Sunday, 31 July 2022 00:00

የታጋዮች የትግል ወረት እና ሀቀኝነት

Written by  ከነቢይ መኮንን
Rate this item
(0 votes)

  በታሪክ የምናውቃቸው ሊዮ-ሻዎ-ቼ እና ማኦ ወዳጅ ሆነው ከርመው፣ እስከ መጋደል ደረሱ። ቼ እና ካስትሮ ግን እንደተከባበሩ እንደተዋደዱ  ተለያዩ።…
በታሪክ ሳይሆን በምናባችን ቼ እንዲህ ብሎ ያስል፡- በዚህ በኩል ቀድመው ለሕዝባቸው የታገሉና ታግለው፣ አሸንፈው በኋላ “ቀኝ-ኋላ ዙር!” ብለው እርስ በርስ የተፋጠጡ አሉ። በዚህ በኩል ደግሞ የመላው ዓለም ጭቁኖች ብዙ ናቸው። የኩባ ሕዝብ ትንሽ ነው። እናም ነፃ ወጥቷል፤ በሚቀጥለው ምዕራፍ እኔና ፊደል መጠራጠር መጠንቀቅ፣ መጠማመድ፣ መገዳደል ከሚኖርብን፣ ቀድሞ ውልቅ አልለውም? ነጻነት የጠማው ህዝብ መች ጠፋና? ሰው እንደሆነ ያው ሰው ነው። የትም ቢኖር ምንም ዓይነት መልክ ቢኖረው - ምንም ዓይነት እምነት ቢኖረው።… ስለዚህ ወደ ቦሊቪያ!
ምናብ ምን ይሳናታል? አሁን ደሞ ፊደል ካስትሮን እንሆናለን። በምናብ ፀጋ ያስባል። ፊደል። ያየዋል፤ ቼ የጤና ጥበቃ ሚኒስትርም ሆኖ ኩባን ሲመራ፣ የኢንዱስትሪ ሚኒስትርም ሆኖ ሲያገለግል፡-
ገና! ይኸ ሰውዬ እዚህ ከመምጣቱ በፊት፣ እኛን ነጻ ከማውጣቱ  በፊት በሶስት ሌላ አገር ውስጥ ተዋግቷል።
- ዒላማውን ባንድ እጁ እያስታመመ፣ ጠላት ላይ በሌላ እጁ እየተኮሰ- ተኩሱ ጋብ ሲል ቁስለኞችን እያከመ።
- ያን ሁሉ ጀብድና ከሞት መፋጠጥ ለምዶ፣ አሁን ኩባን ለማስተዳደር ይቸከዋል - ይሰለቸዋል። ምን በወጣው?
በል እንግዲህ ቼ፣ ቢሮክራሲውና ወረቀቱ በቃህ። ከንግዲህ እኛ እንቀጥላለን። ሂድና ደሞ ሌላ ኩባ ውስጥ ገብተህ ተዋጋ። ተዋጊ ነህ! አስምን በየደቂቃው ትዋጋለህ-ብቻህን! ምነው አንዲቷን እንኳ በአስም መታፈን እኔ ልታመምልህ በቻልኩ፡
ሂድ በቃ ተዋጋው ሰይጣንን! ይቅናህ የኔ ጎበዝ
 ይለውና ይሰነባበታሉ፣…
ይህ በኩባ ሆነ፡፡  ወደ ቻይና ስንመለስ ግን ማኦና ሊዮ-ሻዎ-ቺ ተቃቅረው እናገኛቸዋለን። ነገሮች እየተባባሱ ይሄዳሉ። አንድ ቀን ሊዮ-ሻዎ-ቺ ካገር ለመጥፋት በአውሮፕላን ሲበር፣ የሊቀ መንበር ማኦ ወገኖች ነቅተውበት ኖሮ፣ ተኩሰው አውሮፕላኑን አጋይተው ይገድሉታል። ዘመናት ካለፉ በኋላ ደግሞ እነ ዴንግ- ሲያዎ- ፔንግ የሊቀመንበር ማኦን ሚስና ሶስት ግብረ-አበሮቿን “አራቱ ወንበዴዎች” (ጋንግ ኦፍ ፎር) ብለው በይፋና በብዙ ልፈፋ አዋርደው ያቀርቧቸዋል።
መንግሥት በአንድ መልኩ የሕዝብ ጠባቂ ነው። ከውጪ ጠላት ይጠብቀዋል። በሌላ በኩል ግን መንግስት ምንም ያህል  ጥሩ መንግስት ቢሆን፣ አስገዳጅ ኃይል ነው። ለዚህም ፖሊሶቹ፣ ፍርድ ቤቶቹ፣ እስር ቤቶቹ ምስክር ናቸው። ስለዚህ አንዳንድ ሽፍቶች አሉ፤ ከሽፍትነቱ በኋላ መሪነቱ የማይጥማቸው። ከነዚህም እጅግ ዝነኛውና የመላው ዓለም ተራማጆች “የሚያመልኩት” ጀግናው ቼ ጉዌቬራ ነው፡፡ ቪቫ ቼ!
ቼ የአብዮታዊያን አርአያ ነው። “ሀ” ብለን ስንጀምር፣ የኩባን ሽፍቶች ወደ ድል ከመሩዋቸው ቀንደኛ ተዋጊዎች አንዱ የሆነው፣ ቼ ጉዌቬራ ኩባዊ አይደለም፣ የአርጀንቲና ሰው ነው።
“ለ” ብለን ስንቀጥል ቼ ጉዌቬራ በኩባ “ከመከሰቱ” በፊት በሶስት ሌሎች የላቲን  አሜሪካ አገሮች ከጭቆና ወታደሮች ጋር የተፋፋመ የሽምቅ ውጊያ ተዋግቷል። ኩባ አራተኛ አገሩ ናት። በመጨረሻም ኢምፔሪያሊዝምን እየተዋጋ በጀግንነት የወደቀው በአምስተኛ አገሩ በቦሊቪያ።
ቼ ጉዌቬራ የአብዮታውያን አብዮታዊ ነው ልንል እንችላለን። አብዛኛዎቹ አብዮታውያን በትውልድ አገራቸው ውስጥ የገዛ ሕዝባቸውን ከጭቆና ለማውጣት ነው የሚተጉት፡፡  ቼ ግን ሌላ ነው። የሰውን ልጆች ከጭቆና ለማላቀቅ ነው። “የትም ይሁን የትም፣ ጭቆናን እንዋጋለን! ማንም ይሁን ማንም ለጭቁን እንታገላለን!” በማለት፡፡

Read 2305 times