከፖለቲካ አልወጣሁም፡፡
ሰሞኑን በሙስጠፋ ሙሐመድ ዑመር የሚመራው የሶማሌ ክልል አስተዳደር ድንበር ዘለል አሸባሪዎችን በሚገባቸው ቋንቋ አናግሮ ልሳናቸውን መዝጋቱን በዓለም አቀፍ መገናኛ ጭምር ሲዘገብ ሰምተናል፣ አይተናል፡፡ የኢትዮጵያ የጠረፍ ህዝቦች ያልተዘመረላቸው ኢትዮጵያን የጠበቁ፣ የመሀሉ አገር ዳር እንዳይሆን በየዘመኑ ከጠላት ጋር የተናነቁ፣ ጠንከር ያለ ጠላት ሲመጣ የመሀል አገር የወገን ጦር ኃይል ተጓጉዞ እስኪመጣ ብዙ ብዙ መስዋእትነት የከፈሉ ግንባር ቀደም የኢትዮጵያ ፊትአውራሪዎች ናቸው፡፡ በዚህ መጣጥፍ የማቀርብላችሁ ከጠረፍ ህዝቦች ታሪክ የተጨለፈ ነው፡፡
ከዓመታት በፊት “እቴጌ መነን ሊበን - የዘመነ መሳፍንት ‘አፍሪካዊቷ ካተሪን’” በሚል ርእስ አንድ መጣጥፍ መጻፌ ይታወሳል፡፡ በዚያ መጣጥፍ መግቢያ ላይ ያሰፈርኩትን ማስታወሻ አሁንም ደግሜ ማንሳት እወዳለሁ፡፡ ብዙ ጊዜ የሚገርመኝ አንድ ጥያቄ አለ፡፡ ጥያቄው፤ “በሀገራችን ሴት የታሪክ ጸሐፊ ለምን የለም?” የሚል ነው፡፡ የዚህን ጥያቄ መልስ በተለይ ሴቶች ብትወያዩበት መልካም ነው፡፡ የሀገራችን ሴቶች ከጥንት ጀምሮ በሀገራችን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ባህላዊ ጉዳዮች ዙሪያ ያላቸው ተሳትፎ የላቀ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ይህ የሀገራችን ሴቶች ታሪክ በአግባቡ አልተመዘገበም፤ አልተዘገበምም፡፡ ቢዘገብም በወንዶች ታሪክ ውስጥ ጠቀስ ተደርጎ የሚታለፍ እንጂ ራሱን ችሎ እንዲጻፍ አልተደረገም፡፡ አቅም በፈቀደ ይህ የተዳፈነ ግማሽ ታሪካችንን ለማስታወስና የታሪክ ጸሐፊዎችን ለማነቃቃት በማሰብ ነው ይቺን ጽሁፍ ያዘጋጀሁት፡፡ ወደፊት “ዮዲት ጉዲት”ን ጨምሮ የሌሎች ሴቶችን ታሪክ አቀርባለሁ፡፡ የዛሬው መጣጥፌ በ15ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በነበረች አንዲት ኢትዮጵያዊት የሀገር መሪ (የኢማም ሚስት) ታሪክ ዙሪያ የሚያጠነጥን እንዲሆን ፈቀድኩ፡፡
የማቀርብላችሁ ባለ ታሪክ ሙሉ ስሟ ባቲያ ድል ወንበራ ማህፉዝ ትባላለች፡፡ አባቷ የአዳል ሱልጣኔት የጦር መሪ የነበረው ማህፉዝ ሙሐመድ ሲሆን፣ ባሏ ደግሞ አባቷ ከሞተ በኋላ የአባቷን ገዳዮች አጥፍቶ የነገሰው፣ 15 ዓመታት ኢትዮጵያን ከጫፍ እስከ ጫፍ ዞሮ የገዛውና ስሙ በጥሩም በመጥፎም የሚነሳው ኢማም አሕመድ ኢብን ኢብራሂም አልⷛዚ፣ ብዙዎች ግራኝ አሕመድ በሚል ሥም የሚያውቁት ሰው ነው፡፡
“ድል ወንበራ” የሚለውን ቃል ትርጉም በተመለከተ የተለያዩ ሃሳቦች ይነሳሉ፡፡ አንዳንድ የታሪክ ጸሐፊዎች “ድል ወንበራ” ማለት “ድል ወንበሯ ወይም ድል ዙፋኗ” ማለት ነው ይላሉ፡፡ አፋሮች ደግሞ “ከሁሉም በላይ የምትመረጥ፣ ተወዳጅ፣ ተመራጭ” ማለት ነው ይላሉ፡፡ “ባቲያ” የሚለው ከስሟ ቀድሞ የሚጨመረው ቃል “ልዕልት ወይም እቴጌ” የሚለው ዓይነት የማዕረግ ስም ይመስላል፡፡ በዚያ ዘመን ለነበሩ የበለው ጎሣ ተወላጆች ለሆኑ ሴቶች የሚሰጥ ማዕረግ ነው፡፡ ወንዶቹ የበለው ጎሣ ተወላጆች “አውራይ” ይባሉ ነበር፡፡
ባቲያ ድል ወንበራ መቼ እንደተወለደች የታሪክ መዝገብ ላይ የሰፈረ ጊዜ አልተገኘም፡፡ የት እንደተወለደቺም በትክክል አይታወቅም። ይሁን እንጂ አባቷ ዋና ከተማው አድርጎ ባስተዳደረበት “ሁበት” በተባለ አካባቢ እንደተወለደች ለእውነት የቀረበ ግምት መናገር ይቻላል፡፡ አባቷ ኢማም ማህፉዝ ሙሐመድ አንዳንድ ጊዜም የሐረር አሚር ይባላል፡፡ ኢማም ማህፉዝ የአዳል ሱልጣኔት ወይም የወላስማ ስርወ መንግሥት መሪ ነበር፡፡
ማህፉዝ ሰለሞናዊውን ማዕከላዊ የሐበሻ መንግሥት ለ25 ዓመታት ደጋግሞ በመውጋትና ዓመታዊ ግብር አልገብርም በማለት ይታወቃል። በዚህም ምክንያት በወቅቱ የነገሰው ወጣቱ አፄ ልብነ ድንግል ወደ ማህፉዝ ግዛት ዘመተ፡፡ ማህፉዝ በዚህ ጦርነት እንደማያሸንፍ ሲገባው መላ ቤተሰቡንና የስርወ መንግሥቱን አሚር ወደ ሐረር በመላክ ከአፄ ልብነ ድንግል ጦር ጋር ውጊያ ገጠመ፡፡ እንደጠረጠረውም በጦርነቱ ተሸነፈ፣ ሞተ፡፡
***
ማህፉዝ ከወንዶቹ ልጆቹ እሱን የሚተካ አልጋ ወራሽ ማግኘት ባይችልም ሴት ልጁ ድል ወንበራ ግን የወላስማን ብቻ ሳይሆን የመላዋን ኢትዮጵያ ታሪክ መቀየር የቻለች አስደማሚ ሴት እንደነበረች የታሪክ ጸሐፊዎች ጭምር መስክረዋል፡፡ ከግብጻዊቷ ክሊዎፓትራ ጋርም ያነጻጽሯታል፡፡ ድል ወንበራ አባቷ መሞቱን ስትሰማ በጣም እንዳዘነች በሐረርጌ አካባቢ በስነ-ቃል ትውፊቶች በስፋት ይነገራል፡፡
አሚር ማህፉዝ ሲሞት ህጻኗን ድል ወንበራን ከሌሎች ወንድሞችና እህቶቿ ጋር ማን ያሳድጋቸው በሚለው ላይ ምክክር ከተደረገ በኋላ በወቅቱ የሚከበርና በርካታ ተከታይ በነበረውና ከአዳል የጦር መሪዎች አንዱ በሆነው ገራድ አቡን አዱሽ በተባለው የአባቷ የቅርብ ሰው ቤት እንድታድግ ተደረገ፡፡ ድል ወንበራ በገራድ አቡን ቤት በምትኖርበት ወቅት የአባቷን ጓደኞች ስታይ ገና በህፃን አእምሮዋ “የአባቴን ገዳይ እበቀላለሁ” የሚል ቁጭት እንዳደረባት በኋላ ላይ ካደረገቺው ድርጊት ጭምር መገንዘብ ይቻላል፡፡
በዚያው ወቅት ሌላ የገራድ አቡን ጓደኛና የሁበት ግዛት ገዢ የነበረ ኢብራሂም አሕመድ የተባለ ሰው ነበር፡፡ ያ ሰው ማህፉዝ ሲሞት ኢሚር ቢሆንም፣ ከሦስት ወራት በኋላ እሱም ስለተገደለ ልጆቹ የገራድ አቡን ጦር ጋር እንዲቀላቀሉ ተደረገ፡፡ ከኢብራሂም ልጆች አንዱ የ15 ዓመት ታዳጊ ሲሆን በዚያው በገራድ አቡን ቤት የፈረስ ጉግስና የጦር ትምህርት እየተማረ ይኖር ነበር፡፡ የአጋጣሚ ነገር ያ ወጣት በኋላ ላይ ድል ወንበራን ያገባት ጦረኛው ግራኝ አሕመድ ኢብራሂም ነበር፡፡ የሁለቱ ወጣቶች አስደማሚ ታሪክ የሚጀምረውም በዚህ መልኩ በአንድ የወላጆቻቸው የቅርብ ሰው በነበረ ግለሰብ ቤት አንድ ላይ መኖር በጀመሩበት ወቅት ነበር፡፡
***
ድል ወንበራ እና ግራኝ አሕመድ በገራድ አቡን አዱሽ ቤት አንድ ላይ በሚኖሩበት ወቅት ተዋወቁ፡፡ በወግ በማዕረግም ተጋቡ፡፡ ድል ወንበራ ብልህ አማካሪና ከፍተኛ የሞራል ድጋፍ ሰጪ ሆና የምትከሰተው በልዩ ልዩ አጋጣሚዎች ነበር፡፡ የግራኝ ሚስት የነበረቺው ባቲያ ድል ወንበራ፣ ግራኝ ስልጣን ላይ በነበረበት ወቅትም በተደረጉ ጦርነቶች እና ግራኝ ከሞተ በኋላም ከእቴጌ ሰብለ ወንጌል ጋር በተደረገ የምርኮኞች ልውውጥና የዲፕሎማሲ ግንኙነቶች ከፍተኛ አስተዋጽዖ አድርጋለች፡፡
ባቲያ ድል ወንበራ የአባቷን የአሚር ማህፉዝ ደም የሚበቀልላት ብቻ ሳይሆን ዓላማውን ተረክቦ እዳር የሚያደርስላትን ጀግና ለመምረጥ መቻሏ ወይም የዚያ ጀግና ሚስት ለመሆን መቻሏ አንዱ የዓላማ ጽናቷ መገለጫ ነው ማለት ይቻላል፡፡ በዚህ ሂደት የወጣቱን የግራኝ አሕመድን ግልጽና ስውር ባህሪያት ሁሉ ለመቋቋም መቻሏና ብቃት ኖሯት ለግራኝ ምክር ለመስጠት መቻሏ በአድናቆት የሚታይ ነው ይላሉ፤ የታሪክ ጸሐፊዎች፡፡
ሌላው የባቲያ ድል ወንበራ ጠንካራና ቆራጥ ባህሪ በታሪክ ጎልቶ የሚወጣው ደግሞ ከግራኝ ጋር ዘመቻ የጀመረቺው ገና አፍላ ወጣት በነበረቺበት ጊዜ ሲሆን፤ ታሪኩን ተከታትሎ የመዘገበው አረብ ፋቂህ የተባለ የታሪክ ዘጋቢ እንደሚነግረን፤ የጦር አበጋዞቹ “ካንተ በፊት የቀደሙት አሚሮች አንዱም ሚስቱን አስከትሎ ወደ ጦር ሜዳ ሄዶ አያውቅምና ሚስትህ ባቲያ ድል ወንበራም ወደ ሐረር ትመለስ” ብለው ሲነግሩት፣ እሷ ግን እምቢ ብላ ገደላ ገደሉን በሰው ትከሻ፣ ሜዳውን በፈረስና በበቅሎ እየተጓዘች ጦርነቱን በድፍረትና በግለት መካፈሏን ቀጠለች፡፡ በሸዋ፣ በወሎ፣ በትግራይ፣ በጎንደር፣ በጎጃም በተደረጉ ጦርነቶች ሁሉ ከግራኝ ጎን አልተለየቺም፡፡ ግራኝ ያካሄዳቸው ጦርነቶች እጅግ አስከፊና ከፍተኛ መስዋእትነትን የጠየቁ ነበሩ፡፡ ጀግናዋ ድል ወንበራ ግን ቆራጥ ስለነበረች “ምንም ቢሆን ካንተ ተነጥዬ አልቀርም፤ የሚለየን ሞት ብቻ ነው” በሚል መንፈስ የባሏንና የሰራዊቱን ሞራል እየገነባች ከግራኝ ጋር ቀጥላለች፡፡ ይህም መንፈሰ ጠንካራና ከፍተኛ ወኔ የነበራት መሆኑን ያመለክታል፡፡
ባቲያ ድል ወንበራ ከባሏ ጋር አብራ መሄዷ ብቻ ሳይሆን በወቅቱ ተቀናቃኝ ወገንን በረቀቀ ዘዴ በመመረዝ መግደል በእጅጉ የተለመደ ስለነበር በዚህ ረገድ ድል ወንበራ የምትወደው ባለቤቷ እንዳይሞትባት ምግቡን በማዘጋጀት ትረዳው እንደነበር ይነገራል፡፡ ባቲያ ድል ወንበራ በተፈጥሮ ተሸንፋ፣ ከጦር ግንባር ገለል ብላ የምናገኛት ስትወልድ ብቻ ነው፡፡ አረብ ፋቂህ “ኃይለኛዋ ድል ወንበራ ቀኗ የደረሰ ነፍሰጡር ሆና እንኳ እስክትወልድ ድረስ ሐረር ለመቆየት ትእግስት አጥታ ተዋጊውን ባሏንና ዘማቹን ጦር ለማበረታታት ስትል አብራ ተጓዘች፡፡ ዚፋህ በተባለ አገር ስትደርስ በመውለዷ ከግራኝ እህት ከሙኒሳእ ጋር እዚያ እንድትቆይ ተደረገች” በማለት ጽፏል፡፡ ባቲያ ድል ወንበራ ሌላው የምትደነቅበትና የሴቶች ሁሉ ቁንጮ መሆኗን ያስመሰከረቺበት ጀግንነቷ ደግሞ ባለቤቷን እስከ መጨረሻው “ግፋ ቀጥል በርታ” ስትል ቆይታ ግራኝ በጎንደር ደንቀዝ በተባለ ስፍራ በተደረገ ጦርነት ሲሞት አስከሬኑን አስነስታ ሩቅ ስፍራ በመውሰድ ለመቅበርና ሀብቱን ይዛ ወደ ሐረር ለመመለስ መብቃቷ ነው፡፡
ግራኝ በሞተበት ወቅት ልጇ ሙሐመድ አሕመድ በአፄ ገላውዲዎስ ሰራዊት ተማርኮባት ነበር፡፡ ከግራኝ የተረፈውን ጦር እየመራች ወደ ሐረር በመመለስ ላይ የነበረቺው ባቲያ እግረ መንገዷን ከአሸናፊው ኃይል ጋር በመደራደር ቀደም ሲል በግራኝ የተማረከውን የአፄ ልብነ ድንግል ልጅ የሆነውን ሚናስን በመመለስ ተማራኪ ልጇን በምርኮኛ ልውውጥ ለማስመለስ ችላለች፡፡ ይህም ሁኔታ ባቲያ ድል ወንበራ ከፍተኛ የዲፕሎማሲና የድርድር ብቃትና ችሎታ የነበራት መሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡ ከጀግንነቷና ከዲፕሎማሲ ችሎታዋ በተጨማሪ ተጠቃሽ የሆነው የባቲያ ድል ወንበራ ባህሪ ቀናተኛ አለመሆኗ ነው፡፡ ባቲያ ድል ወንበራ ባሏን ኢማም አሕመድን (ግራኝን) በጣም ትወደዋለች። ከሞት በስተቀር የሚለየን የለም ብላ አብራው ስትንከራተት ነበር፡፡ ለህይወቷ አስጊ በሆኑ ጦርነቶችም አብራው ሆና አሳልፋለች፡፡ በዚህ ሂደት ግራኝ አሕመድ ከሐዲያ፣ ከባሌ፣ ከአንጎትና ከጎንደር ሚስቶችን ሲያገባ ሲፈታ ድል ወንበራ ተቃውሞ ያቀረበቺበት ሁኔታ አልነበረም፡፡ እውነታውን ተቀብላ ባሏን መንከባከቧን አላቋረጠቺም ነበር።
ታሪክ እንደመዘገበው፤ ጦረኛውን መሪ ግራኝ አሕመድን ገድሎ ስልጣኑን የተረከበው አፄ ገላውዲዎስ ነበር፡፡ በዚህም ድል ወንበራ የምትወደውን ባሏን በማጣቷ ሀዘኗ መሪር ነበር። ይሁን እንጂ፣ ሀዘን ለባቲያ አዲስ አልነበረም፡፡ ገና በልጅነቷ አባቷን በአፄ ልብነ ድንግል ተነጥቃ ነበር፡፡ ባቲያ ሀዘኗን በውስጧ ይዛ የአባቷን ገዳይ ብትችል ራሷ ካልሆነም በሌላ ጀግና እንዲገደል በማድረግ መበቀልን ሰንቃ ተነሳች፡፡ የቅርብ ዘመዶቿ ይህንን እንደማያደርጉላት ስትገነዘብ በአንድ ቤት አብሯት ያደገውን፣ ገና በ17 ዓመቱ የጦር መሪ የሆነውን ኢማም አሕመድን አገባች፡፡ ባሏ የአባቷን ገዳይ ተበቀለላት፡፡
የምትወደው ባሏ ኢማም አሕመድ በአፄ ገላውዲዎስ ሲገደልባት ሌላ ሀዘን ገጠማት። ሀዘኗን በውስጧ ይዛ አሁንም የባሏን ገዳይ የሚገድል ጀግና እያሰበች ሳለ የግራኝን ቤተሰብ አሰባስቦ የማስተዳደር ኃላፊነትን የተረከበው የግራኝ የእህት ልጅ የሆነው አሚር ኑር ሙጃሂድ የጋብቻ ጥያቄ ሲያቀርብላት ያቀረበቺለት ቅድመ ሁኔታ “የባሌን አንገት የቆረጠውን የአፄ ገላውዲዎስን አንገት ቆርጠህ ካመጣህልኝ እኔን ማግባት ትችላለህ” የሚል ነበር፡፡ አሚሩም ከአፄ ገላውዲዎስ ጋር ጦርነት ገጥሞ በማሸነፍ የግራኝን ገዳይ የአፄ ገላውዲዎስን አንገት ቆርጦ በማምጣት ባቲያ ድል ወንበራን አገባት፡፡ ድል ወንበራ የአባቷንም የባሏንም ገዳዮች በዚህ መልኩ በመበቀል እውነትም እንደ ስሟ “ድል ዙፋኗ”  መሆኑን አስመስክራለች፡፡
የታላቁ እንግሊዛዊ የታሪክ ጸሐፊ የፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት ልጅ የሆነቺው ዶክተር ሪታ ፓንክረስት “የጣይቱ ቀዳሚ እናቶች” በሚለው መጽሐፏ፤ ድል ወንበራን ከቀደምት እቴጌዎች ዝርዝር ውስጥ አካታታለች፡፡ እውቁ የህዝብ ታሪክ ዘጋቢ (public historian) የሆኑት አቶ ተክለ ጻዲቅ መኩሪያ ደግሞ ባቲያ ድል ወንበራን እና ዓለም የሚያውቃትን ክሊዮፓትራን በማነጻጸር ጽፈዋል፡፡ ክሊዮፓትራና ድል ወንበራ ሁለቱም ሴቶች ቆንጆዎች ናቸው፡፡ ድል ወንበራ ሦስት ጀግኖች መስዋዕት ሲሆኑ አይታለች፡፡ የሁለት ጀግኖችም ሚስት ሆና ነበር፡፡ ክሊዮፓትራ ጁሊየስ ቄሳርን በፍቅሯ ማርካ ሀገሯን ከወረራ አተረፈች፡፡ እሱ ሲሞት የማርክ አንቶኒ እቁባት ሆና ንግስትነቷን ጠበቀች፡፡ በፍቅር የመማረክና የማንበርከክ ዘዴዋን በኦክቶቪያን ላይ መድገም ስላልፈለገች ራሷን አጠፋች፡፡ ባቲያ በፍቅሯ ማርካ ባሎቿ የምትፈልገውን እንዲፈጽሙ አስደረገች፡፡ ራሷን ግን አላጠፋችም - ልዩነቱ ይሄ ነው፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻው፡- This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ወይም This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡Read 1551 times