Saturday, 20 August 2022 13:18

“የፌደራል አወቃቀሩ የሃገራዊ ምክክሩ አጀንዳ ሊሆን ይገባል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

- ሕዝብ ያልተወያየበት የወሰን አከላለል ጥርጣሬና ተቃውሞ ይፈጥራል
       - የአዲስ አበባ ነዋሪ የራሱ ን ከንቲባ ራሱ በቀጥ ታ መምረጥ አለበት


          አንጋፋው ፖለቲከኛና ምሁር ዶ/ር አለማየሁ አረዳ፤  የሰሞኑ የመነጋገሪያ አጀንዳ ሆነው በዘለቁት የክልሉ አደረጃጀት የወሰን አከላለል ጉዳዮች ላይ ለአዲስ አድማስ ሃሳባቸውን አጋርተዋል- የኋላ ዳራ እየተፈተሹና ታሪካዊ እውነታዎችን እያጣቀሱ።
ከአዲስ አድማስ ጋዜጠኛው አለማየሁ አንበሴ ጋር ሰፊ ቃለ-ምልልስ ያደረጉት ዶ/ር አለማየሁ አረዳ ያልዳሰሱት ችግር የለም። ያላነሱት ክልል አይገኝም። ችግሮቻችንን ብቻ ሳይሆን መፍትሄዎችን ይጠቁማሉ። የመንግስት ባለሥልጣናትም በክልል አደረጃጀቶች ጉዳይ ላይ በጥድፊያ ከመወሰን ይልቅ ህዝብ ማወያየትና ጥናት ማድረግ ብልህነትም ተገቢ መሆኑን ይመክራሉ።
ከዶ/ር አለማየሁ አረዳ ጋር የተደረገውን ቃለ-መጠይቅ እነሆ ሃሳብ አዕምሮን ከአዕምሮ የሚያገናኝ ድልድይ ነው።

           በአሁኑ ወቅት በየቦታው የሚነሱ የማካለልና የክልል እንሁን ጥያቄዎች ለምን ጎልበት አሉ? በ1983 ዓ.ም የተጀመረው በዘውግ ክልሎችን የማደራጀት  ያስከተለው መዘዝ ነው ማለት ይቻላል?
1983 ዓ.ም በኢትዮጵያ የፖለቲካ ሥርዓት አደረጃጀት ታሪክ ውስጥ ለየት ያለ ሁኔታ የተፈጠረበት ዘመን ነው፡፡ እስከ 1983 ዓ.ም ድረስ ኢትዮጵያ በአሃዳዊ ስርዓት ውስጥ ሃገራዊ ብሔርተኝነት የጎለበተበትና ማዕከላዊነት የጠነከረበት መንግስታዊ ሥርዓት ነው የነበረው፡፡ በወቅቱ አሃዳዊ ሥርዓት ነው ስንል ሁሉም ስልጣን ተማክሎ፣ ከማዕከል ወደየ ክፍለ ሃገሩ ትዕዛዝና መመሪያ የሚወርድበት  ነበር ማለታችን ነው፡፡ የአሠብ ልዩ አስተዳደርን ጨምሮ ሁሉም ክፍለ ሃገሮች በማዕከላዊነት ተጠርንፈው የሚመሩ ነበሩ፡፡  የሃብት ክፍፍሉም ቢሆን ፍትሃዊ አልነበረም፡፡ 1983 ላይ ስንመጣ ግን ራሱ የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለሙ ወደ ነገዳዊ ብሔረተኝነት ተቀየረ፡፡ የወቅቱ ርዕዮተ ዓለም መነሻው፣ በኢትዮጵያ ውስጥ  የብሔር ብሔረሰቦች መብት ሳይከበር ስለኖረ አሁን መከበር አለበት የሚል ነበር። የብሔረሰቦች ራስን በራስ የማስተዳደርና ሉአላዊነት መከበር አለበት የሚለው ሃሳብ ነበር በወቅቱ ጎላ ብሎ የወጣው። በዚያም የተነሳ አወቃቀሩ ማዕከላዊ (አሃዳዊ) ከሆነ አስተዳደር ይልቅ ያልተማከለ አስተዳደር እንዲከተል የሚል አቋም በፖለቲከኞቹ ተያዘ። ነገር ግን እነዚህ ያልተማከሉ አስተዳደሮች ሲፈጠሩ ገና ህገመንግስቱም አልተረቀቀም ነበር፡፡ ዋነኛው ጉዳይ በአሃዳዊ ስርዓት ውስጥ የሃብትና የስልጣን ክፍፍሉ ፍትሃዊ አልነበረም፣ የብሔር ብሔረሰቦች መብት አልተከበረም፣ አስተዳደራዊ ስርዓቱ ቀልጣፋና ተደራሽነት ያለው አልነበረም፤ የልማቱን ሥራ ማሳለጥ፣  ባህልና ቋንቋን የማሳደግ የመሳሰሉ መብቶች ያልተከበሩበት ነው የሚለው ነበር መነሻ የሆነው፡፡ የፌደራል አወቃቀር ሲመጣ እነዚህን ከላይ የተዘረዘሩትን ችግሮች ያቃልላል ተብሎ ነበር፡፡ ነገር ግን ባለፉት ሦስት አስርት ዓመታት እነዚህ ችግሮች በእርግጥ ተቃለሉ ወይ? ለምሳሌ ክልሎች ተከልለው ቢመሰረቱም፣ ራስን በራስ የማስተዳደር መብት (Autonomy) የተወራለትን ያህል ነበር ወይ? አስተዳደሩ ራሱ በሚፈለገው ደረጃ ቀልጣፋ ብቃት ያለውና ተደራሽ ነበር ወይ? ብለን ስንጠይቅ፣ የእውነት እንዳልሆነ ነው የምንገነዘበው፡፡ ምክንያቱም ፌደራላዊ የተባለውን አወቃቀር ስናየው በሁለት ዘርፍ ተከፍሎ አንደኛው የኢህአዴግ  የሚባሉትን አራት ክልሎች የያዘ ሲሆን፤ ያልተማከለ ነው ቢባልም ግን በህወኃት-ኢህአዴግ ፓርቲ ሥር ተማክሎ ዲሞክራሲያዊ ማዕከላዊነትን በጠበቀ መልኩ የሚመራ ስለነበረ፣ በውስጥ አሃዳዊነት የተጠረነፈ ነበርና ከላይ የተዘረዘሩትን ችግሮች ያቃለለ  የፌደራል አወቃቀር በአራቱ ክልሎች ውስጥ ነበር ማለት ያስቸግራል፡፡ የተቀሩት ክልሎች በአጋር ፓርቲዎች የሚመሩ ናቸው ቢባልም በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ከሕወኃት ተፅዕኖ ውጪ አልነበሩምና እንደታዘዙ የሚኖሩ ነበሩ ማለት ይቻላል፡፡
ለምንድን ነው ሁነኛ የፌደራል አወቃቀር መፍጠር ያልተቻለው?
ይሄ እንግዲህ ከህወኃት መራሹ ኢህአዴግ የነገዳዊ ብሔረተኝነትና አብዮታዊ ዲሞክራሲ የሚለው ርዕዮተ አለም ከእውነተኛው ፌደራላዊ ሥርዓት ጋር ባለመጣጣሙ የመጣ ነው። ሥርዓቱ ዲሞክራሲያዊ መሆን ያለመቻሉ ነው የመጀመሪያው ችግር፡፡ ፌደራሊዝም  ደግሞ በዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ውስጥ ቢዋቀር ነው ይበልጥ ውጤታማ የሚሆነው። የብዙኃንና የህዳጣን መብቶች ተከብረው የሚኖሩት በዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ውስጥ ነው፡፡ ህወኃት/ኢህአዴግ ደግሞ በባህሪው ዲሞክራሲያዊ ድርጅት አልነበረም፡፡ ሌላው ራሱ የፌደራል አወቃቀር የሚለው ሃሳብ የመጣው ከትግራይ ለመነጨው ገዥ ቡድን (ህወኃት)፣ ለስልጣን እርካብነት የሚገለግሉ መሰል ድርጅቶች ፈጥሮ ለድርጅቶቹ ልሂቃን ክልሎችን በማከፋፈል በእነሱ ለመጠቀምና ለህውኃት መራሹ የተማከለ አስተዳደር አመቺ እንዲሆኑ ነበር እንጂ ለዲሞክራሲ፣ ለአስተዳደር መቀላጠፍ፣ ለፍትሃዊነትና ለእኩልነት አልነበረም፡፡ እኩልነትና ሉአላዊነት የሚሉት ሃሳቦች በነገዳዊ ብሔርተኝነት ውስጥ  በስም ይጠሩ እንደው እንጂ በተግባር አይታወቁም፡፡ ለምሳሌ አራቱን ክልሎች ያስተዳድሩ የነበሩት ህወኃት እና የህወኃት ፍጡራን ናቸው፡፡ ትግራይን ያስተዳድር የነበረው ህወኃት ራሱ ነው፡፡ አማራን ያስተዳድር የነበረው ብአዴን፣ በህወኃት ነው የተፈጠረው፡፡ ደቡብን ያስተዳድር የነበረው ደኢህዴን፣ በህወኃት ነው የተፈጠረው። ኦሮሚያን ያስተዳድር የነበረው ኦህዴድም በህወኃት ነው የተፈጠረው፡፡ ስለዚህ ህወኃት ራሱን ነው በአምሳሉ ያባዛው እንጂ የህዝብ ስምምነት ባለበት ማለትም የኦሮሞ፣ የአማራ፣ የደቡብ ህዝብ ሌላውም በተስማሙበት መንገድ የተፈጠረ ፌደራላዊ  አወቃቀር አልነበረም፡፡
የኢህአዴግ ድርጅቶች ተብለው ከሚጠሩት አራቱ ድርጅቶች ጎን ደግሞ አጋር የሚባሉ ድርጅቶች ከህወኃት ጋር በእጅ አዙር ተፅዕኖ ብቻ እንዲቆሙ ተደርገው የተሠሩ ነበሩ፡፡ እንደውም እነዚህ ድርጅቶች በሃገሪቱ ጉዳይ ላይ በፍጹም የማያገባቸው፣ ሁሉም ነገር ከታቀደና ውሳኔ ከተሰጠ  በኋላ የሚነገራቸው ነበሩ ማለት ይቻላል። ህወኃት የአካባቢያቸውን ሃብት እንደፈለገ የሚያዝባቸው ነበሩ። ኦሮሚያን ጨምሮ ቤኒሻንጉል፣ ጋምቤላ፣ ሱማሌና አፋር ክልሎች በዚህ ምን ያህል እንደተበዘበዙ እነሱም ያውቁታል፡፡ በአጠቃላይ ስንመለከተው የነበረው ፌደራላዊ አወቃቀር  የውሸት ስለነበረ ነው፣ ዛሬ የተለያዩ  እና ጠንከር ያሉ ጥያቄዎች እየቀረበበት ያለው፡፡ በህዝቦች መካከል መተማመንና ስምምነት መፍጠር ያልቻለ ፌደራሊዝም ዛሬ የት እንዳደረሠን ማስተዋል የሚሳነን አይሆንም፡፡
አሁን እየቀረቡ ያሉ የብሔር ክልልነት ጥያቄዎች መነሻቸው እኒህ ችግሮች ናቸው ብሎ መደምደም ይቻላል ወይስ ሌሎችም ምክንያቶች ይኖራሉ?
በ27 ዓመቱ የሥልጣን ዘመን ህውኃት በማዕከላዊነት ሥርዓቱ ጭብጥ እርግጥ  አድርጎ ያስተዳድር ስለነበረ በሌላ በኩል የየድርጅቱ ራሳቸው እርስ በእርስ በስልጣን እየተሻኮቱ ለህወኃት አገልጋይነታቸውን ያረጋግጡ ስለነበሩ፤ በወቅቱ ተቃውሞ ቢያሰሙ እንኳ መረር ያለ እርምጃ ይወሰድባቸው ስለነበረ፤ ለምሳሌ፡- ህወኃት በተከፋፈለ ወቅት አቶ አባተ ኪሾ የሚመራው ደቡብ እና ኩማ ደመቅሳ ይመራው የነበረው ኦሮሚያ ትንሽ በማፈንገጣቸው የተነሳ ምን አይነት በደል እንደተፈጸመባቸው እናውቃለን፡፡ ህወኃት ከመስመር ሲወጡበት በጠንካራ ጫና በማስተካከል ነበር ሲገዛቸው የኖረው፡፡ ከ2010 በኋላ ግን ይሄ አፈና እና እመቃ በመጠኑ ተነስቷል፡፡ ይሄን የሥልጣንና የሃብት ክፍፍሉ ፍትሃዊ ያለመሆን፣ በየአካባቢው እንደ አዲስ ጥያቄ አስነስቷል ማለት ይቻላል። ፌደራሊዝሙ የይስሙላ እንደነበር ግልፅ ሆኗል፡፡ ለምሳሌ ደቡብ ክልል መጀመሪያ ላይ በአምስት ክልሎች እንዲዋቀር ተደርጎ ነበር፣  ትንሽ ቆይቶ ደግሞ ሁሉንም በአንድ ሰንዱቅ አስገብቶ፣ የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች ክልል ብሎ እንደገና አዋቀራቸው፡፡ 2010 ላይ እንግዲህ በፊትም ቢሆን፣ በውስጡ ቅሬታ ስለነበረ፣ እመቃው ሲላላ ቅሬታቸው መፈንዳት ጀመረ። ሲጀምር ደግሞ ሲዳማ ለብቻው ክልል ሆነ። ሲዳማ ለብቻው መውጣቱ ለሌሎች መንገድ መክፈቱ አልቀረምና ይህም ችግር ፈጥሯል። በበጀት ድልድል ክልል መሆን፣ ዞን መሆን፣ ወረዳ መሆን የራሱ ልዩነት አለው፡፡ ስለዚህ የደቡብ አንዳንድ ወረዳዎች  ሌሎች ዞን ወይም  ክልል የሆኑ አካባቢዎች  ያህል ወይም ይበልጥ  የህዝብ ቁጥር ያላቸው፣ ነገር ግን በዞን ደረጃ ወይም በወረዳ ደረጃ በመወሰናቸው ፍትሃዊ የሆነ የስልጣንና የሓብት ክፍፍል እንዳላገኙ ይታወቃል፡፡ ለምሳሌ ስልጤ ከጉራጌ ተነጥሎ በዞንነት እንዲደራጅ ሲጠየቅ መነሻው ከላይ የተባለው የስልጣንና የሃብት (በጀት) ክፍፍሉ ኢ-ፍትሃዊነት እንጂ ስልጤ ጉራጌን ስለጠላ አይደለም፡፡
ሌሎችም በዚሁ ልክ እኛ ክልል፣ ዞን፣ ወረዳ ብንሆን የተሻለ ጥቅም፣ የተሻለ በጀት እናገኛለን፤ አካባቢያችንን በልዩነት ማልማት እንችላለን ብለው ስለሚያስቡ፣ ጉዳዩ የስልጣንና የፍትህ ጥያቄ ሊያስነሳ ችሏል፡፡ ደቡብ ውስጥ ያለው ጥያቄ ከሞላ ጎደል ይሄ ነው፡፡
አማራ ክልልን ደግሞ ብንመለከት፣ በክልሉ አማራ ብቻ አይደለም ያለው፤ አገውአዊ  ፈላሻ፣ ቅማንት፣ ኦሮሞ፣ አገው - ህምራ፣ ራያ አሉ፡፡ እነዚህ ህዝቦች በታሪክ ተደባልቀው በልዩ ልዩ መመዘኛዎች  ተሳስረው ተቀምጠው ሳለ፣ ይሄ የህወኃት አወቃቀር እርስ በእርስ እንዲጋጩ ነው ያደረጋቸው፡፡ ድሮ እኮ የወሎ አማራ ከወሎ ኦሮሞ ጋር በፍቅር ኖሯል፤ የሚዋጋበት ሁኔታ እምብዛም አልነበረም፡፡ አሁንስ? ክልል የሚባል ነገር ከመጣ በኋላ ብዙ ችግር ተፈጠረ፡፡ ከዚህ በመለስ  በሌሎች አካባቢዎች በአማራ ተወላጆች ላይ የሚደርሰው በደል፣ ማንነት ላይ የተመሰረተ ጥቃትና ጭፍጨፋ የአማራ ብሔረተኝነትን አጠናክሯል፡፡ የአማራ ብሔርተኝነት  በጨመረ ቁጥር ደግሞ የሌላውም ብሔርተኝነት እየጨመረ ነው  የሚመጣው። በተለይ ከአማራ ህዝብ ጋር ያሉ ህዝቦች ብሔርተኝነት መጨመር ነው የበለጠ አደጋው። ደቡብም ያለው እንደዚያው ነው። የአንዱ ነገዳዊ ብሔርተኝነት በጨመረ ቁጥር የሌላውም ይጨምራል፡፡ ይሄን አይነት አካሄድ ያመጣው ወይም በሃይል ተዳፍኖ የነበረውን ያወጣው ደግሞ ከ2010 በኋላ የመጣው ለውጥና እመቃን የማላላት አካሄድ ነው፡፡ አንዱ ዋነኛ ሊባል የሚችለው የአመለካከት ለውጥ ይሄው ይመስለኛል፡፡ ኦሮሞን ብትመለከት ኦሮሞና ኦሮሞነት በኢትዮጵያ ሃገረ መንግስት ግንባታ ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረከተ ቢሆንም ተበድሎ የኖረ ህዝብ ነው፡፡ የኩሻዊ ስልጣኔ መገለጫ የሆነውን የገዳ ሥርዓቱን እንኳን ኢትዮጵያ ውስጥ አስፋፍቶ ለኢትዮጵያ ህዝብ እንዲያደርስ እድል አላገኘም፡፡ የኢሬቻ ሥርዓቱ ሳይቀር እንደ ባዕድ እንዲታይ ነው ያደረጉት፡፡ የኦሮሞን ህዝብ በጠባብነት የአማራን ህዝብ በትምክህተኛነት እየፈረጁ፤ እነዚህ ህዝቦች እየተፈራሩ እርስ በእርስ እየተጠራጠሩ እንዲኖሩ ነው ያደረጉት። ህወኃት በአጠቃላይ አንዳንዶቹን ትልልቅ ክልሎች አድርጎ ማስፈራሪያ ሲያደርጋቸው፣ አንዳንዶቹን ደግሞ ትንንሽ አድርጎ መጠቀሚያ ነው ያደረጋቸው፡፡ ይሄ ሁኔታ አሁን እየፈነዳ ነው፡፡
በአማራ ክልል የቅማንት ህዝብ ጥያቄ ምንድን ነው? ሁሉም ጋ የሃብትና የስልጣን ክፍፍል  ጥያቄ ነው እየተነሳ ያለው፡፡ ስለዚህ ይሄ አንዳች መፍትሔ ማግኘት አለበት፡፡ ምክንያቱም የአንዱ ብሔርተኝነት መጎልበት የሌላውንም ብሔርተኝነት እያጎለበተ ነው የሚሄደው፡፡ የአማራ ብሔርተኝነት እኮ ዝም ብሎ የጎለበተ አይደለም፡፡ የአማራ ህዝብ እኮ የነጻነት ግንባር ተመስርቶለት የሚያውቅ ህዝብ አልነበረም፤ ግን ዛሬ አለው። ዛሬ እነዚህ ብሔርተኝነቶች የመጎልበታቸው ምንጭ  የፌደራል አወቃቀሩ ፍትሃዊነትን አላረጋገጠም የሚል መነሻ ነው፡፡ እነዚህ ነገሮች ደግሞ ሃገራዊ አንድነትን እየሸረሸሩ ነው የሄዱት፡፡ ይሄ አሁን ያለው አወቃቀር ካልተቀየረ አሊያም ካልተሻሻለ በስተቀር ጥያቄውም ማቆሚያ ይኖረዋል፣ መፍትሄም ያገኛል ብዬ አላስብም፡፡ በሌላ በኩል ሃገራዊ ምክክር ለማድረግ እየተዘጋጀን ባለንበትና የአወቃቀሩ ጉዳይም የምክክሩ አንዱ አጀንዳ ሊሆን ይችላል ተብሎ በሚታሰብበት ጊዜ ላይ አዲስ አበባ ከኦሮሚያ ጋር ወሰን ይካለላል፤ በተመሳሳይ ደቡብ ውስጥ ደግሞ ከትልልቅ ክላስተር ወደ ትንንሽ ክላስተሮች (የህዝቡ ስምምነት ይኑርም አይኑርም) ገዥው ፓርቲ በሚጭነው ሁኔታ ይመስላል እየተሰራ ነው የሚገኘው፡፡ ይሄ ራሱ አደገኛ ነው። ምክንያቱም ሃገራዊ ምክክሩ በኋላ የተለየ ሃሳብስ ቢያመጣ? ህገመንግስቱ እንዲሻሻል ሃሳብ ቢያቀርብስ ምንድን ነው የሚሆነው? እንደ እኔ ይሄ የአወቃቀር ጉዳይ በእርጋታ በተጠና መልኩ ነው መመለስ ያለበት፡፡ ለዚህ ደግሞ ብልፅግና ብቻ ሳይሆን ህዝቡ ውስጥ ሃሳብ ያላቸው ሰዎች ሃሳባቸው መደመጥ አለበት። ህዝቡ ውስጥ ሃሳቡ መንሸራሸር አለበት፡፡ ለዚያም ነው እኔ ይሄን ሃሳብ ላጋራ የፈለግሁት፡፡ እዚሁ ያቀረብኩት ነጻ ሃሳቤን ነው፡፡ በኋሳብ ልዕልና የሚያምን ሁሉ ሃሳቤን በሃሳብ ሊሞግት ይችላል፡፡
የአዲስ አበባና የኦሮሚያ ክልል ፊኒፊኔ ዙሪያ ልዩ ዞን የአስተዳደር ወሰን ማካለል ጉዳይስ እንዴት ያዩታል?
ህገመንግስቱ አዲስ አበባ የራሷ ምክር ቤት ያላት ነጻ አስተዳደር ናት ብሎ ነው የሚያስቀምጠው፡፡ ተጠሪነቷ ለፌደራል መንግስቱ ነው ይላል፡፡ ነገር ግን ለፌደራል መንግስቱ ሲል ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ነው ወይስ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ነው የሚለው በህገ መንግስቱ በግልጽ አልተቀመጠም። የከተማዋ ከንቲባ ግን ከጠቅላይ ሚኒስትሩ መመሪያ ይወስዳሉ፡፡ የከተማዋ ምክር ቤትም አለ፡፡ ነገሩ ዝብርቅርቅ ያለ ይመስለኛል፡፡ እዚያው ህገ መንግስቱ ላይ ደግሞ በኦሮሚያና በአዲስ አበባ አስተዳደር መካከል ያሉ ግንኙነቶች፣ በህግ ይወሰናሉ ይላል፡፡ ይሄ እስካሁን አልተወሰነም፡፡ ታዲያ እንዴት ነው ዛሬ ብድግ ብለው ወደ ማካለል የገቡት? በእውነቱ ምን እየተሰራ እንደሆነ ለመረዳትም አስቸጋሪ ነው፡፡ ክልል እያካለሉ ነው? ለወደፊት ክልል የማካለል ስራ የሚጠቅም ሥራ እየሰሩ ነው? ምን እንደሆነ አይታወቅም። ይሄ በጣም የተጣደፈና በእውነቱ ለአዲስ አበባም ሆነ መሃሉ አድርጎ ላቀፉት የኦሮሚያ ህዝብ ይጠቅማል የሚል እምት የለኝም፡፡ የቆየውን ጭቅጭቅ የሚያሰነብት እንጂ ለአንዴና ለመጨረሻ ታሪክን መሰረት አድርጎ የሚፈታ አይደለም፡፡ የተያዘው አካሄድ የኦሮሞን ህዝብ የማስጠላት ዘመቻ መስሎ ነው የሚታየኝ፡፡ አዲስ አበባን ሊበላት ያሰፈሠፈ ሃይል አድርጎ የሚስሉ አካላት እድል የሠጠ አካሄድ ነው፡፡
በተለይ የአዲስ አበባ ጉዳይ በምን መልኩ ነው ሊስተናገድ የሚገባው ይላሉ? መፍትሄው ምንድን ነው?
 አንደኛ ከታሪክ፣ ሁለተኛ አዲስ አበባ ለወደፊቱም እድገቷ፤ ዛሬ ያለችበት ሁኔታ ብቻ ሳይሆን የዛሬ 30፣50 ዓመት የምትደርስበት እድገቷ ታይቶ፣ የአዲስ አበባና  በዙሪያዋ ያለው አካል ተስማምቶ እንዲኖር ማድረግ የሚያስችል ሁኔታ ነው መፈጠር ያለበት። በመጀመሪያ ደረጃ አዲስ አበባ የሁሉም ነች የሚለው እንዲሁ ሲታይ ትክክል ነው። ነገር ግን አዲስ አበባ  በውስጧ የሚኖር ህዝብ አለ፡፡ ይሄ ህዝብ ነው የምክር  ቤት አባላትን የመረጠው፡፡ እዚህ ውስጥ የተለያዩ ኢትዮጵያውያን አሉ፡፡ ከዚህ አንጻር የሁሉም ኢትዮጵያውያን ነች የሚለው፣ በዚህ ማዕቀፍ ውስጥ የሚታይ ይመስለኛል። በሌላ በኩል፤ አዲስ አበባ መደራጀት ካለባት እንደ አንድ ራሷን የቻለች ክልል ነው መደራጅት አለባት ብዬ አምናለሁ፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ተወካይ ያላት፡፡ ምክንያቱም በኢትዮጵያ ህገመንግስት መሰረት፣ መሬት የህዝብና የመንግስት ነው እንጂ የአንድ ክልል የአንድ ሰው ወይም የአንድ ቡድን አይደለም፡፡ ስለዚህ በህገመንግስቱ መሰረት፣ መደራጀት ካለባት፣ ከዚህ በፊት በዙሪያዋ ካሉትና  ዛሬ የኦሮሚያ ልዩ ዞን የሚባሉት (ቀድሞ መናገሻ አውራጃ የሚባሉት ናቸው) ተጠቃለው፣ አንድ ራሷን የቻለች ክልል ነው መሆን ያለባት፡፡ አዲስ አበባ ቀድሞ ከኢትዮጵያ ዋና  ከተማነቷ ባሻገር የሸዋ ክፍለ ሃገርም የመናገሻ አውራጃም ዋና ከተማ ነበረች፡፡ ለምሳሌ የመናገሻ አውራጃ የነበሩት፡- ሆለታ፣ ሠንዳፋ፣ ጫንጮ፣ አቃቂ፣ ሠበታ፣  የመሳሰሉትን አቅፎ የያዘ ነበር፡፡ ይሄ የቀድሞ መናገሻ አውራጃ፣ በቀጣይ የአዲስ አበባ አካል ግዛት ሆኖ መያዝ ነው ያለበት፡፡ አዲስ አበባ ያላትን ቀድሞም ቢሆን አቅፈው የያዟትን ዛሬ የኦሮሚያ ልዩ ዞን የሚባሉትን ያካተተች ክልል መሆን አለባት፡፡ ይህም ይሳካ ዘንድ አዲስ አበባ እና የልዩ ዞኑ ህዝብ በግልጽ ተወያይቶ በውሳኔው መሳተፍ አለበት፡፡ በተጨማሪም በህዝብ በቀጥታ የተመረጡ ከንቲባና ምክር ቤት ሊኖራት ይገባል፡፡ ለምሳሌ  ዩናይትድ ኪንግደም፣ (በእንግሊዝ) በፓርላማው  ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይመረጣል። ዋና ከተማዋ ለንደን ግን ከንቲባዋን ራሷ በቀጥታ በነዋሪዎቿ ነው የምትመርጠው። ይሄን ተሞክሮ ወደኛ ሃገር ማምጣት አለብን። አዲስ አበባ ልዩ ከተማ ናት፤ ስለዚህ ስልጣኑ ጎልበት ያለ ከንቲባ ያስፈልጋታል፡፡ ሰዎች በደንብ ሊረዱት የሚገባው ነገር  እነ ለገዳዲ፣ ገፈርሳ፣ አባ ሳሙኤልና የመሳሰሉት ከአዲስ አበባ ጋር የሚጠቃቀሙ አካባቢዎች፣ ቀድሞ ከአዲስ አበባ ጋር አብረው የመናገሻ አውራጃ ተብለው ነው የሚታወቁት፡፡ አዲስ አበባ ከተማዋ በኦሮሞ ህዝብ መሃል ነው ያለችው፤ የአሁኑ የኦሮሚያ ክልል አወቃቀር ኦሮሞንና ኦሮሞነትን አስከብሯል የሚል እምነት የለኝም፡፡ አዲስ አበባም  በውስጧ ባሉ የኦሮሞ ተወላጆች ብቻ ሳይሆን በሠፈር ስሞችም ሳይቀር የኦሮሞ ህዝብ አሻራዎች አሉባት፤ የምታቅፋቸው ህዝቦች ስለሆኑ  የራሷ እንደሆኑ መታሰብ አለበት፡፡ ልክ ከኦሮሚያ ልዩ ዞን መሬት እንደነጠቀች፣  ተደርጎ መታሰብ የለበትም፡፡
በዙሪያዋ ያለው የኦሮሞ ህዝብ አዲስ አበባን በልዩ ልዩ ግብአቶች እየጠቀመ ያለ ቢሆንም ለዘመናት የበይ ተመልካች ሆኖ ኖሯል፣ አሁን ይሄ ይበቃል። አዲስ አበባ አቅፎ የያዛትን ህዝብ እንደባዕድ (ቱርክና ግሪክ…) የምትታይበት አይን ሊኖር አይገባም እላለሁ፡፡
በየአካባቢው የሚነሱ ግጭቶች ወደ ክልልነት ጥያቄ ቢያመሩ ጥያቁዎቹ በምን መልኩ ነው መፍትሄ ሊያገኙ የሚችሉት?
እዚህ ላይ መታሰብ ያለበት ህዝቦች ራሳቸውን የማስተዳደር፣ ቋንቋና ባህላቸውን የማበልፀግ መብቶቻቸው ሳይሸራረፉ ሊከበሩ ይገባል፡፡ ነገር ግን ቋንቋና ዘርን መሰረት ያደረገ አከላለል በፍፁም ጠቃሚ አይመስለኝም። የአንድ ህዝብ ቋንቋ እንዲከበር የግድ በአንድ ቋት ተሰብስቦ መደራጀት ያለበት አይመስለኝም። ከዚህ አንጻር በደቡብ ክልል መጠነኛ ክላስተር ያላቸው ክልሎች ቢቋቋሙ ተገቢ ይመስለኛል። የስልጣንና የሃብት ክፍፍሉ ተመጣጣኝ ሆኖ የአማራ ክልልን በተመለከተ፣ “የአማራ ክልል” ማለቱ በራሱ በውስጡ ያሉ ሌሎች ህዝቦች ብሔርተኝነትን በጣም ነው ከፍ ያደረገው፡፡ ራሱን የአማራ ብሔርተኝነትንም እንደዛው፡፡ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ እየተባለ ብሔርተኝነትን ከፍ ባደረገ ቁጥር ውስጥም ውጪም ላሉት ስጋት ነው የሚሆነው፡፡ ይሄ ደግሞ የአማራን ህዝብ አይጠቅመውም፤ አልጠቀመውምም፡፡ አሁንም በየሄደበት ቦታ ሰብአዊ ክብሩ ተረግጦ የሚሳደድ ህዝብ ሆኗል፤ ይሄ ያሳዝናል፡፡
የአማራ ህዝብ እኮ ቋንቋና ባህሉን ማንነቱን ጭምር ለኢትዮጵያ ሰጥቶ በኢትዮጵያዊነቱ ኮርቶ የኖረ ህዝብ ነው። በዚያው ልክ በየአካባቢው የራሱን ማንነት ፈጥሮ፣ ያንን ማንነቱንም በፍቅር ሲንከባከበው የኖረ ህዝብ ነው፡፡ ዛሬ ቅማንትን  ሄደህ “ጎንደሬ ነህ ወይ?” ብለህ ብትጠይቀው፣ አይደለሁም አይልህም፤ ነገር ግን አማራ ነህ ወይ ብለህ ብትጠይቀው፣ አይደለሁም ይልሃል፡፡ ስለዚህ ለምንድን ነው ቅማንትንና ወልቃይትን ይዞ በጌምድር በመባል ክልል የማይሆነው? ጎጃም ቢሆን አዊንና መተከልን ይዞ ራሱን ችሎ ጎጃሜ ስነልቦናውን አጎልብቶ፣ ክልል የማይሆነው ለምንድን ነው? የወሎ ህዝብ እጅግ የተደበላለቀ ነገር ግን የራሱ ውበትና ማንነት መገለጫዎች ያሉት ህዝብ ነው ለምንድን ነው  ራሱን ችሎ ክልል የማይሆነው? በዚህ አወቃቀር አማራ አማራነቱን ያጣል ብለው የሚሰጉ ካሉ ባህር ዳር ላይ ሁሉንም ክልሎች ያቀፈ የጋራ ምክር ቤት ሊኖራቸው ይችላል። በዚህ ምክር ቤት አማካኝነትም ባህላቸውን፣ ቋንቋቸውን፣ ልማታቸውን የሚያሳልጥ፤ ከየትም አቅጣጫ የመጣን ጠላት በጋራ መከላከል የሚያስችል ወንጀልን የሚከላከሉበት የጋራ ሠላምና ፀጥታቸውን የሚያስከብሩበትም ምክር ቤት ሆኖ ሊያገለግል ይችላል፡፡
ሸዋን በተመለከተ ደግሞ በውስጡ ብዙ ማንቶች ያሉት ግን የሸዋነት መገለጫ ያለው ነው፤ ለምን ራሱን የቻለ ክልል አይሆንም?
ቀደም ሲል የሸዋ ክፍለ ሃገር በምስራቅ፣ በምዕራብ፣ በደቡብ እና በሰሜን ሸዋ ተከፋፍሎ የተደራጀ ነበር፡፡ እዚህ ውስጥ ኦሮሞ፣ አማራው፣ ጉራጌው፣ ስልጤው፣ ከንባታውን፣ ሀድያው፣ አላባው አሉ፡፡ እነዚህ በአንድ ሰፊ ክልል ተዋቅረው አዲስ አበባ ማዕከላቸው ብትሆን ችግሩ ምንድን ነው?  ኦሮሞ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ በማንም የማይተካ ሚና ያለው ህዝብ ነው። የኦሮሞን ህዝብ ማንነትና ልዩ ልዩ መብቶች መከበር የሚያረጋግጥ አደረጃጀት ያስፈልገዋል። ኦሮሞ በገዳ ስርዓቱ አማካኝነት ራሱን በየአካባቢው አደራጅቶ እያስተዳደረ ለበርካታ ምዕተ ዓመታት ኖሯል። እነዚህ አደረጃጀቶች ዛሬም ቢሆን ዋጋ አላቸው። በኔ አመለካከት ኦሮሚያ ቢያንስ በአምስት ክልሎች ብትደራጅ ህዝቡ የየራሱን አካባቢ ለማልማትና ቀልጣፋና ብቃት ያለው አስተዳደር እንዲያገኝ  ያስችላል ብዬ አስባለሁ። በዚህ መሰረት፡- 1. አርሲ እና ባሌ፣ 2. ሃረርጌ ፣ 3. ወለጋ፣ 4.  ጅማ እና ኢሉአባቦር፣ 5. ቦረና ጉጂ፣ ቡርጂ የሚባሉ ክልሎች ቢፈጠሩ ጠቃሚ ይሆናሉ እላለሁ። እነዚህ ክልሎች በገዳ ስርዓት አማካይነት በመተሳሰር የኦሮሞን ማንነት መጠበቅ ስላለባቸው ክልል አቀፍ ሆኑ የልማትና ሌሎች ተግባራትም መከናወን ስላለባቸው አዳማ ላይ የሚሰየም የጋራ የአባገዳዎችና የየክልሉ ፕሬዚዳንቶች የሚሳተፉበት ምክር ቤት ቢኖር ጠቃሚ  ይሆናል። በነገራችን ላይ የኦሮሞን ህዝብ ህውሃት ለፖለቲካው ማሰንበቻ ተጠቅሞበታል። ሰፊ ክልል ሰራሁልህ ብሎ ግዙፍ አድርጎ ከልሎ አዲስ አበባን እንደሚውጣት አውሬ አድርጎ ነው ያቀረበልን። ይሄ ስዕል በፈጠረው ስሜት በተነሳሱ አካላት ኦሮሞን ለማስጠላት የሄዱበት ርቀት ቀላል አይደለም።
ነገሩን ለማጠቃለል ያህል የፌደራል አወቃቀር ስርዓቱን በተመለከተ ወደፊት የማደርገው ብሔራዊ ምክክር የሚያስቀምጣቸውና ህዝብ የደገፋቸው አካሄዶች ሊኖሩ እንደሚችሉ ታሳቢ እየተደረገ በኔ እምነት ከላይ የቀረበው የአማራና ኦሮሚያ ክልሎች አወቃቀር እና የአዲስ አበባ ጉዳይ ባቀረብኩት ሃሳብ ላይ ተመስርቶ ቢሰራ ለዲሞክራሲያዊ ስርዓት መጎልበት ሆነ ለሃገሪቱ ብልፅግና እንቅፋት የሚሆን አይመስለኝም።


Read 1211 times