Saturday, 20 August 2022 12:56

መንግስት ህወሐትን በዓይነ ቁራኛ እንዲከታተል ኢዜማ ጠየቀ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

 "ቡድኑ ዳግም በህዝብ ላይ ጥቃት እንዲፈፅም ሊፈቀድለት አይገባም” - ኢዜማ

         የፖለቲካ ልዩነቶችና አለመግባባቶች ሁሉ በጠረጴዛ ዙሪያ መፈታት አለባቸው ብሎ እንደሚያምን የጠቆመው ኢዜማ፤  ለዚህም ነው ሃገራዊ ምክክሩ ልዩ አትኩሮት ሊሰጠው ይገባል የሚለውን እምነቱን ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ አጽንኦት ሰጥቶ የሚያስረዳውም በዚህ ምክንያት ነው ብሏል።
“ሁሌም ቢሆን ለሰላም ቅድሚያ መስጠት አግባብ ነው። ለሰላም ሲባል የሚደረጉ ድርድሮችም ሆኑ ስምምነቶች ግን ህውሃት በሃገር መከላከያ ሰራዊት ላይ በፈጸመው ክህደት ተገድደን የገባንበትን ጦርነት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ዘላቂ መፍትሄ የሚያመጡ መሆናቸው ሊረጋገጥ ይገባል” ሲል አሳስቧል። ፓርቲው ትላንትና ባወጣው መግለጫ ህወሃት የሰላም ድርድሩን አማራጮች እየገፋ እራሱን ለጦርነት እያዘጋጀና በተለመደው አውዳሚ መንገድ የጥፋት ነጋሪት እየጎሰመ መሆኑን መረጃዎች እንደሚጠቁሙ ያመለከተው  ኢዜማ፤ መንግስት በአካባቢው ያለውን ማህበረሰብ ዳግም ለከፋ ሰብአዊ ጉዳትና መፈናቀል እንዳይዳርግ ወቅታዊ ሁኔታውን ያገናዘበ ጥንቃቄ እንዲወስደን አስጠንቅቋል።
“የህወሃት መሰረታዊ ባህርይ ሰላም ጠል ቢሆንም፣ የእውነት ለትግራይ ህዝብ የሚቆጣጠር ከሆነ ከጦርነት ይልቅ ሰላም አማራጮችን ተቀብሎ ተግባራዊ ማድረግን ቅድም ቅድሚያ መስጠት ይጠበቅበታል ሲል ለአማጺው ቡድን ምክር የለገሰው ኢዜማ፤ “መንግስትም ለሰላም እያሳየ ያለውን ጥረት  አጠናክሮ መቀጠሉ የሚበረታታ ቢሆንም፤ ቡድኑ እንደዚህ ቀደሙ በህዝብ ላይ  አስከፊ ጉዳትና ስቃይ እንዲፈጽም ቅንጣት ዕድል ሊሰጠው አይገባም ብሏል- በአጽንኦት።
“በአሸባሪነት የተፈረጁ ቡድኖች ለአገር ህልውናና ቀጣይነት እንቅፋት እየሆኑ፣ ዜጎች ደህንነትና ሰላም ጥያቄ ውስጥ እየከተቱ፣ ህዝቡን በስጋና ፍርሃት ውስጥ እንዲኖር ማድረጋቸውን እንዲቀጥሉ ፈጽሞ መፍቀድ የለበትም” ሲል ኢዜማ መንግስትን በአጽንኦት አሳስቧል- ትላንት ባወጣው መግለጫው።

Read 11790 times