Monday, 08 August 2022 00:00

ኮስታራ የሥነ ምግባር መርህ፣ “የፍቅር መርህ” ነው።

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(2 votes)

    ትክክለኛ የሥነ ምግባር መርህ፣ ወዲህ ወዲያ የሚለመጥ የሚወላውል አይደለም። ሊያጣምሙት ሊጠመዝዙት ቢሞክሩ እሺ አይልም። እንደ ሰይፍ ስለት የጠራና የጠነከረ፣ ጥሩን ከመጥፎ የሚለይ፣ ፍፁም የማያሻማ፣ አስተማማኝ የብያኔ መስመር ነው። ኮስታራ ነው።
ከሚዛን በፊት፣ ጥሩን ከመጥፎ፣ መብትን ከወንጀል የሚለይ ስለታማ መስመር ያስፈልጋል። የወንጀልን ክብደት ለመመዘን፣ በቅድሚያ ወንጀል መሆን አለመሆኑን መለየት ያስፈልጋል። “ቁርጡ” መታወቅ አለበት። የዚህ ተምሳሌት ነው፣ የፍትህ አድባር የታጠቀችው ሰይፍ። የፍትህና የህግ መርሆች፣ እንደ ሥነ ምግባር መርሆች ኮስታራ ናቸው።
ጥሩ ነገሮች፣ ሁሉም እኩል አይደሉም። መጥፎ ነገሮችም መጠናቸው ይለያያል። ሚዛን ያስፈልጋል። የሥነ-ምግባር ሰይፍ፣ ጥሩን ከመጥፎ ለይቶ ያሰምራል። የሥነ ምግባር ሚዛን መጠናቸውን ያመዛዝናል። የመስመርና የሚዛን ድምር ነው - የሥነ ምግባር ዳኝነት።

በአትሌቶች ብቃት ስንደነቅ፣ በስኬታቸው ስንደሰት ሰነበትን። የብቃታቸውና የጥረታቸው ያህል ከበሩ። በሜዳሊያ አጌጡ። እውነት ነው። ሜዳሊያ ጌጥ ነው። ክብራቸው ከሜዳሊያ ይቀድማል።
የብቃታቸውን ልሕቀት በአደባባይ ሜዳ ላይ አሳይተው ነው የከበሩት። ሌላው ሁሉ ትርፍ ነው። ሜዳሊያው ከክብር በኋላ፣ ለእውቅና ለምስክርነት የሚቀርብ ጌጥ ነው። ሌላም ጌጥ አለ። ለአትሌቶቹ በሚመጥን ክብር፣ “በጉሮ ወሸባዬ” ስሜት የደመቀው የጀግና አቀባበል፤… መንፈስን የሚያፈካ ነበር። ይበል ያሰኛል።
ጀግናዋ ደራርቱ ቱሉ፣ አትሌቶችን እያደነቀች ስታስመሰግንና ፍቅሯንም ከልቧ ስትገልጽ ደግሞ አየን፤ ሰማን። የስንቱን ኢትዮጵያዊ ልብ እየፈወሰች ይሆን?
በእልፍ ምክንያቶች ሳቢያ መንፈሳቸው የጨፈገገባቸው ስንት ሚሊዮን ሰዎች፣ የተስፋ ብርሃን እየደረሳቸው ይሆን? ብዬ አሰብኩ። መንፈሷም፣ ንግግሯም እንደ ስሟ አበባ ነው።
ታዲያ ከቅንነትና ከፍቅር መንፈሷ ጋር፣ የዚያኑ ያህል ኃይል ተዋጊ፣ ብርቱ የአትሌቶች ተቆርቋሪም ናት። በኦሎምፒክ ዝግጅት ጊዜና በሌሎች አጋጣሚዎች ለአትሌቶች አለኝታነቷን አሳይታለች። ደግሞም፣ ቅንነትና ፍቅር፣ ከኃያል ተቆርቋሪነትና ኮስታራነት ጋር አብረው ሲገኙ ነው የሚያምርባቸው።
የፍቅር መርህ
ለምን እንደሆነ በደንብ ባይገባንም እንኳ፣ የሰዎችን ብቃትና ጥረት፣ ውጤትና ሽልማት እንደ ራሳችን ጉዳይ በአድናቆት ለማየት እንጓጓለን። ምን ዓይነት የፍቅር ፀጋ እንደሆነ አብጠርጥረን ባናውቀውም እንኳ፣ የፍቅር ፀጋነቱ አያጠራጥርም።
ብቃትና ጀግንነት ይማርከናል። አንዴ ወይም ሁለቴ ብቻ አይደለም። እንደገና ይናፍቀናል። እንደ አዲስ ማየት እንፈልጋለን። ተፈጥሯዊ የሕይወት ረሃብ ሳይሆን አይቀርም።
የላቀ ብቃት፣… እስከ ጥግ የተወጠረ ብርቱ ጥረት፣… እስከ ውጤት ድረስ ፀንቶ የሚዘልቅ ጀግንነት፣ ለአፍታም ቢሆን፣ ከነፍሬውና ከነሽልማቱ የማየት ፍላጎት፣ ጤናማ ተፈጥሯዊ ፍላጎት ነው።
እንደ ምኞታችን፣ የብቃት ልህቀትን በእውን ስንመለከት፣ ሙቀት ይሰማናል። የደነዘዘ መንፈስ እንኳ ይፍለቀለቃል። አንዳንዴም ከምኞታችን የተሻለ ጀግንነትን የማየት እድል ሲገጥመን፣ መንፈሳችን ይፈካል። የሕይወት ኃይል በሁለመናችን የሰረፀ የተሰራጨ ያህል፤ መንፈሳችን ይነቃቃል።
ለየግላችን ለየራሳችን የነበረን ክብር ይታደሳል። ለሌሎችም ያለን ግምት፣ በአጠቃላይ ለሰው ተፈጥሮ ያለን ክብርና ለብቃት ያለን ፍቅር ከፍ ይላል።
አትሌቶችን በክብር ለመቀበል ወደ አደባባይ የወጡ አድናቂዎች፣ ምን ዓይነት ፍቅር ከቤት አስነስቶ እንዳመጣቸው አያውቁ ይሆናል። ፌሽታውን በቴሌቪዥን የሚከታተሉ ተመልካቾች፣ ለምን ልባቸው “ስቅል” እንደሚል፤ ለምን ፊታቸው እንደሚበራ አይመራመሩም። ግን፣ ጀግናን ማክበር፣ ብቃትን ማድነቅ ለራስ ነው ይባል የለ! አድናቂዎች ሁሉ ነፍሳቸው ሲታደስ ይታወቃቸዋል።
ተደብቆብን ወይም ሸሽቶን የነበረ፣ የጣልነውና ያባረርነው የቅንነት አየር በዙሪያችንና በውስጣችን እንደ ልብ ይናኛል።
አትሌቶችን በክብር ለመቀበልና አድናቆታቸውን ለመግለፅ ሲጎርፉ የነበሩ ሰዎችን መታዘብ ትችላላችሁ። በቅንነት መንፈስ ተሞልተው እርስ በእርስ በበጎ ስሜት ሲተያዩና ሲነጋገሩ ለራሳቸው ይገርማቸዋል። የአንድነት የህብረት መንፈስ ያድርባቸዋል።
እውነትም፣ የጀግኖችን የላቀ ብቃት ማክበር፣ ብርቱ ጥረትን ማድነቅ ለራስ ነው። የሰውን ክብር (የራስንም ክብር) እንደ አዲስ የማየት እድል ነውና። በውጤታቸውና በሽልማታቸው መደስት፣… የፍቅር መንፈስ ነው። ግን የፍትህ መንፈስም ጭምር ነው።
እንደየብቃቱ፣ እንደየጥረቱ፣ እንደየውጤቱ መጠን፣…. ፍሬው ቢበዛ፣ ሽልማቷ ቢበረክት፣ የዚያኑ ያህል ክብራቸው ቢዳብር ተገቢ ነው። “ሁሉም እንደስራው ይቅናው”፣… የሚል የፍቅር መንፈስ፣ ያለ ጥርጥር የፍትህ መርህም ነው። እናም ክብር ይገባቸዋል።
በአርአያነት መንፈሳችንን የሚያድስ የጀግንነት ብቃታቸውን በእውን የምናይበት እድል ስለሰጡን ምስጋና ይገባቸዋል። ማመስገን ሲባል ግን፣ እንደ ውለታ አይደለም። ጀግኖችን ማመስገን ለራስ ነው። ደራርቱ ቱሉ፣ ጀግኖቹን አትሌቶች ያደነቀችበትና ያመሰገነችበት የፍቅርና የቅንነት መንፈስዋን ማየት ትችላላችሁ።
የሰውን ብቃት ማክበርና ማድነቅ፣ ነፍስን ያንፃል። ያድሳል። ያፈካል።
በሌላ በኩል ደግሞ፣ ፕሬዝዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ እንደገለፁት፣ ባለፉት ዓመታት ብዙ የከፋትና የጭካኔ መጥፎ ጥፋቶችን አይተናል፤ ሰምተናል። ሕይወት ጠፍቷል፤ ኑሮ ተጎሳቁሏል። የክፋትና የጭካኔ ጥፋቶች፣ ለሰው ያለንን ግምት ያሟሽሻሉ። ያቆሽሻሉ።
በእልፍ የክፋትና የጭካኔ ተግባራት ሳቢያ፣ መንፈሳችን ጨልሟል። ነፍሳችን ታሟል። ውስጣችን በጥላሸት ጠቁሯል።
ፕሬዝዳንቷ እንደገለጹት፣ ክፋትንና ጭካኔን በዝምታ ማየት ተገቢ አይደለም። መሳተፍና መደገፍ ይቅርና በይሁንታ መቀበል፣ በዝምታ ማለፍም ሆነ መላመድ አይገባንም። ለስብዕናውና ለሕይወቱ ክብር ያለው ሰው፣ ለክፋትና ለጭካኔ ፊት መስጠት የለበትም። ታዲያ፣ እሱም በተራው በጭፍን ስሜት ወደ ጅምላ ውንጀላና ወደ ጥላቻ፣ ወደ ጭፍን ፍርጃና ወደ ጥፋት ዘመቻ ይሂድ ማለት አይደለም። ለሕይወትና ለፍትህ የሚቆረቆር ሰው ከኮስታራነቱ ጋር ጠንቃቃም ነው።
ይህም ብቻ አይደለም። የሥነ ምግባር ሰው፣ ከኮስታራነቱ ጋር፣ የፍቅርና የቅንነት ሰው ነው። እኛም መሆን አለብን። ያኔም፣ የሰዎችን ብቃትና ጥረት፣ ውጤትና ሽልማት ስናይ፣ ውስጣችንን የሚያነጻ፣ መንፈሳችንን የሚያፈካና የሚያነቃቃ እድል ይሆንልናል። ነፍሳችን ይታከማል።
እንግዲህ ዛሬ “ማርች 8” ይመስል፣ ተጨማሪ ሁለት “ሴቶችን” እንጠቅሳለን። ከፈላስፋዋና ከደራሲዋ አየን ራንድ፣ ዋና ዋና የፍቅርና የፍትህ መርሆችን እናያለን። የፍትህ እመቤትን ደግሞ በምሳሌነት እንጠቅሳታለን።
የአየን ራንድ መሠረታዊ የሥነ ምግባር መርሆች
ለፍቅር የተዘረጉ፣ ለፍትህ የሰሉ ናቸው - የፈላስፋዋ የሥነ ምግባር መርሆች። ሦስቱን እንመልክት።

1. ለእውነታ የታመነ “ንቁ አእምሮ” (Reason)።
እውቀትን የሚሻና የሚያስፋፋ፣ የራሱን አእምሮ በአግባቡ የሚጠቀም ነው የሥነ ምግባር ሰው። ራሱን ችሎ ለማሰብ ይጥራል። ከሌሎች ሰዎች ለመማርም ይጓጓል። የራሱንና የሰዎችን ነፃነት ያከብራል።
ይሄ ነው፣ የመሠረታዊ መርሆች ሁሉ “መሠረት”።
አእምሮ በሌለበት ቦታና ጊዜ፣ “የሥነ ምግባር መርህ” ብሎ ነገር የለም። ዕፅዋትና ሌሎች እንስሳት፣ “ሥነ ምግባር” ወይም “መርህ” እያሉ አይፈላሰፉም። ከአእምሮ አቅም ጋር ነው፤ የመርህና የሥነ ምግባር ጉዳይ የሚመጣው።
እውነትን ከውሸት፣ ጥሩን ከመጥፎ፣ መልካምን ከክፉ መለየት የሚችል የአእምሮ አቅም፣… የተፈጥሮ እውነታ ነው። በመርሆች አማካኝነት የምንፈጥረው ወይም በምርጫችን የምናመጣው ነገር አይደለም።
ተፈጥሯዊ የአእምሮ አቅም፣ ከምርጫና ከመርህ ይቀድማል። የመርሆች ሁሉ “ተፈጥሯዊ ምንጭ” ነው።
ተፈጥሯዊውን የአእምሮ አቅም በአግባቡ መጠቀምና አለመጠቀም ግን፣ የምርጫና የመርህ ጉዳይ ነው።
የአእምሮ አቅምን በአግባቡና በልህቀት የመጠቀም ትጋት፣ የመጀመሪያው የሥነ ምግባር መርህ ነው። የመርሆች ሁሉ “መሠረት” ነው ማለት ይቻላል።

2. በሙያ ብቃትና በፍሬያማ ትጋት ወደ ከፍታ የሚራመድ “ትክክለኛ የኑሮ አላማ” መያዝ (Purpose)።
ኑሮን የሚያሻሽል ጽኑ የሕይወት አላማ ይዞ፣ በሙያ ጥበብና በፍሬማ ትጋት ይጓዛል - የሥነ ምግባር ሰው።
መንገዱ፣ የተቃና የበረከት መንገድ ነው። ግን ደግሞ፣ ትክክለኛ የሥነ ምግባር ጉዞ፣ ብርቱ ጥረትን የሚጠይቅ ፈታኝ መንገድም ነው።
በዚህም ምክንያት የሥነ ምግባር ሰው፣ ለራሱና ለሰዎች ምርት ተገቢውን ዋጋ ይሰጣል። በአድካሚ ፈታኝ መንገድ ከብርቱ ጥረት የተገኘ ፍሬ እንደሆነ ያውቃልና።
የራሱንና የሰዎችን የንብረት መብት ያከብራል። እንደየ ምርቱ በሐቅ የሚገበያይና እንደየ አቅሙ የሚተጋገዝ ነው - የሥነ ምግባር ሰው።
ይሄ ነው፣ የመርሆች ሁሉ “መሪ አሽከርካሪ”።
ጥያቄዎችን በማንሳት እንየው። ጥሩና መጥፎ፣ ክፉና መልካም… ብለን ነገሮችን የምንለያቸው (የምንበይናቸው) በየትኛው ማስመሪያ ነው? መጠናቸውንና ደረጃቸውን የምንለካውስ በየትኛው ሚዛንና መስፈሪያ ይሆን?
የብያኔ መስመራችንና የልኬት ሚዛናችን “የሰው ሕልውና” እንደሆነ ትገልጻለች - ፈላስፋዋ።
ለሰው ሕይወትና ለኑሮው በሚያመጡለት ፋይዳ ወይም ደግሞ በሚያስከትሉበት ፍዳ፣ “ጥሩ” እና “መጥፎ” ብለን እንለያቸዋለን።
“የሰው ሕይወትና ኑሮ” ስንል ግን፣… የሰው እንጂ የአውሬ ማለት አይደለም። “ከተፈጥሯዊ የአእምሮና የአካል አቅሙ ጋር የሚጣጣም የሰው ሕልውና” ማለት ነው - ትክክለኛ የሰው ሕይወት። በፈቃደኝነት “ኮማ” ውስጥ መግባትና የድንዛዜ እድሜን ማስቆጠር ማለት አይደለም። በቅዥት እየተቅበዘበዙ ጊዜ ማሳለፍ ማለትም አይደለም።
ቀስ በቀስ ራሱን እየቻለና እያመረተ ኑሮውን መምራት ማለት እንጂ፣ ለእለት ጉርስ እርስ በርስ መበላላት፣ እንደ አውሬ መናከስና መናጨት ማለት አይደለም።
ተከባብሮ እየተገበያየ ወይም በልግስና እየተደጋገፈ እንዲኖር እንጂ፣ በባርነት ሌሎች ሰዎችን እያገለገለ እንዲመነምን ወይም የሌሎች ሰዎችን ንብረት እየዘረፈ እንዲያራቁት አይደለም።
በአጠቃላይ፣ “ከሰው ተፈጥሮ ጋር የሚስማማና ለሰው ክብር የሚመጥን አኗኗር”፣… ጥሩን ከመጥፎ የሚለይ የብያኔ መስመር ነው። የተግባሮች ሁሉ መለኪያና መመዘኛ ነው።
ለዚህም ነው፣ ትክክለኛ የኑሮ አላማ፣ የሌሎች መርሆች ሁሉ መሪ አሽከርካሪ የሚሆነው። በሙያ ብቃትና በፍሬያማ ትጋት የሚራመድ የኑሮ አላማ፣… ሌሎች መርሆችን በተግባርና በእውን ይተረጉማል። የግል ማንነት የሚታነፀውም በዚህ ሂደት ነው።

3. ለራሱ ተግባርና ለራሱ ባሕርይ “የግል ሃላፊነትን” በመጨበጥ፣ “የብቃትና የፅናት ማንነትን” ለመገንባት ማለም (የእኔነት ክብር - Self-esteem)።
የሰውን ሕይወት አለመንካትና ማክበር፣… የግድ ያስፈልጋል። ራስን ከማክበር ጋር የተቆራኘ ባሕርይ ነው። ራስን አላግባብ አዋርዶ ሌሎችን በአግባቡ ማክበር አይቻልም።
ሌሎች ሰዎችን አላግባብ አጣጥሎ ወይም የሰውን ተፈጥሮ ሁሉ በደፈናው አጥላልቶ፣ ራስን በአግባቡ ማክበር አይቻልም። ከንቱ ሙከራ ነው።
ሰዎች የየራሳቸውን አላማና ተግባር የመምረጥ፣ የየራሳቸውንም ማንነት የመቅረፅ አቅም እንዳላቸው አክብረን፣ እንደየ ምርጫቸውና እንደየ ተግባራቸው፣ እንደየ ልካቸው እንመዝናቸው።
የአድናቆት ወይም የነቀፋ ዳኝነታችን፣ ሁል ጊዜና በሁሉም ሰው ላይ፣ በትክክለኛው የሥነ ምግባር መርህ ብቻ ይሁን።
የመስመርና የሚዛን ድምር ነው - የሥነ ምግባር ዳኝነት።
ትክክለኛ የሥነ ምግባር መርህ፣ ወዲህ ወዲያ የሚለመጥ የሚወላውል አይደለም። ሊያጣምሙት ሊጠመዝዙት ቢሞክሩ እሺ አይልም። እንደ ሰይፍ ስለት የጠራና የጠነከረ፣ ጥሩን ከመጥፎ የሚለይ፣ ፍፁም የማያሻማ፣ አስተማማኝ የብያኔ መስመር ነው። ኮስታራ ነው።
“የፍትህ እመቤት” የተሰኘችውን ምስል አስታውሱ። በአንድ እጇ ሰይፍ ይዛለች። የፍርድ ውሳኔንና የቅጣት አፈጻጸምን ለማሳየት ሊጠቅም ይችላል። የመርህ ኮስታነትንም ያመለክታል።
ከሚዛን በፊት፣ ጥሩን ከመጥፎ፣ መብትን ከወንጀል የሚለይ ስለታማ መስመር ያስፈልጋል። የወንጀልን ክብደት ለመመዘን፣ በቅድሚያ ወንጀል መሆን አለመሆኑን መለየት ያስፈልጋል። “ቁርጡ” መታወቅ አለበት። የዚህ ተምሳሌት ነው፣ የፍትህ አድባር የታጠቀችው ሰይፍ። የፍትህና የህግ መርሆች፣ እንደ ሥነ ምግባር መርሆች ኮስታራ ናቸው።
ታዲያ፣ የሥነ ምግባር ኮስታራነት፣ ከአፍቃሪነቱ ጋር አይነጣጠልም። አንዱ ከተገነጠለና ያለ ሌላው ለብቻው ከተነጠለ፣ የሁለቱም ትርጉም ይጣመማል። ኮስታራነቱ፣ ከፍቅር የሚመጣ ነው።
እንደ ስሙ፣ “መልካም የሥነ ምግባር መርህ” ከሥረ መሠረቱ፣ “የፍቅር መርህ” ነው።
መልካም ሕይወትን ከመውደድ የሚመነጭ፣ ወደ መልካም ፍሬዎች የሚመራ የተባረከ ብሩህ የፍቅር መንገድ ነው።
ሕይወትን ከማፍቀሩና መልካምነትን ከመውደዱ የተነሳም፣ ጨለማና ጠማማ መንገድን አይታገስም። ኮስታራ ነው ብለን የለ! ለመጥፎ ፍሬዎች ቦታ የለውም። ለክፋት መንገድም ቅንጣት ታህል ፊት አይሰጥም። አያቀላቅልም።
በማያወላውል ስለታማ መስመር፣ ጥሩን ከመጥፎ ይለያል፤ ይበይናል።
በዓይነታቸው ግራና ቀኝ፣ ብርሃንና ጨለማ ከለያየ በኋላ፣ ስራው ያልቃል ማለት አይደለም።
ጥሩ ነገሮች፣ ሁሉም እኩል አይደሉም። መጥፎ ነገሮችም መጠናቸው ይለያያል። ሚዛን ያስፈልጋል። የሥነ-ምግባር ሰይፍ፣ ጥሩን ከመጥፎ ለይቶ ያሰምራል። የሥነ ምግባር ሚዛን መጠናቸውን ያመዛዝናል። የመስመርና የሚዛን ድምር ነው - የሥነ ምግባር ዳኝነት።
በአንድ በኩል፣ አፍቃሪነትንና ኮስታራነትን ያዋሕዳል። “ባየነው ብቃት ልክ ሰውን እንቅረብ፣ እናድንቅ፣ እንውደድ፣ እናፍቅር። ባየነው ድክመት ልክም ሰውን እንገስፅ፣ እንራቅ፣ እንውቀስ፣ እንፍረድ” ይላል።
በሌላ በኩልም፣ ጥንቃቄንና ቅንነትን ያዋሕዳል።
“ውሸት መጥፎ ነው” የሚል መርህ ስለያዝን ብቻ፣ “እገሌ ዋሽቷል” ብለን መፍረድ፣ ከዚያም አልፈን “እገሌ ውሸታም ነው” ብለን መፈረጅ እንችላለን ማለት አይደለም። ሰው ላይ መፍረድ፣ እጅግ ከባድ ሃላፊነትንና ከባድ ጥንቃቄን ይጠይቃል። እናም፣…
አላግባብ ለነቀፋ መቸኮል መጥፎ ባሕርይ ነው። ተገቢውን አድናቆት መንፈግም ክፉ ልማድ ነው።
ይሄ ነው፣ “ለፍቅርና ለፍትህ” በፅናት የቆመ፣ የጥንቃቄ ሃላፊነትንና ቅንነትን ያዋሐደ መልካም ሰብዕና።
የሥነ ምግባር መርሆች፣ አንድ ሁለት ሦስት ተብለው ቢዘረዘሩም፣ የተነጣጠሉ አማራጮች አይደሉም። በኅብር መሟላት ያለባቸው ገፅታዎች ናቸው።
ሥነ- ምግባር፣ከአንድ ጎን እየገነባ ከሌላ ጎን አያፈርስም፣ ከወዲህ እያሟላ ከወዲያ አያጎድልም። የሁሉም ውሕደት ነው፤ ምሉዕ የሥነ ምግባር ሕይወት።
ውሕደቱ የሚፈጠረው ግን፣ ዋና ዋናዎቹን ገፅታዎች በፈርጅ አጉልተን ማየትና እየመነዘርን ማገናዘብ ስንችል ነው (Reason, Purpose, Selfesteem… እያልን)።Read 10130 times