Saturday, 06 August 2022 11:27

ኢትዮጵያ በፕሬስ ነጻነት ከቀድሞው በ40 ደረጃ አሽቆልቁላለች

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

    -  ኤርትራም በተመሳሳይ ደረጃ ላይ ትገኛለች
     - “የትግራይ ጦርነትን ተከትሎ 63 ጋዜጠኞች ለእስር ተዳርገዋል”
                        
    በህወኃትና በፌደራል መንግስቱ መካከል የተደረገው  ጦርነት፣ በኢትዮጵያ የፕሬስ ነጻነትን በእጅጉ ማዳከሙን የጠቆመው ሲፒጄ፤ ከጦርነቱ በኋላ 63 ጋዜጠኞችና የሚዲያ ባለሙያዎች ለእስር መዳረጋቸውን አመልክቷል።
ከ2014 ህዳር ወር ወዲህ ብቻ 16 ጋዜጠኞች መታሰራቸውን፣ ከእነዚህም ውስጥ 8 ያህሉ አሁንም ድረስ በእስር ላይ እንደሚገኙ የገለፀው ዓለማቀፍ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ቡድን (ሲፒጂ)፤ ይህም ሁኔታ ኢትዮጵያን በአመቱ ጋዜጠኞችን በማሰርና የፕሬስ አፈና በመፈጸም ከሰሃራ በታች ከሚገኙ የአፍሪካ ሃገራት ቀዳሚዋ አድርጓታል ብሏል። ኤርትራም በተመሳሳይ የቀዳሚነቱን ደረጃ ከኢትዮጵያ እኩል ይዛለች።
ኢትዮጵያ በዓለም የፕሬስ ነጻነት የደረጃ ሰንጠረዥ፣ ከቀድሞ ቦታዋ በ40 ደረጃ በማሽቆልቆል፤ ከ180 ሃገራት በ140ኛ ደረጃ ላይ መቀመጧን ሪፖርቱ፡፡
ከጥቅምት 2013 ወዲህ ከሰሜን  ጦርነት ጋር ተያይዞ በርካታ ጋዜጠኞች በተለያየ ጊዜ ወደ እስር ቤት መጋዛቸውን ያወሳው ሲፒጂ፤ ለእስር የተዳረጉት ጋዜጠኞችም በፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ዘገባዎችን በማቅረብ የሚታወቁ እንደሆኑ  አመልክቷል።
በአሁኑ ወቅትም በተመሳሳይ መንገድ የታሰሩ 8 ጋዜጠኞች በእስር ላይ እንደሚገኙና እነዚህ ጋዜጠኞች በአስቸኳይ ተፈትተው መንግስት የሃገሪቱን የፕሬስ ነጻነት ለማስተካከል ጥረት እንዲያደርግ ሲፒጄ በሪፖርቱ አሳስቧል።
የዛሬ አራት ዓመት የጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ የለውጥ መንግስት መምጣትን ተከትሎ፤ ኢትዮጵያ “አንድም ጋዜጠኛ ያልታሰረበት አገር” ተብላ በእነ ሲፒጄ እና ሌሎች የጋዜጠኞች መብት ተሟጋቾች መወደሷና መደነቋ አይዘነጋም፡፡

Read 12229 times