Saturday, 03 September 2022 14:53

«የኪነት ነፍስ »

Written by  አፀደ ኪዳኔ (ቶማስ)
Rate this item
(11 votes)

 የማስበው  እንደ ምንጭ ጥርት ብሎ ወደ ሰዉ  ልቦና ባይፈስም፣ ስለ ደራሲዎች አንዳንዴ እንዲህ አስባለሁ....
የደራሲዎች ትልቁ ችግራቸው ያልተባለ ነገር ለማለት ከመፈለጋቸው  የተነሳ የማያስፈልግ ነገር ይላሉ። ያልተኖረ ህይወት ለመኖር ከመፈለጋቸው የተነሳ የእብድ ኑሮ ይኖራሉ። በሚስማሙበት ነገር ላይ እንኳን በተቃራኒው መቆም ያስደስታቸዋል። ስለ ትልቅ ገድል እየፃፉ እነሱ ግን መብራት አጥፍቶ መተኛት ያስፈራቸዋል። የሚፅፉትን ሩቡን እንኳን ሳይኖሩት የእድሜያቸው ማብቅያ ላይ ይቆማሉ። ስለ ነፃነት እየፃፉ፣ እነሱ የሚስታቸውን ነፃነት ይገድባሉ።  የእግዜርን ስራ እየመረመሩ፣ ኑሯቸውን ግን መመርመር ከብዷቸዋል። ይሄን ነገር ብንረሳው ይሻላል መሰል... እነሱ እንደሆኑ ብዕራቸውም ኑሯቸውም ግራ ያጋባል። ብዙ  ባላነብም ማረጋገጫዬ ቀሽም ደራሲው ባሌ ነው።
“እግዜርን አምርሬ  ሸሸሁ” ብሎ የፃፈው ደራሲው ባሌ፣ ከእኔ በላይ ቤተክርስትያን ይስማል ብላችሁ ታምናላችሁ? ለህመሞቼ ከሆስፒታል ይልቅ ወደ ፀበል እንደሚመራኝ  ታውቃላችሁ?
በእናንተ በኩል ስለ እኔው ቀሽም  ደራሲ ነው ያወራሁትና አትቀየሙኝ...
ቅር አላችሁ እንዴ?
ቀንም  ሌሊትም  እሱ ወደ ብዕሩ ይጓዛል..  እኔ ደግሞ ወደ ልቤ እስበዋለሁ...እሱ ወረቀት ላይ ያቀረቅራል፣ እኔ ተሸግኜ መልኬን እንዲመለከት እጠብቃለሁ።  እሱ ከመፅሃፍ ጋር በፍቅር ወድቆ እረስቶኛል፣ እኔ ደግሞ በእሱ ፍቅር እሰቃያለሁ።
“ፍቅሬ”  ብሎ እንዲጠራኝ እፈልጋለሁ። እንዲያቅፈኝ እፈልጋለሁ። በደንብ እንዲያፈቅረኝ እፈልጋለሁ። እንዲስመኝ እፈልጋለሁ።
“ድርሰት” የሚባል ሰይጣን ግን አብረን ብንሆንም፣ መሃላችን ገብቶ  ለያይቶናል። አብረን ተኝተን ለየብቻ ነቅተናል። አብረን እየተጓዝን መንገዳችን ተለያይቷል።  እንደ መልካችን እጣ ፈንታችንም ለየቅል ነው።  ህልማችን የሁለት አገር ሰው ይመስላል። አይደለም እንዴ?
ከመፃፍ  በላይ እንደማይወደኝ አውቃለሁ። ከመፅሃፍ በላይ እንደማይቀርበኝ እረዳለሁ። ብቸኝነቱን የሚወደውን ያህል እኔን አይወደኝም።  እስቲ እህ ብላችሁ ስሙኝማ.... ገነት ያልኩት ትዳር ሲኦል ሆኖ ጠበቀኝ እኮ ነው የምላችሁ....
ታድያ ለምንድነው አብሮኝ የሚኖረው? አላውቅም... ምናልባት በገንዘብ ስለምረዳው ይሆናል - ማን ያውቃል? ....
ፍቅር ሳይሆን ጥቅም ይሆናል ያስተሳሰረን?!  ይሄን ከእግዜር ውጪ ማን ያውቃል?
ከብዕሩ ሥር የሚፈሰው የፅሁፉ  ጅረት ጣፍጦኝ አያውቅም። አታስዋሹኝና  ስለ ደራሲና ስለ ድርሰት ማውራት ይታክተኛል። በህይወቴ በደንብ  ገልጬው የማውቀው መፅሃፍ ቢኖር መፅሃፍ ቅዱስ ነው። አንዳንድ መፅሃፎችን ግን ማንበቤ አልቀረም።  አጠገቡ አመት ብቀመጥ እንኳን ብዕሩን ይዞ ወረቀት ላይ ካቀረቀረ ቀና ብሎ አያየኝም። “ሴቶች  የኪነት መንፈሴን  ያደክሙብኛል” ይለኛል። “ይሄ የኪነት መንፈስህ ምናለ በሞተ.... ገንዘን ብንቀብረው ጥሩ ነበር” እለዋለሁ።
ይሄኔ ታድያ  ... አይስቅም። ደግሞም አይቆጣም። በሁለቱ መሃል የዋለለ ፊት አያለሁ። እንዳይናገር ዝምተኛ ነው። እንዳይስቅ አፋራም ነው። የቸገረ ነገር...
ጫቱን እየቃማ፣ ቡናውን እየጠጣ ይፅፋል። በዚህ ትልቅ የኪነት ጉዞው፣ ለስራዎቹ  አድናቂ እና አክባሪ የለውም። ሃያሲዎች እንኳን ፅሁፎቹ ከሪፖርት እንደማይሻሉ  ይናገራሉ። ጋዜጣ ላይ መፃፍ እንኳን ካስከለከሉት  ሰነበቱ። አዘጋጁ እንዲህ ነበር ያለው፤ “ብዕርህ የሙት መንፈስ አለበት” ምን ማለት ነው ይሄ ደግሞ? ሙትቻ ነገር ነው ...
እኔ በማመጣው  የኪራይ ገንዘብ ይቀለባል (አፈር ይብላና) ....  አንድ ቀን እስቲ መፃፉን ተወው እና በተማርክበት ስራ ፈልገህ ግባ አልኩት.  . . ፈገግ ብሎ እንዲህ አለኝ :- “ እውነት ይሄን ባደርግ የጥበብ አማልክት ይቀየሙኛል” ሳቅኩኝ እንዴ ያኔ... ቀላል ሳቅኩኝ...
እንዴት ሰው ፅሁፉ  ሊታተም እንደማይችል እያወቀ ይፅፋል? ድርሰት ላይ ቀሽም ነህ እየተባለ ይቸከችካል? በአራቱም መዐዘን “አትችልም” የሚል ቃል እየተሰደደለት ይከትባል?
እሱ የሚለው አልተረዱኝም ነው።
መላዕክ እንኳን አይረዳህም፤ የኔ ቀሽም ደራሲ!  እለዋለሁ።
ደራሲ ሳይሳካለት ሲቀር፣ሰበቡ መቼም አልተረዱኝም ነው። ሃሃሃሃሃ.....
ይሄን ያልተሳካለት፣ ቀሽም ደራሲ አግብቼ መኖር ከጀመርኩ ሁለት ጥንድ አመታት ሆነኝ።
ምኑ ነበር  የሳበኝ?
አዎ!
ንፁህ ልቡ አይደል? ልብሱን አውልቆ ለበረደው ሲሰጥ አየሁ። ኪሱን አራቁቶ ለቸገረው ሲመፀውት ተመለከትኩ። ለክፉ የእንጀራ አባቱ ሲያለቅስ፣ እናቱን ሲወድ ፣ ምንም ሳይኖረው በህይወት ሲረካ፣ ቆስሎ ሲስቅ...  እንባዉን ሲደብቅ፣ ብቸኝነቱን ሲያፈቅር ታዘብኩ። ማንም በሌለው ሰዓት  አጠገቡ ቆምኩኝ። እንዳገኘሁት በርታ ብለውም አሁን ግን ሰልችቶኛል - ማርያምን።
የእሱን ብዕር መመልከት እንደ  እርጉዝ ሴት ያስመልሰኛል። የፃፈውን ማንበብ ሞትን የሚያስመኝ ነው፤ ለእኔ።
እሱ የፃፈውን አንድ አንቀፅ ከማንበብ አርባ ኪሎ ሽንኩርት መክተፍ ይቀለኛል። ቀልዴን አይደለም አትገልፍጡ....
ያሳተመውን መፅሃፍ ለማንበብ እቅድ ነበረኝና ገለጥኩት።  ፅሁፉ  የጀመረበት የመጀመሪያው ገፅ ላይ፣  የመጀመሪያው አረፍተ ነገር እንዲህ ይል ነበር... “እግዜርን አምርሬ ሸሸሁት” ሶስቴ አማትቤ ዘጋሁት። ከእግዜር እንዴት ይሸሻል? ልሽሽስ ቢሉ ከእግዜር ወዴት ይሸሻል?
የደራሲዎች ትልቁ ችግራቸው ያልተባለ ነገር ለማለት ከመፈለጋቸው  የተነሳ  የማያስፈልግ ነገር ይላሉ። ኑራችን ድህነት አይሉት ... ቅንጦት አይሉት እንደ ተሴ ፊት መሃል ላይ የዋለለ ነው። መፅሐፍ ያሳተመው ከእኔ ገንዘብ ወስዶ ነበር። መፅሃፉን የሚገዛ ሰው ጠፋና ከሰርን።  የገረመኝ አለመናደዱ ነው። ቀስ ብሎ በለሆሳስ እንዲህ አለኝ :- “መፅሃፍ ለመሸጥ ብዬ ብዕር  ያነሳሁ ዕለት ነው ብዕሬን  ሰብሬው መፃፍ የማቆመው”
የኪነት ወሬ አይጨርስም መቼም...ስለሚወደው ደራሲ ማውራት ሲጀምር ተነስቼ እወጣለሁ። ስለሚፅፈው ነገር መወያየት ሲያምረው እንኳን አጠገቡ አይደለሁም።
ባይሆን መፅሃፍ መግዢያ  እያለ የሚያስወጣኝን ብር ቢቀንስልኝ ምን ነበር? ..አንዳንዴ መፅሃፎቹን ሰብስበሽ አቃጥይ አቃጥይ ይለኛል። የፃፈበትን ወረቀት ማጋየት ይናፍቀኛል። አንዳንዴ ደግሞ ሰይጣን ነው እንዲህ የሚያደርገው እላለሁ። አዝንለታለሁ።
 አንድ ቀን እንለያይ አለኝ። ምን እንዳስቀየምኩት ጠየኩት። “ችግር ልሆንብሽ አልፈልግም” ነበር መልሱ። ዝም አልኩት...ነገሮች መቀያየር የጀመሩት ግን አድረው ነው።
አዲስ የገባችው የግቢያችን ተከራይ እቃ ፍለጋ  ቤታችን መጣች። በመፅሃፉ ብዛት አፏን ያዘች (ከብት ነገር ነች መሰለኝ)  .. እና ቡና ጠጪ አልኳት። ተሴም ነበር። ጫቱን እየቃመ ይፅፋል። መናገር ጀመረች።
“ደራሲ ነህ እንዴ?”
“እኔንጃ “ አላት...
“ምንድነው የምትፅፈው ታድያ?”
“ልብወለድ ነው”
“ታድያ ደራሲ ነሃ...ልብ ወለድ እኮ የስነ ፅሁፍ አቢይ ክፍል ነው”
“ይላሉ”
ማውራት አልፈለገም። እኔ ግን ዝም ብዬ አዳምጣለሁ። ተነስታ መፅሃፎቹን ማየት ጀመረች። (ማን ፈቀደላት በሞቴ) እና  የፃፈውን  መፅሃፍ አንስታ..
“እንደዚህ መፅሃፍ የምወደው የለም” አለች።
በመጀመሪያ ሁለታችንም ተያየን። ቀጥሎ ተሴ የሆነ ነገር ሊናገር ፈልጎ ዋጠው። ከዚያ እንዲህ አላት በጥርጣሬ :-
“የቱን?”
“ይሄን” አለች።
“ እሱ እኮ ነው የፃፈው” አልኳት፣ በኩራት... ሳቄን  እያመነዠኩ
“እኔ አላምንም፣ አንተ ነህ?”
ዝም አለ።
አቀፈችው... ደነገጥኩ።  ሳመችው... ክው አልኩ።
ታድያ ከዚያ ቀን ጀምሮ ይህቺ ሴት እኛ ቤት እግር ማብዛት ጀመረች።  የተሴም ልብ፣  ልብ ወለድ ከመፃፍ ወደ እዚህች አድናቂው ልብ ማዘንበል ጀመረ። ሴቶች የኪነት መንፈሴን ያደክሙታል ማለቱን እረሳ መሰል፣ እሷን ሲያይ ፃፍ ፃፍ አለው።
  * * *
ስትመጣ የማይገባኝን ነገር ያወራሉ። “አደፍርስ” ስለሚባል መፅሃፍ ይጨቃጨቃሉ። ደበበ ሰይፉ  እና ሰለሞን ደሬሳን ያበላልጣሉ። ገብረ ክርስቶስን ያደንቃሉ። በዓሉ ግርማን አድር ባይ ነው ብለው ይተቹታል።  ፍቅር እስከ መቃብርን ትረካው ተረታማ ነው እያሉ ይነቅፋሉ። ሔርማን ሔስ (ስሙን በትክክል ካልጠራሁት እንጃ) ስለሚባለው ሰው ይሟገታሉ።  ብዕርህ  የካፍካን ይመስላል ትለዋለች። ጨለምተኝነትህ ነው የማረከኝ ትለዋለች።  ቡናዉን እየቀዳሁ እሰማቸው ነበር። ተሴን ሳውቀው ብዙ ማውራት አይወድም ነበር። ከዚህች ልጅ ጋ ግን ብዙ ያወራ ጀመር። በእኔ ገንዘብ የተገዛውን መፅሐፍ ያውሳታል። አይገርምም፤ የእራሴ ገንዘብ መቀራረቢያቸው ሆነ። ቆይተው  እግር መንገድ ጀመሩ። አንድ ነገር ከመፃፉ በፊት ያማክራት ጀመር። ስብሃት ላይ የተፃፈውን ትችት ያነብላታል። ግጥም እየፃፈ ያነብላታል። ትንሽ ከወደደችው  “አሪፍ ነው” ትላለች። በጣም ከወደደችው ተነስታ ታቅፈዋለች። በጣም በጣም ከወደደችው ደግሞ ትስመዋለች። ይሄ ሁሉ ነገር ሲከወን የት የነበርኩ ይመስላችዃል? አጠገባቸው፣ ስራቸው  ነበርኩ።
አንድ ቀን...”ከጨለማ የሚወለዱ ብዕሮች ውብ  ናቸው” ስትል ሰማዃት።
ምን ማለት ነው በሞቴ..
“ከስቃይ የተፈለቀቀ ጭብጥ ይማርከኛል” አለች
ወረኛ...
“ሞትን በጥልቀት የሚረዳ ፅሁፍ አይድፋፋም ኣ?  ... ብርታትህ እዛ ላይ ይመስለኛል። ቋንቋህም ውብ ነው። ትረካህ ቢጎረብጥም እወደዋለሁ። ስትጀምር ቀልብን ማሰር ትችላለህ”
ቀልብሽ ይጥፋ አቦ....
ባሌን ተይልኝ ልላት ፈለኩና ፈራሁ። ቤቴ አትምጪ ማለት ፈለኩና ከበደኝ። ስራዬ እቅፏን መመልከት እና የማይገባ የድርሰት ወሬዋን መስማት ሆነ። እሷ ቀይ ናት። እኔ ጥቁር ነኝ። እሷ ቀጭን ናት፣  ሰልካካ አፍንጫ አላት ፣ ቆንጆም ትመስላለች። እኔ  ለፉንጋነት የምቀርብ መልከ ጥፉ ነኝ። እሷ መፅሃፍ ታነባለች...ዲግሪም አላት። እኔ ስምንተኛ ክፍል ላይ ያቋረጥኩ መሃይም ነኝ። ጎበዝ አንባባቢ ነች (ተሴ እንደሚለው) እኔ ጥቂት መፅሃፍ ባነብም፣ መፅሃፍ ማንበብ እንቅልፍ ከሚያመጣባቸው ወገን ነኝ። እሷ ስለ ድርሰት እና ደራሲ ታውቃለች። እኔ ድርሰት እና ደራሲ ከሚዞርባቸው መሃከል ነኝ። ስመለከተው እኔን እየራቀ እሷን መቅረብ ጀምሯል። ጮክ ብሎ የማይስቅ ሰውዬ ፣ለቀልዷ ጮክ ብሎ መሳቅ ጀመረ። ዝምተኛ ደራሲው ማውራት ጀመረ። እሷን ባገኘ በወሩ አዲስ መፅሃፍ እንደጨረሰ ሰማሁ...ከማ አትሉኝም? ከእሷ...
በዚህ መሃል ውስጥ አለመ’ፈለግ ተሰማኝ። ባዶነት ነፍሴ ላይ አረበበ። ብቸኝነት ጠናብኝ። እስካሁን አብሬው ብኖርም እንደማላውቀው ተገለጠልኝ። የምትወደውን ከሚወድ፣ ሃሳብህን ከሚረዳልህ ሰው በላይ ቅንጣት ያህል  ሳትገባው  እና ሳይረዳህ የቻለህ  ሰው አይልቅም? ለሞተ ዘመዱ ከሚያለቅስ  ሰው ይበልጥ ለመንገደኛ ሰውየሚያነባ አዛኝ አይደለም?
አንድ ቀን ስለ እሷ ስጠይቀው “muse ነች እኮ “ አለኝ።
ቀጠለና.  
“ድንቅ እና ቆንጆ ሴት ናት” አለኝ
መጀመሪያ ምን ማለት እንደፈለገ አልገባኝም። ቀጥሎ ግን ጥቂት ነገሩ ገባኝ።  ባንዳንድ ነገር እንደተበለጥኩ አወቅኩና  አቀረቀርኩ። እኔ ባልሰራሁት መልኬ እንደተቀደምኩ  ሲታወቀኝ እንባዬ መጣ።  መሃይምነቴ  ገና ዛሬ ሲቆጨኝ ተሰማኝ። ስወደው ደራሲ ነው ብዬ አይደለም። ሳፈቅረው ተምሯል፣ መልኩም ቀና ነው ብዬ አይደለም። ስንት አመት የደከምኩት በቅፅበት ለሚጠፋ ፍቅር  ነበር እንዴ? ህልሙ ሳይገባኝ፣ ለህልሙ ልቤን እስክተፋ ሮጬ አልነበር?   ተስፋው ምን እንደሆነ ሳላውቅ፣ ተስፋ አልዘራሁበትም? ካወቅኩት ጀምሮ በፅሁፍ ውስጥ ሆኖ ሲረሳኝ አልተቀየምኩትም።  በሌላ ሴት ሲረሳኝ ግን ቅርታ ከፍቅር ማህፀኔ ተወለደች።
እየቆየ አድሮ መምጣት ጀመረ። ያደረ ቀን የእሷ ቤት መብራት በርቶ አላየሁትም። ያኔ ታድያ ያለ ፍቃዴ እንባዬ ይወርዳል። መሃይም ብሆን...ስለ ድርሰት ባላውቅ እንኳን ይህቺ ትጠፋኛለች እንዴ? ጭንቀቴን ለሰው እንዳላማክር እሱን ስከተል ወዳጆቼን ሁሉ እርቄ ነበር። ከሞት የተረፈ ቤተሰብም አልነበረኝም። በጨነቃችሁ ሰዓት አቅፋችሁት የምታለቅሱበት ወዳጅ ካላችሁ፣ እውነት እውነት እላችኋለሁ ታድላችኋል። እኔ ግን ማንም አልነበረኝም።
ከእራሴ ጋር አንዳንድ ነገሮች ማውራት ጀመርኩ። ያፈቀርከው አድሮ በሰው ሲለውጥህ ብታዝንም፣ ስንት የሆንክለት ትላንት ባወቀው ሰው ሲቀይርህ፣ እልህ ቢተናነቅህም ትግል ግን አያስፈልግም። ሰዎች ሆን ብለው ሲርቁህ በፈገግታ ሸኛቸው። ሳይፈልጉህ እነሱን የራስህ ልታደርግ በለፋህ ቁጥር ይበልጥ ታርቃቸዋለህ። የጥበብ ሁሉ መጀመሪያ አለመ’ፈለግን አምኖ መቀበል ይመስለኛል። ምናልባት ትልቁ ድክመቴ መሃይምነቴ ይሆናል። ምናልባት ትልቁ ጥፋቴ እኔ ያልሰራሁት መልኬ ይሆናል። ምናልባት ትልቁ ስህተቴ ድርሰትና ደራሲን አለማወቄ ይሆናል። ትክክል ነው። እኔ ለእሱ አልገባም ነበር። ስለዚህ ቦታውን ለቅቄ ልሂድ። አሁን እኔ ብዙ ያገለገለ እቃ ነኝ፤ አልፈለግም። ማመን ባልፈልግም ይሄን ሁሉ ማመን አለብኝ። ምንም ነገር ለማድረግ ባልችል እንኳን ሃዘኔን ልሸሽገው እችላለሁ። እንባዬን ልደብቀው እችላለሁ።  መሸነፌን፣ መገፋቴን ልከልለው እችላለሁ ።
እናም ተሰናብቼው ሄድኩኝ።
ከሄድኩ በሁለት አመቱ የእሱ መፅሃፍ ሲሸለም በቴሌቪዥን አየሁ። እንዲናገር በተጋበዘበት መድረክ  ላይ እንዲህ ሲል ሰማሁት፤ “እንደ ሙሴ ባህር ከፍላ የጨለማ የኪነት ዘመኔን ወደ ብርሃን  ያሻገረችኝ ስምረትን  አመሰግናለሁ። ይሄ ያንቺ ውጤት ነው።”  ደስ አለኝ። ዛሬ እሱ ቀሽም ደራሲ አይደለም። “ከሪፖርት የማይሻል ፅሁፍህን ወደ እዚያ ጣል” ሲሉት የነበሩት ሃያሲዎች እያደነቁት ነው። ዛሬ አገር እያጨበጨበለት ነው። ዛሬ  ብዕሩም መልኩም አምሮበታል። አንዳንዴ ከምንወዳቸው ሰዎች ህይወት ውስጥ መውጣታችን እነሱን የተሻለ ቦታ ካስቀመጣቸው፣ ምናለበት ከህይወታቸው ብንወጣ? በዚህስ ደስ ቢለን ምናለበት..  
ደስ ብሎኛል ስለ እውነት... ጥሩ ነው ብዬ ያደረኩት በዜሮ ቢባዛም ደስ ብሎኛል። በእኔ እንባ በኩል እሱ ሲስቅ ቢኖር እንኳን ደስታዬ አይቆምም። በመሃይምነቴ አዝናለሁ እንጂ በእሱ አላዝንም። በመልከ ጥፉነቴ  አቀረቅራለሁ እንጂ በእሱ አልከፋም። ድርሰትና ደራሲን ባለማወቄ እቆጫለሁ እንጂ፣ በእሱ ቅር አይለኝም። ከፍቅር ማህፀኔ የተወለደችው ቅርታ እንኳን አሁን ደብዝዛ ጠፍታለች።

Read 991 times