Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 13 October 2012 13:58

የወግ ማዕድ - ሁለተኛ

Written by 
Rate this item
(3 votes)

የዐጼ ኃይለስላሴ ዘመነ መንግስት ብዙ ኢትዮጵያውያን ከውጭው አለም ጋር ሰፋ ያለ ግንኙነት የጀመሩበት ነው፡፡ በንግድ፣ በፖለቲካ፣ በትምህርት ወዘተ. በርከት ያሉ ኢትዮጵያውያን ወደአውሮፓ ይሄዱ ነበርና በኢትዮጵያና በሚሄዱባቸው የአውሮፓ ሀገሮች መካከል ከፍ ያለ የባህል ልዩነት መኖሩን ያስተዋሉት ንጉሱ በጉዳዩ ላይ መከሩ፡፡ በኋላም በ1917 ዓ.ም “ስለ አውሮፓ መንገድ የምክር ቃል፡፡” የሚል ሰነድ አዘጋጅተው ይፋ አደረጉ፡፡ ይህ ጽሁፍ በእጄ እንደገባ ደጋግሜ አነበብኩት፡፡ አሁን ባለንበት ዘመን ያለውን ቋንቋ አጠቃቀም፣ ባህል፣ “ስልጣኔ”፣ የአነጋገር ለዛ ወዘተ. ከዚህ ጽሁፍ ጋር ሳነጻፅር ብዙ የሚያስታውሰውና የሚያስተምረው ነገር ይኖራል፡፡ ባይኖርም እንኳ የዚያን ዘመን መንፈስ ስለሚያሳይ በአጻጻፍ ውበቱ መደመም ይቻላል፡፡
የምክር ቃሉ የተጻፈው ከላይ እንደተገለጠው ከኢትዮጵያ ወደአውሮፓ ለሚጓዙ መንገደኞች ነው፡ ስለዚህ ጽሁፉን በአሁኑ ዘመን ሚዛን ብንመዝነው “የኢምግሬሽን አዋጅ” ሊባል ይችላል፡፡

የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሰኔ 26፣ 1995 ዓ. ም “የኢምግሬሽን አዋጅ” በሚል በነጋሪት ጋዜጣ አዋጅ ቁጥር 354/1995 ዓ.ም አውጥቷል፡፡ የምክር ቃሉ አንዳንድ ነጥቦች ከዚህ አዋጅ ጋር ይመሳሰላል፡፡ በርግጥ በጊዜው ርዝመት ለውጦችን ማስተዋል ይቻላል፡፡ ለምሳሌ የመርከቡን ሞተር በተመለከተ መደረግ ስለሚገባው ጥንቃቄ የሚከተለው ተጽፏል፡፡
የምክር ቃሉ በአንድ አቢይ እና በአምስት ንኡስ ርዕሶች (በአሁኑ ጊዜ አንቀጽና ንኡስ አንቀጽ የምንላቸው አይነት) ተከፋፍሎ የቀረበ ነው፡፡ ርዕሱ “ስለ አውሮፓ መንገድ የምክር ቃል” ሲሆን ሌሎቹ ንኡሳን ርዕሶች ደግሞ ስለ ይለፍ ወረቀት ፓስፖርት፣ ስለመርከብ መገኘት፣በምድር ባቡር ስለመሳፈር፣ ወደ መርከብ ስለመግባት፣ በመርከብም፤ በባቡርም፤ በሆቴልም በማናቸውም ስፍራ ቢሆን ለማድረግ የማይገባ የሚሉ ናቸው፡፡ ከኢምግሬሽን አዋጁ ጋር አነጻጽረን ስንመለከተው በአንዳንድ ነጥቦች ይመሳሰላል፡፡ ለምሳሌ “ስለ ይለፍ ወረቀት ፓስፖርት” በሚለው ንዑስ ርዕስ ውስጥ የሚከተለው የምክር ቃል ሰፍሯል፡፡ “፩ኛ ወደወጭ አገር ለመሄድ የሚፈልግ የኢትዮጵያ ሰው ሁሉ ለመንገዱ መነሳት ፲፭ ቀን ሲቀረው የይለፍ ወረቀቱን ነገር መጨረስ ያስፈልገዋል፡፡ …” ካለ በኋላ ይህንንም ከኢትዮጵያ መንግስት ማግኘት እንደሚችል ይገልጻል፡፡ አያይዞም “፪ የይለፍ ወረቀቱን ከኢትዮጵያ መንግስት ከተቀበለ በኋላ የሚሄድበትን አገር አስታውቆ ወደ ሌጋሲዮን ሄዶ የቆንስሉን ፊርማ በይለፍ ወረቀቱ ላይ ማስፈረም አለበት፡፡ …” በማለት ንዑስ ርእሱን ያጠቃልላል፡፡ ነገሩ ፓስፖርት ካወጣ በኋላ የሚሄድበትን አገር ለይቶ ቪዛ መቀበል አለበት ለማለት ነው፡፡ በ1995 ዓ.ም አዋጅ በክፍል ሶስት ላይ “ከኢትዮጵያ ስለመውጣት” ይልና ከቁጥር 1 - 3 ድረስ መሟላት ስለሚገባቸው ሁኔታዎች “ከኢትዮጵያ የሚወጣ ማንኛውም ሰው ፩. የጸና የጉዞ ሰነድ ፪. የማያስፈልግ ካልሆነ በቀር ወደሚሄድበት ሃገር ለመግባት የሚያስችል ቪዛ ፤ እና ፫. እንዳስፈላጊነቱ የጤና የምስክር ወረቀት መያዝ ይኖርበታል” በማለት ያሉትን ቅድመ ሁኔታዎች ያስቀምጣል፡፡ የጸና የጉዞ ሰነድ (a valid travel document) የሚለው ውስጥ በርካታ ነገሮች እንደሚካተቱ ማስተዋል ይገባል፡፡ በምክር ቃሉ ላይ ሌላው ቀርቶ በባቡር በሚጓዙበት ጊዜ አደጋ እንዳይደርስባቸው ወይም በዘመኑ አዲስ ቴክኖሎጂ ከነበረው የባቡር ትራንስፖርት ጋር
ለማስተዋወቅ
የሚል ጽሁፍ ይገኛል፡፡
ለዚህ ጽሁፍ የትኩረት ነጥብ የሆነው ግን የመጨረሻው ንኡስ ርዕስ ስለሆነ ወደዚያው እንሂድ፡፡

“በመርከብም፤ በባቡርም፤ በሆቴልም በማናቸውም ስፍራ ቢሆን ለማድረግ የማይገባ”

ከዚህ በታች አልፌ አልፌ እየጠቀስኩ የማነሳቸው ሀሳቦች ባህልን፣ ሞራልን፣ ማህበራዊ ግንኙነትንና የመሳሰሉትን (የራስንም ሆነ የሌላውን) ለመጠበቅና ለማሳመር የሚያገለግሉ ፍጹም ግልጽ ምክሮች ናቸው፡፡ ከመጀመሪያዎቹ ልነሳ :-
“፴፰ኛ በማናቸውም ስፍራ ቢሆን ልብስን አፍንጫ ላይ ማድረግ ራስን መከናነብ አይገባም፡፡”
“፵ኛ በትልልቅ ሰዎች ፊት ይልቁንም በወይዛዝርት ፊት ጥርስን መፋቅ ከጥፍር ውስጥ እድፍ ማውጣት አይገባም፡፡”
አለባበሳችን፣ የንግግር፣ የግንኙነት ሁኔታችንና የአክብሮት መጠናችን በነዚህ ሁለት አረፍተ ነገሮች ጎልቶ ወጥቷል፡፡ ጋቢ ወይም ነጠላ በመልበስ (በባህል ልብሳችን) ወደ አውሮፓ እንደምንሄድ ጥርሳችንንም ሆነ ጥፍራችንን በተገቢው ሰአት ማጽዳት እንዳለብን ይመክራሉ፡፡
ወንበር ላይ ወይም መደገፊያ ላይ ዘንበል ብሎና እግርን አነባብሮ መቀመጥ በተለያዩ ሃገሮች እንደንቀት እንደሚቆጠር አሳስበዋል፡፡ ከዚህ ቀጥሎ ደግሞ ለሴቶች እኩልነት ሳይሆን ቅድሚያ የተሰጠባቸውን ምክሮች እንመልከት፡፡ ሀ. “… ይልቁንም ወይዛዝሮች ለመጠየቅ በመጡ ጊዜ ከወንበር ተነስቶ ቆሞ አክብሮ መቀበል ይገባል፡፡ ለ. “… ከወይዛዝር ጋራ ሲነጋገሩ እግርን አጣምሮ መቀመጥ …አይገባም ሐ. “… ወንበር ለሁሉ የማይበቃ የሆነ እንደሆነ ለወይዛዝር ለቆ መቆም ይገባል” ወዘተ. የሚሉት የምክር ቃሎች ለሴቶች የሚሰጠውን የእኩልነት መብት ብቻ ሳይሆን ክብርና ብልጫም ያመላክታል፡፡
የአመጋገብ ስርአትን፣ ንግግርን፣ አሳሳቅን ወዘተ. ሳይቀር አስመልክቶ የተሰጡ ምክሮች ለመኖራቸው የሚከተሉት ጽሁፎች ያሳያሉ፡፡
አመጋገብን የተመለከቱ፡-
በጉብኝት ጊዜ ትኩረትን ሰብስቦ ስለመመልከት፡-
በውይይት ወይም ከሰው ጋር በማውራት ጊዜ፡-
ይህ የምክር ቃል ከንጉሱ እና በዙሪያቸው ካሉት መኳንንት ልምድ የተገኘም ይመስላል፡፡ ለዚህ ጥሩ ማጣቀሻ የሚሆነው ንጉሱ ራስ ተፈሪ በሚባሉበት ዘመን (አልጋ ወራሽ ሆነው) በአውሮፓና በመካከለኛው ምስራቅ ጉብኝት ማድረጋቸውን ስናስታውስ ነው፡፡
አልጋ ወራሽ ተፈሪ መኮንን እ.ኤ.አ በ1924 /በእኛ 1916 መሆኑ ነው/ ከላይ በተጠቀሱት አህጉሮች ውስጥ ኢየሩሳሌምን፣ ካይሮንና አሌክሳንደሪያን፣ አምስተርዳምን፣ ስቶክልምን፣ ለንደንን፣ ፓሪስን፣ ጀኔቫንና አቴንስን ጎብኝተው ነበር፡፡ በጉብኝታቸውም ራስ ስዩም መንገሻን፣ ራስ ኃይሉ ተ/ሃይማኖትን፣ ራስ ሙሉጌታ ይገዙን፣ መኮንን እንዳልካቸውንና ብላታን ጌታ ኅሩይ ወ/ስላሴን አስከትለው ነበር፡፡ ይህ የምክር ቃል ደግሞ የተጻፈው በ1917 ዓ.ም ከሆነ የነሱ ልምድ ታክሎበታል ያስብላል፡፡ ይህ ማለት ደግሞ ነገሩ ገፍቶ የመጣበትን ዘመን ለማመልከት እንጂ ከዚያ በፊትም ብዙ ኢትጵያውያን የተለያዩ ጉዞዎችንና ጉብኝቶችን አላደረጉም ማለት አይደለም፡፡ በርግጥ ብዙዎቹ የምክር ቃሎች እንኳን በንጉሳዊ ወግ ላደጉት ኃይለስላሴና ተከታዮቻቸው ይቅርና ለኢትዮጵያውያን ሁሉ የጋራ ገንዘብ ነው፡፡

 

Read 3958 times Last modified on Saturday, 13 October 2012 14:02