Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 20 October 2012 10:21

ለመኖር የሚደረግ ሩጫ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

የምግብ እጥረት በዓለም አቀፍ ደረጃ በየዓመቱ ለሚከሰተው የሁለት ሚሊዮን 6መቶ ሺ ህፃናት ሞት መሰረታዊ ምክንያት ነው
በኢትዮጵያ ውስጥ ከሚኖሩ ህፃናት 44 በመቶ የሚሆኑት በምግብ እጥረት የጫጩና ሰውነታቸው የመነመነ ነው፡፡
“በእኛ ት/ቤት ውስጥ ካሉ ተማሪዎች መካከል አንዳንዶቹ ምግብ ሳይበሉ ወደ ትምህርት ቤት ስለሚመጡ ቶሎ ይደክማቸዋል፡፡ የምንማርበት ጠረጴዛ ላይ ተኝተው ብዙ ጊዜ አስተማሪ ገርፏቸዋል፡፡ በጣም ሲርባቸው በእረፍት ሰዓት እየወጡ ብዙ ውሃ ይጠጣሉ፡፡ አንዳንዴም በቃ ትምህርቱን ጥለው ወደቤታቸው ይሄዳሉ፡፡ በማግስቱ ሲመጡ ግን መገረፋቸው አይቀርም፡፡ ስም ሲጠራ ስለማይኖሩ አቤት አይሉም፡፡ አስተማሪው በማግስቱ ይገርፋቸዋል፡፡

አንዳንዴ ደግሞ ጢቢኛ ምናምን ይዘው የሚመጡ ልጆች ያካፍሏቸዋል፤ እነዚህ ልጆች ሁልጊዜም ያሣዝኑኛል፡፡ ግን የምሰጣቸው ነገር የለኝም፡፡ ሕፃናት በምግብ እጥረት እንዳይቸገሩና እንዳይሞቱ ለመንግስት ለማሣወቅ ሩጫ ሊደረግ ነው ሲባል ሰምቼ በጣም ደስ አለኝ፡፡ አስተማሪዎቻችን ከየክፍሉ የሚሮጡ ህፃናትን ሲመርጡ እኔንም መረጡኝና ዛሬ ልሮጥ መጣሁ” ያለው የአስራ ሁለት ዓመቱ ህፃን አደም እድሪስ ነው፡፡ በአማራ ክልላዊ መንግስት በደሴ ከተማ ውስጥ በኤቭሪዋን ካምፔን (ሁሉም ዘመቻ)፣ ሴቭ ዘ ችልድረን (ህፃናት አድን ድርጅት) ሰሜን ቢሮ እና የአማራ ክልል ሴቶች ማህበር በጋራ አዘጋጅነት ለሚካሄደው የማራቶን ሩጫ ውድድር አምባራስ ሆቴል ፊት ለፊት ከተሰበሰቡ ህፃናት መካከል አግኝቼ አደምን ለቃለመጠየቅ ስጠይቀው ፍቃደኝነቱን ያለምንም ማቅማማት ፈቀደልኝ፡፡
በቢለን ትምህርት ቤት ውስጥ የአራተኛ ክፍል ተማሪ ለሆነው ህፃን አደም የተመጣጠነ ምግብ መመገብ የሰማይ ያህል ቢርቅበትም ሆዱ እንዲሞላ ግን ይቀምሰው ነገር አያጣም፡፡ በአሮጌ ልብስ ስፌት ሥራ የሚተዳደሩት አባቱ ሲሆኑ አደምን ጨምሮ ሰባት ልጆቻቸውና ባለቤታቸው የሳቸውን እጅ ጠባቂዎች ናቸው፡፡ ከእህትና ወንድሞቹ መካከል አራቱ ውሎአቸው ትምህርት ቤት ሲሆን ሁለቱ እድሜያቸው ገና ለትምህርት ባለመድረሱ ከእናታቸው ጋር በቤት ውስጥ ይውላሉ፡፡
የአደም ወላጆች ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤት ለመላክ ብዙ ዋጋን ከፍለዋል፡፡ ኑሮአቸው ከእጅ ወደ አፍ የሆነና እጅግ አነስተኛ ገቢ የሚያገኙ ቢሆንም ልጆቻቸው ከትምህርት ብርሃን ርቀው እንዲቀሩ ፈፅሞ ፍላጐት አልነበራቸውም፡፡ እናም ከሚያስፈልጋቸው መሠረታዊ ነገሮች ሁሉ ቀንሰው ልጆቻቸውን ለማስተማር ቅድሚያ ሰጡ፡፡ ስለዚህም እነ አደም በቤት ውስጥ የሚመገቡት ነገር እንደነገሩ ሆነ፡፡ አደምን ስመለከተው ዕድሜው ከ7-8 ዓመት ሊሆነው እንደሚችል ብገምትም የተወለደው ግንቦት 18/1993 ዓ.ም መሆኑን ገልፆ አስራ ሁለተኛ ዓመት ዕድሜው ላይ መድረሱን አስቆጠረኝ፡፡ የጫጫው አካሉና ያጠረው ቁመቱ ከእድሜው በታች እንድገምተው እንዳደረገኝ ገባኝ፡፡ ይህ ደግሞ እንደ ብዙዎቹ ኢትዮጵያውያን ህፃናትና ልጆች በተመጣጠነ ምግብ እጥረት አማካኝነት የሚከሰት የሰውነት መመንመንና መቀጨጭ ችግር ነው፡፡ ለከፍተኛ የምግብ እጥረት የተጋለጡ ህፃናት አዕምሮአዊና አካላዊ እድገታቸው የጫጫ ይሆናል፣ የማገናዘብ፣ የመመራመር ችሎታቸው ይቀንሣል፣ ትምህርታቸውን በአግባቡ ለመከታተልና የተሻለ ውጤት ለማምጣት ይቸገራሉ፡፡ ከዚህም ባለፈ እጅግ አስጊ ለሆኑ የጤና ችግሮች ሊጋለጡ ይችላሉ፡፡ እንደ አለም ጤና ድርጅት መረጃ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ህፃናትን ለኒሞኒያና ለተቅማጥ በሽታ እንዲጋለጡ ያደርጋቸዋል፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ከሚኖሩ ህፃናት መካከል 44 በመቶ የሚሆኑት በምግብ እጥረት የጫጩና ሰውነታቸው የመነመነ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ከሚወለዱ 8 ህፃናት መካከል አንዱ አምስተኛ ዓመት ልደቱን ሣያከብር ይሞታል፡፡ የምግብ እጥረት በአለም አቀፍ ደረጃ በየዓመቱ ለሚከሰተው የሁለት ሚሊዮን ስድስት መቶ ሺህ ህፃናት ሞት መሠረታዊ ምክንያት ነው፡፡ አሁን ያሉት ሁኔታዎች እንዳሉ ከቀጠሉ፣ በሚቀጥሉት 15 ዓመታት ውስጥ በአለም አቀፍ ደረጃ 450 ሚሊዮን ህፃናት የመጫጨት ችግር ይገጥማቸዋል፡፡
የተመጣጠነ ምግብ እጥረት በህፃናት አዕምሮአዊና አካላዊ እድገት ላይ የሚያስከትለውን ተፅዕኖና ከዚህም ባለፈ በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ህፃናት ሞት መሰረታዊ ምክንያት ስለመሆኑ ግንዛቤ የሚያስጨብጥና ለመፍትሄው ሁሉም በጋራ መሥራት እንዳለበት የሚያስገነዝብ የማራቶን ውድድር ባለፈው ማክሰኞ በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ደሴ ከተማ ውስጥ ተካሂዶ ነበር፡፡ ውድድሩን የሴቭ ዘ ችልድረን ኤቭሪዋን ካምፔን (ሁሉም ዘመቻ)፣ የሴቭ ዘ ችልድረን ሰሜን ቢሮ እና የአማራ ክልል ሴቶች ማህበር በጋራ አዘጋጅተውታል፡፡
የዓለም የምግብ ቀን በሚከበርበት ዕለት ውድድሩ በዓለም አቀፍ ደረጃ በአርባ የአለም አገራት ውስጥ የተካሄደ ሲሆን ኢትዮጵያም ውድድሩን ካካሄዱት አገራት አንዷ ነበረች፡፡ በደሴ ከተማ ውስጥ በሚገኙ 36 ትምህርት ቤቶች ውስጥ የሚማሩ 2500 ዕድሜያቸው ከ11-13 ዓመት የሚደርሱ ህፃናት ውድድሩን አካሂደዋል፡፡
በዱላ ቅብብል መልክ የተካሄደው ውድድሩ፣ 42 ኪሎ ሜትር ከ195 ሜትር ርቀትን የሚሸፍን ሲሆን በ31 ቡድኖች በተከፈለው በህፃናቱ ውድድር እያንዳንዱ ህፃን 200 ሜትር ርቀትን እንዲሮጥ ተደርጓል፡፡ በውድድሩም የሜጠሮ ትምህርት ቤት ተማሪና የአስራ ሶስት ዓመቱ ታዳጊ መሀመድ አስራት አሸናፊ ሆኗል፡፡ 2 ሰዓት ከ40 ደቂቃም የውድድሩ ማጠናቀቂያ ሰዓት ሆኖ ተመዝግቧል፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ የዚህ ውድድር ሪከርድ በፓትሪክ ማኩ የተያዘ ሲሆን ይህም 2 ሰዓት ከ03 ደቂቃና ከሰላሳ ስምንት ሰከንድ ነው፡፡
Race for survival (ለመኖር የሚደረግ ሩጫ) የሚል ስያሜ የተሰጠው ይኸው የህፃናት የማራቶን ውድድር፤ በተመሳሳይ ሰዓትና ቀን በዓለማችን ውስጥ በሚገኙ አርባ አገራት ውስጥ ተደርጓል፡፡ በውድድሩም በአለም አቀፍ ደረጃ 20ሺህ የሚደርሱ ህፃናት ተካፍለዋል፡፡ የማራቶን ውድድሩ ዋንኛ ዓላማም በምግብ እጥረት ምክንያት የሚሞቱ ህፃናትን ቁጥር ለመቀነስና ህፃናት የተመጣጠነ ምግብ መመገብ እንደሚገባቸው ለህብረተሰቡ ግንዛቤ ለማስጨበጥ እንደሆነ የተናገሩት በሴቭ ዘ ችልድረን የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ሚስተር ኔድ ኦልኒ ይህም አገሪቱ ከአምስት አመት በታች የሆኑ ህፃናትን ሞት ለመቀነስ ለዘረጋችው ዕቅድ ተግባራዊነት የበኩሉን አስተዋፅኦ ያደርጋል ብለዋል፡፡
ቀደም ሲል በሰባት የተለያዩ አገራት ይተዳደር የነበረው ሴቭ ዘ ችልድረን እ.ኤ.አ ከኦክቶበር 1/2012 ዓ.ም ጀምሮ ወደ አንድ እንዲጠቃለል በተደረገው መሠረት ሁሉም የሴቭ ዘ ችልድረን ተቋማት ወደ አንድ መጠቃለላቸውን የገለፁት ዳይሬክተሩ ይህም የተቀናጀና ጥምረት ያለው ሥራ ለማከናወን ከፍተኛ እገዛ ያደርጋል ብለዋል፡፡ የኤቭሪዋን ካምፔይን (የሁሉም ዘመቻ) አስተባባሪ አቶ ተስፋ ገሰሰ በበኩላቸው ሴቭ ዘ ችልድረን በአገሪቱ የተለያዩ ክልሎችና ለትራንስፖርት አመቺ ባልሆኑ አካባቢዎች ሁሉ በመሄድ አገልግሎት በመስጠት ላይ መሆኑን ጠቁመው የድርጅቱ ዋና ዓላማም የእናቶችንና ህፃናት ሞት ቁጥር ለመቀነስና ህብረተሰቡ በጉዳዩ ላይ ግንዛቤ ኖሮት ትኩረት እንዲያደርግበት ማሳሰብ ነው ብለዋል፡፡ አያይዘውም ይህም መንግስት ላቀደው በ2015 የህፃናትን ሞት በ2/3ኛ ለመቀነስ ዓላማ ላደረገው የሚሊኒየም ግብ መድረስ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው ተናግረዋል፡፡ እ.ኤ.አ በ2009 ዓ.ም በ36 አገሮች በይፋ የተጀመረው የኤቭሪዋን ካምፔይን (የሁሉም ዘመቻ) በአገራችን በከፍተኛ ደረጃ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ መሆኑንና በየክልሎች ገጠራማ አካባቢዎች በመድረስ ህብረተሰቡን የማስተማርና የመቀስቀስ ሥራ በመከናወን ላይ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
ኢትዮጵያ ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ ህፃናትን ሞት በ40% ብትቀንስም አሁንም አገሪቱ በዓለም በየዓመቱ በርካታ ህፃናት ከሚሞቱባቸው አገራት መካከል አንዷ ነች፡፡ በየዓመቱም ከ17ሺ በላይ እናቶችና ከ100ሺ በላይ ጨቅላ ህፃናት በእግርዝናና ከወሊድ ጋር በተገናኙ ጉዳዮች ህይወታቸው ያልፋል፡፡
በ2011 የተደረገው የኢትዮጵያ የሕዝብና የጤና ጥናት (DHS) እንደሚያመለክተው፤ ከአምስት ዓመት እድሜ በታች የሆኑ ሕፃናት የሞት ደረጃ ከአንድ ሺህ በህይወት ከተወለዱ ህፃናት መካከል 88 ደርሷል፡፡

Read 3764 times