Tuesday, 23 August 2022 00:00

የዓመታት ስያሜና አቆጣጠር፣ “በግንባታ” ወይስ “በጦርነት”?

Written by 
Rate this item
(2 votes)

• በባቢሎን፣… የዓመታት አሰያየም፣ ከግንባታ ጋር የተዛመደ ነበር። “የከተማዋ ግንብ በታነፀ በሁለተኛ ዓመት”፣ በሦስተኛ ዓመት ብለው
    ዓመታትን ይሠይማሉ፤ ይቆጥራሉ። የግድብና የመስኖ ግንባታዎችም፣ ለሥያሜ ያገለግለሉ።
   • ነነዌ ግን፣ በየዓመቱ ለጦርነት የመዝመት ልማድ ስለነበረ፣… “1ኛው የዘመቻ ዓመት”፣… “2ኛው የዘመቻ ዓመት”፣ “3ተኛው የዘመቻ     ዓመት”፣… እያሉ ዓመታትን ይቆጥራሉ፤ ይሰይማሉ። ከዚህስ ይሰውረን። የግንባታ ዑደት ይሻላል።

         ቀንና ማታን የሚያፈራቅ እለታዊ ዑደት ላይ እንጀምር።
እያንዳንዱ እለት፣ “ራሱን የቻለ እለት” መሆኑን ለመግለፅ፣… እሁድ እለት፣ ሰኞ እለት…እያልን እንናገራለን።
ግን፣ ለእያንዳንዱ እለት የግል መጠሪያ ስም እያወጣን፣ የት እንደርሳለን?
እሑድ፤ “አንድ” እንደማለት አይደል? አሐዱ ብሎ ይጀምራል። ሰኞ፣… ሁለት እንደማለት ነው። የሰኞ ማግስት ደግሞ አለ። ማክሰኞ ብለውታል። ሠሉስ ተብሎም ይታወቃል። ሶስተኛ ቀን ነው።
ረቡዕ እና ሐሙስ፣ አራተኛ እና አምስተኛ ቀናት ናቸው።
አርብ፣ መገባደጃ እንደማለት ነው። ምዕራብ እንል የለ!
ቅዳሜ እለት፣ ድሮ ድሮ ሰንበት ተብሎ ይታወቅ ነበር። ሰባተኛ ቀን ስለሆነ።
በዚሁ መንገድ፣ ስምንተኛውን ቀን “ሰሙን”፣ ከዚያም “ዘጡኝ”፣ “አሱር”፣ … እያለን ብንሰይማቸውስ? 11ኛውን ቀን “አሱር እሁድ”፣ ከዚያም “አሱር ሰኞ… እያልን መቀጠል አያቅተንም። ግን፣ እንዲህ ቀናትን በቅደም ተከተል እየሰየምንና እየቆጠርን እስከየት እንዘልቃለን? ሂደት ወይም ጉዞ ነው።
ግን “ጉዞ” ብቻውን፣ ከተፈጥሮ ጋ ሙሉ ለሙሉ አይገጥምም። የዑደት ባህርይም ያስፈልጋል። ዑደት የሌለው ጉዞ ለአእምሮም ያስቸግራል። ምዕራፍ እንደሌለው መጽሐፍ ነው።
በቅደም ተከተል ብቻ ሳይሆን፣ ነገሮችን በረድፍ መልክ ለማስያዝ፣ በክፍል በፈርጅ ጠቅለል ሰብሰብ ለማድረግ የሚችል ዑደት ያስፈልጋል።
ለእያንዳንዱ ቀን፣… አንድ፣ ሁለት፣ ሦስት እያልን እስከ ሠላሳኛ ቀን ድረስ በቁጥር እንሰይማቸዋለን፤ እንቆጠራቸዋል። ከዚያ በኋላ ግን፣ እንደገና አንድ ብለን ዑደቱን እንጀምራለን። ሠላሳዎቹን ቀናት አንድ ላይ የሚያጠቃልል፣ “ወር” የተሰኘ የዑደት ስም እንጠቀማለን።
የወር ዑደትም ግን መብዛት የለበትም። ከመስከረም ጀምረን ነሀሴ ድረስ እንሄዳለን። ወይም 1ኛ ወር፣ 2ኛ ወር ብለን መቁጠር እንችላለን። ነገር ግን ይሄም ከልክ ማለፍ የለበትም። ጠቅለል የሚያደርግ ሰፊ ዑደት ያስፈልጋል። እንደገና 1ኛ ወር ብለን የምንጀምርበት ነው ዓመታው ዑደት። ነሐሴ ብለን መስከረም እንላለን።
በነገራችን ላይ፣ የኢትዮጵያ የወር እና የዓመት አቆጣጠር በተወሰነ ደረጃ ከጥንታዊ የግብጽ አቆጣጠርና አሰያየም ጋር ይዛመዳል።
በጥንቱ የግብጽ አቆጠጠር ላይ፣ የአዲስ ዓመት በዓልን ተከትሎ “መስከር” የተሰኘ ትልቅ “የፌሽታ” በዓል ነበራቸው። በእርግጥ፣ የመስከረም ወር ስያሜ ከክረምት ጋር ቢቀረረብም፣ ከጥንታዊው በዓል ጋር የተዛመደም ሊሆን ይችላል። በተለያዩ የደቡብ አካባቢዎችም “መስጋር”፤ “መስቃሮ” የተሰኙ ትልልቅ የአዲስ ዓመት በዓሎች አሉ።
መስከረም የተሰኘው ቃል፣ የወር ስያሜ ከመሆኑ በፊት፣ የበዓል መጠሪያ የነበረ ስም ይሆን? ለማንኛውም፣ የቁጥር ወይም ሌላ የመጠሪያ ቃላት እየተጠቅመን፣ ከእለታዊና ከወርሃዊ ዑደት ወደ ዓመታዊ ዑደት ተሸጋግረናል።
ከዚህ በኋስ ምን እናድርግ? ለእለታትና ለወራት እንዳደረግነው፤ ለዓመታትም መጠሪያ ስም ማውጣት አለብን? ቁጥሮችንስ እንጠቀማን? ታሪኩ እንደዚያ ነው።
የአዋቂዎችና የጥበበኞች አቆጣጠርን ማየት እንችላለን። “አጼ እገሌ በነገሱ በሁለተኛው ዓመት”፣… በሶስተኛው ዓመት እያሉ ጽፈዋል።
ከኃይማኖታዊ መጻሕፍት፣ ከአዳምና ከሔዋን ትረካ ተነስተው፣ ዓመታትን ቆጥረው፣ “7 ሺ ምናምን ዓመት” ብለውም ዘግበዋል። ዓመተ ዓለም ብለው ይሰይሙታል።
የኢየሱስን ልደት እንደ መልሕቅ በመጠቀም፣ “በ2 ሺ ምናምን ዓመት” ብለን እንጽፋለን። ዓመተ ምህረት የሚል ነው ሥያሜው።
ከዚህ ጎን ለጎን፣ “የፓርላማ የአራተኛው ዓመት፣ ሃያኛ ስብሰባ” የሚል ዘገባ ሰምታችሁ ይሆናል። “በነገሠ በአራተኛው ዓመት” ከተሰኘው የድሮ አሰያየም ጋር ይመሳሰላል።
“ከታህሳስ ግርግር በአስረኛው ዓመት” የሚል የድሮ ጽሑፍ ካጋጠማችሁ፤ 1963 ዓ.ም ማለት ነው።
“የጣሊያን ወረራ የመጣ ጊዜ”፣ “የነጻነት አርበኞች ድል ያገኙ ጊዜ”፣ … እንዲህ የሚሉ የዓመት ስያሜዎችም ጥቅም ላይ ውለዋል። ግን ከቁጥር ጋር ነው። “ካሌብ በነገሠ በ5ኛው ዓመት፣ በሶስተኛው ወር፣ በ20ኛው ቀን”…. ተብሎ ይጻፋል።
“የህዳሴ ግድብ ግንባታ አስረኛ ዓመት”፣… “ሦስተኛው ዙር የውኃ ሙሌት”፣… ብሎ መናገርም ይቻላል። የዑደት ስያሜዎች ናቸው።
የጥንት ዘመን አዋቂዎችም፣ ተመሳሳይ ሥያሜና አቆጣጠር ይጠቀሙ እንደነበር ታሪክ ይነግረናል። ያው፣ እዚህ ላይም ቀዳሚዎቹ የሥልጣኔ ፈር ቀዳጆች፣ የመሰፓታሚያ ከተሞች ናቸው - እነ ባቢሎን እነ ነነዌ።
“እገሌ በነገሠ 1ኛ ዓመት”፣ በ2ኛ ዓመት እያሉ ይቆጥራሉ።
ነገር ግን፣ በባቢሎን ዘንድ እጅግ የተለመደው የዓመት አሰያየም፣ ከግንባታ ጋር የተዛመደ ነበር። “የከተማዋ ግንብ በታነፀ በሁለተኛ ዓመት”፣ በሦስተኛ ዓመት ብለው ዓመታትን ይሠይማሉ፤ ይቆጥራሉ። የግድብና የመስኖ ግንባታዎችም፣ ለሥያሜ ያገለግለሉ።
በነነዌም ተመሳሳይ ልማድ ነበረ። ነገር ግን፣ የጦርነት ዘመቻዎችን ነው የሚያዘወትሩት። በየዓመቱ ለጦርነት መዝመት እንደ ልማድ አድርገውት ነበር።
እናም “አንደኛው የዘመቻ ዓመት”፣… “ሁለተኛው የዘመቻ ዓመት”፣ “ሶስተኛው የዘመቻ ዓመት”፣… እያሉ ዓመታትን ይቆጥራሉ፤ ይሰይማሉ።
ከዚህስ ይሰውረን። የግንባታ ዑደት ይሻላል።

Read 7569 times