Sunday, 28 August 2022 00:00

በትግራይ ሴቶችና ልጃገረዶች ህይወታቸውን ለማቆየት ገላቸውን ለመሸጥ ተገድደዋል - The Gurdian

Written by  ትዕግስቱ በለጠ
Rate this item
(0 votes)

 በሰብአዊ ቀውስ ውስጥ በሚገኘው የትግራይ ክልል፣ ባለሥልጣናት፣ ሚሊዮኖች እጅጉን የሚያስፈልጋቸውን ከወዳጅ ዘመድ የሚላክ ገንዘብ፣ በስልታዊ መንገድ እያገዱና እየወረሱ በመሆኑ ሳቢያ፣ ረሀብ፣ በርካቶችን  አስከፊ ወደ ሆነ እርምጃ እየገፋቸው ነው፡፡
ክልሉ ከባንክ አገልግሎቶችና ከሁሉም ዓይነት ግንኙነቶች፣ ካለፈው ዓመት ጀምሮ በፌደራሉ መንግስት እንዲነጠል የተደረገ ሲሆን፣ በዚህም ሳቢያ 6 ሚሊዮን ያህል ህዝብ፣ የራሱን ገንዘብ የማግኘት መብቱን ተነፍጓል፡፡
እርዳታና የባንክ አገልግሎት በሌሉበት ሁኔታ፣ ሰዎች ህይወታቸውን ለማቆየት በአብዛኛው የሚተማመኑት ቤተሰብና ወዳጆች ከባህር ማዶ በሚልኩላቸው ገንዘብ ነበር፤ ነገር ግን ከውጭ በሚላክ ገንዘብ ላይ የትግራይ ባለስልጣናት ገደቦችን ከመጣላቸውም ባሻገር፣ በየፍተሻ ጣቢያዎቹ በህገወጥ የገንዘብ አስተላላፊዎች ላይ የሚወሰዱ እርምጃዎች እየተጠናከሩ መጥተዋል፡፡
ከትግራይ የሚወጡ ሪፖርቶች፣ በርካታ ሴቶችና ልጃገረዶች ገላቸውን ሸጠው ለማደር እየተገደዱ እንደሚገኙ ሲገልጹ፤ ሌሎች ደግሞ በክልሉ ራሳቸውን የሚያጠፉ ሰዎች ቁጥር መጨመሩን  ይጠቁማሉ፡፡
የትግራይ አማፂ ሃይሎች ለ8 ወራት ከፌደራል መንግስት ጋር ከተዋጉ በኋላ የዛሬ ዓመት መልሰው ሥልጣን ሲቆጣጠሩ፣ ሔዋን፣ ህይወት ሊሻሻል ይችላል የሚል ግምት ነበራት። ጥሩ የሚባል ህይወት ለነበራቸው የ16 ዓመቷ ሄዋንና ቤተሰቦቿ፤ ምግብ ፈጽሞ ችግር ሆኖ እንደማያውቅ ትናገራለች፡፡  
“አሁን ተርቤአለሁ። ወላጆቼና ወንድም እህቶቼም ተርበዋል። ለወራት እርዳታ ለመቀበል በከንቱ ስንጠብቅ ቆይተናል” ብላለች ሄዋን።
“ባህር ማዶ ያሉ ዘመዶቻችን በህገወጥ አስተላላፊዎች በኩል ገንዘብ ሲልኩልን ቆይተዋል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ግን ገንዘብ አስተላላፊዎችን ማግኘት ፈተና ሆኗል፡፡ ቀድሞ የምናውቃቸው   በሥራ ላይ አይደሉም፡፡ ያለንን ንብረት ሁሉ ሸጠናል። ቤት ውስጥ ምንም የሚበላ ነገር የለም። ስለዚህ ገላዬን ለመሸጥ ጎዳና ወጣሁ። ሌላ ታዲያ ምን አማራጭ አለኝ?” ስትል ሄዋን ትጠይቃለች።
በትግራይዋ መዲና መቀሌ፣ እንደ ሄዋን ሁሉ ዕድሜያቸው ያልደረሰ ታዳጊ ሴት ህጻናትንና ተስፋ - ሰጪ ሙያ የነበራቸውን ጨምሮ በርካታ ሴቶችና ልጃገረዶች፣ ለህልውናቸው ሲሉ በወሲብ ሥራ ላይ ተሰማርተው ይገኛሉ፡፡
በፕሮጀክት ማኔጅመንት የማስተርስ ድግሪ ያላት የ27 ዓመቷ ዙፋን፤ ከጦርነቱ በፊት አስተማማኝ ሥራና ጥሩ ደሞዝ የነበራት ስትሆን፤ ዶክትሬቷን ለመቀጠልም ዕቅድ ነበራት። በአሁኑ ወቅት ግን የወላጇን ህይወት የቀማትን ረሃብ ለማሸነፍ ገላዋን ሸጣ ለማደር ተገድዳለች፡፡
“አባቴ በምግብ እጦት ሲሞት ተመልክቻለሁ። በእጆቼ ላይ ነው የሞተው። እናቴ አጥንቷ ብቻ ነው የቀረው። መጋዘኖች ከተማዋን ለመመገብ በሚያስችል እርዳታ ተሞልተዋል፡፡ በመቀሌ ዙሪያ እርዳታ ለማከፋፈል ነዳጅ አያስፈልግም። ሰዎች ግን ማግኘት የሚገባቸውን እርዳታ ባለማግኘታቸው እየሞቱ ነው። አባቴን በረሃብ ካጣሁኝ በኋላ፣ የራሴንና የእናቴን ህይወት ለመታደግ አንድ ነገር መስራት ነበረብኝ። ረሃብ ጊዜ አይሰጥም። ልመናን ሞከርኩት። ብዙ ለማኞች ስላሉ አያዋጣም። ስለዚህ ሴተኛ አዳሪ ሆንኩ” ትላለች፤ ዙፋን፡፡
ዙፋን በባንክ ሂሳቧ  ገንዘብ የላትም። ነገር ግን ባንኮች በትግራይ ገንዘብ መስጠት አቁመዋል፤ ከማዕከላዊው የፌደራል ስርዓት በመነጠላቸውና ገንዘብ አልባ በመሆናቸው።
ሁሉንም አማራጮች ላሟጠጡ በርካታ የትግራይ ችግረኛ ሴቶች፣ ገላን ቸርችሮ ማደር ብቸኛው የህይወት ማቆያ ሆኗል፡፡
ባለፈው ወር በመቀሌ፣ ሦስቱ ህጻናት ልጆቹ ሲራቡና ሚስቱ ምግብ ስትለምን ማየት ህሊናው ሊቀበለው ባለመቻሉ፣ ራሱን ያጠፋው የመንግስት ሰራተኛ ዜና፣ በከተማዋ በስፋት ተሰራጭቶ ነበር።
የ60 ዓመቱ አቶ አርአያ፣ ቤታቸውን አከራይተው በሚያገኙት ገቢ ነበር የሚተዳደሩት። ነገር ግን ከሥራ ውጭ የሆኑ ተከራዮች የሚከፍሉት ገንዘብ የሌላቸው በመሆኑ፣ ገቢያቸውን መሰብሰብ  አልቻሉም።
ህይወታቸውን ማቆየት የቻሉት ታዲያ፣ ልጆቻቸው በህገወጥ አስተላላፊዎች በኩል በሚልኩላቸው ገንዘብ ነበር።
ከላኪው ጋር በሚደረስ ስምምነት መሰረት ህገወጥ አስተላላፊዎች፣ ከ30-50 በመቶ የሚደርሰውን ገንዘብ ለራሳቸው ወስደው ቀሪውን ለተቀባዩ ያደርሳሉ፡፡
“የሚላክልኝ ገንዘብ ባይኖር ኖሮ፣ ወይ ለልመና እወጣለሁ፤ ወይ ደግሞ በረሃብ እሞት ነበር። ብዙዎቹ የገንዘብ አስተላላፊዎች ሥራቸውን ለማቆም እየተገደዱ መሆኑን መስማቴ ለስጋት ዳርጎኛል፡፡ ምክንያቱም ሌላ ህይወትን ማቆያ መንገድ የለም፡፤” ብለዋል፤ አቶ አርአያ።
ባለፈው ግንቦት ወር በትግራይ ባለስልጣናት ድንበር ላይ ከተያዘ በኋላ ሥራውን ያቆመው የቀድሞ ገንዘብ አስተላላፊ፤ ከባህር ማዶ የሚላክ ገንዘብ ለተቸገሩ ትግራዋይ እንዳይደርስ እንቅፋት የሆኑት የትግራይ ባለስልጣናት መሆናቸውን ይናገራል፡፡
“በመጀመሪያ ደረጃ ገንዘብ ወደ ትግራይ ለማስገባት መሞከር ተስፋ  አስቆራጭና አደገኛ ስራ ነው። በፌደራል መንግስት አይፈቀድም። ወደ ክልሉ የትራንስፖርት አገልግሎት ተዘግቷል። እኛ የምንሰራው በትስስርና ባለስልጣናትን በጉቦ በመደለል ነው። ከገንዘቡ ላይ እስከ 50 በመቶ ድረስ የምንወስደውም ለዚያ ነው። ያለበለዚያ ግን አይሞከርም። ትግራይ ለመድረስ በብዙ መሰናክሎች ውስጥ ካለፍን በኋላ፣ ገንዘቡን ለተራቡ ወገኖች ለማድረስ ከትግራይ ባለስልጣናት ዋስትና ካላገኘን፣ ለምንድን ነው አደጋ የምንጋፈጠው?” ብሏል - የቀድሞው ገንዘብ አስተላላፊ።
ገንዘብ አስተላላፊዎች በስራቸው ወቅት ይደርስብናል ብለው ከሚጠቅሷቸው ችግሮች መካከል፡- የባለሥልጣናት ወከባ፣ ውንጀላ፣ አንድ ሰው ወደ ትግራይ በሚያስገባው የገንዘብ መጠን ላይ የሚጣል ድንገተኛ ገደብ፣ ለተራቡ ሰዎች የሚደርስ  ገንዘብ መወረስ… ይገኙባቸዋል፡፡
“ይህ ለእኛ ስራ (ቢዝነስ) ነው፤ በረሃብ ለሚሞቱት ሰዎች ግን ህይወትን የሚታደግ ነው። ሚሊዮኖች በረሃብ እየሞቱ ባሉበት ሁኔታ፣ ባለስልጣናት በኛ ላይ እንደዚህ ያሉ ገደቦች ለምን እንደሚያደርጉ አላውቅም፡፡ ቀደም ሲል አንድ ጊዜ  ትግራይ ድንበር ላይ ከደረሰ ፍሰቱ ችግር አልነበረውም። ከመጋቢት ወዲህ ግን መከራ ሆኗል። እኔና ባልደረቦቼ ስራውን የተውነው በዚያ ምክንያት ነው።” ብሏል፤ አባዲ የተባለ ሌላ የቀድሞ ገንዘብ አስተላላፊ፡፡
ሌሎች ደግሞ በፍተሻ ጣቢያዎች ላይ የትግራይ ባለስልጣናት፣ ገንዘቡን ለራሳቸው ይወርሱታል ሲሉ ይወነጅላሉ፡፡
“73 ሺ ብር ለማስገባት እየሞከርኩ ነበር። ገንዘቡ ምንም የሚበላ ነገር ለሌላቸውና በአስከፊ ሁኔታ ውስጥ ለሚገኙ የቤተሰብ አባላት የተላከ ነበር። የትግራይ ባለስልጣናት ገንዘቡን ወሰዱት። ምንም በቂ ምክንያት ግን አልሰጡኝም። በእርግጥ በአደባባይ ብዙ ምክንያቶችን ይደረድራሉ። እውነታው ግን የፍተሻ ጣቢያዎችን ያቋቋሙት፣ በሟች የቤተሰብ አባላት መስዋዕትነት ገንዘብ ለመዝረፍ ነው። ከዚህ ክስተት በኋላ ስራውን አቆምኩ። ለመቀጠል ምንም ዋስትና አልነበረኝም።” ብሏል፤ ሌላው በረከት የተባለ የቀድሞ ገንዘብ አስተላላፊ።
ዘ ጋርዲያን የተመለከተው ውስጣዊ አዋጅ፣ ከላይ የተሰጡትን ምስክርነቶች የሚያረጋግጥ ነው፡፡ አዋጁ ከ100 ሺ ብር በላይ መያዝ ህገወጥ መሆኑን የሚደነግግ ሲሆን ወደ ክልሉ የሚገባ ገንዘብ በድንበር ለሚገኙ የፍተሻ ጣቢያዎች ሪፖርት መደረግ አለበት ይላል፡፡ ማንም ሰው ከዚህ ውጭ ሲሰራ ከተገኘ በወንጀል የሚከሰስ ሲሆን ገንዘቡ በቀጥታ በትግራይ መንግስት ሊወረስ ይችላል፤ ለዚሁ ተግባር በተቋቋመው ኮሚቴ ውሳኔ ላይ ተመስርቶ፡፡
ኮሚቴውን በሊቀመንበርነት የሚመሩት የክልሉ ምክትል ፕሬዚዳንት ፈትለወርቅ ገብረእግዚአብሔር ናቸው፡፡ አዋጁ የተፈረመው በፈትለወርቅ ሲሆን ካለፈው ሚያዝያ ወር ጀምሮ ተግባራዊ ተደርጓል፡፡
የትግራይ መንግስት ቃል አቀባይ ገንዘብ ይወረሳል የሚለውን ክስ ያስተባበለ ሲሆን፤ መሰል ገደቦችን ለመጣል የሚያስችል በቂ ገንዘብ ወደ ክልሉ እየገባ አይደለም ሲል ለጋርዲያን ተናግሯል።
“እኛ እንደውም ወደ ክልሉ የሚገባ የካሽ ፍሰትን እናበረታታለን። ህገ-ወጥ ተግባራትን ግን መቆጣጠር ያስፈልጋል” ብሏል- ቃል አቀባዩ።
ማስታወሻ፡- በታሪኩ የተጠቀሱት ስሞች በሙሉ የተለወጡ ናቸው፡፡
(ምንጭ፡ The Gurdian, 19 Aug 2022)

Read 2319 times