Saturday, 27 August 2022 12:32

የክፉ ቀን መዘዝ!

Written by  ኢዮብ ካሣ
Rate this item
(5 votes)

    “እናንተ ልጆች ዛሬ ነግሬአለሁ ትንሽ አልበዛም እንዴ?” አለች ሜሪ፤ ወጥ ቤት ውስጥ ጉድ ጉድ እያለች። መንትዮች የሚመስሉት ሁለት ወንድ ልጆቿ ከተፋቀሩና ልፊያ ከጀመሩ ማንም አይችላቸውም። ቤቱን እብድ የዋለበት ያስመስሉታል። በአንድ ነገር ከተጣሉና ከተኮራረፉ ግን ቤቱ ሰላም ያገኛል። ሁለቱም የየግል መጫወቾቻቸውን ያነሳሉ ይጥላሉ።
በሁለቱ የጋዝ ምድጃዎች ላይ የተጣዱት ድስቶች እየተንተከተኩ ነው። የትኩስ ጎመን ሽታ ሳሎኑን ጭምር አውዶታል። አንዱ ድስት ጎመንና ድንች፣ ሌላኛው ፎሶልያ ተጠብሶባቸዋል። መአድ በቀረበ ቁጥር ባለቤቷ ጆሴፍ የሚያሳየው ንጭንጭ ሜሪን ያሳቅቃታል። ንጭንጩ ሚስቱ የሰራችው ምግብ ላይ አይደለም። እንደውም የሷ እጅ የነካው ነገር ሁሉ ይጣፍጠዋል። “ይሄ መንግስት በግድ ቬጅቴሪያን ያድርገን እንዴ?” ይላል ጠረጴዛውን በቡጢ እየደበደበ። ሜሪ ዝም አትልም። “ስጋ እኮ ያስረጃል” ትለዋለች፤ ንዴቱን ያበረደች እየመሰላት። “አማረብኝ ብለሽ ነው” ይላል ጆሴፍ።
አባቱ በከብት እርባታ የታወቁ ነበሩ። ከብት አርዶ ለሆቴሎች በማቅረብ ነው የሚታወቁት። ታዲያ በወጣ በገባ ቁጥር የተጠበሰ ስጋ ሲቆነጥር አድጎ፣ አሁን በጎመን ሆዴን ልሙላ ሲል እንዴት በጄ ይበለው።
“እራት ደርሷል፤ ቶሎ ወደ ምግብ ጠረጴዛ!” አለች ሜሪ በትዕዛዝ ቃና፣ የልጆቹ መኝታ ቤት በር ላይ ቆማ።
“እንደምን አ…መ…ሻችሁ?” ጆሴፍ ነበር- ዛሬ ከወትሮው መሸት አድርጎ ነው የመጣው። ወዲያው ቤቱ በመጠጥ ሽታ ታወደ። ጆሴፍ በትልቅ ፌስታል ያንጠለጠለውን ነገር ለሚስቱ አቀበላትና ወደ ውስጥ ገባ።
“ለእራት ነው…እስቲ ዛሬ እንኳ እንቅመስ በስንት ዘመናችን…” አለ፤ ሲናገር አፉን ያዝ እያደረገው። ፌስታል ውስጥ ተጠቅልሎ የተቀመጠውን ነገር አውጥታ ጠረጴዛ ላይ አደረገችውና፤ “ምንድን ነው?” እያለች በጉጉት ትከፍተው ጀመር። ጆሴፍ ዘወትር ለገና እለት የሚያመጣላትን የተጠቀለለ ስጦታ ከፍታ እስክታይ ድረስ በፊቱ ላይ የሚታየው ዓይነት ስሜት ነበር የሚስተዋልበት። “እኔ አላምንም ስጋ…ስጋ…” አለች ሜሪ፤ በአድናቆትና በመገረም ባሏን እየተመለከተች። ወዲያው ዘላ አንገቱ ላይ ተጠመጠመችበት።
“ዛሬ ፌሽታ ነው! ጎመን ደህና እደሪ!” አለች ድስቶቹን ከምግቡ ጠረጴዛ ላይ እያነሳሳች። ሜሪ እንቅስቃሴዋ ሁሉ በዳንስ ቅኝት ነበር።
“ልጆች፤ ስጋው እስኪጠበስ ትንሽ ተጫወቱ” አለ ጆሴፍ፤ ልጆቹን እየሳመ። ልጆቹ በደስታ ወደ ልፊያቸው ተመለሱ። ህጻናቱ ሲላፉ ቢያድሩ ደስታቸው ነው፤ለስጋው ብዙም ደንታ ስላልሰጣቸው ትንሽ ቅር ቢለውም፣ እነሱን ጥሎ ወደ ወጥ ቤቱ ሄደ።
ሜሪ ለብዙ ጊዜ ቁምሳጥን ውስጥ ደብቃ የቆየችውን ጎራዴ የመሰለ ቢላ አውጥታ፣ ከሞረድ ጋር ካፏጨች በኋላ ስጋውን በቄንጥ መቆራረጥ ጀመረች።
“ጆሲ ለመሆኑ ከየት ተገኘ?” ሜሪ ጠየቀች ባሏን።
“ከሩቅ ሰፈር ነው፤ ይልቅስ ቶሎ ጥበሽው”
“አሁን ነው የማደርሰው” አለችው፤ ወደ ባሏ ዘወር ብላ በአይኗ ጠቀስ እያደረገችው። ጥቅሻዋ መላ ሰውነቱን ወረረው። ጠጋ አለና ማጅራቷን ሳማት። ጭስ ጭስ ትላለች። ሰፋ እያለ የሚወርደው መቀመጫዋን በእጁ ቸብ አደረገና፤ “በይ ቶሎ በይ!” ብሎ ከወጥ ቤቱ ወጣ።
የአገሪቱ መንግስት የውጭ ሀገር ምንዛሬ ያስገኛል በሚል ሰበብ ነዋሪው ህዝብ ከብቶቹን እንዳያርድ ያሳሰበው የዛሬ ሁለት ዓመት ነበር። ስጋ መግዛት የሚቻለውም ከመንግስት ሱፐር ማርኬቶች ብቻ ነው። ቀስ በቀስ ግን የስጋ ግሮሰሪዎች በሙሉ ወደ ጎመንና ፍራፍሬ መሸጫዎች ተቀየሩ። በሰላም አገር ከፍተኛ የስጋ እጥረት መኖሩ በሬዲዮና በቴሌቪዥን በይፋ ታወጀ። ይባስ ብሎ በየሆስፒታሉ ያሉ የመንግስት ዶክተሮች ራሱን ታሞ ለሄደው ሁሉ፣ አትክልት መብላት ጤነኛ እንደሚያደርግና እድሜ እንደሚያስረዝም መስበክ ጀመሩ። “ታዲያ ድሮ ምነው አልነገሩን፤ ይሄው ስጋ እየበላን እድሜያችንን ፈጀን አይደል” እያሉ አዋቂ ሰዎች መሳለቅ ከጀመሩ ከራርመዋል።
“ስጋው መልኩ ያስጎመዣል ጣእሙ ግን…” አለች ሜሪ።
“ስንት ዘመንሽ ነው ስጋ ከበላሽ? ጣእሙን ዘነጋሽው አይደል! እድሜ ለዚህ መንግስት” አለ ጆሴፍ፤ በሹካ ስጋውን አሁንም አሁንም እየጠቀጠቀ፣ ወደ አፉ በመላክ። ህጻናቱ ጥብሱን የወደዱት አይመስሉም። አንዲት ስጋ ይጎርሱና እያላመጡ ይተፉታል።
“እነዚህ እኮ ደህና ነገር አይወድላቸውም… የድሃ ልጆች!” አለ ጆሴፍ፤ የህጻናቱን ምግብ እያነሳ።
“ጎመን ይሻላችኋል?” አለች እናታቸው። ሁለቱም ህጻናት በአዎንታ ጭንቅላታቸውን ነቀነቁ። ጆሴፍ ቶሎ ቶሎ እየጎረሰ ልጆቹን ሊያስቀና ሞከረ። ልጆቹ ግን በአበላሉ ፍርስ ብለው ሳቁ። በቴሌቪዥን የሚያዩትን ኮሜዲያን እያስታወሱ ይመስላል።
“ዛሬ እንዴት ነው ፍቅር በፍቅር ሆነሃል?” አለች ሜሪ፣ ፒጃማዋን አላስቀይር ብሎ እየተላፋ ቢያስቸግራት፣ ባሏን በግርምት እያየችው።
“አንቺም ትንሽ ብራንዲ ብትጠጪ እኮ…”
“ብራንዲው ነው ብለህ ነው? መጠጥ ላንተ አዲስ አይደለም!”
“እና ምኑ ነው ታዲያ?”
“ስጋው!” አለች ሜሪ! ለብቻዋ ለመሳቅ እየሞከረች።
“ሌሊቱን እኮ እንቅልፍ ነሳኸኝ… እኔ አረጀሁ እንዴ?” አለች ሜሪ፤ ለባለቤቷ ቁርስ እያቀራረበች።
“እንዳልሽው ስጋው ይሆናላ። በይ ቀሪውን ስጋ ለምሳ ጥሩ ጉላሽ…” አለ ጆሴፍ፤ በፊቱ ላይ ፈገግታ እየተነበበ።
“ስጋው እንኳ ጣዕምም የለው ብቻ…”
“ነገርኩሽ አጣፍጠሽ ስሪው። ሙያውን እረሳሽው እንዴ?” አለና ከንፈሯን ስሞ ከቤት ወጣ።
“ወቸ ጉድ! ከንፈሬን ከሳመኝ እኮ ብዙ ጊዜው ነው። ወይ ይሄ ስጋ! እንዲህ ከሆነስ ከሽኜ ልስራለት” ብላ አሰበች።
ወጥ ቤት ሆና ስጋውን ስትቆራርጥ፣ ከቤታቸው አጠገብ ያለችው ምስኪን ጎረቤቷ ትዝ አለቻት- የቤት ሰራተኛ ሲሄድባት መጥታ የምትረዳትና የሆዷን የምታጫውታት ጎረቤቷ። ብዙ ማሰብ አልፈለገችም። ከስጋው ላይ ጎመድ አድርጋ በትንሽ ላስቲክ ከከተተችው በኋላ ወደ ጎረቤቷ አመራች። “ከየት ተገኘ? ስጋ?” አለች፤ ጎረቤቷ በመደነቅ። ጎረቤቷ ከሰማይ የወረደ መና ነው የመሰላት።
 “ጆሲ ነው ያመጣው፤ በይ እስቲ ጠባብሽና…” ብላ ወደ ቤቷ ተመለሰች። ጉላሽ መስራት ብዙ ሰዓት የሚፈጅ ባይሆን ኖሮ፣ ከጎረቤቷ ጋር ማውራት በወደደች። ስለ ዛሬ ሌሊት አዳሯ ለማውራት ልቧ አሰፍስፎ ነበር። ሌሊት ሙሉ የተደረገ ነገር ደግሞ በሰከንድ አይወራም። “ዛሬ ከጆሴፍ ጋር የሰራነው ፍቅር!”... ማለት ብቻ ምኑንም አይገልጸውም። እግር ዘርግቶ በሰፊው የሚወራ ነገር ነው። ከሰዓት ለዚህ የሚሆን በቂ ጊዜ እንደምታገኝ አሰበች። የሌሊቱን ነገር እያሰላሰለች ስጋ ስትከትፍ፣ ትንሿን ጣቷን በከፊል ቆረጠች።
ሜሪ ለባለቤቷ የሚወደውን ጉላሽ በነጭ ሽንኩርትና በፈረንጅ ቃሪያ ከሽና ሰራች። በማንኪያ አንድ ሁለቴ ጨልፋ በማውጣት ቀመሰችው። “እውነቱን ነው ጆሴፍ!” አለች እጇን አስር ጊዜ በማጣጣም እየላሰች።
“ሜሪ…ሜሪ” ከውጭ የሴት ድምጽ ሰማች።
“ውይ ደህና ቢላ እኮ የላትም፤ አንዷንም ሽንኩርት አደንዝዟታል” ብላ አሰበች ሜሪ።
ስጋ ሰጥቶ ቢላ መንሳት አሉ!
“ግቢ ግቢ የእኔ እመቤት” አለች ጎረቤቷን።
“እኔ የምለው ስጋው…”
“ስጋው ምን…ምን ሆነ?” አለች ሜሪ።
“የአሳማ ይሆን እንዴ? የበሬ አልመስልሽ አለኝ”
“የአሳማ እኮ ስብ ይበዛዋል። የአሳማማ አይደለም! ሳንበላ ስለቆየን ጣዕሙን ረስተነው ነው። እኔም…”
ጎረቤቷ አላስጨረሰቻትም… “ግን እኮ ጸጉር… ጸጉር…”
ጎረቤቷ የጀመረችውን ሳትጨርስ የሰዎች ድምጽ ከውጭ ተሰማት። ወደ ቤቱ እየቀረቡ ሲመጡ የእግራቸው ኮቴ በጉልህ ተሰማ። በመጀመሪያ ጆሴፍ ገባ። ሁለት ፖሊሶች ተከትለው ገቡ። ሜሪ መፍዘዝ አይሉት መደንገጥ ብቻ በተወነባበደ ስሜት ተገትራ ቀረች። “ጆሲ…ምንድን ነው? ምንድን ነው?” እያለች ስትጠይቀው፣ ሁለት እጆቹ በእግረ ሙቅ መታሰራቸውን አስተዋለች።
“ሚስትህ ባለሙያ ናት! የምግቡ ሽታ ልዩ ነው” አለ አንዱ ፖሊስ በፌዝ።
ሌላው ፖሊስ ድስቱን ከፍቶ የድስቱ ክዳን ላይ ባገኘው ማንኪያ ጉላሹን እያገላበጠ “የምን ጉላሽ ነው ባክሽ?” አለ ወደ ሜሪ እያየ። ድስቱን ከድኖ ወደ ፍሪጁ አመራ። በትንሽ ሳህን የተቀመጠውን ሙዳ ስጋ አውጥቶ “ተገኝቷል! ተገኝቷል!” አለ ዞር ብሎ ለባልደረባው እያሳየ።
“ይህን ስጋ ከየት አገኛችሁ? እድለኞች ናችሁ፤ እስቲ ለኛም ጠቁሙን” አለ ፖሊሱ ከፍሪጁ ያወጣውን ስጋ አንድ ኪስ ወረቀት ውስጥ እየከተተ።
አንዱ ፖሊስ እንሂድ የሚል ምልክት አሳየ። ጆሴፍ ፊት ፊት፣ ፖሊሶቹ ኋላ ኋላ ሆነው ከቤት ወጡ። ሜሪና ጎረቤቷ ኤሌክትሪክ እንደያዘው ሰው ተገትረው ቀሩ። ሰከንዶች ተቆጠሩ። መጀመሪያ ሜሪ በኋላም ጎረቤቷ ተከታትለው ወጡ። ፖሊሶቹ ራቅ አድርገው ካቆሟት መኪና ሳይገቡ ደረሱባቸው።
“ምንድን ነው ጉዳዩ መብታችንን እኮ…” አለች ሜሪ፤ በራስ የመተማመን ስሜት በጎደለው አነጋገር።
አንደኛው ፖሊስ ከት ብሎ ሳቀና፤ “ለመሆኑ ምን ምን አለሽ? የራስ ያልሆነ ነገር እንዴት እንደሚጥም አየሽ?” አላት።
የፖሊሱ መኪና አቧራውን እላያቸው ላይ እያቦነነ፣ በከፍተኛ ፍጥነት ተፈተለከ።
***
በነጋታው የቺሊ ጋዜጦች ሁሉ ገጾቻቸው ስለ ጆሴፍ እስር ቤት መግባትና ስለፈጸመው ጥፋት ሞቅ አድርገው ዜናዎቻቸውን አቀረቡ!
(የጋዜጣው ዜና እንደ አጭር ልብወለድ፣
አዲስ አድማስ፤ ሚያዚያ 4 ቀን 1995)

Read 1139 times