Saturday, 06 August 2022 14:40

“በተለይ አሥራ አንደኛው” በወፍ በረር ቅኝት

Written by  መልካሙ ተክሌ
Rate this item
(1 Vote)

    መጀመርያ ያየኋት ከሁለት ሦስት ዓመት በፊት ነው፤ሁለት ሦስት መጻሕፍት በእጇ ይዛ ስትሔድ፡፡ ስፈራ ስቸር እንድታሳየኝ ጠየኳት፤ አሳየችኝ፡፡ ከመጽሐፎቹ አንዱ የአለማየሁ ገላጋይ “ወሪሳ” ይመስለኛል፡፡ ይህንኑ መጽሐፍ ከዚያ በኋላም እጇ ላይ አይቻለሁ፡፡
በአጋጣሚ ከዚያን ወዲህ ባሉት ጊዜያት ባየኋት ቁጥር መጽሐፍ ከእጇ ላይ አላጣም፡፡ አንድ ሰፈር ነዋሪዎች እንደነበርንም ቆይቼ ነው የተረዳሁት - አሁን የት እንደቀየረች ባላውቅም። እንዲህ ዘወትር መጽሐፍ ከእጇ የማይጠፋን አንባቢ፣ የራሷን ብትጽፍስ የሚል የዘወትር ምኞት ነበረኝ፡፡
ልጅቱን ከዚህ በተጨማሪ አምና እና ዘንድሮ በተገኘሁባቸው የመጻሕፍት ምረቃ መድረኮች ሁሉ አግኝቻታለሁ፡፡ ከደራስያን ጀርባ  ለሥራቸው መታተም በብርቱ የምታግዝ ነች፡፡
በቅርቡ ደግሞ ይህችው ብርቱ ሴት፣ ይፍቱሥራ ምትኩ፣ የራሷን የመጀመርያ መጽሐፍ ለንባብ አድርሳ ለምረቃ አብቅታለች። ሰኔ 10 ቀን 2014 ዓ.ም አራት ኪሎ በሚገኘው ዋልያ መጻሕፍት፣ መጽሐፉ ሲመረቅ ተገኝቶ አስተያየት የሰጠው ደራሲና ሃያሲ አለማየሁ ገላጋይ፣ የራሷን መጽሐፍ ብትጽፍ የሚል ምኞት እንደነበረውና እውን እንዳደረገችው፣ በዚህም ደስታ እንደተሰማው ገልጿል፡፡
የይፍቱሥራ የበኩር ሥራ የሆነው “በተለይ አሥራ አንደኛው” መጽሐፍ ስምንት የተለያዩ ታሪኮች አሉት፡፡ በታሪኮቹ ውስጥም በርካታ ንዑሳን ታሪኮች አሉ፡፡ በስምንት አርእስት የተቀነበቡት ስምንቱ ታሪኮች፡- ጀበና፣ በተለይ አሥራ አንደኛው፣ ቅቤ፣ አልቴት፣ ጣሪያ፣ አርብ አርብ ይሸበራል ልቤ፣ ቀለም እና ምልዓት በሚሉ ርዕሶች  የተካተቱ ናቸው።
ስምንት ታሪኮች አልን እንጂ ታሪኮቹ ተለጣጣቂነትና አንድነት ያላቸው ናቸው ማለትም ይቻላል፡፡ እያንዳንዱን ለብቻ ነጥሎ ማንበብ ይቻላል፡፡ መጽሐፉን ግን ምሉዕ የሚያደርገው አንድነት ሲነበብ ይመስለኛል። በስምንቱም ያሉት ዋነኛ ገጸባሕርያት ተመሳሳይ ናቸው፡፡ በስምንቱም ግን ሕይወትን ከተለየ አቅጣጫ በእነሱ መነጽርነት እንድንቃኝ ያደርጉናል፡፡
ለምሳሌ የመጽሐፉ ርእስ እንዲሆን ከመሃላቸው የተመረጠው “በተለይ አሥራ አንደኛው” ተራኪዋ አኪዬ የምትላቸው፣ የአንዲት ሴት የትዳር ውጣ ውረድ፣ በራሳቸው አንደበት የሚተረክበት ነው፡፡ ተራኪዋ ራሷ አድማጭ የምትሆንበት ነው፡፡ ታሪኩ የሴትየዋ የአሁኑ የትዳር አጋር የሆኑትና ተራኪት አባባ በምትላቸው፣ አሥራ አንደኛው ባል ባሉበትም ነው ለልጅቱ የሚተርኩላት።  ምን አይነት ባሎች ገጠሟቸው፣ ለምን ተለያዩ፣ ባሎቻቸውን እንዴት ገለጹዋቸው---የሚለውን ከመጽሐፉ ያገኙታል፡፡
የመጽሐፉ መክፈቻ “ጀበና” የሚል ታሪክ የሚቀርብበት ነው፡፡ በዚህ ውስጥ እንደተለመደው ተራኪዋና አኪዬ የምትላቸው አሳዳጊዋ ብቻ ሳይሆኑ “የሥር” ያለቻት ሸክላ ሰሪ አለች፡፡ የሠራሽ ወርቅ ነው ሥሟ፡፡ ጀበና ሠሪ ነች የሥር፡፡ ሸክላ ሠሪ የማይከበርበት ሥርዓት     አሳልፈናል፡፡ በይፍቱሥራ ምትኩ ድርሰት ጀበና ሠሪንም የማያከብር ማኅበረሰብ አለ፡፡ “የሰፈሩ ውሪ አንዳንድ ቀን ሸክላዎቿን ሰብስባ ወደ ገበያ ስትሄድ እየተከተሉ ያበሽቋታል፡፡” (ገጽ 10)። እንዲህ አይነቱ ማብሸቅ እንኳን የሠራሽ ላይ ብቻ የተከሰተ አይደለም፡፡ በመጽሐፈ ነገሥት ነብዩ ኤልሳዕን “አንተ መላጣ ውጣ” ብለው ተሳድበዋል። የሠራሽወርቅ እናት ሲያርፉ መርዶውን በጎዳናው ነገሯት፡፡ ያ ትክክል አለመሆኑንና ከንቀት የመነጨ መሆኑን በድርጊት ጭምር የምትገልጸው ተራኪዋም ሆነች አኪዬ የምትላቸው አሳዳጊ እናቷ፣ የሠራሽን ማስጠጋታቸው ለሙያውና ለሙያተኞቹ ክብር መሥጠታቸውን ከማሳየቱም በላይ ለተደራስያንም፣ ከእናንተም ይኸው ይጠበቃል የሚል መልዕክት ያስተላልፋል፡፡ (ከገጽ 9-25)
በሌሎቹም ድርሰቶች ይፍቱሥራ አካባቢያዊ፣ የአካል፣ የሁኔታ ወዘተ ገለጻ በማራዘም አንባቢን አላሰለቸችም፡፡ ከዚህ ይልቅ አንባቢ ንቁ ነው ሞልቶ ያነባል በሚል የተወችው ይመስላል፤ በብዙ ትረካዎቿ፡፡ በመጽሐፉ ምረቃ መራሔ መድረኩ ጋዜጠኛና ገጣሚ ደመቀ ከበደ፣ “ሰሰትሽ” እንዳለው ሳይሆን፣ በመጽሐፉ ላይ ዳሰሳ እንዳቀረቡት መምህር መሠረት አበጀ፣ ለአንባቢ መተው በሚለው እስማማለሁ፡፡ ምናልባት ደመቀ “እንዲህ አትብተሽ ጽፈሽ አንድ መጽሐፍ ብቻ” ማለቱ ከሆነ እስማማበታለሁ፡፡
ትረካዎቹ በዝርው የተጻፉ ቢሆኑም የቃላት ምርጫዋ ለግጥም የቀረበ ነው። ለዚህም ይመስላል ጋዜጠኛና ገጣሚ ወሰንሰገድ ገብረኪዳን በፌስቡክ ገጹ ስለ መጽሐፉና ጸሐፊዋ በሠጠው አስተያየት፤ “ተዋጥቶልሻል። አተራረኩ ቱባ ነው። የባሕል ውቅሩ ቱባ። ቋንቋው እንደወረደ ቱባ። የትረካው ዘይቤና ፍሰቱ የተባ። ለዛው ጥዑም። በሀገርኛ ፍልስፍና የታጀበ፣ ምጡቅ። የአጭር ተረክ ውበት፣ የተረኩ ዝርጋታ የሚያመረቃ ነው፦ ምሉዕ። እያንዳንዱ ትረካ አጭር ቢሆንም የትየለሌ እውነት፣ እና እምነት የታጨቀ። በአንዲት ገፀ ባህርይ ስር የሚያልፉ ሺ ምንተሺ ሕይወቶችን የሚያስቃኝ ድንቅ ስራ ነው። ወድጄዋለሁ።” ያለው፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጸሃፊውን በኢ-ሜይል አድራሻው፡- This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡

Read 1306 times