Saturday, 06 August 2022 11:03

በኢትዮጵያ ከሚገኙ ወረዳዎች 51 በመቶ ያህሉ ሰብአዊ ቀውስ እያስተናገዱ ነው

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

   2.9 ሚሊዮን ህጻናት ዓመቱን ከትምህርት ውጭ አሳልፈዋል
                     
           በኢትዮጵያ ካሉ አጠቃላይ 1ሺህ 85 ወረዳዎች ውስጥ 51 በመቶው ማለትም 557 ወረዳዎች በተለያየ ደረጃ በሚገለጽ ሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ ቀውስ ውስጥ እንደሚገኙ ያመለከተው የዩኒሴፍ ሪፖርት፤ 2.9 ሚሊዮን ህጻናት በተጠናቀቀው ዓመት ከትምህርት  ገበታ ውጪ ለማሳለፍ ተገድደዋል ብሏል።
ከጥር ወር 2014 እስካለንበት የሀምሌ ወር የኢትዮጵያን የሰብአዊ ቀውስ ሁኔታ የገመገመበትን ሪፖርት ከትናንት በስቲያ ይፋ ያደረገው ዩኒሴፍ እንዳመለከተው፤ በኦሮሚያ፣ ሶማሌና ደቡብ ክልል  በዋናነት በተከሰተው ድርቅም ከ2.1 ሚሊዮን በላይ የቤት እንስሳትም የሞቱ ሲሆን፤ ከ9 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ለእርዳታ ጠባቂነት ተጋልጠዋል ተብሏል።
በኢትዮጵያ ካሉት አጠቃላይ 1 ሺህ 85 ወረዳዎች መካከል በ557 ወረዳዎች ውስጥ የሚገኙ ዜጎች የመጀመሪያ፣ ሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃ እርዳታ የሚሹ መሆናቸውም በሪፖርቱ ተጠቁሟል። ከእነዚህ ወረዳዎች ውስጥ 317 ያህሉ ቅድሚያ (አስቸኳይ) እርዳታ የሚሹ ተብለው የተለዩ ሲሆን፤ 147 በሁለተኛ ደረጃ እንዲሁም 93 ወረዳዎች በሶስተኛ ደረጃ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ተብለው በሪፖርቱ ተለይተዋል።
በግጭትና በተፈጥሮ አደጋዎች ምክንያት በርካታ ተፈናቃይ ከሚገኙባቸው ክልሎችም አማራ በቀዳሚነት ሲጠቀስ፣ ትግራይ፣ ሶማሌ፣ ኦሮሚያ፣ ደቡብ፣ አፋርና ሲዳማ ይከተላሉ።
በአጠቃላይ በግጭትና በተፈጥሮ አደጋ ከቀያቸው ተፈናቅለው በተለያዩ መጠለያ ስፍራዎች ከሚገኙ 4.51 ሚሊዮን ዜጎች መካከል ግማሽ ያህሉ ማለትም 2.4 ሚሊዮን በአፋር፣ አማራና ትግራይ ይገኛሉ ብሏል- ሪፖርቱ።
በሃገሪቱ ለአቅመ ትምህርት ከደረሱ ልጆች መካከል 17 በመቶ ያህሉ ማለትም 2.9 ሚሊዮን ህጻናት በግጭትና በተፈጥሮ አደጋዎች ምክንያት ከትምህርት ገበታ ውጪ ሆነው አመቱን ማሳለፋቸውን ያመለከተው የዩኒሴፍ ሪፖርት፤ ከእነዚህ  ህጻናት 2.53 ሚሊዮን ያህሉ በግጭት ምክንያት፣ 401 ሺህ ያህሉ ደግሞ በድርቅ ምክንያት ትምህርት ለመማር እንዳልቻሉ ጠቁሟል።
በግጭት ምክንያት 8 ሺህ 660 ያህል ት/ቤቶች ወድመው እንደሚገኙ ያወሳው ሪፖርቱ፤ ከነዚህም 70 በመቶ ያህሉ በአፋር፣ አማራና ትግራይ የሚገኙ መሆናቸውንም አመልክቷል።

Read 11692 times