Saturday, 10 September 2022 21:45

ሙዚቃና ዓውደ ዓመት መንፈሳዊም ዓለማዊም!!

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(1 Vote)

የቀን አቆጣጠር ስርዓት ኢትዮጵያ ውስጥ የተፈጠረው ከ3000 ዓመት በፊት እንደሆነ የታሪክ ተመራማሪዎች ይገልጻሉ። የሙዚቃ መሳሪያዎች ታሪክም፤ የዚያኑ ያህል ረዥም ነው። “ምን አገናኛቸው?” እንል ይሆናል እንጂ፤ የቀን አቆጣጠርና የሙዚቃ ታሪክ አብረው ያልገነኑበት የሥልጣኔ ዘመን ወይም የስልጣኔ አገር የለም።
“ዳዊት በበገና፣ እዝራ በመስንቆ” ተብሎ የለ! ክራርና በገና፣ ማሲንቆና ዋሽንት በሁሉም የስልጣኔ ቦታዎች ነበሩ። በኢትዮጵያና በእስራኤል፣ በግብፅና በመሰፖታሚያ፣… እና በግሪክ።
ከጥንታዊ የሥልጣኔ ቡቃያነታቸው በተጨማሪ፣ ሙዚቃና የቀን አቆጣጠር በባሕርያቸው “ሁሉን-አቀፍ” መሆናቸውም ያመሳስላቸዋል። ሰው ሳይለዩ፣ በተከፈተ ዓይንና ጆሮ ገብተው የአእምሮ በሮችን እያንኳኩ ይደመጣሉ። ችቦ እየለኮሱ የሰውን አእምሮ ያደምቃሉ። ሕፃን አዋቂውን እየማረኩ፣ ሁሉንም ሰው ያቅፋሉ። ሥረ መሠረታቸው ሰፊ ነው።
ነገር ግን ደግሞ፣ የቀን አቆጣጠርና የሙዚቃ ስልቶች፣ ተራውን ሰው ይቅርና፣ ጠቢባንንና ሊቃውንትን የሚፈትን ውስብስብ ባሕርይና እምቅ ኃይል አላቸው። በዚህ ባሕርያቸውም ይመሳሰላሉ። ረቂቅነታቸው ተገላልጦ አያልቅም። ጥልቅ ምስጢራቸው ተዝቆ አይነጥፍም።
በአንድ በኩል፣ የከበሮ ትርታና የዜማ ጅረት፣ “ያለ ጥረት፣ እንደ ዘበት” በገሀድ በአደባባይ የሚደመጡ እውነታዎች ናቸው። የንጋትና የምሽት ዑደት፣… “እንኳን ፈልገን ይቅርና ሳንፈልግም”፣ በየእለቱ በግላጭ የሚታዩ ክስተቶች ናቸው። የነሐሴ ልምላሜና የመስከረም አደይ አበባ አምረውና ደምቀው ተከታትለው ሲመጡ፣ ተመልካችን ይጣራሉ። የተጨፈኑ ዓይኖችን ይከፍታሉ። አናይም ብንል ቀረብን እንጂ፣ ውበትና ድምቀታቸው ተመልካች አያጣም። እንኳን ሰው፣ ወፎችም አብረው ያጌጣሉ፤ ይዘምራሉ።
ምናለፋችሁ! የቀንና የሌሊት፣ የክረምትና የበጋ ዑደቶችን ለመገንዘብ፣ ብዙ መራራቅ አያስፈልግም። የምርምር ድካም አይጠይቅም። ዘፈን የምንሰማውም ያለ ጥረት ነው። ራሱ ዜማው ይጣራል፣ ከመቼው እንደማረከን ሳናውቀው እንመሰጥበታለን። የሙዚቃው ኃይል በራሱ ጉልበት፣ ያነቃንቀናል።  
በሌላ አነጋገር፣ የቀን አቆጣጠርና የሙዚቃ ስልቶች፣ ለሁሉም ሰው የሚያቅፉ በረከቶች ናቸው። ህጻን አዋቂው ሁሉ፣ ያለ ብዙ ጥረትና ያለ ብዙ ምርምር፣ በእውን ሊያያቸው ሊሰማቸው ይችላል።
ዜማ ለመስማት ልዩ የሥልጠና ማዕከል አንገባም። እንዲያውም፣ ዜማ ከመስማት አልፈን፣ እንደ ነገሩ በየራሳችን ልሳን ለማዜም እንሞክራለን። አብዛኛው ሰው፣ ቀለል ያለ አጭር ዜማ ሰምቶ ለማጣጣም፣ ከዚያም ለማንጎራጎር አይከብደውም - ለዚያውም ከህፃንነት እድሜ ጀምሮ ነው።
በአጭሩ፣ የቀን አቆጣጠርና የሙዚቃ ስልቶች፣ በእውን እየተከሰቱ በቀላሉ የሚታዩ፣ በአደባባይ እየታወጁ አየር-ባየር የሚደመጡ ግልፅ ነገሮች ናቸው። እንደ ዋዛ፣ እግረ መንገዳችንን ማድመጥም እንችላለን። ሌላ ነገር እየሰራን፣ እናዜማለን። አይከብድም። ቀንና ሌሊት እንደማይጠፉብን ሁሉ፣ ጫጫታና ሙዚቃ፣ ኳኳታና ዜማ አያሳስቱም። የቀን ፀሐይና የሌሊት ጨረቃ፣ ብርሃንና ጨለማ ምስጢር አይደሉም። ክረምትና በጋ፣ ልምላሜና አቧራ  አያምታቱም።
እናም፣ “ሙዚቃና የቀን አቆጣጠር ስልቶች”፣…. ሁሉንም ሰው የሚያቅፉ፣ የሁሉም ሰው ንብረት ናቸው ማለት ይቻላል። ተመራማሪና ጥበበኛ መሆን የማያስፈልጋቸው ፀጋዎች ይመስላሉ።
በሌላ በኩል ግን፣ ከቀላል እስከ ውስብስብ፣ ከግልፅ እስከ ስውር፣ መልከ ብዙ ናቸው።  ከስፋታቸውና ከጥልቀታቸው የተነሳ ለግንዛቤ በጣም የሚያስቸግሩ የምስጢር ባለፀጎች ናቸው። በእርግጥ ምትሃት ወይም ቅዠት አይደሉም። ሊታወቁ ይችላሉ። በትንሽ በትንሹም ቢሆን፣ ሁሉም ሰው ያውቃቸዋል። ነገር ግን፣ ተመርምረው ተገልጠው የሚያልቁ ምስጢሮች አይደሉም። ባወቅን ቁጥር፣ ብዙ ያላወቅናቸው ገጽታዎችን እየተላበሱ በጭላንጭል ያሳዩናል። ለተጨማሪ እውቀት በጨረፍታ ብሩህ መንገድ እየጠቆሙ ያጓጉናል። በመረመርንና በተገለጹልን ቁጥር፣ በቀለማት ሕብር የተዋበ ሌላ ተጨማሪ ምስጢር በውስጣቸው እንዳቀፉ ሹክ ይሉናል። ጠልቀን እንድንገባ ይጠሩናል።
ምስጢራቸው እየረቀቀና እየተጠላለፈ አእምሮን ይፈታተናል። ከብዙ ጥናትና ከረዥም ጊዜ በኋላ፣ “አወቅነው፣ ቻልነው፣ ቀመሩን ደረስንበት፣ ስልቱን ተካንበት”… ብለን በርችት የምንመረቅ ይመስለናል። ነገር ግን፣ ከፍታ ላይ ስንወጣ፣ ዙሪያ ገባውን ስናማትር፣ ካሁን በፊት ያላየናቸው ሰፋፊና ጥልቅ ሚስጥሮችን እናያለን። ገና ቀላል ቀላሉን ነው ለካ ያወቅነው ያሰኘናል።
የሙዚቃና የዓለማት ዑደት፣… የግልፅነታቸውና የቀላልነታቸው ያህል፣ በዚያው መጠን፣ ጥልቀታቸውና ስፋታቸው፣ ርቀታቸውና ረቂቅነታቸው፣… ብዙ መራቀቅን እጅግ መጠበብን ይጠይቃል።
ምስጢር ከተባለ ከዚህ በላይ ምን ሚስጥር አለ? ሙዚቃ፣ ምስጢሩ ተከፍቶ ሊመረመር የማይችል “ምትሃት” አይደለም። ግን ደግሞ፣ እንዲሁ ስታስቡት፣ የሙዚቃ ኃይል ምትሃት ነው ብንል ይበዛበታል?
ዜማውና ግጥሙ፣ ከበሮውና ጭብጨባው፣ ሕብረ-ዝማሬውና ውዝዋዜው፣… እንዴት እንዴት ሲሆን ነው የሚያምረው? በምን ተዓምር ነው ነፍሳችንን የሚሾረው?
ድምፃዊያን በጥበብ ሲያቀነቅኑት፣ የዜማው ውበት ተዓምረኛ ነው። አንዳንዴ፣ እንደ ንሥር ያከንፈናል። ሌላ ጊዜ እንደ ለምለም መናፈሻ ያረጋጋናል። መንፈሳችንን በንፁሕ አየር ያድስልናል። ሲያሰኘው እንደ ማዕበል ወዳሰኘው አቅጣጫ፣ ከፍ ዝቅ እያደረገ ያነጉደናል። እንደ ነጎድጎዳማ ፏፏቴ አገር ምድሩን፣ ስጋና ነፍሳችንን እየናጠ፣… ከአፍታ በኋላ የቀስተ ደመና ሕብረ ቀለማትን ዘርግቶ የሚያስጠልል ይመስላል። እፎይታን ያላብሳል።
ጥበበኛ ሰዎች የሚፈጥሩት ሙዚቃና የሚያቀነቅኑት ዘፈን፣ እውነትም ተዓምረኛ መንፈሳዊ ኃይል አለው። የማይመረመር ጥልቅ ምስጢር ይመስላል። አስገራሚው ነገር፣ ጥበበኛ ባንሆንም እንኳ፣ የጥበበኛውን ሙዚቃ ማጣጣም እንችላለን - በከፊልም ቢሆን ይገባናል። በትንሹም ቢሆን እናዜመዋለን።
ጥበበኛው ሲዘፍንልንና፣ ተራው ሰው እንደ አቅሚቲ ሲያንጎራጉረው፣… የዜማቸውና የድምፃቸው ጣዕም እጅግ ቢራራቅም፣ የትኛውን ዘፈን እያዜሙ እንደሆነ ለማወቅ አይቸግረንም። ጣዕማቸውና ውበታቸው እንደሚለያይ ለመገንዘብም አይከብደንም። ቀላል ነው። ጥያቄን ስናከብደውስ? “የዘፈናቸው የዜማ ተመሳሳይነት፣ እንዲሁም የድምፃቸው የውበት ልዩነት የት ላይ ነው?” ብለን እንጠይቃለን።
ለነገሩ ሩቅ መሄድ አያስፈልገንም። የሙዚቃ መሳሪያዎች የሚፈጥሩት የድምፅ ዓይነት፣ ከነመአዛውና ከነቀለሙ በጣም ይለያያል። ሌላው ቀርቶ፣ ሁለት ተመሳሳይ ክራሮች እንኳ የየራሳቸው ድምፅ አላቸው።
ቢሆንም ግን፣ የሙዚቃ መሣሪያዎች ድምፅ ቢለያይም፣… ማሲንቆ ወይም ቫዮሊን፣ ዋሽንት ወይም ሳክስፎን፣ ክራር ወይም በገና፣ ፒያኖ ወይም ጊታር፣ መሣሪያው ምንም ሆነ ምን፣ ዜማውን ለማወቅ አይከብደንም። በክራር የሰማነው ዜማ፣ በዋሽንት ስናደምጠው ተመሳሳይነቱን ለማየት አይቸግረንም። ይሄ ማለት ግን፣ በምናቸው እንደሚመሳሰሉ በወጉ መረዳትና፣ በምናቸው እንደሚለያዩ በቅጡ መተንተን ቀላል አይደለም።
የሙዚቃው እርምጃ ወይም የከበሮው ትርታ፣… በእርከን ከከፍታ እየወረደ ከሚረጋጋ የዜማ ጅረት፣ በስክነት ከስር ተነስቶ ሽቅብ እየናረ ከሚገሰግስ የዜማ ግልቢያ ጋር፣ እንዴት ነው ተስማምቶ የሚዋሐደው?
የከበሮ ድግግሞሽና የድምፆች ትርታ፣ የዜማ ጅረትና ግልቢያ ብቻ አይደለም። የዘፈኑ ግጥምና አደራደር፣ የቃላትና የሀረጋት መልዕክትም፣… በየራሳቸው ስልት ይለያያሉ። እንዴት ተገጣጥመውና ተጣጥመው፣ እንዴት በህብር ሰምረው ውበትን እንደሚፈጥሩ ማወቅ፣ በጣም ከባድ ነው።
ሌላውን ሁሉ ብንተወው እንኳ፣ ከአንድ የሙዚቃ መሣሪያ የምንሰማው ዜማም፣ በሚስጥሮች የበለጸገ ነው።
በ6 ክሮች የሚፈጠሩ 6 ዓይነት የክራር ድምፆችን ብቻ ብናይ፣ በምን ዓይነት ቅንብር ስንትና ስንት ዜማዎች በጥበብ እንደሚፈልቁ አስቡት። ማለቂያ ያለው አይመስልም። ሊታወቅ የማይችል ምስጢር ቢሆንብን አይገርምም። ባለብዙ ምስጢር ነውና።
ነገር ግን፣ ሌላ ሌላውን ሁሉ ትተን፣ ከ6 ክሮች የሚወጡ ድምፆች በምን ስሌት ተቃኝተው፣ እንዴት እርስ በርስ ሰምረው፣ በምን መንገድ የዜማ ጣዕም እንደሚፈጥሩ ማወቅ ይሳነናል? አዎ ይሳነናል። ተመራማሪዎችና ጥበበኞች ቢያስተምሩን ግን አይከብደንም። ታውቆ የሚያልቅ ባይሆንም፣ ምስጢሩን ከስር ከስር በትንሽ በትንሹ የሚያፍታቱ ጠቢባን አልጠፋም። የመጀመሪያው ሊቅ ፓይታጎራስ ነው። የሂሳብ፣ የስነ-ፈለግ፣ የሙዚቃ፣ የፍልስፍና፣ የሃይማኖት ሊቅ ነው - ፓይታጎራስ።
ክራርን በትክክል ለመቃኘት የተለያዩ ዘዴዎችን መጠቀም ይቻላል። የክሮቹን ቁመት በስሌት በእርከን አበላልጦ ማዘጋጀት አንድ የቅኝት ዘዴ እንደሆነ ፓይታጎራስ አስተምሯል።
ግን ሌላ ዘዴም አለ። ክሮቹ በትክክል በስሌት በመወጠርና በማክረር፣ ክራራችንን መቃኘት እንችላለን። ስድስተኛው ክር ከመጀመሪያው ክር ጋር ሲነፃፀር፤ አራት እጥፍ መክረር አለበት። 4 ኪሎ ግራምና 16 ኪሎ ግራም እንደማንጠልጠል ነው - ልዩነታቸው። አራተኛው ክር ላይ ደግሞ፣ 9 ኪሎ ግራም እንደማንጠልጠል ማለት ነው።
ሦስተኛው ዘዴ፣ የክሮቹን ውፍረት በስሌት አበላልጦ መምረጥና መወጠር ነው። ከስድስተኛው ክር ጋር ሲነፃፀር፣ የመጀመሪያው ክር እጥፍ ይወፍራል። ድምጹም እጥፍ ያህል ይወፍራል። አራተኛው ክር ደግሞ አንድ ተኩል ያህል ይወፍራል።
በእኩል መጠን የተወጠሩና እኩል ውፍረት ያላቸው ክሮችን መጠቀም ከፈለግን ደግሞ፣ በሰንጠረዡ ላይ በምናየው ስሌት ክራራችንን መቃኘት እንችላለን። የክሮቹን ቁመት በስሌትና በእርከን አበላልጠን እናዘጋጃለን። የመጀመሪያው ክር፣ ከ6ኛው ክር ጋር ሲነፃፀር፣ ቁመቱ እጥፍ መሆን አለበት። በሰንጠረዡ ላይ በሚታየው ስሌት ክሮቹ ሲዘጋጁ፣ ክራሩ ተቃኘ ማለት ነው።
ይህ፣ እንዲሁ በእይታ ወይም እንዲሁ በመስማት ብቻ የሚታወቅ አይደለም። የምርምር የጥበብ ሰዎች ናቸው የሚያውቁት። ከዚያም ለኛ የሚያስተምሩን። ነገር ግን፣ የሙዚቃን ምስጢራት ይቅርና፣ የቅኝት ዓይነቶችን ሁሉ ከነጣዕማቸው አብጠርጥረው አውቀዋል ማለት አይደለም። አውቀው አልጨረሱትም። ታውቆ የሚያልቅ ነገር አይደለም። ሁሉም በእውቀት የሚያበለጽግ ጥልቅ ሚስጥር ነው። መንፈሳዊ ነው። ቢሆንም ግን፣ መንፈሳዊ የመሆኑ ያህል፣ በቁጥር ይገለጻል።
የዓለማት ዑደትና ጅረትም እንደዚያው የምስጢራት ባለፀጋ ነው።
“ጅራታም ኮኮብ”፣… እንደ ትንግርት ናቸው። በስንት ጊዜ አንዴ ነው ሰማይ ላይ የሚታዩት። ብርቅ ስለሆኑም፤ የአገር ወሬ ይሆናሉ። ዝነኛ ናቸው። ስለ ጅራታም ኮኮብ መስማታችን አይቀርም አይተን ባናውቅ እንኳ።
እንደ ስማቸው በመልክ መለየታቸውም፣ የሰው መነጋገሪያ እንዲሆኑ አደርጓቸዋል። ጅራታም ናቸው።  የከዋክብት ባሕርይ ከዚህ ይለያል። ዘወትር የምናያቸው ከዋክብት፣ በጨለማው ጠፈር ላይ የተነደፉ አብረቅራቂ እንቁዎች ይመስላሉ። “ጭል ጭል” እያሉ የሚብለጨለጩ ብርሃናት፣ ከዋክብት ናቸው። ርቀት ቢያግዳቸው እንጂ፣ እንደ ጸሐይ በጣም ኃይለኛ ናቸው። ብዙዎች ከዋክብት፣ በግዝፈትና በጉልበት ከጸሐይ በብዙ እጥፍ ይበልጣሉ።
ጭልጭል የማይሉ የብርሃን ነጸብራቆች ደግሞ አሉ። በተለምዶ ከዋክብት ተብለው ቢሰየሙም እንደ ምድር ናቸው- ፕላኔቶች (ዓለማት) ይሏቸዋል።
እንደ ጨረቃ፣ የጸሃይ ብርሃንን ያንጸባርቃሉ እንጂ የብርሃን ምንጭ አይደሉም። ለምድራችን ቅርብ ስለሆኑም ደምቀው ይታያሉ። አያብረቀርቁም።
በአጭሩ፣ የማይርገበገብ ደማቅ ኮከብ ካያችሁ፤ ፕላኔት እንጂ ኮኮብ አይደለም።
ከአንድ ሰዓት በኋላ ቀና ብላችሁ ስትመለከቱ፣ ከሌሎቹ ከዋክብት ቀድሞ ወደ ምዕራብ አቅጣጫ የተጓዘ ኮኮብ ካያችሁ፤ ፕላኔት እንጂ ኮኮብ አይደለም።
እንዲህ ሲናገሩት፣ በብዙ ምዕተ ዓመታት ምርምርና ልፋት የተገኘ እውቀት አይመስልም።
በተለይ የፕላኔቶች ነገር ስንቱን ተመራማሪ ሲያስገርም ሲስጨንቅ የኖረ ነው።
የሌሎቹ ከዋክብት አቀማመጥና የእለት ለእለት ዑደት፣ ለአስተዋይ አእምሮ ላያስቸግር ይችላል። ከዋክብት አይሽቀዳደሙም፤ አይዘናጉም። አሰላለፋቸው ሳይዛነፍ በዝግታ ከምስራቅ ወደ ምዕራብ ይዋኛሉ።
በቀስታ የሚሽከረከር ጉልላት ላይ የተጠለፉ ጌጦች ይመስላሉ። ሁሉም ሌሊቱን  አብረው ይጓዛሉ። በዝታ። በዚያ ላይ ከእለት ተእት ቦታቸውን ብዙም አይቀይሩም። ትናንት ማታ እከለ ሌሊት ላይ ያየናቸው ኮኮቦች፣ ዛሬ በተመሳሳይ ሰዓት አራት ደቂቃ ቀደም ብለን ብንመለከት እዚው ቦታ ላይ እገኛቸዋለን። ነገም እንዚያው። በየቀኑ በአራት ደቂቃ ልዩነት። ከዚህ ቀመር የሚዛነፍ ኮኮብ የለም ማለት ይቻላል።
ጨረቃ ደግሞ አለች። በተመሳሳይ አቅጣጫ ከምስራቅ ወደ ምዕራብ ትቀዝፋለች። ግን በግስጋሴ ነው። ፕላኔቶችም እንደዚያው።
በዚህ ምክንያት፣ ጨረቃና ፀሐይ፣ ቬነስና ማርስ የመሳሰሉ ዓለማት፣ እንደ ሕያው አካል እየተቆጠሩ ለብዙ ዘመናት በአምልኮ ተዘምሮላቸዋል። የአማልክት መንኮራኩር ናቸው በሚል እምነት በጥንት ዘመን ተተርኮላቸዋል።
በአጭሩ ከዋክብትና ዓለማትን ስናነጻጽራቸው፣ ነባር ባህልን እና ወቅታዊ ሃሳቦችን እንደ ማስተያየት ሊሆን ይችላል። የሽምግልናና የጉርምስና ምሳሌ ተደርገውም ይታዩ ነበር። የእልፍ አእላፍ ከዋክብት የእለት ተእለት ዑደትና አሰላለፍ፣ ተመሳሳይ ነው። የፕላኔቶች ዑደትና እንቅስቃሴ ግን  የችኮላ ነው። ምን ይሄ ብቻ። የፕላኔቶች ዑደት ወሰብሰብ ይላል። ብዙ ተመራማሪዎችን ሲምታቱ ስንት ዘመናቸው!
እንቅስቃሴቸውን በቅጡ ለማገናዘብ አስቸጋሪ ቢሆንም፣ በዘፈቀደ ይደናበራሉ ማለት አይደለም።
የጅራታም ኮከብ እንቅስቃሴ ግን፣ “የዘፈቀደ” የሚሉት አይነት ነው። በአንድ በሁለት ዓመት የሆነ ጅራታም ኮኮብ ይታያል። ከአራት ከአምስት ዓመት በኋላ ሌላ ጅራታም ኮኮብ ለጥቂት ቀናት ሰማዩን ይጋልብበትና ይጠፋል።
ተመራማሪዎች፣ ለበርካታ ምዕተ ዓመታት የጅራታም ኮኮቦችን ክስተት ቢመዘግቡም፣ ዑደታቸውን ለመገንዘብ ቀላል አልሆነላቸውም። አመጣጣቸው ድንገተኛ ነው። ከጥቂት ቀናት በኋላ በየት በኩል ሄደው ወዴት እንደሚያቀኑ ሳይታወቅ ሰፊውን ሰማይ ተሰናብተው ይወጣሉ።
የወሬ መዓት ለኩሰው ይጠፋሉ። “የእግዚአብሔር ቁጣ ናቸው” ተብሎ ነበር የሚታመንባቸው። ጅራታም ኮኮብ የታየ ጊዜ፣ “ጊዜው ቀርቧል፣ ምፅዓት ደርሷል። የቁጣ መዓት ይመጣል” የሚሉ ትንቢቶች ይበረክታሉ።
“ያኔ አታስታውሱም? ጅራታ ኮኮብ በታየ በዓመቱ የበሽታ ወረርሽኝ መጣና ሰውን ፈጀ። ሌላ ጅራታም ኮከብ የመጣ ጊዜ፣ ከተማዋ በእሳት አልጋየችም?”... እንደዚህ የተወራላት ከተማ የእንግሊዟ ለንደን ከተማ ናት። የዛሬ 350 ዓመት ገደማ ነው። ከዚያስ?ወሬው ገና ሳይረሳ፣ ከጥቂት ዓመታት በኋላ ሌላ “ጅራታም ኮኮብ” መጣች። በእርግጥ የያኔው ዘመን እንደቀድሞው አይደለም። የኒውተን ጊዜ ነው። የፕላኔቶች የዑደት ቀመር ተገጦለታል የሳይንስ ዘመን ተወልዷል። ከመዓትና ከምፅዓት የተለየ፣ ሌላ “የትንቢት ዓይነት” በኩራት ይዞ መጥቷል። ቀመሩ የኒውተን ነው። ትንቢቱ ደግሞ የኤድመን ሃሌ ትንቢት ነው።
በ1674 ነሐሴ ወር መጨረሻ ላይ ነበር፤ ጅራታሟ ኮከብ የታየችው። ልክ የዛሬ 340 ዓመት መሆኑ ነው።
እንደወትሮው አስፈሪ የአደጋ ትንቢቶች መወራታቸው አልቀረም። የኤድመንድ ሃሌ ትንቢት ግን ከሁሉም ይለያል።
ኤድመንድ ሃሌ ጅራታሟ ኮኮብ፣ ከሰባ አምስት ዓመታት በላይ በ1751 ታህሳስ ወር ላይ እንደምትመጣ ተነበየ።
እንደዚያ ዓይነት ትንቢት ከዚያ በፊት ታይቶም ተሰምቶም አያውቅም።
ለመሆኑ ጅራታሟ ኮከብ በተያዘላት ቀጠሮ ተመልሳ መጣች? ትንቢቱ ያዘለት?
በእርግጥ ኤድመን ሃሌ እና ባልደረቦቹ ገና ድሮ ሽምግልለናው በሞት ተለይተዋል። የተተነበየው ዓመትና ወር ግን መድረሱ አልቀረም። ደረሰ። የተባለው ዓመት መጣ። ታህሳስ ወር ገባ።
ጅራታሟ ኮከብ ከተፍ አለች። ጉድ ተባለ። ለኤድመንድ ሃሌ መታሰቢያም፣ ጅራታሟ ኮኮብ በስሙ ተሰየመች። ሃሌ ኮሜት ተባለች።
ትንበያው፣ በዘፈቀደ የታወጀ ትንቢት አይደለም።
የአይዛይክ ኒውተን የፊዚክስ መሠረታዊ እውቀቶችን ላይ የተመሰረተ ትንያ ነው።
ግን ደግሞ፣ ኒውተን “አዲስ ግራቪቲ”፣ “አዲስ የፕላኔቶች ምሕዋር”፣ “አዲስ የእንቅስቃሴ ዓይነት” አልፈጠረም። እውቀቱ ነው አዲስ ግኝት።
ከኒውተን በፊት “የግራቪቲ ሕግና ቀመር” የተሰኘ እውቀት አልነበረም። ዛሬ ግን ነባር እውቀት ነው።ከእውኑ ዓለም አንጻር ግን የስበት ሃይልና የዓለማት ዑደት ቀድሞም የነበሩ ወደፊትም የሚኖሩ እውነታዎች ናቸው። እንዲያውም ዘላለማዊ እና መንፈሳዊ ናቸው ማለት ይቻላል።
ከኒውተን ግኝት በኋላ ደግሞ፣ የዓለማትና የጅራታም  ኮኮቦች ዑደት፣… በቀመር በስሌት ምስጢራቱ ተገለጡ። ማለትም ይቻላል። ከዚያ በፊትስ? ከኒውተን በፊት የነበረው ዘመን ከሕፃንነት እድሜ ጋር ይመሳሰላል ይል።  አርተር ከስለር።
አርተር ኮስለር በአራት ዓመት እድሜው፣ አባቱ የነገሩትን  ትምርህርትና ምክር ያስታውሳል። አባትዬው ጣታቸውን ወደ ላይ ዘርግተው፣ እግዚሄር እዚያ ላይ ሆኖ፤ያይሃል፤ ይጠብቅሃል” ብለውታል። ሕጻኑ ኮስለር ወደ ኮርኒሱ ያያል። የሚያምሩ ስዕሎችን ይመለከታል። እነሱም ያዩታል። በየቀኑ ወደ ኮርኒሱ ይጸልያል።
የሌሊት ጨለማ እንኳን ለሕጻናት፣ ለአዋቂዎችም በጣም አስፈሪ ሊሆን ይችላል። የሚሰቀጥጡ ተረቶችን ሲሰማ የዋለና ያመሸ ሕፃን፣ ምናባዊ አስፈሪ ፍጡራን በጨለማ ነፍስ ዘርተው የሚመጡበት ቢመስለው ምን ይገርማል? ግን ችግር የለውም። እግዚሄር ከላይ ሆኖ ይጠብቀዋል። ከኮርኒስ ላይ።
 የሕጻንነት ሃሳቡ፣ ከእድሜውና ከእውቀቱ ትንሽነት አንጻር ለኮስለር አሳማኝ መስሎ ታይቶታል። አምኖበታል። ከእድሜው ጋር እውቀቱ እስካደገ ድረስ ከልጅነት የተረት ሃሳብ ጋር ተጣብቆ ካልቀረ፣ ችግር የለውም።
የጥንት ዘመን ሃሳቦችን፣ ከሕጻንነት እድሜ ጋር ያመሳስለዋል - ኮስለር። የጥንት ዘመን ሃሳቦችን እየጠቀሰም ያስረዳል።
በባቢሎን ጥንታዊ ሃሳብ መሰረት፣ ዓለማችን እንደ ድፎ ዳቦ ናት። ግን፣ ከላይና ከታች እሳት የሚለበልባት አይደለችም።
ከታች ውሃ ነው። አንዳንዴ ከስር እየፈለቀ ምድርን ያረሰርሳል። ፏፏቴ ይሆናል።
 ከሰማይ ጣሪያ ላይም ውሃ አለ። አንዳንዴ እየሰረገ ይንጠባጠባል፤ ከወንፊት ስር እንደሚወርድ ዱቄት ወደ ምድር ይዘንባል።
ፀሐይ፣ ጨረቃና ከዋክብት፣ የሰማይ ጉልላት ላይ በዝግታ ይጓዛሉ። በምስራቅ በሮች ይመጣሉ። በምዕራብ በሮች ይሄዳሉ።
በስተምዕራብ በኩል የሚገኝ የምሽት ተራራ ወደ ምድር ስር የሚያስገባ በር አለው። በዚሁ በር ወደ ከርሰ ምድር፣ ወደ መቀመቅ፣ ወደ እንጦሮጦስ ይገባሉ።
ፀሐይ በምድር ስር አድራ፣ ማግስቱ ወደ ላይ ትወጣለች። ጨረቃና ሌሎች ከዋክብት ደግሞ ከምድር ስር ውለው፣ አመሻሽ ላይ ወደ ላይ ይመጣሉ። አንዳንዴ፣ የጨረቃንና የፕላኔትን ዑደት “ከገመድ ዝላይ ጨዋታ” ጋር ያመሳስሉታል። ከእግር ስር አልፎ፣ ከአናት በላይ ዞሮ፣ እንደገና ዑደቱን ይደግመዋል።
ጥንታዊ የግብጽ አዋቂዎችም፣ የዘመናቸውን ሃሳብ ጽፈዋል። ዓለም እንደ ቤት ወይም እንደ ዳስ አድርገው ያስቧታል። ምድር ወለል ናት። ሰማይ፣… በአራት እግር እንደቆመ ጠረጴዛ ነው። ሰማይ፣ ልጆቿን ከስር ስብሰባ እንደምታጠባ ላም ነው ብለውም ጽፈዋል። ሌሎች ሰዎችም በፊናቸው፣ የሰማይን ምንነት ለመግለጽ ሞክረዋል። ከጀርባዋ ተገልብጣ በእጅና በእግር ጣቶቿ መሬት እንደነካች ስፖርተኛና ዳንሰኛ ይመስላል ይላሉ። ወይም እንደ ጣሪያ ነው - ሰማይ።
ከጣሪያው ወይም ከሰማይ ላይ፣ እንደ ፋኖስ የተንጠለጠሉ ከዋክብት አሉ።
ሰማዩ ላይ፣ እንደ አሸንዳ በተዘረጋ ወንዝ ላይ ደግሞ፣ ጸሐይና ጨረቃ በታንኳ ይጓዛሉ - በዝግታ። በየራሳቸው ሰዓት በምስራቅ በኩል ይመጣሉ። በምዕራብ በሮች ወደ ጨለማ ከርሰ ምድር ይወርዳሉ።
ሰማያዊውን ዑደት በመንፈሳዊ ዓይን ያከብሩታል። ባለ ግርማ ሞገስ ነው ይላሉ። ግን በመከራ የተሞላ ዑደት ነው። በተለይ የጨረቃ።
በወሩ በአስራ አምስተኛ ቀን ላይ፣ በሙሉ ግርማ ሞገስ እንደ አበባ ደምቃ የቆየችው ጨረቃ፣ ወሮ-በላ ይመጣባታል። አሳማ ነው። በየቀኑ ትንሽ ትንሽ እየገመጠ ይበላታል። በተለይ አንዳንዴ፣ አሳማው ድንገት መጥቶ በአንድ ጉርሻ ጨረቃዋን ይውጣታል። የጨረቃ ግርዶች ይሆናል። ፀሐይን የሚውጥ ሌላ አውሬም አለ - የፀሐይ ግርዶሽን ያስከትላል።ይሄ ግን አንዳንዴ ብቻ ነው። የጨረቃ መከራ ግን በየወሩ ነው። በአንድ ጉርሻ ሳይሆን በትንሽ በትንሽ ነው። ጨረቃ እንደ አምባሻ በየቀኑ እየተገመጠች፣ ስቃይዋ ለሁለት ሳምንት ይባባሳል፣ ትከሳለች፣ ትመነምናለች።
ደግነቱ፣ በቀናት ውስጥ ከህመሟ ማገገም ትጀምራለች። እንደ ተዋጊ የበሬ ቀንድ መስላ ትመጣለች። እየተፈወሰችና እያደገች፣ አካሏ እየሞላና ብርሃኗ እየደመቀ፣ እንደገና ግርማ ሞገስ ትላበሳለች።ምንም እንኳ፣ የፀሐይና የጨረቃ ጉዞ፣ ፈተና የበዛበትና አደገኛ ቢሆንም፣ ከሞላ ጎደል ዑደታቸው አይዛነፍም። አስተማማኝ ነው። ቀንና ማታ ሁሌም ይኖራለ። ነገ ፀሐይ በእውን ትመጣ ይሆን? በሚል ስጋት እንቅልፍ አጥቶ የሚያድር ሰው የለም።
 አንዳንዴ ዝናብ በዝቶ ጎርፍ ቢበረታም፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ የዝናብ እጥረት የሚያጋጥም ቢሆንም፣ የክረምትና በጋ፣ የእርሻና የአዝመራ ወቅቶችም፣ ከሞላ ጎደል እየተፈራረቁ ከመምጣት አይቦዝኑም። ዑደታቸው አስተማማኝ ነው። ፈፅሞ የማይሞት ዘላለማዊ የልብ ምት እንደማለት ነው። እንኳንም በሰው ሃሳብ የሚታዘዙ አልሆኑ!

Read 10809 times