Sunday, 14 August 2022 00:00

የኢትዮጵያ የአስገዳጅ ስምምነት ጥያቄዎች

Written by  አያሌው አስረስ
Rate this item
(0 votes)

 “ኦል አፍሪካ” የተባለው የዜና ምንጭ ከግብፅ አገኘሁት በማለት ሰኔ 2 ቀን 2014 ዓ.ም በበይነ መረብ ባሰራጨው ዘገባ፣ በአፍሪካ ኅብረት አማካይነት በግብጽ፣ ሱዳንና ኢትዮጵያ መካከል በህዳሴ ግድብ ጉዳይ ላይ የሚደረገው ድርድር ወደ ጫፍ መድረሱን ጠቁሞ፤ ድርድሩ እንደገና እንዲጀመር የማነሳሳቱን ሥራ የተወጣችው ዩናይትድ አረብ ኤምሬትስ፣ የምስራች ለመስማት መጓጓቷን አመልክቷል፡፡ ለዜናው ወኪል መረጃውን የሰጠችው ግብጽ፤ ነገሩን በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የኤሜሬት ተወካይ ከሆኑ ሰው እንዳገኘችውም አስታውቃለች፡፡
የግብጽን መንግስታዊ የመገናኛ ብዙኃን የሚከታተሉ ወገኖች፣ ግብጾች በህዳሴ ግድብ ዙሪያ እንደ ቀድሞው ሲደነፉ ወይም ያዙኝ ልቀቁኝ ሲሉ እንደማይታዩ ይገልጻሉ፡፡ የግብጽ ፕሬዚዳንት ሰሞኑን በሰጡት መግለጫም፣ ተለሳልሰው ታይተዋል፡፡ “ኢትዮጵያ አንድ አይነት አስገዳጅ ስምምነት ሳትፈርም፣ የህዳሴን ግድብ  መሙላት የለባትም” በማለት ሲዝቱ የከረሙት፣ አምና ከሱዳን ጋር በመሆን ኢትዮጵያ ድንበር ላይ ሶስት ጊዜ ወታደራዊ ልምምድ ያደረጉት ፕሬዚዳንቱ፤ ምን አግኝተው ቀዘቀዙ ብሎ መጠየቅ ተገቢ ነው፡፡
ሰኔ 4 ቀን 2014 ዓ.ም በዚሁ ጋዜጣ ላይ “የተቀደሰውን ነገር ለውሾች አትስጡ” በሚል ርዕስ ባቀረብኩት ፅሑፍ፣ የአረብ ኤምሬትስ ወደ ጉዳዩ መግባትና አደራዳሪ ሆኖ ለመሰየም መፈለግ ሊያስከትል የሚችለውን ጉዳት መጠቆሜን አስታውሳለሁ፡፡ የግብፅ መረጃ እውነት ሆኖ ከተገኘ፣ የኢትዮጵያ መንግስት፣ ድርድሩ በአፍሪካ ህብረት እጅ ውስጥ እንዲቆይና በእሱም አማካይነት እንዲካሄድ በማድረጉ፣ እኔ በግሌ ከልቤ አመሰግነዋለሁ፡፡ መመስገንም አለበት፡፡
አንድ ዓመት ከተቋረጠ በኋላ እንደገና ተጀምሮ ወደ ጫፍ ደረሰ እየተባለ ስላለው የታላቁ የህዳሴ ግድብ ድርድር፣ የኢትዮጵያ መንግስት እስከ አሁን የሰጠው ምንም  መግለጫ የለም፡፡ አስራ አንድ ዓመት ሙሉ በተደረገው ድርድር የተገኘው ፍሬ፣ እ.ኤ.አ በ2015  አገራቱ ተስማምተው የተፈረሙት ውል ብቻ ነው። ሦስቱ አገሮች አሜሪካ ላይ በተደረገው ድርድርም “ዘጠና ከመቶ የሚሆነውን ጨርሰን የቀረው ጥቂት ነው” ሲሉን ቆይተው ነው፤ ነገሩ እንደገና ከዜሮ ለመነሳት የተገደደው፡፡ የአስር ከመቶ ድርሻ የተሰጠው ጉዳይ፣ የኢትዮጵያን ዕጣ ሊያጠፋ የሚችል በሽታ የያዘ ነበር ብሎ መገመትም ያስችላል፡፡
ግብፅና ሱዳን እ.ኤ.አ በ1929  እና 1959 በተደረጉ ውሎች  ተጣብቀው፣ ኢትዮጵያ እነዚህን ውሎች የማትቀበል መሆኗን አስረግጣ ይዛ፣ በውሃ ሃብቷ ላይ ሙሉ መብት  እንዳላት አስባና አምና የምታደርገው ድርድር፣ እንዲህ በሁለት ወር ጊዜ ውስጥ ከእልባት ይደርሳል ብሎ ማመን ይከብዳል፡፡ እስከ አሁንም በነበረው-ታሪካቸው አንዳቸውም እግራቸውን ከተከሉበት መሬት የመንቀል ፍላጎት አሳይተው አያውቁምና፡፡
 ኢትዮጵያ የሁለቱን አገራት ማስፈራራትና ዛቻ ወደ ጎን  ብላ፣ ያለምንም አሳሪ ስምምነት፣ የመጀመሪያውን፣ ሁለተኛውንና ሶስተኛውን የታላቁን የህዳሴ ግድብ ውሃ ሙሌት አከናውናለች፡፡ እስከ አሁን ሁለቱ አገሮች ይዘውት ከተነሱት አስገዳጅ የስምምንት ጥያቄ አንጻር፣ የራሷን አስገዳጅ የስምምነት ጥያቄ ማንሳት ይገባታል እላለሁ፡፡
በመጀመሪያ መሆን ያለበት ግን ግብጽና እንግሊዝ እ.ኤ.አ በ1929፣ ነፃ የወጣችው ሱዳንና ግብጽ እ.ኤ.አ በ1959፣ በአባይ ውሃ ላይ ኢትዮጵያን አግልለው የተዋዋሉትን ውል ውድቅ እንዲያደርጉ መጠየቅ ነው፡፡ ከዚያም ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት መዝገብ ውስጥም እንዲፋቅ መደረግም አለበት፡፡
ሁለቱ አገሮች እየተደራደሩ በነበረበት ጊዜ፣ የንጉሡ መንግስት፣ ሶስተኛ ተደራዳሪ ሆኖ ለመግባት ያቀረበውን ጥያቄ “አንቀበልም” ብለው የገፉት ራሳቸው ናቸው፡፡ ለዛሬው ውዝግብ ምክንያት የሆኑት እነሱ በመሆናቸው ለዚህ ጥፋታቸውም በአደባባይ ይቅርታ እንዲጠይቁ ማድረግ፣ ሁለተኛው የግዴታ ስምምነቱ ጉዳይ መሆን ይኖርበታል፡፡
ከኡጋንዳ የሚነሳው ነጭ ዐባይ፣ ከኢትዮጵያ የሚነሳው ጥቁር ዐባይ ሲባሉ ቆይተው፣ ካርቱም ከደረሱ በኋላ ናይል በሚል የጋራ ስያሜ እንደሚጠሩ ይታወቃል፡፡ የኡጋንዳው ነጭ አባይ  ያለው ድርሻ  ከ14.5% ከመቶ የማይበልጥ በመሆኑ፣የወንዙ አጠቃላይ ስም ከፍተኛ ድርሻ ባለው ስም እንዲጠራ መደረግ ይኖርበታል፡፡ ስለዚህም ግብፅም ሆነች ሱዳን የሚደርሳቸውን ውሃ፤ “የአባይ ውሃ” ብለው መቀበል ይኖርባቸዋል፡፡ በተጨማሪ ለሱዳንና ግብጽ የሚደርሰው 85.5% ውሃ ከኢትዮጵያ የሚገኝ በመሆኑ፣ ሁለቱ አገራት፣ ይህን የኢትዮጵያን ባለቤትነት ሙሉ እውቅና ሊሰጡት ይገባል፡፡
የኤርትራ የመገንጠል ንቅናቄ እንዲጀመር በማሰልጠንና በማስታጠቅ ግብፅ ከፍተኛ ድርሻ እንደነበራት የራሷ ሰዎች ሳይቀር ዛሬ እየተናገሩ ነው፡፡ በሱማሌና በኢትዮጵያ መካከል ጦርነት ያስነሳችውም ግብጽ ናት፡፡ ለዚህም በቂ መረጃዎች አሉ፡፡ ለሱዳን መውጫ መግቢያ ከመስጠት ጀምሮ የኢትዮጵያን አንድነት በማናጋት ከፍተኛ ሚና መጫወቷም ግልፅ ነው፡፡ ስለዚህ ሁለቱም አገሮች  ለጸረ-ኢትዮጵያ  ኃይሎች አጋርና መጠለያ ሰጪ ሆነው ከመዝለቃቸው አንጻር፣ በኢትዮጵያ ላይ ለደረሰው ጉዳት ተጠያቂነታቸውን መቀበል አለባቸው፡፡  
ከግብጽና ሱዳን የአስገዳጅ ስምምነት አንጻር፣ ኢትዮጵያ እነዚህን የራሷን የአስገዳጅ ስምምነት ጥያቄዎች ይዛ መነሳት አለባት ብዬ አምናለሁ። በዚህም እኛም አስገዳጅ ስምምነት የሚሹ ጉዳዮች እንዳሉን፣ ለእነሱም ለዓለምም የምናሳውቅበት ጊዜ አሁን ነው።
በዚህ አጋጣሚ፣ የሶስተኛው የታላቁ የሕዳሴ ግድብ ሙሌት እንዲሳካ ላደረጉ ሁሉ ያለኝን ከፍተኛ አክብሮት የምገልፀው፣ከተቀመጥኩበት ወንበር ተነስቼ ነው፡፡ ክበሩልኝ!!
Read 749 times