Saturday, 13 October 2012 13:08

.....የማለዳ ሕመም...Morning sickness … ነበር.....

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ
Rate this item
(1 Vote)

.ስሜ ሲስተር ብርሀኔ ይባላል፡፡ በአሁኑ ወቅት የሰባት ወር እርጉዝ ነኝ፡፡ አኔ እርግዝናዬን አቅጄና ፈልጌ ባለቤንም አሳምኜ ስላረገዝኩ በሁኔታው እጅግ ደስተኛ ነኝ፡፡ በተለያዩ ሴቶች እንደሚታየውም በአመጋገብም ሆነ በአለባበስ ወይንም በተለያዩ ምክንያቶች የደረሰብኝ የፍላጎት ወይንም የመጥላት ሰሜት የሚያስቸግር አልነበረም፡፡ በመጀመሪያዎቹ ሶስት ወራት በጣም በመጠኑ የማቅለሽለሽ ስሜት ብቻ ነበረኝ፡፡ በሐኪሜም እንደተነገረኝ ከሆነ በእርግዝና ወቅት የሚከሰቱ የተለያዩ ስሜቶች በአብዛኛው እንደሕመም የማይታዩ  ስለሆኑ እኔም አምኜበት ስለተቀበልኩት ያለችግር ከዚህ ደርሻለሁ፡፡..  ከእርግዝና ጋር በተያያዘ የሚከሰቱ የተለያዩ የስሜት ለወጦች ይስተዋላሉ፡፡ አንዳንድ ሴቶች ከሚያሸቱት እንዲሁም ከሚያዩት ነገር ጋር በተያያዘ የጥላቻ ስሜት ያድርባቸዋል፡፡

ቀጥሎ የምታነቡት እማኝነት ከዚህ ጋር የተያያዘ ነው፡፡  ..... እኔ በመጀመሪያ እርግዝናዬ ጊዜ ባለቤ ሽቶ  በስጦታ መልክ ሰጠኝ፡፡ ያ ሽቶ ከፈረንሳይ አገር የሚመጣ ደምበኛ ሽቶ ነበር፡፡ መልኩም ወደ አረንጉዋዴነት የሚወስደው ነው፡፡ እኔ ግን በጊዜው ሳሸተው በጣም ነበር ያቅለሸለሸኝ፡፡ እነሆ ከሰላሳ አመት በላይ አረንጉዋዴ ሽቶ አልወድም፡፡ ዛሬም ሳስበው ያመኛል፡፡ .. ወ/ሮ ዘለቃሽ ይመር /ከተክለሀይማኖት/እርግዝና ገና ሲጀምር ጀምሮ አንዳንዶች ለተወሰኑ ወራት ሌሎች ደግሞ እስከመውለጃ ጊዜያቸው ድረስ በተለያየ ምክንያት ያገኙትን ለመመገብ የሚቸገሩ እንዲሁም ሊያገኙ የማ ይችሉትን የሚሹ አሉ፡፡ እንደዚሁም ከማየት እና ከማሽተት ጋር በተያያዘ ጥላቻን ወይንም መውደድን የሚያስከትልባቸው ሴቶች የእርግዝናው ጊዜ እስኪያበቃ እንደሁኔታው የሚቸገሩ ብዙ ናቸው፡፡ ለመሆኑ እንደዚህ ያለው ክስተት ከምን ይመነጫል?  እንደሕመምስ ይቆጠራልን? በሚል ባለሙያ አነጋግረናል፡፡ ለዚህ እትም የተጋበዙት ባለሙያ ዶ/ር ባልካቸው ንጋቱ የጽንስና ማህጸን ሐኪም ናቸው፡፡ በአሁኑ ወቅትም በቅዱስ ጳውሎስ ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ በመስራት ላይ ይገኛሉ፡፡ ኢሶግ/ በእርግዝና ጊዜ የሚከሰቱ የሁኔታዎች አለመመቸት ምክንያታቸው ምንድነው?ዶ/ር በእርግዝና ጊዜ ብዙ የአካላዊና የስነልቡና ለውጦች ይከሰታሉ፡፡  አንዳንድ ጊዜ እነዚህ ለውጦች ከሚገመተው በላይ በመሆን ችግር የሚያስከትሉበት ሁነታ ይኖራል፡፡ በአብዛኛውም ተፈጥሮአዊ ለውጦች የሚኖሩ ሲሆን ይህም እንደሰዎቹ ሁኔታ የለያያል፡፡በእርግጥ ምንም እንኩዋን ችግሩን በተለያየ ሁኔታ መቀበል ቢኖርም በአብዛኛው ግን እርግዝናው ከተከሰተ ከጥቂት ሳምንታት ጀምሮ የማቅለሽለሽና የማስታወክ እንዲሁም የራስ ምታት እና የሆድ ድርቀት የመሳሰሉት ችግሮች ይከሰታሉ፡፡ ለዚህ ዋናው መነሻው በእርግዝና ጊዜ በልጁና በእንግዴ ልጅ አማንኝነት በሚፈጠሩ መሰረታዊ ለውጦች ማለትም ሆርሞን  ቅመሞች... የእናትየው የስነልቡና ሁኔታ ...ባህልና ልማድ የመሳሰሉት ሁሉ የሚፈጥሩት ችግር ነው፡፡ኢሶግ/ ይህ ሕመም በቀድሞው አጠራሩ Morning sickness ወይንም የጠዋት ሕመም በሚል ይታወቅ ነበር፡፡ ይህ አጠራሩ አሁንም አለ?ዶ/ር በእርግጥ ቀደም ባለው ጊዜ ይህ ችግር የጠዋት ሕመም መባሉ ብዙ ጊዜቶች ከእንቅልፋቸው እንደተነሱ የሚታይባቸውን የማቅለሽለሽና የማሰታወክ ሕመም ተከትሎ የተሰጠ ስያሜ ነበር፡፡ ነገር ግን ሁኔታው ጠዋት ብቻ ተከስቶ የሚያበቃ ሳይሆን በተለያዩ ሰአታት ልዩነት ...እንደተፈጠረው አጋጣሚ የሚታይ በመሆኑ በአሁኑ ሰአት  ይህ አጠራር  አይስተዋልም፡፡ ኢሶግ/ በእርግዝና ወቅት የሚከሰቱት ችግሮች ከምግብ ጋር በተያያዘ ብቻ ሳይሆን በማስተዋል፣ በማሽተት በመሳሰሉት ስሜቶችም ጭምር ነው፡፡ ይህ ከምን ጋር ይያያዛል?ዶ/ር በእርግዝና ጊዜ በተለያዩ መንገዶች የሚገለጹ ችግሮች አሉ፡፡ ብዙውን ጊዜ የሚከሰቱት ጥላቻዎችም ሆኑ መውደዶች ተመሳሳይነት ሲኖራቸው እነሱም ጣፋጭ ምግቦችን መጥላት... ሽቶ... ቤንዚን... ሰንደል የመሳሰሉትን እንዲሁም ባልተለመደ ሁኔታ የሰው ጠረንን ጨምሮ መጥላት ይኖራል፡፡ በማስጠላት ረገድ ዋናው ምክንያት ካረገዙት ሴቶች ማህበራዊና ባህላዊ እንዲሁም ልማድ በመነሳት የሚከሰቱ ናቸው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ አስቀድሞውኑ የነበሩ ሕመሞች ለምሳሌ ማይግሬን የተባለው የራስ ሕመም የሚያሰ ቃያቸው ሴቶች  እንዲሁም መንታ ያረገዙ ሴቶች እና ከባለቤቶቻቸው ጋር ስምምነት የሌላቸው እንዲሁም ሌሎች የማህበራዊ ችግሮች ያሉባቸው ሴቶች ይህ ችግር በከፍተኛ ሁኔታ ያታይባቸዋል፡፡ ኢሶግ/ እርግዝና ሲከሰት ሊመገቡት የማይችሉትን ነገር የመሻት ነገር በአንዳንዶች ላይ ይስተዋላል፡፡ ይህ ከምን የተነሳ ነው?ዶ/ር ይህንን ሁኔታ ስንመለከት አልፎ አልፎ የሚያጋጥመው ጨርሶውንም ሊመገቡት የማይችሉትን ወይንም የማይገባቸውን ነገር ጽዳቱ አስተማማኝ ያልሆነ ወይንም ለምግብነት በአገልግሎት ላይ ያልዋለ እንዲሁም ከአቅም አኩዋያ ሊገኝ የማይችል ሲሆን አንዳንድ ጊዜ ደግሞ በቀላሉ የማይገኙ የምግብ ፍላጎት ይከሰታል፡፡ በእርግጥ እርጉዝ ሴቶች ብዙውን ጊዜ ተጨማሪ ምግብ ሊያምራቸው የሚችለው በሰውነታቸው ውስጥ አይረን የተባለው ንጥረ ነገር እጥረት ሲያጋጥማቸው ነው፡፡ኢሶግ/ የእርግዝናው ጊዜ በዛ ያሉ ወራትን እስኪያስቆጥር ምግብ የማይወስዱና የሚታመሙ ሴቶች ያጋጥማሉ፡፡ በእንደዚህ ያለው ችግር ሳቢያ ለተረገዙት ልጆች የሚተርፍ የጤና መታወክ ሊያጋጥም ይችላልን? ዶ/ር በተወሰኑ ሴቶች ላይ ምልክቱ ይከብዳል ብቻ ሳይሆን ለረጅም ጊዜ ሊቆይ ይችላል፡፡ ብዙዎቹ ከሶስት ወርና ከአራት ወር ባለፈ የማይቸገሩ ሲሆን ወደ 5ኀ የሚሆኑት ግን እስከሚወልዱ ድረስ የምግብ አለመውሰዱና የመሳሰሉት ችግሮች ሊቀጥሉ ይችላሉ፡፡  ይህ ሁኔታ ለጽንሱም ይሁን ለእናትየው አደገኛ ስለሚሆን በህክምና የቅርብ ክትትል ማድረግን ይጠይቃል፡፡ ሁኔታው በዚህ መልክ ከቀጠለ በእርግዝና ወቅት የሚጠበቅ የክብደት መጨመርን ሊያስቀር ይችላል፡፡ ስለዚህ በተለያዩ የህክምና ዘዴዎች ምግብ የማስጠላቱ ስሜት እንዲወገድና ለእናቶቹም ይሁን ለጽንሱ ተገቢውን የሰውነት ማዳበርና የጤና ሁኔታ በማሻሻል ጤነኛ ልጅ እንዲወለድ ማድረግ ይቻላል፡፡ ኢሶግ/ በእርግዝና ወቅት ከሚከሰቱት የጥላቻ ስሜቶች የሰው ጠረን አንዱ ነው፡፡ ይህ ከትዳር አጋር ጋር ባለው ግንኙነት እንዴት ይገለጻል?ዶ/ር አንዳንድ ጊዜ ለሕክምና የሚመጡ እርጉዝ ሴቶች አስጠላኝ ከሚሉት መካከል የባለቤታቸው  ጠረን ወይንም ድምጽ የሚሉ ይገኛሉ፡፡ ይህ በእርግጥ በቅርብ እና በየእለቱ የሚገናኙ በመሆናቸው እንጂ አብሮ በመስራት ወይንም በመኖር ከሚያገኙዋ ቸው ከሌሎች ሰዎችም ጋር ሊፈጠር ይችላል፡፡ ችግሩ የባለቤ ጠረን ወይንም ድምጽ አስጠላኝ በሚል የሚገለጽ ከሆነ የተለያዩ ምክሮችን በመስጠት ሁኔታውን ለማለዘብ ይሞከራል፡፡ ባልና ሚስቱ በጋራ ችግሩን ለመፍታት ጥረት እንዲያደርጉ ይነገራቸዋል፡፡ ብዙ ጊዜም ምናልባትም የባልየው እርዳታ እንደሚያስፈልግ እና አንዳንድ የማይፈለጉ ባህርይዎች ካሉት እንዲያስወግድ ይመከራል፡፡ ባጠቃይላም  ሚስቱ ስታረግዝ ባልየው ከመቼውም በበለጠ አይዞሽ ማለት እንዲሁም ከቃላት ይልቅ ፍቅሩን በተግባር መግለጽ እና እንክብካቤ ማድረግ በሐኪም ከሚሰጥ የህክምና እርዳታ ጎን ለጎን ከፍተኛ እርዳት ይሰጣል፡፡ኢሶግ/ በእርግዝና ጊዜ የሚከሰትን የተለያየ የመጥላትና የመውደድ ስሜት እንደሕመም መቁጠር ይቻላልን?ዶ/ር በእርገጥ ችግሩ የሚከሰተው ልጁና እንግዴ ልጁ በሚፈጥሩአቸው ተፈጥሮአዊ በሆኑ ቅመሞችሆርሞን ሳቢያ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ነገር ግን የሚወደደው ምንድነው የሚጠላውስ ምንድነው የሚለውን ስንመለከተው ለተለያዩ የጤና መታወኮች ሊያጋልጡ የሚችሉ ይገኙበታል፡፡ ለምሳሌ...ሴትየዋ ሲጋራ፣ አልኮሆል ፣ጫት የመሳሰሉትን ነገሮች አማሩኝ በማለት ብትወስድ በጽንሱ ላይም ሆነ በእራስዋ ጤንነት ላይ ችግር ሊያስከትል ይችላል፡፡ እንደዚሁም ምግብ በመጥላት ምክንያት ምግብ የማትወስድ እና የተመገበችውንም የምታስወግድ ከሆነ ከሰውነትዋ ውሀ ሊያልቅና እሱዋም ልጁዋም ሊጎዱ ይችላሉ፡፡ ስለዚህ ምንም እንኩዋን መውደድ ማስጠላቱ የተከሰተው በሕመም ምክንያት ባይሆንም የተፈጠረው ስሜት ግን ለህመም መንስኤ ሊሆን ይችላል፡፡ ስለዚህ እንደሕመም መቁጠር የሚገባን በእርግዝናው ምክንያት የተከሰተውን ስሜት ሳይሆን በስሜቱ ምክንያት የሚፈጠረውን ችግር ነው፡፡ ኢሶግ/ ምንም አይነት የማስጠላትና የመውደድ ስሜት የማይሰማቸው እርጉዞች ይኖራሉን?ዶ/ር በተለይ እርግዝናው የመጀመሪያ ባልሆነበት ጊዜ ይህ የማማር እና የማስጠላት ስሜት ላይኖር ይችላል፡፡ የአእምሮ ዝግጅት ያላቸው ፣የማህበራዊ ኑሮአቸው የተመቻቸ ከሆነ  እና ልምዱ ካላቸው ብዙም ሳይቸገሩ የሚወልዱ እናቶች አሉ፡፡ ነገር ግን በማንኛውም የእርግዝና ወቅት የማይቀሩ አካላዊና ስነልቡናዊ ለውጦች አሉ፡፡ ለምሳሌ ሽንት ቶሎ ቶሎ መምጣት፣ የረሀብ ስሜት፣ የራስ ምታትና የድካም ስሜት ሁሉም እርጉዞች ላይ ይኖራል፡፡ በእርግጥ ትኩረት ተሰጥቶት ሐኪም ቤት የሚያስኬድ ላይሆን ይችላል፡፡

Read 9539 times Last modified on Saturday, 13 October 2012 13:38