Saturday, 20 August 2022 12:57

ከጅምሩ እንቅፋት የበዛበት የሰላም ድርድር

Written by  መታሰቢያ ሳሣዬ
Rate this item
(9 votes)

  • ህውኃት ከድርድሩ ራሱን እየገፋና የጦርነት ነጋሪት እያጎሰመ ነው
     • የህውሃቱ ቃል አቀባይ ጌታቸው ረዳ፤ “ሃይል ብቸኛ አማራጫችን ነው” አሉ
     • ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም ስለትግራይ የሰጡትን መግለጫ መንግስት ነቀፈ
     • መንግስት የሰላም ድርድሩን በአስቸኳይ ለማስጀመር የሚያስችል ሰነድ አዘጋጅቷል
             
         በመንግስትና በህወሃት ታጣቂ  ሃይሎች መካከል እየተካሄደ ያለውንና ላለፉት 22 ወራት የዘለቀውን ጦርነት ለማስቆምና ሰላም እልባት ለመፈለግ እየተደረገ ያለው ጥረት በህወሃት ታጣቂ ሃይሎች በኩል እንቅፋት እየገጠመው ነው።
መንግስት የሰላም ድርድሩን በአስቸኳይ ለመጀመር የሚያስችል የሰላም ምክረ- ሃሳብን፣ የያዘ ሰነድ ማዘጋጀቱን ይፋ ቢያደርግም፣ ህውሃት በተቃራኒው፣ የተኩስ አቁም ስምምነቱ መፍረሱን በመግለጽ “ኃይል ብቸኛ አማራጩ” እንደሆነ አስታውቋል- ሰሞኑን በቃል አቀባዩ በኩል በሰጠው መግለጫ።
የህውሃት ቃል አቀባይ አቶ ጌታቸው ረዳ ከትናንት በስቲያ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ የፌደራል መንግስት በትግራይ ሃይሎች ላይ በተለያዩ ግንባሮች ጥቃት መሰንዘሩን በመግለጽ፣ “የተኩስ አቁም ስምምነቱ ቴክኒካሊ ፈርሷል” ብለዋል። የኢትዮጵያ  መከላከያ ሰራዊት በሰሜን ምዕራብ ትግራይ ደደቢት አካባቢ በከባድ መሳሪያ የታገዘ ድብደባ አድርሶብኛል በማለት ያወጣውን መግለጫ መንግስት ሃሰት ነው ብሎታል።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ ፕሬስ ሴክረተሪያት ቢልለኔ ስዩም ትናንት ለዓለማቀፍ ጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫቸው ላይ፤ የኢትዮጵያ መንግስት ሰላማዊ ድርድር በፍጥነት እንዲጀምር ከፍተኛ ጥረት በሚያደርግበት በአሁኑ ወቅት  በህውሃት በኩል ተቀባይነት ማጣቱን ጠቁመው  ሰላማዊ ድርድሩ እንዳይሳካ ለማድረግ በየጊዜው የተለያዩ ሰበቦችን ሲደረድር መቆየቱን ተናግረዋል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አቢይ አህመድ የተቋቋመው የሰላም አማራጭ አብይ ኮሚቴ፣ የሰላም ንግግሩ በአስቸኳይ ተጀምሮ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ መድረስ የሚቻልበትን ምክረ-ሃሳብ  የያዘ ሰነድ ያዘጋጀ ሲሆን ይኸው  ሰነድ የሰላም ንግግሩ በአስቸኳይ ተጀምሮ  የተኩስ አቁም ስምምነት መድረስ ይቻል ዘንድ ከአፍሪካ ህብረት ጋር በቅርበት እየሰራ መሆኑን ያመለከተው መንግስት በክልሉ መሰረታዊ አገልግሎቶችን ማቅረብ የሚጀምረው የተኩስ አቁም ስምምነቱን ተከትሎ በሚፈጠረው አስቻይ ሁኔታ እንደሆነም በመግለጫው ላይ አስፍሯል።
ግጭቱ ከተከሰተበት ጊዜ ጀምሮ መንግስት ለሰላም ዕድል ለመስጠት ተደጋሚ ሙከራዎችን ሲያደርግ ቆይቷል ያለው የመንግስት መግለጫ የሰላም አማራጩን በዘላቂነት እውን ለማድረግና በሰሜኑ የትግራይ የአፋርና የአማራ ክልል አካባቢዎች የሚኖሩ ዜጎችን ከገጠማቸው ችግር ለማላቀቅ የህውሃት ታጣቂ ቡድን ለሰላም ድርድሩ ፍቃደኛ ሊሆን እንደሚገባ አመልክቷል።
በፌደራል መንግስቱ በኩል የቀረበው ይህ የሰላም ጥሪ በህውሃት ታጣቂ ሃይሎች በኩል እምብዛም ተቀባይት እያገኘ አይደለም።  ከመንግስት ጋር ለመደራደር የሚያስችል ነገር አለመኖሩን ለቪኦኤ የተናገሩት የህውሃት ቃል አቀባዩ፤ አቶ ጌታቸው ረዳ የፌደራል መንግስቱ የሰላም ፍላጎት የለውም፤ የተኩስ አቁም ስምምነቱንም አፍርሷል ሲሉ ተናግረዋል። ከዚህ በኋላ ሃይል ብቸኛ አማራጫችን መሆኑን ተገንዝበናል ብለዋል።
“ለጦርነቱ ብቸኛ ተጠያቂ የኢትዮጵያ መንግስት ነው” ሲሉ ከሰዋል- ቃል አቀባዩ። ይህ አባባላቸው ብልጭ ያለውን የሰላም ጭላንጭል ጨርሶ የሚያጠፋ ነው ያሉት የፖለቲካ ተንታኞች፤ ቡድኑ ራሱን ለጦርነት ዝግጁ እያደረገ መሆኑን ጠቋሚ ነው ብለዋል። የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም ሰሞኑን  ለዓለማቀፍ መገናኛ ብዙሃን በሰጡት መግለጫ፤ “በትግራይ ያለው ሁኔታ በዓለም አስከፊው ሰብአዊ ቀውስ ሆኖ እያለ ጉዳዩ ትኩረት ያላገኘው በትግራይ ባሉ ሰዎች የቆዳ ቀለም ሳቢያ ነው ብለዋል።
“ትግራይ ከውጪው ዓለም ተገልላ እንደ ስልክ፣ መብራትና ባንክ ያሉ አገልግሎቶች በሌሉበት ሁኔታ ስለ ሰላም ድርድሩ ማውራት አይቻልም ያሉት ዶ/ር ቴዎድሮስ፤ በአሁኑ ወቅት በትግራይ ያለው ሰብአዊ ቀውስ በዩክሬንም ካለው የበለጠ ነው ብለዋል።
ዋና ዳይሬክተሩ ባለፈው ረቡዕ ለአለም መገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች በኢንተርኔት ሰጡት በተባለው መግለጫቸው ላይ የተናገሩትና ሮይተርስ የዘገበውን ይህንኑ ጉዳይ አስመልክቶም የጠቅላይ ሚኒስትሩ ፕሬስ ሴክረታሪት ስነ-ምግባር የጎደለውና ለቦታው የማይመጥን ነው ሲሉ አጣጥለውታል።
ሁለት ዓመት ሊሞላው ቀናት የቀሩት የመንግስትና የህውሃት ታጣቂ ቡድን ጦርነትን በድርድር ለመቋጨት እየተደረገ ያለው ጥረት በህውሃት ቡድን በኩል በየጊዜው በሚቀርቡ የተለያዩ ሰበቦች ሳቢያ ሊደናቀፍ ይችላል የሚል ስጋት አሳድሯል። የህውሃት ታጣቂ ቡድን ለጦርነት ዝግጅት እያደረገ መሆኑ እየተነገረ ነው።



Read 12085 times