Monday, 22 August 2022 00:00

ከዓመት ዓመት ያድርሰን እንበል ሰዎች።

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(0 votes)

• ዓመት አልፎ ሌላ ዞሮ ሲመጣ፣ “እዚያውና ያው” ሊሆን ይችላል - ኑሮ።
      • ይባስ ብሎም እየዞረ እየተሽከረከረ ቁልቁል የሚወርድ ይኖራል- በዋጋ ንረት እና የኑሮ ውድነት።
      • “30 ጥጆች አስረው” እንደሚባለው፤ 30% የዋጋ ንረት ሳይሆን፣… የኑሮ እድሳትና ሦስት እጥፍ የገቢ እድገት ያድርግላችሁ። ያድርግልን።
      • ዓመታዊው ዑደት፣ የነውጥ እና የጦርነት አዙሪት አይሁንብን። ሕይወታችን፣ እንደ ሕዳሴ ግድብ በየዓመቱ ከፍታው እየጨመረ ውኃው              እየበዛና እየሰፋ የሚሄድበት የተባረከ የዓመት ዙር (ዐውደ ዓመት) እንዲሆንልን እናድርገው።
              ዮሃንስ ሰ

       ሄዶ የማይቀር፣ ዞሮ የሚመጣ፣… ርቆ ቢጓዝም፣ መልሶ “ከመነሻ ላይ የሚያደርስ” ምህዋር እና ሂደት ነው ዐውደ ዓመት።
ባናስብበት እንኳ፣ ችላ እንድንለው አይፈቅድልንም። ዝናብና ጎርፉን ተከትሎ፣ ልምላሜና አበባ ሲመጣ እያየን፣ እንዴት ደንታ ቢስ እንሆናለን? ትንሽ ቆይቶም ውርጩና ነፋሱ፣… ከዚያም የበጋው ፀሐይና ሙቀት፣… እንደገና ክረምትና ልምላሜ፣ አበባና አዝመራ ተመልሶ ሲመጣስ፣… “አይሞቀኝ፣ አይበርደኝ!” ማለት የሚችል ማን ነው?
“ከመነሻ ላይ የሚያደርስ” ዑደት መሆኑ ብቻ አይደለም ጉልበቱ። በእርግጥ፣ መነሻውንና መድረሻውን ነጣጥሎ ከማሳየት ይልቅ አንድ ላይ የሚዋሕድ ይመስላል። ምሕዋር እና ዑደት ስንል፤… በክብ መስመር ዙሪያውን የመሽከርከር ትርጉም ነው የሚመጣልን።
ዑደቱ እንቅስቀሴው ነው። ዐውዱ ደግሞ፣ ቦታው ወይም ሁኔታው ነው። ሑረቱ ድርጊቱ ነው። ምሕዋሩ ደግሞ መስመሩ፣ አቅጣጫው፣ ቦታው።
ነገር ግን፣ ምሕዋሩና ዓውዱ የግድ ከሽክርክሪት ጋር ብቻ የተገናኘ ላይሆን ይችላል።
ምሕዋር የግድ ክብ መሆን የለበትም። የመሄጃ ጎዳና ወይም መስመርን የሚመለክት ቃል ነው። ሖረ ማለት ተጓዘ፣ ሄደ፣ ነጎደ እንደማለት አይደል?
ነጎደ ድርጊቱ ነው። “መንገድ” ወይም ጎዳና፣ ድርጊቱ የሚከናወንበት ስፍራ ደግሞ ነው። ድርጊቱ ደግሞ፤ ሖረ (ሐወረ) ነው። መስመሩ ወይም አቅጣጫው፤ ምሕዋር ነው።
ዑደት ግን፣ ጉዞንና ሂደትንም የሚያሳይ ቢሆንም፣… “ደርሶ መመለስን”፣ “ዞሮ መምጣትን” የሚገልጽ ነው።
ሁለቱንም እንፈልጋቸዋልን - ዑደቱንና ሑረቱን። ዙረቱንና ሂደቱን።
ዑደት ለብቻው፣ ዜማ እንደሌለው የከበሮ ኳኳታ ነው። “ያለ ዜማ ጅረት”፣ የጭብጨባ ድግግሞሽ ብቻ፣ ያሰለቻል፤ ያደነዝዛል። አየር ላይ እንደተንሳፈፈ የመኪና ጎማ ነው። ቢሽከረከርም አይገሰግስም። ዑደት ብቻ ከሆነ፣ አዙሪት ብቻ ይሆንብናል።
“ሄደ ነጎደ” ብቻ ከሆነ ደግሞ፣ የሚጨበጥ ነገር ያሳጣል። ጭው ያለ በረሃ ላይ እንደመንከራተት ወይም፤ ለምልክት ያህል ቅንጣት መሬት የማይታይበት ውቅያኖስ ላይ እንደመቅዘፍ ይሆንብናል።
ተፈጥሮና ሕይወት ግን፣ የዑደት እና የሂደት ውሕደት ናቸው። ሂደቱ፣ የድንዛዜ ወይም የማሽቆልቆል ሳይሆን የእድገት እንዲሆንልን ማድረግ እንችላለን። እያንዳንዱ ዓመት፣ “የእድገት ዙር መለኪያ”፣ እያንዳንዱ ዑደት እንደ መመተሪያ አንጓ ይሆንልናል። አንጓን ወይም ዑደቱን እየቆጠርን እንጓዛለን።
ያኔ ሕይወት ይቃናል። እንደ መኪና ጎማውን እያሽከረከረ ወደ ፊት ይገሰግሳል፣  እንደ አውሮፕላን “ሞተሩን” እያሽከረከረ ከፍታ ይመጥቃል።
“ነገ ሌላ ቀን ነው” የሚለውን የተለመደ አባባል ተመልከቱ።
በአንድ በኩል፤ ነገ፣… ያው “ቀን” ነው ማለታችን ነው። ነገ፣ “ሌላ ቀን” ቢሆንም፤ ከሌሎቹ ቀናት የተለየ አይደለም። ተመሳሳይ ነው። ይህን ለመግለፅ፣ “ነገም ሌላ ቀን ነው” ብለን መናገር እንችላለን። ዑደት ነው።
በሌላ በኩል ደግሞ፤ ነገ ከዛሬና ከትናንት ጋር የሚመሳሰል ቀን ቢሆንም፤ “ያው” አይደለም። “ሌላ” ነው። በድጋሚ የመጣ ቀን አይደለም። ራሱን የቻለ ልዩ ቀን ነው ማለት አንችላለን።
በእርግጥ፣ ዑደት መሆኑን አንዘነጋም። ከሌሎች ቀናት ጋር ተመሳሳይ መሆኑን አንረሳም። ነገር ግን፣ “ሂደት” መሆኑን አጉልተን ለማየት ስንፈልግ፤ “ሌላ-ነቱን” የሚስጮህ አባባል እንጠቀማን። “ነገማ ሌላ ቀን ነው” እንላለን። “ሌላ” የሚለውን ቃል አድምቀን በድርብ እንጽፋለን።
ሂደት መሆኑን ሳንዘነጋ፣ “ዑደት-ነቱን” እና ተመሳሳይነቱን ለማጉላት ደግሞ፤ “ነገም ሌላ ቀን ነው” ብለን እንናገራለን። ታዲያ፣ የዛሬና የነገ ተመሳሳይነትን ብንመለከትም፣… እያንዳንዱ ቀን ልዩ ቀን መሆኑን ለመካድ አይደለም። “ተመሳሳይ” ለመሆን፣ ራሳቸውን የቻሉ የተለያዩ ነገሮች፣ የተለያዩ ሁኔታዎች፣ አኳሃኖች ወይም ክስተቶች መኖር አለባቸው።
የቀናት ተመሳሳይነትን አድምቀን ለማሳየት ወይም ዑደትነትን ለማጉላት ስንፈልግ፤... “ሌላ” የሚለውን ቃል ሳንስተው፣ “ቀን” የሚለው ቃል ላይ እናሰምርበታለን።
ይሄ፣ “ፍሬ ሃሳብ”ን እንደመገንዘብ ነው። ሁሉንም ቀናት እንደ አንድ አዋህደን እንደማሰብ ነው።
የእያንዳንዱን ቀን “ሌላነት” ላይ ስናተኩር ድግሞ፣ እንደመቁጠር ነው።
“መጪው ዓመት” ወይም “አዲስ ዓመት” ብለን ስንናገርም፣ በአንድ ጊዜ ሁለቱንም ገጽታዎች ያውጃል። መጪው ዓመት፣ ከዘንድሮው ዓመትና ከአምና ጋር ተመሳሳይ ነው። “ዓመት” የተሰኘው ለምን ሆነና! ዑደት ነው። አንድ ዙር ነው።
ግን ራሱን የቻለ፣ ካሁን በፊት ያልነበረና ያልተከሰተ አዲስ ዙር ነው። አዲስ ዓመት ነው።
እንዲህ ሲናገሩት ቀላል ይመስላል። ግን አይደለም።
የዓመት ዑደት (ዓውደ ዓመት) እንደ እለታዊ ዑደት፣ በቀንና በሌሊት ፈረቃዎች ተከፍሎ በቀላሉ የምናየው አይደለም።
ነጋ፤ መሸ፤… አንድ ቀን። ነጋ፤ መሸ፤… ሌላ አንድ ቀን። ይሄ አይከብድም። የዓመት ዑደት ግን፣ አዋቂዎችን፣ ተመራማሪዎችን ጥበበኞችን ይፈልጋል። ለዚያውም፣ ከዘመን ዘመን እየተደማመረ እየተጣራ እየበለጸገ የሚጓዝ እውቀትና ጥበብ ሲኖር ነው፤ የዓመት ዑደትን በቅጡ አበጥሮ የመገንዘብ ብቃት የሚፈጠረው። ጥበበኞች ሲያስተምሩን ነው፤ የዓውደ ዓመት ምንነትን የማወቅ እድል የምናገኘው።
እውቀትና ጥበብ፣ ትምህርትና ልምድ፣… የዑደት ባህርይ አላቸው። የእውቀትና የትምህርት ጉዞዎች፣ ሁሉም ሰው ላይ ተመሳሳይ ናቸው። ትምህርት፣ “ከባዶ” ነው የሚጀመረው። እናትና አባት ከደረሱበት የትምህርት ደረጃ ላይ አይደለም የልጆች ትምህርት የሚጀምረው። የዱላ ቅብብል አይደለም። እውቀት፣ ሁልጊዜ፣ ከጥቂት ወደ ብዙ፣ ከቀላል ወደ ከባድ ነው።
ሁሉም ሰው፣ “ሀ” ብሎ ይጀምራል። የክፍል ደረጃውም እንዲሁ። በጥቅሉ ሲታይ፤ ትምህርቱን ከቅኔ ወይ ከፒኤችዲ የሚጀምር ሰው የለም።
ደግነቱ ዑደቱን የጥበብ፣ የእድገት፣ የስልጣኔ፣ የከፍታ ዑደት ልናደርገው እንችላለን። ነባር እውቀትን ከቀላል ወደ ከባድ የቻልነውን ያህል እንማራለን፤ እንጓዛለን። ከዚያም ባሻገር ወደ አዲስ የእውቀት ግኝት የሚራመዱ ይኖራሉ። ይሄው ነው ዑደቱ።
ነባሩን እውቀት ይማራሉ። ለአዲስ የእውቀት ግኝትም መመራመር ይችላሉ። ከዚህ ዑደት ውጭ፣ ሌላ ስኬታማ የስልጣኔ ጉዞ የለም (ወደ ኋላ ቀርነት ለመመለስና ለማሽቆልቆል ካልሆነ በቀር)።
የእውቀት ግንባታ፣ “ዑደት ነው” ስለተባለ ግን፤ ሽክርክሪነት ብቻ ነው ማለት አይደለም።
ነባር እውቀትን ሳይማሩ ሳይገነዘቡ መቅረት አለ። ጭራሽ ነባሩን እውቀት ማጥላላትና ማጠልሸት፣ ይባስ ብሎም መፃህፍት የማቀጣጠል ዘመቻም በየዘመኑ ታይቷል። ይሄ የቁልቁለት ጉዞ እንጂ፣ “የዘወትር ዑደት” ብቻ አይደለም።
በሌላ በኩል ደግሞ፤ ነባሩን እውቀት ተምሮ ስህተቶችን አስተካክሎ፤ አጠራጣሪ ጥያቄዎችን አጣርቶ፣ እውነታውን አረጋግጦ መራመድም ይቻላል። ምን ይሄ ብቻ። እስከ ዛሬ ያልታወቀ ነገር የማወቅ እድልም ይኖራል። አዲስ ግንባታ ማለት ነው።
አዲስ ነገር የማወቅ እድል ግን፣ ነባር እውቀትን ለተማሩ፣ ለትጉሃን፣ ለአስተዋዮች ብቻ የሚታይ እድል ነው።
አዲስ የእውቀት ግኝት፣ የቀድሞ ዘመን እውቀትን የመከለስ ዑደት ብቻ አይደለም። የፈር ቀዳጅነት ጉዞም ነው።
በነባር ምሕዋር ላይ መጓዝ ብቻ ሳይሆን፣ ቀድሞ ያልነበረ መንገድ መጥረግም ነው።
ነባር የብርሃንና የጨለማ ዑደት ብቻ አይደለም።
በአዲስ ደማቅ ብርሃን የቀድሞውን ጨለማ የመግፈፍ፤ አዲስ ፋና የመለኮስ ጀግንነት ነው።
የዘወትር የማብሪያና የማጥፊያ ዑደት አይደለም።
አዲስ ፀሐይ እንደ መፍጠር ነው።
ዘርቶ የማጨድ ነባር የልማድ ዑደት ብቻ አይደለም።
አዲስ የኤሌክትሪክ ኃይልና ብርሃን እያስፋፉ በየዓመቱ መሰልጠንም አለ።
በአጭሩ ዓመታዊውን ዑደት፣ የእድገት ዑደት ልናረገው እንችላለን።

Read 2296 times