Saturday, 06 August 2022 13:09

እቴጌ ሰብለ ወንጌል - ግራኝን ያሸነፈች ጀግና

Written by  (ከአብዱራህማን አህመዲን፤ የቀድሞ የፓርላማ አባል)
Rate this item
(0 votes)

 የእቴጌ ሰብለ ወንጌል መታሰቢያ ቴምብር
ባለፈው ሳምንት ባቀረብኩት መጣጥፍ የግራኝ አሕመድ ሚስት ስለነበረቺው ባቲያ ድል ወንበራ ማህፉዝ አጠር ያለ ማስታወሻ ማቅረቤ ይታወሳል፡፡ በዚያው ማስታወሻ ላይ የሀገራችን ሴቶች ከጥንት ጀምሮ በሀገራችን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ባህላዊ ጉዳዮች ዙሪያ ያላቸው ተሳትፎ የላቀ እንደነበር ጠቅሻለሁ፡፡ ይሁን እንጂ ይህ የሀገራችን ሴቶች ታሪክ በአግባቡ አለመመዝገቡንና አለመዘገቡን፣ ቢዘገብም በወንዶች ታሪክ ውስጥ ጠቀስ ተደርጎ የሚታለፍ እንጂ ራሱን ችሎ እንዲጻፍ አለመደረጉን፣ አቅም በፈቀደ ይህ ያልተጻፈ ግማሽ ታሪካችንን ለማስታወስና የታሪክ ጸሐፊዎችን ለማነቃቃት በማሰብ መጣጥፉን ማዘጋጀቴን፣ በቀጣይ ጊዜያት “ዮዲት ጉዲት”ን ጨምሮ የሌሎች ሴቶችን ታሪክ ለማቅረብ ቃል መግባቴ ይታወሳል፡፡
በዚሁ መሰረት በዛሬው መጣጥፌ ከግራኝ አህመድ ሚስት ጋር ግብግብ የገጠመው የአፄ ልብነ ድንግል ሚስት በነበረቺው እቴጌ ሰብለ ወንጌል (1482 – 1560 ዓ.ም) ታሪክ ዙሪያ የሚያጠነጥን እንዲሆን ፈቀድኩ፡፡ ወደዚያው እናምራ…
እቴጌ ሰብለ ወንጌል በ1482 ዓ.ም ተወልዳ በ1560 ዓ.ም እንደሞተች የታሪክ ሰነዶች ያመለክታሉ፡፡ እቴጌ ሰብለ ወንጌል የአፄ ልብነ ድንግል ሚስት ስትሆን፤ በአስራ አምስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን በኢትዮጵያ የመንግስት አስተዳደር ውስጥ ከንግስት እሌኒ ሞት በኋላ ከፍተኛ ቦታ የነበራት ሴት ናት። እቴጌዪቱ የነበረችበት ዘመን፣ የግራኝ አሕመድ ጦር ብዙውን የኢትዮጵያን ክፍል የተቆጣጠረበት ወቅት ነበር።
ግራኝ አሕመድ አፄ ልብነ ድንግልን ለአስራ ሁለት ዓመታት ያህል ያሳድድ በነበረበት ወቅት ባለቤቱ እቴጌ ሰብለ ወንጌል በዚያ ክፉ ጊዜ ከአጠገቡ አልተለየችም፡፡ አብራው ትንከራተት ነበር፡፡ የግራኝ ማሳደድ ሲበረታ አፄ ልብነ ድንግልና እቴጌ ሰብለ ወንጌል ትግራይ ደብረ ዳሞ ገዳም ገብተው ዋሻ ውስጥ ተደበቁ፡፡ የደብረ ዳሞ ገዳም ተራራ ላይ የሚገኝ፣ በገመድ እየተጎተቱ የሚወጣበት፣ አንድ በር ብቻ ያለው በመሆኑ የግራኝ ጦር እዚያ ገዳም መግባት ባለመቻሉ ተስፋ ቆርጦ መመለሱ ይነገራል፡፡ አፄ ልብነ ድንግል ደብረ ዳሞ በእፎይታ እየኖረ ሳለ እ.ኤ.አ በ1540 ዓ.ም በተፈጥሮ ህመም ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል፡፡
እቴጌ ሰብለ ወንጌል ከባለቤቷ ከሞተ በኋላ እዚያው ደብረ ዳሞ ተራራ ላይ ለአንድ ዓመት እጅ ሳትሰጥ በግራኝ ጦር ተከባ በተቀመጠችበትና ሁለተኛ ልጇ አጼ ገላውዲወስ አባቱን ተክቶ ንጉስ ከሆነ በኋላ በተለያዩ የጦር ግንባሮች ውጊያ ከፍቶ ከግራኝ ጦር ጋር በመዋጋት ላይ እያለ በክሪስቶፈር ደጋማ የሚመራው የፖርቹጋል ጦር ምፅዋ መድረሱ ተሰማ።
ይህንን ዜና ስትሰማ ደብረ ዳሞ ተራራ ላይ ከሚገኘው ምሽጓ ላይ ሆና ከፖርቹጋሎቹ ጋር በመልእክተኛ አማካይነት በመነጋገርና በመደራደር ጠላት አለመሆናቸውን ካረጋገጠች በኋላ ከፖርቹጋሎቹ የጦር ኃይል ጋር ተቀላቀለች። የፖርቹጋሎቹ አራት መቶ (400) ወታደሮች እሷ ወዳለቺበት መጥተው በፊቷ በሰልፍ ሲያልፉ በቅሎ ላይ ሆና ትመለከት እንደነበርም የታሪክ ሰነዶች ላይ ሰፍሯል። በኋላም ከነበረችበት የተራራ ምሽግ ወርዳ ከፖርቹጋል ጦር ጋር ሆና የግራኝን ጦር እስከመጨረሻው ታግላ አታግላለች - እቴጌ ሰብለ ወንጌል።
የንግሥቲቷን ድጋፍ ተከትሎ የአካባቢው ህዝብ ለፖርቹጋሎቹ ምግብና እርዳታ እንዳደረገ፤ ብዙዎችም ይህን ሰራዊት እንደተቀላቀሉ ይነገራል። የፖርቹጋል ሰራዊት ከግራኝ ጦር ጋር ሲዋጋ እቴጌ ሰብለ ወንጌል የለበሰቺውን ጨርቅ በመቅደድ የቁስል ማሰሪያ ባንዴጅ በመስራት ቁስለኛውን በማከም፣ ለሞቱትም በማልቀስና በማስቀበር በጦር ውሎው ሁሉ ተሳታፊ ነበረች። እ.ኤ.አ በ1543 የክሪስቶፈር ደጋማ ጦር እና ከደቡብ በኩል የመጣው የአፄ ገላውዲዎስ ሰራዊት ተገናኝተው አንድ ላይ በመሆን “ወይና ደጋ” በተባለ ስፍራ በተደረገ ውጊያ፣ ግራኝ አሕመድን አሸንፍው ሲገድሉት እቴጌ ሰብለ ወንጌል “ያዝ! - በለው!” እያለች እዚያው ጦርነት አቅራቢያ ላይ ነበረች። ባሏን አፄ ልብነ ድንግልን ለ12 ዓመታት ሲያሳድደው የነበረው ግራኝ አህመድንም ከባሏ ሞት በኋላ ኃይል አሰባስባና አስተባብራ በመዋጋት ለመበቀል ችላለች፡፡ የግራኝ ሚስት ባቲያ ድል ወምበራ ከመገደልና ከመማረክ ብታመልጥም ልጇ ሙሐመድ ግን በእነ እቴጌ ሰብለ ወንጌል ጦር ተማርኮ ነበር።
እቴጌ ሰብለ ወንጌል በጦርነት ተሳታፊ ብቻ ሳትሆን የሰላምና የዲፕሎማሲ አርበኛም ነበረች። በዚህም መሰረት ቀደም ሲል በግራኝ ጦር ተማርኮ ለግዞት ወደ የመን ተልኮ የነበረውን የልጇን የሚናስን (በኋላ አፄ ሚናስ የተባለው) ጉዳይ ለመፍታት ከባቲያ ድል ወምበራ (ከግራኝ ሚስት) ጋር በመልዕክተኛ አማካይነት የዲፕሎማሲ ግንኙነት በመፍጠር ለመወያየትና ለመደራደር ችላለች። በእነ እቴጌ ሰብለ ወንጌልም በኩል የግራኝ ልጅ ተማርኮ ስለነበር ሁለቱ እናቶች ባደረጉት ድርድር የምርኮኛ ልውውጥ በማድረግ ልጆቻቸውን ከሞት አትርፈዋል፡፡
በምርኮ ልውውጥ የመጣው የሰብለ ወንጌል ልጅ ከስድስት ዓመት በኋላ ወንድሙ አፄ ገላውዲዎስ ድል ወምበራን ባገባው የግራኝ የእህት ልጅ በሆነው በአሚር ሙጃሂድ በጦርነት ሲገደል “አፄ ሚናስ” ተብሎ ስልጣን ላይ ወጣ። እቴጌ ሰብለ ወንጌል ለሚቀጥሉት አራት ዓመታት፣ እንደ ንግስት እሌኒ በሐበሻ ማዕከላዊ የመንግሥት አስተዳደር ውስጥ ከፍተኛ ተሰሚነትን አግኝታ ነበር።
በዚያ ወቅት ፖርቹጋሎቹ ባመጡት የካቶሊክ ክርስትና እምነት እና በኢትዮጵያ በነበረው የኦርቶዶክስ ሃይማኖት መካከል በተነሳው ሽኩቻና ፀብ የፖርቹጋል ካቶሊኮች ሊገደሉ ሲሉ እቴጌ ሰብለ ወንጌል የሰላምና የዲፕሎማሲ ልዑክ ሆና ባደረገቺው ጥረት ጉዳት እንዳይደርስባቸው አድርጋለች። ቤርሙዴዝ የተባለው ታውቂው የፖርቹጋል ተጓዥም አፄ ገላውዲዎስን በማናደዱ ከመገደል የተረፈው በእቴጌ ሰብለ ወንጌል አማላጅነትና ምህረት ነበር። የስፔኑ ጀስዊት ፓትሪያርክ ኦቨዶ ከሞት የተረፈውም በንግሥቲቱ ጣልቃ ገብ ዲፕሎማሲ ምክንያት ነበር።
አፄ ሠርፀ ድንግልን ወደ ስልጣን እንዲወጣም ከሰራዊቱ በላይ ያገዘችው እናቱ ንግሥት ሰብለ ወንጌል ነበረች። እቴጌ ሰብለ ወንጌል ለአፄ ሠርፀ ድንግል ድጋፍ ያደረገችበት ምክንያት ልዑሉ ለንጉሥነት ብቃት ያለው ሰው መሆኑን ቀድማ ለመገንዘብ በመቻሏ እንደነበር ይነገራል። በዚሁ መሰረት በወቅቱ የእናቱን ድጋፍ አግኝቶ የነገሰው አፄ ሠርፀ ድንግል 34 ዓመታት የገዛ ሲሆን፤ በዚህም ጊዜ ሀገሪቱን በመጠበቅ ወደ ሰላም ለማሸጋገር ችሏል። ይህም ሁኔታ እቴጌ ሰብለ ወንጌል ብቃት ያለው መሪ መምረጥ መቻሏ ትክክለኛ እንደነበር የሚያረጋግጥ ነው ይላሉ የታሪክ ታዛቢዎች፡፡
የሰላምና የዲፕሎማሲ ባለሟል የነበረቺው እቴጌ ሰብለ ወንጌል፣ በአፄ ሠርፀ ድንግል ዘመነ መንግሥት በ1560 ዓ.ም አመድ በር በተባለ ቦታ ከዚህ ዓለም በሞት እንደተለየች የታሪክ ሰነዶች ያመለክታሉ።
የእቴጌ ሰብለ ወንጌል ባለቤት የነበረው አፄ ልብነ ድንግል በህይወት በነበረበት ወቅት የራሱንና የሰብለ ወንጌልን ምስሎች ሠዓሊ በመቅጠር እንዲሳል ካደረገ በኋላ ግብፅ ወደ ሚገኘው ቅዱስ አትናቲዮስ ገዳም እንዳስላከው በታሪክ መዝገብ ተመዝግቦ ይገኛል። በዚህ መጣጥፍ የተጠቀምንበት የእቴጌ ሰብለ ወንጌል ምስል የዚያ ቅጂ ከሆነ ቴምብር ላይ የተወሰደ ነው፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊውን በኢሜይል አድፋሻው፡ This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ወይም This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡

Read 3288 times