Saturday, 03 September 2022 14:15

“የጦርነቱ ዳግም መቀስቀስ የሰላም ተስፋችንን አጨልሞብናል”

Written by  መታሰቢያ ሳሣዬ
Rate this item
(3 votes)

          የትግራይ መዲና የመቀሌ ውስጥ ላለፉት 8 ዓመታት የኖረው የሕክምና ባለሙው አቶ ቴዎድሮስ (ለዚህ ጽሁፍ ስሙ የተቀየረ)፤ ላለፉት 2 ዓመታት ያለምንም ደመወዝና ገቢ በሙያው ሲያገለግል መቆየቱን ለአዲ አድማስ ተናግሯል።
በከተማው ብዙም እንቅስቃሴ የለም። ከተወሰኑ ሱቆችና መደብሮች ውጪ አብዛኛዎቹ አገልግሎት እየሰጡ  አይደሉም። ሌብነቱና ዘረፋው አስፈሪ ነው። የደህንነትና የጸጥታ ስጋት ከቀን ወደ ቀን እየተባባሰ ነው። ቀደም ሲል በጥሩ ስራና  ደረጃ ላይ የነበሩ ሰዎች ሁሉ ወደ ዘረፋ ገብተዋል። ምን ይደረግ… ረሃብ የማያደርገው ነገር የለም”  ሲል ስለመቀሌ ከተማ የየውን መስክሯል።
ለሙያው ስነ-ምግባር በመገዛትና ከራሱ ህይወት የህሙማንን ህይወት በማስቀደም ከታጣቂ ቡድኑ በሚሰፍርለት የዕለት ቀለብ ብቻ ላለፉት ሁለት ዓመታት ህብረተሰቡን ሲያገለግል እንደቆየ የሚናገረው ቴዎድሮስ፤ ታጣቂ ቡድኑ ለዳግም ጦርነት ዝግጅት ማድረግ መቀጠሉና ለሰላማዊ ድርድር እምብዛም ፍላጎት አለማሳደሩ ተስፋ እንዳስቆረጠው ይገልጻል።
በመጨረሻም ያለው አማራጭ ከመቀሌ መውጣትና ወደ አዲስ አበባ መግባት ብቻ እንደነበር ይናገራል። ሆኖም ለጉዞው የሚያስፈልገው ገንዘብ አልነበረውም። የጣት ቀለበቱን በ800 ብር በመሸጥ የመቀሌ ከተማ ነዋሪዎች መሃል አገር ወይም ባህር ማዶ ካሉ ቤተሰቦቻቸው ጋር በስልክ ወደሚገናኙበት  ከአፋር ክልል ጋር በሚዋሰነው ምላባት በመሄድ አዲስ አበባ ለሚገኙ ቤተሰቦቹ ስልክ ደውሎ ገንዘብ እንዲልኩለት ማድረጉን ይናገራል።
ከቤተሰቦቹ የተላከለት 20 ሺ ብር 12 ሺ ብር, ሆኖ ሲደርሰው ደስታው ወሰን አልነበረውም። ይህንን ገንዘብ በመያዝ ድንበር አሻግረው ወደ ቆቦና ወልድያ በሚያስገቡ ደላሎች ከመቀሌ፣ ማይጨው፣ ኮረም፣ አላማጣ፣ ዋጃ፣ ቆቦና ወልድያ በመጓጓዝ አዲስ አበባ ገብቷል።
ቴዎድሮስ እንደሚናገረው አብዛኛው የመቀሌ ከተማ ነዋሪ ተስፋ ቆርጧል።  በህውሓትና በመንግስት መካከል ሊደረግ ታስቧል በተባለው የሰላም ድርድር ብዙዎች ተስፋ አድሮባቸው ነበር። ሆኖም ግን የህውሓት ታጣቂ ቡድን  ለሰላም ምንም አይነት  ፍላጎት የሌለው መሆኑ እሱን ጨምሮ ብዙዎችን ተስፋ ያስቆረጠ ጉዳይ መሆኑን ይገለጻል።
ነሐሴ 18 ቀን 2014 ዓ.ም ህወሓት የተኩስ አቁሙን በመጣስ ሦስተኛ ዙር ጦርነት መቀስቀሱ የትራይ ህዝብ የነበረውን ተስፋና ምኞት አጨልሞበታል ይላል። የትግራይ ህዝብ ጦርነቱ ቆሞ በሰላም ከኢትዮጵያውያን ወገኖቹ ጋር  የመኖር ከፍተኛ ፍላጎት አለው።
ሆኖም ግን ይህ ፍላጎቱ በቅርቡ ተሳክቶ ለማየት የምንታደል አይመስለንም። መጪው ጊዜ ካለፈው የከፋ እንዳይሆን ያስፈራል ይላል ቴዎድሮስ።
ከመቀሌ ከተማ በ260 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ  በምትገኘው ወልዲያ ከተማ ሙጋድ በሚባል ሰፈር ውስጥ ነዋሪ የሆነው አቶ ሰይድ ኡስማን፤ የህውሃት ታጣቂ ሃይሎች የቀሰቀሱት ዳግምጦርነት የአካባቢውን ነዋሪዎች በከፍተኛ ስጋት ላይ እንደጣላቸው ይገልጻል። ህብረተሰቡ ጦርነቱ በሰላማዊ ድርድር ሊቋጭ ነው በሚል ጉጉት እየተጠባበቀ ባለበት ጊዜ በድንገት የተቀሰቀሰው ጦርነት ሁሉንም ለከፍተኛ ስጋት  ነው የሚናገረው። ሁላችንም ለስደት ዝግጁ ሆነን ነው የምናድረው፤ ሲገቡ እንወጣለን ብለን እየጠበቅን ነው። መቼም ሲገድሉንና ሴቶቻችንን ሲደፍሩ ቁጭ ብለን  ማየት አንችልም። ከእነሱ ጋ የምንዋጋበት ምንም አይነት መሳሪያ የለንም። መሳሪያ ይዞ  ሊገድለኝ የመጣውን ባዶ እጄን ቁጭ ብዬ ላመልጠው አልችልም። ያለኝ አማራጭ ሽሽት ብቻ ነው። ይላል ሰይድ።
የአዲስ አመት ተስፋውን  ጠይቀነው በሰጠን ምላሽ ነው። ለእኛ አዲስ አመት ከዚህ ሁሉ ስጋትና ሰቆቃ ወተን ሰላማችንን የምናገኝበት ጊዜ ነው። በ2014 ዓ.ም ያየነውን አይነት መከራና ስቃይ ዳግም አለማየት ነው ምኞታችን ይህ ግን የሚሆን አይስመልም ካለፈው መከራችን ይልቅ የመጪው ያስፈራል።  ምንም ተስፋ የምናይበትና ተስፋ የምናደርግበት ነገር አጥተናል” ብሏል አማፂው ቡድን የቀሰቀሰው ጦርነት በህብረተሰቡ ላይ የፈጠረውን ስሜት ሲገልፅ።
ሃና (ስሟ ለዚህ ፅሁፍ የተቀየረ) እዚህ አዲስ አበባ እናቷና በአንድ የእርዳታ መስጫ ድርጅት ውስጥ የምትሰራ ሲሆን ጦርነቱ ቆሞ በመቀሌ የሚኖሩበትን ሁለት ታናናሽ ወንድቿን የማግኘት ትልቅ ተስፋ ነበራት። እየሆነ ባለው ነገር  እጅግ ማዘኗን ገልጻ፤ጦርነቱ ሊያበቃና ቤተሰቦቼን ላገኝ ነው የሚለው ተስፋዋ መጨለሙን ትናገራለች።
“ጦርነት በባህርይው የማይገመቱ ነገሮች የሞላበት ነው። በቀጣይ ቤተሰቦቼን በህወት ላገኝ የምችልበት አጋጣሚ ላይፈጠር እንደሚችል አውቃሁ።
እናም ሰላምን ብቻ ነው የምመኘው” ትላለች ወጣቷ።የሰላም ድርድሩ አነቃቅቶት የነበረው አካባቢው ሰላም ተስፋ የህውሓት ታጣቂ ቡድኑ በተቀሰቀሰው ዳግም ቶርነት ሳቢያ ተስፋው ጨላልሟል።
 በትግራይ ክልልና አጎራባች የአማራና አፋር ክልሎች ውስጥ በሚገኙ  አንዳንድ ከተሞች በአዲስ ዓመት ዋዜማ ስጋት አንዣቦባቸዋል።

Read 12859 times Last modified on Saturday, 03 September 2022 14:27