Saturday, 03 September 2022 14:37

የገጣሚና ደራሲ ነቢይ መኮንን ሦስት መጻሕፍት ሰኞ ይመረቃሉ

Written by  ናፍቆት ዩሴፍ
Rate this item
(0 votes)

የአዲስ አድማስ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ  የሆነው አንጋፋው  ደራሲ፣ ገጣሚና  ተርጓሚ ነቢይ መኮንን፤ የጻፋቸውና የተረጎማቸው  ሦስት መጻሕፍት የፊታችን ሰኞ ይመረቃሉ፡፡
መጻሕፍቶቹ “ነገም ሌላ ቀን ነው”፣ “የመጨረሻው ንግግር” እና “የእኛ ሰው በአሜሪካ” የተሰኙ  ሲሆን ፤ አንጋፋ  የኪነጥበብ ባለሞያዎች ሥራዎቻቸውን በሚያቀርቡበት ልዩ  መድረክ እንደሚመረቁ ነው የተነገረው፡፡
የፊታችን ሰኞ ነሐሴ 30፣ ከቀኑ 11 ሰዓት ጀምሮ፣ ቦሌ በሚገኘው  ፍሬንድሺፕ ኢንተርናሽናል  ሆቴል በሚካሄደው ልዩ የምረቃ ሥነሥርዓት ላይ አንጋፋዎቹ  አርቲስት አበበ ባልቻ፣ አርቲስት ተፈሪ አለሙ፣ ወግ አዋቂው  በሃይሉ ገብረመድህንና  አርቲስት ጌትነት እንየውን ጨምሮ ሌሎች የኪነጥበብ ባለሞያዎች ሥራዎቻቸውን  ያቀርባሉ ተብሏል።
የምረቃ ሥነሥርዓቱ  መደበኛ የመግቢያ ዋጋ 300 ብር ሲሆን  ከነጻ ኮክቴል እራት ጋር  ለVlP 1000  ብር መሆኑ ታውቋል፡፡
በዕለቱ ከሚመረቁት መጻህፍት መካከል አንዱ የሆነው “ነገም ሌላ ቀን ነው”፣ ዝነኛው የአሜሪካ ክላሲክ መጻሐፍ “Gone With The Wind” ትርጉም  ሁለተኛ ጥራዝ  ሲሆን፤ ገጣሚ ነቢይ መኮንን በደርግ ዘመን በእስር ላይ እንዳለ በሲጋራ መጠቅለያ ወረቀቶች ላይ በድብቅ የተረጎመው እንደሆነ ይታወቃል፡፡
መጽሐፍቶቹን  በጠይም መጻሕፍት /አራት ኪሎ ቅድስት ሥላሴ ሕንፃ አንደኛ ፎቅ /ላይ ማግኘት ይቻላል ተብሏል፡፡
 ከ20 ዓመታት በላይ የዘለቀችውን ሳምንታዊ አዲስ አድማስ ጋዜጣ ከመሰረቱት አንዱ የሆነውና አሁንም  በዋና አዘጋጅነት እየሰራ የሚገኘው ገጣሚ ነቢይ መኮንን፣ ከዚህ ቀደም ሁለት የግጥም መድበሎችን ያሳተመ ሲሆን “ናትናኤል ጠቢቡ” የተሰኘውን ጨምሮ ሌሎች ተውኔቶችንም ለመድረክ ማብቃቱ ይታወሳል፡፡

Read 12123 times