Saturday, 30 July 2022 14:38

ቀበጡ ሳቅዋ!

Written by  ኢዮብ ካሣ
Rate this item
(5 votes)

 አሁን የምነግራችሁን የፍቅር ገድል በየትኛውም የፈጠራ ሥራ ላይ እንደማታገኙት እወራረዳለሁ፡፡ በሌላ ምክንያት ግን አይደለም። በእውነት የተከሰተ እውነተኛ ታሪክ እንጂ ልብወለድ ባለመሆኑ ብቻ ነው፡፡ የዚህ ታሪክ ብቸኛ ባለቤት እኔ ብቻ ነኝ፡፡ ስለዚህም የትኛውም የደራሲ ምናብ የማይፈጥረው የፍቅር ገድል መሆኑን መቶ በመቶ ላረጋግጥላችሁ እችላለሁ፡፡ ምን ያደርጋል… መጨረሻ ላይ የፍቅር ገደል ሆነ፡፡ እንደ ቀሽም ደራሲ መጨረሻውን ስለነገርኳችሁ የማንበብ ስሜታችን ይረግባል ብላችሁ እንዳትሰጉ፡፡ የፍቅሬ ገድል (ገደል) ከመጨረሻውም ተጀመረ ከመሃል ብዙም ለውጥ የለውም፡፡ ምክንያቱም የፍቅር ገድሌ ከላይ እስከ ታች በጉድ የታጨቀ ነው፡፡
የሚገርመኝ ደግሞ ከዚያ ጉድ ለማምለጥ አንዳችም ጥረት አድርጌ አለማወቄ ነው፡፡ አምስት አመት ሙሉ ከነጉዴ ነው የኖርኩት፡፡ አንዳንዴ ራሴን ሳጃጅል … ድግምት አድርጋብኝ ይሆን እያልኩ፣ እሷን ሳይሆን ህሊናዬን እጠይቀዋለሁ። እሷን ብጠይቃትማ ያንን ልቤን የሚሰልበውን ረዥም “የኤሌክትሪክ ሳቋን” ትለቀው ነበር። አንዳንዴ አልጋ ላይ ተጋድመን ለፍቅር ሥራ ዳር ዳር ስንል፣ ድንገት ረዥሙን ሳቅዋን ጆሮዬ ላይ ትለቀዋለች፡፡ ከዚያም በጆሮዬ በኩል ሰተት ብሎ ገብቶ እንደ ገደል ማሚቶ መልሶ በጆሮዬ ያስተጋባል፡፡ ምናልባት ድግምትዋ ይሄ ረዥሙ ሳቅዋ ይሆን እንዴ? እላለሁ - አንዳንዴ፡፡ መልሴ ግን ሁሌም እኔጃ ነው፡፡
የሷ ሳቅ እንደ ሌላው ድምፅ ብቻ አይደለም። ይነዝራል - እንደ ኤሌክትሪክ፡፡ ሳቅዋ እኮ ይቆጣል፡፡ ሳቅዋ እኮ ይናደዳል፡፡ ሳቅዋ እኮ ይከፋል፡፡ ሳቅዋ እኮ ይደሰታል፡፡ ሳቅዋ እኮ ይስቃል፡፡ የእሷ ሳቅ ለብቻው ነው፡፡ ከሳቅ ዘሮች ሁሉ ይለያል፡፡ እሱ ይሆን… አምስት አመት ሙሉ ፍዝዝ ድንግዝ ያደረገኝ፡፡ ሳቅዋ ይሆን “ስትጠራኝ አቤት ስታዘኝ ወዴት” ሲያስብለኝ የነበረው፡፡ እሱ ይሆን ማንም ወጠምሻ ጐረምሳ ሊሸከመው የማይችለውን ትልቅ የበደል ሸክም እንድሸከም ያደረገኝ - ያ ቀበጡ ሳቅዋ!!
ስምን መልአክ ያወጣዋል እንዲሉ ፍቅረኛዬ ስሟ ፍልቅልቅ ይባላል፡፡ እድሜዋን አላውቀውም፡፡ እሷም የምታውቀው አይመስለኝም፡፡ ስገምት ግን 40ን አልፋለች። ውበትዋ “ሲሰራት ውሎ ሲሰራት ያደረ” የሚባልለት ነው - እንከን የለሽ ቆንጆ ናት። ጡቶችዋን እድሜ አልተፈታተናቸውም፤ እንደተቀሰሩ ናቸው፡፡ ዳሌዋ ማግኔት ነው - የሰው ዓይንና ሥጋ ይጐትታል፡፡ ዓይኖቿን ግን አልወዳቸውም፡፡ ከውሸት ተድቦልቡለው የተሰሩ ይመስላሉ - ሰውን ለማታለል፡፡
እኔና ፍልቅልፍ ፍቅረኛሞች የነበርነው ከአምስቱ ዓመት ውስጥ ለአንድ ዓመት ከስድስት ወር ብቻ ነው፡፡ ከዚያ በኋላ ባለው ጊዜ ውስጥ ግን እኔ ለእሷ ምን እንደሆንኩ፣ እኔም አላውቅ እሷም አልነገረችኝ፡፡ ቀበጡ ሳቅዋ ሲጠራኝ እሄዳለሁ፡፡ ፊት ሲነሳኝ አርፌ ቤቴ እቀመጣለሁ፡፡
“እኔ ለእሷ ምኗ ነኝ” ብዬ ከአንዴም ሁለት… ሦስት… አራት… ጊዜ ራሴን ጠይቄአለሁ፡፡ የረባ መልስ አላገኘሁም እንጂ፡፡ አንዳንዴ ግን “ድልድይዋ ነኝ” ብዬ አስባለሁ፡፡ ከድሮው ፍቅረኛ ወደ አዲሱ የምትሻገርበት የሰው ድልድይ! እኔ ላይ እረፍት አድርጋ ነው፣ በወርም በሁለት ወርም ከአዲስ ፍቅረኛ ጋር ግንኙነት የምትጀምረው፡፡ አዲሱ እስኪመጣ ፈፅሞ ከአጠገቡዋ እንድርቅ አትሻም፡፡ ከአልጋ እንድወርድባት አትፈልግም፡፡ እንደ አራስ መጋረጃ መከለል ብቻ ነው የሚቀራት፡፡ ነፋስ ልቀበል ብያት ልወጣ ስል ትጠራኝና “ይኸው ሳሚ፤ ከአንዲት ሴት ጋር ባይህ ዋ! በትራስ አፍኜ ነው ጭጭ የማደርግህ” ትለኝና ረዥሙን ሳቅዋን ትለቀዋለች - የቅናትና የቁጣ ቅልቅል ረዥም ሳቅ! ይሄኛውን ሳቅዋን ግን ሁሌም እፈራዋለሁ - ልቤን ያርደዋል፡፡
ፍልቅልቅ እኮ ጉደኛ ሴት ናት፡፡ ለጥቂት ወራት ከአዲሱ ፍቅረኛዋ ጋ አሸሼ ገዳሜዋን ታጧጡፍና ሲበቃት ወደ እናት ክፍሉዋ ትመለሳለች - ወደ እኔ ማለት ነው፡፡ በሞባይል ትጠራኛለች - ናፍቀኸኛል ብላ፡፡ እውነትዋን ይሁን ውሸትዋን የማውቀው ነገር የለም፡፡ ስንት ጊዜ እሷ ጋ ተመልሼ ላለመሄድ፣ ስንት ጊዜ ዓይኗን ላለማየት ምዬ ተገዝቼ እንደነበር፣ እኔና የሰማዩ ጌታ ብቻ ነን የምናውቀው፡፡ ግን በሞባይል ደውላ ስትጠራኝ እምቢ ብዬአት አላውቅም፡፡ እንዴት ብዬ?
ቀበጧ ፍልቅልቅ ጉዷ ማለቂያ የለውም። ለወራት ወደረሳነው የፍቅር ህይወታችን እስክንመለስ “የኮንትራት ፍቅሯን” ገድል ትተርክልኛለች፡፡ ለምን እንደሆነ አላውቅም… የፍቅር ተረኩን አልጠላውም፡፡ ቅናት ቢያንገበግበኝም መስማት እፈልጋለሁ፡፡ በፍቅር ጓደኞቿ በኩል የማላውቃትን ፍልቅልቅ የማውቃት እየመሰለኝ ይሆን?
ከ3 ወር መለያየት በኋላ በሞባይሏ የጠራችኝ ዕለት ቤቷ ውስጥ አዲስ ሰው አየሁ፡፡ የቤት ሠራተኛዬ ነች አለችኝ - አመንኳት፡፡
ማርታ ትባላለች - የፍልቅልቅ የቤት ሠራተኛ። 20 ዓመት እንኳን የሞላት አትመስልም፡፡ መልኳ ቸኮሌት፣ መካከለኛ ቁመት ያላት፣ ዓይኗ የሚያምር… የቤት ሠራተኛ ናት፡፡ የግል ኮሌጅ ትማራለች - ማታ ማታ፡፡ አንድ ቀን በሞባይሌ ደወለችልኝ - ማርታ፡፡
ጥቂት ካወራን በኋላ ስልኬን ዘጋሁ፡፡
ከግማሽ ሰዓት በኋላ ራሴን ፍልቅልቅ ቤት ውስጥ አገኘሁት፡፡ ማርታን ለግማሽ ሰዓት አካውንቲንግ የሚባል ትምህርት አስጠናኋት፡፡
ከዚያ በኋላ ግን አስጠኚው እኔ ልሁን እሷ ለማወቅ ቸገረኝ፡፡ ፍልቅልቅ አዲስ የኮንትራት ፍቅረኛ አግኝታ ሰውየው ቤት ጠቅልላ ገብታለች፡፡ እኔና ማርታ ደግሞ የእሷ አልጋ ላይ ነን፡፡ እስከዛሬም ድረስ ግን በምን ተዓምር እዚህ ደረጃ ላይ ልንደርስ እንደበቃን አላውቅም። እሷም የምታውቅ አይመስለኝም፡፡ አልጋ ላይ የሚያስወጣ ቅርበት አልነበረንም ግን ወጣን፡፡
ያለምንም ይሉኝታ አልጋው ላይ ተዝናናን። ያለምንም ይሉኝታ ተሳሳምን፡፡ ያለምንም ይሉኝታ ተሻሸን፡፡ ያለምንም ይሉኝታ ተዋደድን፡፡ ያለምንም ይሉኝታ ተፋቀርን - እርቃናችንን ሆነን፡፡ ይሄ ሁሉ ዱብዕዳ ፍቅር በፍልቅልቅ ቤት ነው፡፡ ይሄ ሁሉ ተዓምረኛ ፍቅር በፍልቅልቅ አልጋ ላይ ነው፡፡ እዚህች ቤት ውስጥ የእኛ የምንለው ንብረት የሌለን ምስኪን ፍቅረኞች ነን - እኔና ማርታ፡፡
“ደስ አለህ” አለችኝ በጀርባዋ ተንጋላ - ጥርሷን ብልጭ እያደረገች፡፡
“በጣም! አንቺስ?” አልኳት
“እኔም” አለች ደስታዋ ፊቷ ላይ እየተንቦገቦገ።
“ፍልቅልቅ ብትመጣብንስ?” ስጋት በሌለበት ቃና ጠየቀችኝ፡፡
“በስመዓብ በይ!” አልኩ ድንግጥ ብዬ፡፡
“ትፈራታለህ? እኔ ግን ምንም አትመስለኝ” ንግግሯ በራስ መተማመን የታጀበ ነበር፡፡ እኔ ደግሞ የፍልቅልቅን ማስፈራሪያ በሃሳቤ እያጠነጥነኩ ነበር - “ሳሚ - ከሴት ጋር ባይህ ዋ! በትራስ አፍኜ ጭጭ ነው የማደርግህ!” ያለችኝን፡፡
“መፍራት ሳይሆን…” የጀመርኩትን ሳልጨርስ በር ተንኳኳ፡፡ ዕጢዬ ዱብ አለ። ከአልጋው ውስጥ ለመውጣት ስንደፋደፍ “ተረጋጋ! የጐረቤት ልጅ ናት” ብላኝ ከመቅጽበት ዱብ አለች - ከአልጋው ላይ፡፡ ተረጋጋሁ፡፡ በሩ ተከፈተ፡፡ የጐረቤት ልጅ ግን አልነበረችም፡፡
የፍልቅልቅን ረዥም ሳቅ ሰማሁት፡፡ ሳቅዋን አስቀድማ እሷ ተከተለች - የተኛሁበት ድረስ፡፡
“አንተ ሳሚ…ምን እየሰራህ ነው? --- ምን እየሰራችሁ ነው?”
መልስ የለም፡፡ ማርታን በዓይኔ ፈለግኋት። የለችም፡፡ ፍልቅልቅ ቁጭ ብላ መንሰቅሰቅ ጀመረች፡፡
“አውሬ ነህ! የገዛ እህቴን በገዛ አልጋዬ ላይ?”
አሁን የበለጠ ደነገጥኩኝ፡፡
“ማርታ እህትሽ ናት እንዴ? እኔኮ ሠራተኛሽ መስላኝ ነው”
“ሠራተኛዬ ብትሆንስ?” ያ የማልወደውን ዓይኗን አጉረጠረጠችብኝ፡፡
ከ30 ደቂቃ በኋላ ራሴን ቤቴ አገኘሁት። አልጋዬ ላይ ተጋድሜ ለምን ማርቲን የቤት ሠራተኛዬ ናት ብላ እንዳስተዋወቀቺኝ እያሰብኩ ነበር፡፡ መልስ ግን አላገኘሁም፡፡ የሞባይሌ ጩኸት ከሰጠምኩበት ሃሳብ ጐትቶ አወጣኝ፡፡
ቁጥሩን አየሁት - ፍልቅልቅ ናት፡፡ መልስ ያላገኘሁለትን ጥያቄ እንደማቀርብላት እያሰብኩ “ሄሎ” አልኳት፡፡ ረዥም ሳቋ ተቀበለኝ፡፡ ያ የሚቆጣው ቀበጡ ሳቋ!!
ከአዘጋጁ፡- ከላይ የቀረበው አጭር ልብወለድ ቀድሞ ከወጡት ተመርጦ በድጋሚ ለንባብ የበቃ ነው፡፡Read 984 times