Saturday, 20 October 2012 10:02

ሥራ አጥነት የኢትዮጵያ ህዝብ መሠረታዊ ችግር መሆኑ ተገለፀ

Written by  መታሰቢያ ካሣዬ
Rate this item
(8 votes)

ሥራ አጥነትና ስውር ሥራ አጥነት የኢትዮጵያ ህዝብ መሠረታዊ ችግር መሆኑ ተገለፀ፡፡ የከተሞች የሥራ ስምሪትና የሥራ አጥነት ላይ በተደረገ ጥናት መሠረት፤ የሥራ አጥነት ደረጃ ከገጠር ይልቅ በከተማ ከፍ ብሎ የሚታይ ሲሆን የሥራ አጥነት ችግርም ከወንዶች ይልቅ በሴቶች ላይ እንደሚጐላ ታውቋል፡፡ የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ሰሞኑን ይፋ ባደረገው መረጃ፤ የሥራ አጥነት ሽፋኑ በከተሞች 18 በመቶ ደርሷል፡፡ በየዓመቱ የሥራ ገበያውን የሚቀላቀለው ከፍተኛ ቁጥር ያለው የሰው ኃይል ከግምት ውስጥ ሲገባ፣ ሥራ አጥነት የወጣቶችን የሥራ ዕድል የማግኘት መብትም ሆነ የብሔራዊ የልማት ራዕይን ከማሳካት አኳያ ትልቅ ጋሬጣ እንደሆነ መረጃው ይጠቁማል፡፡

እ.ኤ.አ በ2011 በተደረገው የህዝብና ጤና ጥናት መሠረት፤ 27 በመቶ የሚሆኑ ዕድሜያቸው ከ5 ዓመት እስከ 14 ዓመት የሚደርስ ህፃናት ትምህርታቸውንና የመጫወቻ ጊዜያቸውን መሥዋዕት በማድረግ የጉልበት ሥራ በሚጠይቁ የሥራ መስኮች ውስጥ ተሰማርተው ይገኛሉ፡፡ 
የአገሪቱ የሥራ ገበያ በበቂ ሁኔታ አድጓል ብሎ በድፍረት መናገር እንደማይችል የገለፀው ሰነዱ፤ በዝቅተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው የሠራተኞች ምንዳ፣ በበቂ ሁኔታ ያላደገ የግብይት ሥርዓት፣ ከፍተኛ የግብይት ዋጋና በሥራ ገበያው ውስጥ ወቅቱን የጠበቀ የመረጃ ፍሰት ሥርዓት አለመኖር ለሥራ ገበያው አለማደግ መገለጫዎች እንደሆኑ ተጠቁሟል፡፡
በሥራ ላይ ያሉት ተቆጣጣሪ ተቋማት በአብዛኛው መደበኛ የሆነው የምንዳ ተቀጣሪ ክፍለ ኢኮኖሚ ሴክተር ላይ ብቻ ያተኮሩ መሆናቸው፣ የሥራ ዋስትና አለመኖር፣ የማህበራዊ ምክክር አለመጐልበት እንዲሁም የተደራጀ የሥራ ገበያ አገልግሎት አለመኖር ፍፁም ባልሆነው የሥራ ገበያ ውስጥ የገበያ መነቃቃትን የገደቡ ክፍተቶች መሆናቸውን መረጃው ጠቁሟል፡፡

 

Read 3202 times Last modified on Saturday, 20 October 2012 10:08