Saturday, 30 July 2022 14:13

የቡና ዓመት - ከ1.4 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ

Written by  ስንታየሁ ግርማ
Rate this item
(1 Vote)

    ኢትዮጵያ ለዓለም ካበረከተችው እንቁ ስጦታዎች መካከል ቡና ዋነኛውና የመጀመሪያው ነው፡፡ ቡና ዛሬ በዓለም ላይ በየቀኑ ከ3 ቢሊዮን በላይ ስኒ ይጠጣል፡፡ ከ50 በላይ ሀገሮች ይመረታል፡፡ ከ120 ሚሊዮን በላይ የዓለም ህዝብ ኑሮው በቡና ላይ የተመሠረተ ነው፡፡
ጥናቶች እንደሚያሣዩት፤ የቡና የጤና ጠቀሜታዎች ብዙ ናቸው፡፡  ለመጥቀስ ያህል “ኢትዮ ጤና”ን በምንጭነት ተጠቅሜያለሁ፡-
የስኳር በሽታን በ50% ይቀንሣል፣
የአልዛይመር በሽታ ስጋትን ይቀንሣል፣
በቆዳ እና በጡት ካንሰር የመያዝ እድሎችን ይቀንሣል፣
ብጉርን በመከላከል የቆዳ ጤንነትን ይጨምራል፣
የሰው ልጅ ፀጉር እድገትን ይጨምራል፣
የፋይበር አወሳሰዶችን ይጨምራል፣
ሲርሆሲስ የተባለ ጉበት በሽታን ይከላከላል፣
ድብርትን/የመደበት ስሜትን ይቀንሣል፣ የሰውነት መጉረብረብ ወይም መመረዝን /ኢንፍላሜሽንን/ ይቀንሣል፣
በፓርኪንሰንስ በሽታ የመያዝ እድላችንን ይቀንሳል፤
በማህበራዊ ፋይዳ በኩል ቡና በሀዘንም በደስታም ወቅት የሚቀርብ ነው፡፡ ለእኛ ቡና የኩራት ምንጫችን ነው፡፡ ከ3ዐ ሚሊዮን በላይ ዜጐች ህይወታቸው የተመሠረተው በቡና ላይ ነው፡፡
ከኢኮኖሚያዊ እና ከማህበራዊ ፋይዳው የበለጠ ቡና ለአለምም ባለ ዉለታ ነዉ፡፡ በዓለም ዲሞክራሲ እንዲበለጽግ  ያደረገው አስተዋጽኦ መነሣት ያለበት ነው፡፡  ጀርገን ሀቨርማስ የተባለው የጀርመን ሶሽዮሎጂስት እና የፖለቲካል ሣይንስ ምሁር፣ 18ኛው ክፍለ ዘመን የዲሞክራሲ ወርቃማው ዘመን ነበር ይላል፡፡ ለዚህ ደግሞ Public Sphere  በሚለው ፅንሰ ሀሣቡ በወቅቱ ሠዎች በቡና ካፌዎች በመሰባሰብ ስለ ህይወታቸው፣ ስለ የጋራ ጉዳያቸው ስለተለያዩ ሀሳቦች ያለምንም ገደብ ውይይት ያደርጋሉ፡፡ በምክንያት ይከራከራሉ።  መግባባት የተደረሰበት ስምምነትን በተግባር ያውሉታል፡፡ ሠዎች በቡና ካፌዎች ተሠብስበው ሲወያዩ የገንዘብ፣ የትምህርት፣ የመደብና የመሣሠሉት ልዩነቶች ግምት ውስጥ አይገቡም ነበር፤ ይላል ሀቨርማስ፡፡ እሱ እንደሚለው፤ መንግስታትም ተቀባይነት ለማግኘት ዜጐች በቡና ካፍቴሪያዎች ተሰባስበው የተወያዩበትንና ስምምነት የደረሱበትን ሀሳብ ተቀብለው ተግባራዊ ያደርጉት ነበር፡፡
በሂደት ግን የመገናኛ ብዙሃን እና የህዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች እና ተቋማት Public Sphere በግለሰቦች ሉዐላዊነት/private sphere) ተተካ ይላል፡፡ እንደ ሀቨርማስ አረዳድ፤ የህዝብ ወሳኝነት የበላይነት በነበረበት ዘመን ቡና እና የቡና ካፌዎች አስተዋፅኦ አድርገዋል ማለት ነው፡፡
ለመንደርደሪያ ያህል ይህንን ካልኩ ወደ ዋናው ጉዳይ ልግባ፡፡ የባለፈው  በጀት ዓመት በተለይም የቡና ዓመት ተብሎ ሊገለፅ የሚችል ነው፡፡  በኢትዮጵያ ታሪክ በመጠንም በገቢም ሪከርድ የሆነ ኤክስፖርት የተመዘገበበት ነው።  300000 ቶን ቡና ወደ ውጭ በመላክ ከ1.4 ቢሊዮን  ዶላር በላይ ገቢ ተገኝቷል፡፡  ከ2013 በጀት ዓመት ጋር ሲነፃፀር  22  በመቶ ብልጫ አለው፡፡  ለዚህ አስተዋፅኦ ካደረጉት መካከል  ኢትዮጵያ በቡና ዘርፍ ያካሄደችው የሪፎርም ስራ  ተጠቃሽ ነው፡፡
መንግስት በግሎባላይዜሽን /ሉላዊነት/ መተዳደር የህልውና ጉዳይ ነው የሚል አቋም አለው፡፡ ግሎባላይዜሽን የአማራጭ ጉዳይ ሣይሆን የስርዓት ጉዳይ ነው፡፡  ከመወዳደር ውጭ ሌላ አማራጭ የለም፡፡ በዓለም ገበያ ተወዳድሮ ማሸነፍ የሀገሪቱን ህልውና ማስቀጠል ነው ብሎ የሚያምነው መንግስት፤ በገበያው ንቁ ተሳታፊና ተጠቃሚ በመሆን ጥረቶችን ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ ባለፉት ጥቂት አመታት  ትኩረት ከተሰጣቸው የኤክስፖርት ምርቶች መካከል ቡና ይገኝበታል፡፡
ዘርፉን የሚያስተባብርና የሚመራ የቡናና ሻይ  ባለሥልጣን አቋቁሟል፡፡  በተጠናቀቀው በጀት ዓመትም የቡናውን ሪፎርም በአግባቡና በባለቤትነት በመምራት ሪከርድ የሆነ የኤክስፖርት እድገት ተመዝግቧል፡፡ በሪፎርሙ ውስጥ ከተከናወኑ ቁልፍ ተግባራት መካከል፡-
የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ያሉበትን ችግሮች በመለየት ተገቢው የአሠራርና የአደረጃጀት ስርዓት ተዘርግቷል፡፡
በተለያዩ የክልል ከተሞች ባለድርሻ አካላትን በማሣተፍ ማነቆዎችን በመለየት መፍትሄዎችን በጋራ አስቀምጠዋል፡፡  የባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ የባለቤትነት ስሜት በማዳበር በህገ-ወጥ የቡና ንግድ ዝውውርና ቁጥጥር ላይ የራሳቸውን አስተዋጽኦ ማድረግ ጀምረዋል፡፡
የቡና ግብይት ጥራትና ቁጥጥር አዋጅ ቁጥር 1051/2009 ባለድርሻ አካላትን ባሣተፈ መልኩ ውይይት ተደርጐበት በህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ፀድቆ ከሀምሌ 1, 2009 ዓ.ም. ጀምሮ ተግባራዊ እየሆነ ነው፡፡  አዋጁ የልማታዊ ባለሀብቶችን ተስፋ እና በራስ መተማመን በእጅጉ ያለመለመ ነው፡፡
የቡና ምርታማነትና ጥራት ማሻሻያ ፓኬጅ ተዘጋጅቶ ታትሟል፡፡  እስከ ወረዳ ድረስ ሥልጠናም ተሰጥቷል፡፡ ምንም እንኳን ቡናን ለአለም ገበያና ለአገር ውስጥ ፍጆታ ብናመርትም አሁንም የምርታማነታችን ደረጃ ዝቅተኛ እንደሆነ መረጃዎች ያሣያሉ፡፡  ለመጥቀስ ያህል ቡናን ከዛሬ 290 ዓመት በፊት ማብቀል የጀመረችው የዓለም የመጀመሪያዋ አምራች እና ሁለተኛዋ ቡና ጠጪ ሀገር ብራዚል ስትሆን በሄክታር የቡና ምርታማነት መጠኗ 1.4 ቶን ነው፡፡  የቬትናም 2.1 ቶን፣ የኮሎምቢያ 0.9 ሲሆን የቡና መገናኛ እና የልዩ ጣዕም ቡናዎች ባለቤት የሆነችው ኢትዮጵያ የቡና ምርታማነት በቶን 0.3 ብቻ ነው፡፡ ይህንን ዝቅተኛ የምርታማነት መጠን በማሻሻል አርሶ አደሩን ተጠቃሚ ለማድረግ እና የቡናን ህልውና ለማስቀጠል የቡና ምርታማነትና ጥራት ማሻሻያ ፓኬጅ ተዘጋጅቶ እስከ ወረዳ ድረስ ስልጠና ተሰጥቷል፡፡  በቀጣይ አርሶ አደሩን ማሰልጠን ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ተግባር ነው፡፡
በበጀት ዓመቱ የቡና ምርታማነትንና ጥራት ለማሻሻል ትኩረት ከተሰጣቸው ጉዳዮች መካከል በቡና ላይ ትኩረት ሰጥተው የሚሰሩ የምርምር ተቋማትን ማስፋፋት ነው፡፡ ብራዚልና ሌሎች ግንባር ቀደም ቡና አምራች ሃገራት በቡና ላይ ብቻ ምርምር የሚያደርጉ ብዛት ያላቸው ተቋማት ባለቤት ናቸው፡፡ ከሃገራቱ ተሞክሮ በመማር የኢትዮጵያን የቡና ምርምር ኢንስቲትዩት ለማቋቋም ደንብ በመዘጋጀት ላይ ነው፡፡ የቡና ጥራት መቆጣጠሪያ ረቂቅ ደንብም ተዘጋጅቷል፡፡
ሌላው ሪከርድ ለሆነ የቡና ኤክስፖርት መመዝገብ ምክንያት ደግሞ ቡናችን ከማስተዋወቅ አኳያ የተሠሩ ስራዎች የበኩላቸውን አስተዋፅኦ አድርገዋል፡፡ አገራችን 15ኛውን የአፍሪካ ልዩ ቡና አብቃዮች ማህበር ጉባኤ በማስተናገድ ቡናን አስተዋውቃለች። ሰፊ የውጭ መገናኛ ብዙሃን ሽፋን ያገኘም ጉባኤና ኤግዚቢሽን ነበር፡፡ በጃፓን፣ በአሜሪካን፣ በዱባይ፣ በሀንጋሪ፣ በሴኔጋል፣ በቻይና፣ በህንድ በኤግዚቢሽን፣ በባዛርና በኤክስፖ በመሣተፍ ቡናን የማስተዋወቅ፣ አዳዲስ ገዥዎችን የማፍራትና ውል የማዋዋል ሥራዎች ተሰርተዋል፡፡
ሲጠቃለል ዓመቱ ከኤክስፖርት ምርቶች ሁሉ የቡና ዓመት ተብሎ ሊታወስ የሚችል ነው። በበጀት  ዓመቱ የተሠሩ የሪፎርም ሥራዎች እና የተገኘውን ውጤት የበለጠ ማስቀጠል ከተቻለ ፋይናንሻል ታይምስ እንዳለው፣ ኢትዮጵያ ከቡና የምታገኘውን ገቢ በከፍተኛ ሁኔታ ማሣደግ ትችላለች፡፡  
ቡናን በመገኛ አገሩ አምርተን አለምን እናጠጣለን!
ከአዘጋጁ፡- ጸሃፊውን በኢሜይል አድራሻው፡- Sintayehu This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡

Read 1568 times