Saturday, 17 September 2022 13:01

ህወሓት ሦስተኛ ዙር ጦርነት ለምን ቀሰቀሰ?

Written by  (ከኢሳይያስ ልሳኑ - ቤተሳይዳ ሜሪላንድ- አሜሪካ)
Rate this item
(3 votes)

በቅርብ ርቀት ከሰማናቸው ዜናዎች እንነሳ፡፡ መንግሥት የተናጥል የተኩስ አቁም ስምምነት አደረገ፡፡ የሰላም ድርድር ሊጀመር ነው - ያለምንም ቅድመ ሁኔታ፡፡ በምስጢርም ተነጋገሩ  - የሚሉትን ጭምጭምታዎችና ዜናዎችን ስንሰማ ከነበረበት እንዴት ወሬው ዘሎ ጦርነት ውስጥ ተገባ ወደሚል እንደተለወጠ ፍጥነቱ ይገርማል፡፡ በዚህ መንግሥት የተናጥል የተኩስ ማቆም አደረገ ከተባለበት ስምንት ወራት ጊዜ ውስጥ ከሰሜን አማጽያኑ ይወጣ የነበረው መረጃ ደግሞ - ‘ለጦርነት እየተዘጋጁ ነው - በምልዓት እየመለመሉ - በግዴታ ዕድሜያቸው አስራ ሦስት የሆኑትን ጨምሮ እያሰለጠኑ ነው’ - የሚል ነበር፡፡ የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ‘ከወጣቶች’ ጋር ውይይት ባደረጉበት ጊዜ እንደተናገሩት ደግሞ (በይፋ) - ሕወሀት በእርዳታ ስም የጦር መሳሪያ ሲያስገባም መንግሥታቸው ያውቃል፡፡ እና መሳሪያም ስልጠናም ቀጥሎ ነበር፡፡ በነገራችን ላይ መንግሥት እያወቀ ነው ሲባል ታዲያ ምን አደረገ? ወይም ምነው እንዳላየ ሆኖ አለፈ? ብለን የምናነሳቸው ጥያቄዎች አሉ፡፡ ከዚያ በፊት ከዋናው ርዕሰ ጉዳያችን - ከጦርነቱ ማገርሸት ጋር ወደተያያዘው መዘርዝር እንሻገር፡፡
 ከሁለት ዓመታት በፊት ጦርነቱ የተቀሰቀሰበትና ኢትዮጵያ በክተት የተነሳችበት ጉዳይ - የኢትዮጵያን መከላከያ የደፈሩና ማዕከሉን ለማፍረስ የተነሱትን አደብ ለማስገዛት፣ ቢያንስ አደጋ እንዳይሆኑ ለመግታት እንደነበረ አንዘነጋውም፡፡ አቅማቸውን አመናምኖ - ለሀገሪቱ አደጋ እንዳይሆኑ ማስቻል አይነተኛው ግቡ ነበር፡፡ የትግራይን ምስኪን ሕዝብ ከዚህ የግጭት አዙሪት ሰለባነት መታደግና ትግራይን ማዳንም ዋነኛ ግብ ነው፡፡ ይህን ለማድረግ የመንግሥቱ ማለትም የማዕከሉ ውሳኔና አካሄድ በቅጡ ሊመረመር ይገባዋል፡፡ ጦርነቱን እስከ ትግራይ ክልል መስመር ድረስ ገፍቶ - የተናጥል ተኩስ ማቆም ሲታወጅ - እስከ ደብረሲና ጦሩን አዝምቶ ያወደመና ሕዝብን ከመኖሪያ ያፈናቀለው  - በጎንደር አቅጣጫ እስከ ዳባት በተመሳሳይ ውጊያና አውዳሚ ጦርነት የዘለቀው ቡድን፣ አቅሙ ተመናምኖ ለሰላማዊው ጥሪ አዎንታ እንዲሰጥ ከሚችልበት፣ አለያም መልሶ ጥቃት መሰንዘር ከማይችልበት ደረጃ መድረሱን ያገናዘበ ነበር ወይ? ብሎ መጠየቅ ይገባል፡፡ በዚህ ረገድ ዛሬ የምናነሳቸውና ለጦርነቱ ማገርሸት ምክንያት የምንፈልጋቸውን ምላሾች በተለያየ አቅጣጫ እንድንፈትሽ ይረዱናል፡፡  
 የሰሜኑ ጦርነት እንደገና ተቀስቅሷል ሲባል ቀደም ሲል የተጠናቀቀና የተቋጠረ አልነበረም ወይ? ብለን እንጠይቅ፡፡ ቀዳዳው ጆንያ አፉን ቢቋጥሩትም የሚተነፍስበት አላጣምና፡፡ ከዓመታት በፊት ከትግራይ አማጽያኑ ጋር የተቀሰቀሰው ግጭት ምክንያት ከምንጩ አልደረቀም፡፡ የንጹሀንን ህይወት አኗኗርና ሀብት አውድሟል፡፡ ውድመቱ አሁንም ቀጥሏል፡፡ የሰላም ጠረጴዛ ሊተካው ነው የተባለው ሁኔታ ቀርቶ ወደነበረበት ግጭት ተመልሷል፡፡ ወትሮም ሰላማዊ መፍትሄ አይገኝለትም - እልባቱ ከጠመንጃ አፈሙዝ ብቻ ነው የሚወለደው የሚል አመለካከት ያላቸው አሉ፡፡ የቅራኔው ውስብስብነትና በተናጥል ያለው ጥቅምና ፍላጎት፣ ግጭቱን ለማብረድ የሚያስችለውን ጎዳና ለመጥረግ አዳጋች እንዳደረገው ዘርዝሮ ማየት እንደሚያስፈልግ የሚመክሩም ወገኖች አሉ፡፡ ጦርነትን የሠራ ጭንቅላት ሰላምን ለማምጣት ይቻለዋል የሚል ተስፋ ይዘው መልካሙን የዘመሩም አሁንም የሚዘምሩም አሉ፡፡ ‘ሦስት ዓመታት ከምንዋጋ አስር አመት ሰላማዊ ንግግር ብናደርግ ይሻላል’ ነበር ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፡፡ የሰላም ንግግር ለማድረግ የሚያስቸለው ግብአትና ሁኔታ ሲኖር እንጂ ምኞቱ ብቻውን ግን ዋጋ የለውም፡፡
ህወሓት የጦርነት መሻቱ ሳቢያዎች ምንድን ናቸው?
 “ትግራይ ዙሪያዋን ተከባ ምግብና መድሃኒት መሰረታዊ ፍላጎት የሚሟላበት ሁኔታ ተገድቦባት ትገኛለች፡፡ ብዙዎች በምግብ እጦት - በመድሃኒት አለመኖር - መሰረታዊ አገልግሎትን ከማጣትም እየረገፉ ናቸው” የሚለው ዜና በተደጋጋሚ የሰማነው ነው፡፡ የትግራይ ነፃ አውጭ ነኝ የሚለው ቡድን፣ በእርዳታ የሚገኘውን ምግብና ሌሎችንም ቁሳቁሶች - በግል ሳይቀር የሚገቡ ገንዘቦችን በመቆጣጠር - ነዋሪውን ማስገደጃ እንዳደረገው በይፋ ይታወቃል፡፡ የትግራይ ሕዘብ ይሄ ይሁንልኝ - ያ ይደረግልኝ ለማለትና በነፃ ለመምረጥ የሚያስችለው መንገድም ሙሉ ለሙሉ የተዘጋበት፣ አነስተኛ ልዩነት እንኳን ከእስርና ከሞት የሚያደርሰው እንደሆነ ብዙ ማስረጃዎችን ማጣቀስ ይቻላል፡፡ በትግራይ ኤሊትና በፖለቲካ አመራሩ መካከል ከጦርነቱ ጋር ተያይዞና ፋታ ከተገኘበት ጊዜ ወዲህ የነበረውን ሁኔታ በጥሞና ለተመለከተው - የነበረው ውይይትም ፤ ትግራይ በኢትዮጵያ ውስጥ ትቀጥል? ወይስ ትግራይ ነፃ መንግሥት ትመስርት? የሚል ነው፡፡
 በትግራይ ማህበረሰብ ውስጥ ትህነግ ብቸኛ ወኪል ለመሆን የተጓዘባቸው የሴራ መረቦችን በጥሞና ማጤንና ማስጤን ከላይ ላነሳነው ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት መንደርደሪያ ሊሆን ይችላል፡፡ የትግራይን ህዝብ በመያዣነት አፍኖ ይዞ ‘ብቸኛ ወኪል’ መስሎ የመቅረቡ ክስተት ላለፉት ዓመታት በብርቱ የተገፋበትና ይህንኑም የሚያጸና ሴራ የተከናወነበት ነው፡፡ ከሁሉም በላይ ሁሉም በትግራይ ላይ የተነሳ አስመስሎ የማቅረቡ ፕሮፓጋንዳና ሴራም በተወሰነ ደረጃ የተሠራበት ስለመሆኑም መከራከር አይቻልም፡፡ በትግራይ በኩል የሚደርሰው የህወሀት ጥፋትና ውድመት ኢትዮጵያዊውን የሚያሳስበው የመሆኑን እውነታ በበቂ ደረጃ እንዲታወቅ የተደረገበት ዘመቻ አለመኖር፣ ቢኖርም የተቀዛቀዘ መሆን የራሱ ችግር ፈጥሯል፡፡ ይህን መሰል መቃቃርና መጠራጠርን በሕዝቡ ውስጥ መትከልና ‘ቅራኔ’ ያለ የማስመሰል ዘመቻን ማካሄድ፣ ጥላቻን በመንዛትና አንዱን በሌላው ላይ በማስነሳት የተፈጸሙት ሴራዎችን ጨምሮ ሲከናወኑ ታዝበናል፡፡
 የህወሀት የፀረ-አማራና ዘለግ ብሎም ፀረ-ኢትዮጵያ ትርክትና በዚያ ላይ የተመሰረተው ዝርዝር ታሪኩና አካሔዱ ሰፊ እንደመሆኑ በጥሞና መጤን ያለበት ክስተት ነው፡፡ ይህንንም (ማለትም ፀረ-ዐማራነትን) በንድፈ ሀሳብና በርዕዮት ደረጃ ይዞ የተነሳው የ’ጎሳ’ ድርጅት፤ አመንኩት ያለውን ትርክቱን ህዝቡ ውስጥ ለማጋባትና ለማስረጽ የተጓዘባቸው መንገዶች፣ በዚህ ትውልድ ውስጥ ላለን ኢትዮጵያውያን አዲስ አይደለም፡፡ ዛሬ በመላ ሀገሪቱ ለተንሰራፋውና ውስጥ ውስጡን እንደነቀዝ የሚበላን ‘ጎሰኝነት’ን መንግሥታዊ ስርዓት እንዲሆን የተከለብንና የቀየሰውን መንገድ እንደዘበት የምናየውም ሊሆን አይገባም፡፡ ባለፉት አራት ዓመታት ውስጥ ደግሞ የትግራይ የፖለቲካ ኤሊት በ’ግንባሩ’ አማካይነት ‘ከአብራክህ የወጣሁና ለአንተ የቆምኩ’ የሚለውን ትርክቱን በትግራይ ሕዝብ ላይ ለማሰራጨት፣ ሽግግሩ የፈጠረለት ዕድል ረድቶታል፡፡
  ይህ ምን ማለት ነው? ብለን እንጠይቅ፡፡
 የህሐወት አንኳር ቡድን ከሁለት አስርታት በላይ በመዳፉ ጨፍልቆ ይዞት የነበረውን ስልጣን ከማዕከሉ እያጣ በመጣበት ወቅት - ለእነዚያ አስርታት በስሙ ሲነግድበት ወደነበረው የትግራይ ክልል ሲያመራ አለጥርጥር ህዝቡን በሚፈልገው መንገድ ለመቀየድና እሳቤውን ለማጋባት፣ ከዚያም ይልቅ በ’ህወሀት’ የተሠራውን ወንጀልና ወንጀለኞችን የሚሸሸጉበትን ጥግና ዋሻ ለማመቻቸት መልካም አጋጣሚ ሆኖለታል፡፡ ከዚህም ሌላ በሀገሪቱ በትህነግ ስርዓት የተፈጸመን ኢ-ፍትሃዊነትና አማቂነት እምቢኝ ብሎ የተነሳው ተቃውሞና ብሶት የወንጀሉ ተጠያቂዎች ላይ ማነጣጠር ሲጀመር፣ ሕዘብን በደም ሲያጥቡ የነበሩ ተጠያቂ የሆኑ ግለሰቦች መሸሸጊያና ጭምብል ማድረግ የጀመሩት ‘መንደራቸውን’ ነበር፡፡
 እና  ‘በትግሬነት’ የመጣ መቅሰፍት እንዲመስልና የየዋሁን ሕዝብ ቀልብና ልቡና ለመግዛትም የሚቻልበትን ዘዴ ሲያቀናጁና ሲሠሩበት ዓመታት አስቆጥረዋል፡፡
 የህወሀት ስርዓት በማዕከላዊ ይዞታው በበቃኝ ትግል እየፈራረሰ በነበረበት ጊዜ የለውጡ አካሄድና አቅጣጫ በለሱን ያዞረላቸውና ስልጣን በአጋጣሚ የወደቀላቸውም ክፍሎች ደግሞ ስለራሳቸው ይዞታና መደላደል የሚያስቡበት ሆነና ለትህነግ የተመቻቸ አጋጣሚ ሰጠው፡፡ ከስልጣን ላይ በአመፅ የተወገዱት ሀይሎች በተጠያቂነት ከሕዘብ ፍርድ የመቅረባቸው ሂደት - የፍትህ ጥያቄዎች ምላሽ ሳይፈለግላቸው መታለፍ ያዙ፡፡ የህወሀት የስልጣን ቡድን ማዕከሉ በደፈረሰበትና በስሜት ተውጦ በሰላምና በእርቅ የሚል ስሜት በሚሟሟቅበት ጊዜ - የተጠያቂነት ጉዳይ የሚያነሳም ጠፍቶ ባሸለበበት ወቅት፣ ወያኔ መቀሌ መሽጎ የመፃኢ ዕድሉን እንዲነድፍ አስቻለው፡፡ ማዕከሉን የተቆጣጠረውና የሽግግሩ ባለሟል የሆነው ክፍል - ህወሀት ያደራጀውና ህገ መንግሥት ብሎ ባጸደቀው አደረጃጀት ውስጥ የተገኘ -ጥቅሙን በብሄረሰቡ ርዕይ ውስጥ የሚያይም ነበረ፣ ነውም፡፡  ይህ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የሚመራው (የለማ ቡድን) የተሰኘው አካል ከህወሀት ቁጥጥርና መዳፍ ፈልቅቆ ሲያወጣ እጅግ አደገኛና ህይወትን የሚጠይቅ ሁኔታን እንዳለፈ መገመት አያዳግትም፡፡ ህወሀት ያንን ወቅት በዚህ መልክ ለማለፍም ባይችል ኖሮ በሕዝባዊ ማዕበል በአስከፊ ሁኔታና በደም መፋሰስ ስርዓቱ እንደሚያከትምለት መገመት ይቻላል፡፡ በእርግጥ በታሪክ ‘እንዲህ ቢሆን ኖሮ’ ተብሎ ባይተረክም፣ የህወሀት ስርዓት አብቅቶለት እንደነበር ማንም አይከራከርም፡፡ የሆነው ሆኖ ከህወሀት መዳፍ ፈልቅቆ የተረከበው የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ መንግሥት - በአፈጣጠሩም ሆነ በነበረበት ሁኔታ የ’ፍትህን ጥያቄ ከሽግግሩ ጋር አገናኝቶ ለማየት የሚያስችል አቅም አልነበረውም፡፡ ህወሀት ትኩረቱን መነሻዬ ወዳለው ክልል ሲያደርግ - የማዕከሉ ገዢዎች ፋታውን እንደቡራኬ ነበር የወሰዱት፡፡ ህወሀት ደግሞ በብቸኝነት ራሱ ድርጅታዊ ሥራ ሠርቶ ያረቀቀውና ያፀደቀው ህገ መንግሥቱን ተንተርሶ ‘እስከ ነፃነት’ የሚያደርሰውን ጉዞ ለማሳካት ያለመበትን ጉዞ ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችለውን መንገድ ያኔ ነው የመረጠው፡፡ ህወሀት በእርሱ አምሳልና እሳቤ ያዋቀረው ህገ መንግሥት እንዳይነካ ከእርሱ ውጭ ያሉ ዘውጎች በስልጣን ጥም የሰከሩትን ልሂቃንን ቀርጾና አሳምኖ የያዘበትን መተማመኛም በ’ፀረ-ኢትዮጵያ’ የተጠመቀ እንዳለ በማወቅ ነው፣ በህቡዕና በይፋ መንቀሳቀስ የያዘው፡፡ በእነዚህ አራት ዓመታት ጉዞ ውስጥ ህወሀትን መንካት ‘ትግራይን’ ከመንካት ጋር እንደተያያዘ አድርጎ በማቅረብ ያደረገው ዘመቻም ቀላል አይደለም፡፡ ህወሀት በመቀሌ በመሸገባቸው የመጀመሪያ ዓመታት ውስጥ በተለያዩ ጉዳዮችና ትንንሽ በሚመስሉ፣ ሰላማዊ ሰልፎች - የስታዲዮም ትዕይንቶች - የወታደራዊ ትርዒቶችን በመሳሰሉና - ዘለግ ሲልም ‘ምርጫን በክልል ደረጃ በተናጥል እስከማካሄድ - ከአጎራባች ክልሎች ጋር ያለውን ቁርቋሶ በማጉላትና በይፋ እስከመቃረን ድረስ የተጓዘበትን ክስተቶችን መለስ ብሎ ማየት ይቻላል፡፡ ችግሮቹን በማጋጋል ‘ክልላዊ’ በማስመሰል፣ ደምም በማቃባት  ሴራዎች ሲከናወኑ ቆይተዋል፡፡ ማዕከላዊ መንግሥት በራሱ ውጥንቅጦች መያዙና በትግራይ ያለውን የወያኔ መገዳደር የሚፈታበትን ስልት ለመቀየስ አቅምም ችሎታም እንዳነሰው አንዳንዴም ‘ይደርሳል’ የሚል ንቀት ያለ በሚመስል ሁኔታ ተደፋፍኖ ነው የቆየው፡፡
መረሳት የሌለበት ቁም ነገር ህወሀት ላይ የተነጣጠሩትን ተቃውሞዎች ወደ ትግራይ የተነጣጠሩ የማስመሰሉ አባዜና ዘዴ በተሳካ ሁኔታ እንደተከናወነላቸው ለመረዳት አያስቸግርም ነበር፡፡ የትግራይ ኤሊት ወጥ አስተሳሰብ ይዞ ከህወሀት ጋር የሚዳክርበት ክስተትንም ስለምን? በሚል መፈተሽ አለበት፡፡ ኢትዮጵያዊ በሆነው ወገንና በማዕከሉ በሚገባው ደረጃ የትግራይን ህዝብ ማነጣጠሪያ ያደረገ የማሳወቅ ዘመቻ፣ ከፕሮፓጋንዳው የማላቀቅ ሥራ ተሠርቷል ወይ? ብሎም ጥያቄ ማንሳት ይቻላል፡፡ ህወሀት በዚህ ሕዝቡን የማነካካት ተግባሩ ስኬታማ የመሆኑን ሂደት፣ የማዕከላዊው መንግሥት ሳይጎለብትና ሳይፈረጥም - በችግሮች ኩይሳ ውስጥ እንዳለ - ቀውሶችን መፍጠር ነበረበት፡፡ በዝምታ ህወሀት መቀሌ ተቀምጦ ማዕከላዊው መንግሥት እስኪጠናከር ሊያልፈው እንደማይችል የፖለቲካውን አካሄድ ላጤነ ግልጽ ነበረ፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ራሱ ህወሀት በነደፈው ህገ መንግሥትና የቋንቋ ክልሎች እውነተኛ ፌደራሊዝም ተግባራዊ ቢሆን አለጥርጥር ተጠቃሚ ሊሆን እንደማይችል ለመረዳትም አላዳገተውም፡፡ በእርሱ ስር እንዳሻው የሚታዘዝና እንደ ዳማ ጠጠር የሚንቀሳቀስ ፌደራሊዝም ካልሆነ፣ ትግራይን ‘ነፃ’ እስከማድረግ የሚደርስ ጉዞ እንደሚጠብቀው ህወሀት ተረድቷል፡፡ ከሁሉ በላይ በኢትዮጵያ መደላደልና አቅጣጫ መያዝ ሲመጣ የፍትህ ጥያቄ እያደር እንደሚነሳና የዚህም ዋነኛ ተጠያቂዎቹ  የህወሀት ባለስልጣናት እንደሚሆኑ ታሳቢ ያደረገ ስጋትም እንዳጠላበት ማመን ይገባል፡፡
ህወሀት መቀሌ መሽጎ ከሕዝቡ ጋር አለሁ የማለቱን ተውኔት የሚያጨናግፍ አንድም ጥረት በማዕከላዊው መንግሥት በኩል ለማድረግ በእርግጥ አልተሞከረም፡፡ የመገናኛ ዘዴዎች ሳይቀሩ የመንግሥትም ይሁን የግል ምንም የተፈጠረ ነገር እንደሌለ በማድረግ - የትግራይን ዕጣ ፈንታ ለህወሀት ሙሉ ለሙሉ ተላልፎ የተሰጠ ይመስላል፡፡ ኢትዮጵያዊ መሰረት ያላቸው ከትግራይ ጋርም የጠበቀ ግንኙነት ሊመሰርቱ የሚችሉ - ትላንት በነበረው ትግል - የህወሀት ቡድን ሰለባ የሆኑ - ለትግራይ ሕዝብ ጥቅምና ሰላም የቀረቡ ልጆቹ ሳይቀሩ ለዚህ ቡድን መስዋዕት እንዲሆኑ የተፈረደባቸው እስኪመስል ድረስ ነበር ዝምታው፡፡
 ወርሃ ጥቅምት 2012 ህወሀት ጦር ሰብቆ የሰሜን እዝን በወታደራዊ ሀይሉ ለማጥቃት ከመሞከሩ በፊት ብዙ ምልክቶች፣ ብዙ ፍንጮች ነበሩ፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ መንግሥት ችግሮች በተቃዋሚው ወይም በተፋላሚው መልካም ፈቃድ ወይም በመዋል በማደርና በጊዜ መግፋት ይቃለላሉ የሚል ሞኛሞኝ  እሳቤ አለው አልልም፡፡ ይሁንና አነስተኛ የሚመስሉ መሰናክሎች ተስተውለው ነበር፡፡ እነዚህም ከወታደራዊው ጥቃት በፊት ከትግራይ ክልል የፌደራሉ ወታደራዊ ይዞታዎች ከቦታ ቦታ አይዘዋወሩም ወይም አይጓጓዙም የሚባለውን አመፅ ማንሳት ይቻላል፡፡ ያኔ የተሰጠው ምላሽ ምን ነበረ? የትግራይ ክልል በህወሓት ውሳኔ (ፌደራሉን አሌ ብሎ) ያከናወነው ምርጫም አለ፡፡ በዚህ ዙሪያ የተወሰደ እርምጃ ነበርን?  እርግጥ ነው አንዳንዴ ወደ ኋላ መለስ ብለው ሲያዩት ‘እንዲህ ቢሆን ኖሮ’ ሊባል ይችል ይሆናል፡፡ ቀላልም ይመስላል፡፡ ዋናው ቁም ነገር ግን ግጭቱ እንደሚከሰት ለመገመት አዳጋች አይሆንም ነበር፡፡ የፍትህ ጥያቄዎችን ማንሳትና የህወሓት ዛሬ በተጠያቂነት የተነሱት ግለሰቦች ላይ ብቻ ያነጣጠረ ዘመቻ ለማካሄድስ የሚቻልበት መንገድ አልነበረም ወይ? ማለት ይቻላል፡፡ የህወሀት ቡድን እያደር የሚመጣበትን ችግር ለመቋቋም - በቀዳሚነት ሕዝቡን የእኔ እንዲለው በማስቻል ረገድ ዘመቻውን አካሂዷል፡፡ ከዚያ በለጠቀው ‘ትግራይ ከኢትዮጵያ ጋር መኖር አይገባትም’ የሚለውን ሀሳብ ገዢ ለማድረግ እስካሁን የቀጠለ ሴራውን አፋፍሟል፡፡
  በጥቅምት 2012 ወያኔ አረመኔያዊ ግፍ በሰራዊታችን ላይ ባደረሰ ጊዜ፣ ከጫፍ ጫፍ ሕዘብን ብድግ አደረገው፡፡ ማዕከላዊ መንግሥት ህወሀት ያደረሰውን በገለጸበት እግር በእግር አምርሮ ተንቀሳቀሰ፡፡ የማዕከላዊው መንግሥት በሦስት ሳምንታት ሁሉን በቁጥጥሬ ስር አድርጌ እመለሳለሁ አለ፡፡ ሁሉም ወደ ጦር ግንባር ሆነ፡፡ የሀገሪቱ ብሄራዊ አመራር የጠቅላይ ሚኒስትሩን የሦስት ሳምንታት ዘመቻ ትርክት በሰሙ ጊዜ ከዚያው ከማዕከሉ ከታደሙት መካከል - “ከሳምንት በሁዋላስ?” የሚል ጥያቄን ያቀረቡ እንደነበሩ መረጃዎች ያወሳሉ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከወጣትነታቸው በተቀዳ እልህ “ወታደራዊውን ዘመቻ ለእኛ ተውት” አይነትም ነበር መልሳቸው፡፡ ጦርነትና ግጭት የሚጓዙበት ፍኖትን መወሰን ያዳግታል፡፡ መግባቱን እንጂ መውጣቱን ያለማወቅ ችግር በብዙዎች ላይ ተከስቷል፡፡ ህወሀት ደግሞ የሚመጣውን ከመገመት - ለሦስት ዓመታት ለዚህ መሰል ሁኔታ የተዘጋጀበት እንደነበረ አሁን ደፍሮ መናገር ይቻላል፡፡
 ህወሀት - ለሁለተኛ ዙር ኢትዮጵያን አዳክሞና ከፋፍሎ በሚፈልገው መንገድ ለመግዛት ያሰበበት ዕቅዱ ብዙ ዋጋ አስከፈለ፡፡ የኢትዮጵያ መከላከያ መቀሌ በሁለት ሳምንት ገባ የመባሉ ዜና ተሰማ፡፡ ቀደም ብሎ የትግራይን ሕዝብ ከህወሀት የነጠለ - የዚህም ዘመቻ ዓቢይ ተልዕኮ ትግራዋይን ነፃ ለማውጣት እንደሆነ - ከዚህ የዘለቀና የጠለቀ ሌላ ምንም ፍላጎት አለመኖሩን ያሳየ አንዳችም እንቅስቃሴ አልነበረም፡፡ በዚህ ጦርነት ‘ሠላሳና አርባ ሰው ለመያዝ” መላ ሕዝባችን ላይ የቦምብ ናዳ አይውረድ - ጥይት አይዝነብ የሚል ጩኸትና አቤቱታ ከትግራዋዩ በተለይ በውጭ ካለው ተሰምቶም ነበር፡፡ ለዚህ በበቂ ሁኔታ ምላሽ ለመስጠት ሳይቻል - ይብሱኑ ሦስተኛ አካል (የኤርትራ ሀይል) በትግራይ ሰብዓዊ በደልና ግፍ ፈጸመ የሚለው  ዜና ተከተለ፡፡ የማዕከላዊ መንግሥቱ መቀሌ መግባት እንጂ የማረጋጋትና የማስቀጠል ዕቅድም በውል የተጨበጠ አለመኖሩ ሌላ እክል ሆነ፡፡ የህወሀት ባለስልጣናት መቀሌን ለቀው ካሰቡበት የምሽግ ጣቢያቸው ሲገቡ እነርሱን በተመለከተ ብቻ የሚገባውን ርምጃ ወስዶ - ትግራይን ለቆ እንደመውጣት አጋርና ደጀን እንዲሆን ባልተዘጋጀበት ሁኔታ  ለተሳሳቱ ፕሮፓጋንዳዎች በተጋለጠው ሕዝብ መካከል በወታደራዊው ይዞታ ለመቆየት ሙከራ ተደረገ፡፡ ብዙም አልሰነበተም፤ ከመቀሌ ሰራዊቱ እንዲወጣ ሆነ፡፡ ህወሀት በበኩሉ ለዓመታት ያከማቸውን የጦር መሳሪያ እየተጠቀመ ሰራዊቱ ላይ ዘመተ፡፡ የማዕከላዊ መንግሥት መቋቋም እያዳገተው ጦርነቱ ገፍቶ እስከ ደብረሲና መጣ፡፡ አዲስ አበባ ሊገቡ ነው የሚል የምዕራባውያንም ዜና መሰማት ጀመረ፡፡ ሀገሪቱ ያላትን ጥሪት አሟጣ - በጥፍሯ ቆማ - ዜጎቿ ከውጭም ከውስጥም ተባብረው የህወሀት ታጣቂ ወደ ኋላ እንዲያፈገፍግ አደረጉት፡፡ እና በመልሶ ማጥቃት የገፋው የኢትዮጵያ ሀይል ከትግራይ ክልል ወሰን ላይ ሲደርስ፣ መንግሥት የ’ተናጥል’ የተኩስ ማቆም አደረኩኝ ብሎ አወጀ፡፡
 ከስምንት ወራት በፊት ነው ይህ የሆነው፡፡ ከመግቢያዬ የተነሳሁበት ሀሳብ እዚህ ላይ ይነሳል፡፡ ይህ የተናጥል የተኩስ አቁም ውሳኔ ለማድረግ ያስፈለገበት ምክንያቶች ምንድን ናቸው? ምንን ታሳቢ ያደረገ ውሳኔ ነውን? የሚሉትን ጥያቄዎች ያስነሳል፡፡ ለ’ሰላም ዕድል ለመስጠት’ የሚል ምላሽ አለ፡፡ ሰላም ደግሞ በአንድ ወገን የሚመጣ ሳይሆን እንደታንጎ ዳንስ ሁለት አካሎችን ይጠይቃል፡፡ የጦርነቱ ውጤት እንደማያዋጣና ዘላቂ ሰላምን ለማምጣት ሁሉም አትራፊ የሚሆንበትን መንገድ የመቀየስን ብልሃት ይጠይቃል፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት የተናጥል የተኩስ አቁም ስምምነት ሲል - ከተፋላሚው ወገን ‘ለሰላም ዕድልን ለመስጠት የሚችል መሆኑን ወይም ለዚያ አስገዳጅ ሁኔታን የፈጠረ መሆኑን ይጠይቃል፡፡ አስገዳጅ ሁኔታው ይቆየንና በማዕከላዊው መንግሥት በኩል ህወሀት ያሰለፈውን ሀይል አባሮ ወደነበረበት ከመመለስ ባለፈ - ዳግመኛ ጥቃትን ለመሰንዘር ያለውን አቅምና ችሎታ መመዘን የ’ተኩስ አቁም’ ውሳኔን ከማሰማት ይቀድማል፡፡ ተመልሶ ለመምጣትና ሀገሪቱን ከቀውስ ውስጥ መልሶ ለመክተት የሚያስችለው አቅሙ ተመቷል ወይ? የሚለውንም መመለስ ይገባዋል፡፡ አደጋ የመሆኑ አቅም በብርቱ መኮስመኑን ማረጋገጥም ይገባል፡፡ አፋርና አማራ ክልል እየገባ መልሶ የሚያወድምበት አቅም እንደሌለው እርግጠኛ ከመሆን ጋር - በባህርይው ትህነግ አውዳሚ ነውና፣ ግጭትን ከተቀሰቀሰበት መከላከያ ገዢ መሬትን የኢትዮጵያ ሰራዊት ይዞም ነው የተኩስ አቁም አዋጅ መሆን የነበረበት፡፡  
 አሁን በሰሜን ኢትዮጵያ የተቀሰቀሰው ጦርነትና ተከሰተ የሚባለውን ዜና ስንሰማ የምንጠይቃቸው ጥያቄዎች ብዙ ናቸው፡፡ ህወሀት አፈራርሶና ዘርፎ ከወጣባቸው የአማራና የአፋር ክልሎች - ዜጎች እንዲረዱ መልሰው እንዲገነቧቸው ሲጠየቁ የነበረበትና በምላሹም ሁሉም የተረባረቡበት ሁኔታ የተስተዋለው - ጥቃቱ በዚህ ፍጥነት አይከሰትም ከሚል የመነጨ ነበር፡፡ ከቶውንም ጥቃት ፈጻሚው ፍጹም የተዳከመ መሆኑን ታሳቢ ያደረገም ነው፡፡ ማዕከላዊው መንግሥትም ይህንን በማረጋገጥና አስተማማኝ መሆኑን ያሰመረበት እንደሚሆን ህዝብ ይገምታል፡፡ መንግሥት ሰላም በሚል የተኩስ አቁም ሲጠይቅ - በህወሀት በጎ ፈቃድና መልካም ርህራሄ ላይ ተመስርቶ ነው ብሎ አያስብም፡፡ “ህወሀት አይወጋንም - እንደቀደመው በህዝብ ማዕበል ሰው ለመጨረስና ለማስጨርስ አይመጣም” በሚል ቤሳ እሳቤ መንግሥቱ የተማመነ ከሆነ ግን በውጤቱ ሀገርንና ወገንን ከጉዳት እንደጣለና ለከፋ ግጭት እንደዳረገ በድፍረት መናገር ይቻላል፡፡ መንግሥት ሕዝቡን ከጫፍ ጫፍ ያነሳሳበትና ለጦርነቱ ብዙዎች የተሰውበት መሰረታዊው ዓላማ - ለተወሰነ ጊዜ እርፍት ተሰጥቷቸው መልሰው ታጥቀውና ተደራጅተው እንዲገጥሙን እንዳልሆነ ነው የምናምነው፡፡ ይህ እንዳይሆን ደግሞ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አስተዳደር ምን አከናወነ? የሚለውን ዘይቤያዊ ጥያቄ ያስነሳል፡፡
 ጦርነቱን በተኩስ አቁም የተናጥል ስምምነት ሲታወጅበት - ለግጭቱ ዋነኛ ተጠያቂ የሆነውን የህወሀት ክፍል ይዞታን በቅጡ የወሰነና የገደበ ነውን? የሚለውን ጥያቄም ማንሳት ይገባ ይሆናል፡፡ በህወሀት ቁጥጥር ስር የወደቀውን የትግራይን ሕዝብ ችግር የሚያቃልል ወይም ለመፍታት የሚያስችል የመፍትሄ ሀሳብ የያዘ ስለመሆኑም መጠየቅ ይቀጥላል፡፡
ህወሀት ዛሬ ጦርነት የጀመረበት ሁኔታ አንድምታው ምንድን ነው? - አዲስ አበባ ተመልሶ ገብቶ ለመግዛት? ኢትዮጵያን ከቀውስ ለመክተት? ለምን?
እነዚህን ጥያቄዎች ለመመለስ የከዚህ ቀደሙ ግጭትና ጦርነትን - ሂደቱን እንዴት ነበር ማለትን፣ ከፍና ዝቁን ወይም ስኬቱንና ብክነቱን መመዘንን ተገቢ ያደርገዋል፡፡ ከዚያም በትይዩ የውጭ ሀይላትን ተፅዕኖ አብሮ መቃኘትም ይመጣል፡፡
 ህወሀት የኢትዮጵያ ሰራዊትን ከመቀሌ አባረርኩ ባለበት ፕሮፓጋንዳው፣ የአንተ ነኝ ለሚለው ሕዝብም ይሁን ለውጭው ማህበረሰብ ‘አዲስ አበባ’ ገብቶ እንደገና መንግሥት የማዋቀርን ትርክት ጭምር እስከማሳመን የደረሰበት አጋጣሚ ነበር፡፡ ወደ ደብረሲና በተጠጋባቸው የጦርነት ወቅቶች - “ማዕከሉን” ስለሚያደራጅበት ሁኔታ ሳይቀር የሚነጋገርበት ተውኔት በውጭ መፍጠሩን እናውቃለን፡፡ ከዚህ በኋላ በገጠመው ሽንፈት ወደ ኋላ ሸሽቶ መቀሌ ሲገባ፣ በራሱም ውስጥ ይሁን በውጭ ዓቢይ መነጋገሪያ የነበረው - የሰላም ስምምነት ጉዳይ ነበር፡፡ ‘ሰላም’ ከሚለው ጋር  በወያኔ ውስጥ ትግራይ ለብቻዋ ነጻ ወይም የኢትዮጵያ አካል ሆና መቀጠል የሚለው ሀሳብ በትግራዋዩ በተለይም በፖለቲካ ኤሊቱ መካከልም  ሙግት መከሰቱ አልቀረም፡፡ በዚህ የሀሳብ መጓተት አንዳንድ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፣ በትግራይ ውስጥ ‘ከኢትዮጵያ’ ጋር አብሮ የመኖር እሳቤ ያላቸውን የማፈንና የማስወገድ ሥራ በወያኔ ድርጅት ተፈጽሟል፡፡ ብዙዎችም በወህኒ ቤቶች መኖራቸውንም ታሳቢ ማድረግ ይገባል፡፡ በጦርነቱ የተፈጠረውን ምሬት በማስታወስና በማመልከት - ከእንግዲህ ‘ነፃነታችንን’ የሚሉት ድምፅ እንዲገንም ተደርጓል፡፡ ከዚህ  የትግራይ ነፃነት ከሚለው ውጭ ማሰብ - የ’ጠላት ወገን ነህ አሰኝቶ የሚያስገልል የሚያስመታም ሆኗል፡
ይኸው የነፃነት እሳቤና ትርክት ደግሞ ‘ህወሀት’ እንዲገፋበትና ከቶም መልክ እንዲይዝ በድርጅታዊ ሥራ ታጅቧል፡፡ “ከውጭ በሚገባ ምግብ እየታገዝን የማዕከላዊ ኢትዮጵያን መንግሥት የተለያዩ አግልግሎቶች እናግኝ በሚል እየለመንን እስከመቼ እንቀጥላለን?” የሚለው ስሜትን የሚቆሰቁሰውና ወደ ግጭት ለማምራት ጋዝ የሚሆነውን ሁኔታም እየፈጠረ መጥቷል፡፡ ሕወሀት ደግሞ ሁኔታውን ቀድሞ ወደሚፈልገው አቅጣጫ በመውሰድና ግጭቶችን በመፍጠር ሕዝቡን ማንቀሳቀስ እንደሚችል ይረዳል፡፡ በግጭትና ጦርነት በሚመስል ሁኔታ ውስጥ ሕዝብን በተሳሳተ መረጃ በሚፈልጉት ጥግ ማሰለፍ እንደሚቻል ከፖለቲካ ተሞክሮው የተቀዳ ሴረኝነት አለው፡፡ ህወሀት ‘በሰላም ድርድር’ ሰበብ ተቀይዶ እርሱ ከሚሻው ውጭ ሁኔታዎች እንዳያመሩ ለማድረግ ሴራዎቹን በመፍጠር የሚጋጋምበትን ሁኔታ እግር በእግር ይተገብራል፡፡ ተንኩሶ በተንኳሽነት - ሰርቆ በሌባነት ሌሎችን የመወንጀልና በዚያ የማምታታት ረዥም ታሪክ ያለው የፖለቲካ ድርጅት ነው፡፡ ይህ ድርጅት የትግራይን ‘ነፃነት’ የሚመለከት ክስተትን የመፍጠር እቅድ እንዳለው ማሰብ ይጠቅማል፡፡ የፖለቲካ ኤሊቶቹ በውጭም በውስጥ የሚያቀርቧቸው የፖለቲካ ትንተናዎች ‘ከትግራይ ሀገረ መንግሥትነት’ ጋር የተያያዙ መሆናቸውን መመስከር ይቻላል፡፡ ትግራይ ራሷን ልትችል አትችልም - እንኳን ትግራይ ኤርትራም አልሆነላትም ወዘተ... የሚሉት አገላለጾች ብዙውን ጊዜ የምንሰማቸው ቢሆኑም፣ እነዚህ እሳቤዎች ዛሬ ከትግራዩ ኤሊት ውስጥ እንደምክንያት ቀርበው የሚነገሩ እንኳን አይደሉም፡፡
  ወደ  ዋናውና ሰሞነኛው ጦርነት ስንመጣም - ትግራይ ነፃ የመሆን ፍላጎትና ውሳኔ ጋር የተያያዙ እርምጃዎች ይመስላሉ ብለን እንነሳ፡፡ ትግራይ በህወሀት በተጫነው የሀገሪቱ ህገ መንግሥት ክልል አደረጃጀት መሰረት ወሰኗ ከሱዳን ጋር የሚያገናኛት አለ፡፡ ይህ በህወሀት አጠራር ምዕራብ ትግራይ የሚባለው ወልቃይትና ጸገዴ የምንለው ነው፡፡ ከህወሀት ጋር በተደረገው ውጊያ እስካሁን በማዕከላዊው መንግሥት ወታደራዊ ይዞታ ስር ያለና በብርቱ የተመሸገበት ስፍራ ነው፡፡ ይህ አካባቢ ለህወሀት የትግራይ የነፃነት ህልም ዋነኛው ህልቅ ወይም ጉሮሮ ነው፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት ይህን አካባቢ ለብሄራዊ ደህንነት ሲባል በወታደራዊው ይዞታ ስር እንደሚያቆየው ይፋ አድርጓል፡፡ ከውጭ የሚመጡ ወራሪዎችን ለመከላከል አይነተኛ ወሽመጥ ነውና፡፡ ህወሀት ደግሞ በዚህ በኩል የመሸገውን ወታደራዊ ሀይል ለመስበር የሚያስችል አቅም እንደሌለው በውል ይረዳል፡፡ ብዙ ሙከራዎቹም አመድ ሆነዋል፡፡ አሁን የያዘው ስልት በሌሎች አካባቢዎች ጥቃትን በመሰንዘር ሀይሉ እንዲሳሳ የማድረግ ሴራ ነው፡፡
በወልቃይትና ጸገዴ ባለው ስፍራ የህወሀት ሀይል አንድ ዕድል ለአፍታ ለመያዝ ቢገጥመው ተሽቀዳድሞ ‘ነፃነት’ ለማወጅና የውጭ ሀይላትን ድረሱልን ብሎ ለመጮህ፣ በግርግሩም እውቅናን ለማግኘት መሞከሩን ታሳቢ ማድረግ ይገባል፡፡ ለዚህ ሁኔታ ደግሞ ይህ ወቅት - አውሮፓ በሩሲያና በዩክሬይን (ቀዝቃዛው ጦርነት በሚመስል) መልክ የተዋጠችበት ከመሆኑም በላይ - ምዕራባውያን ዩኤስ አሜሪካንን ጨምሮ - ከሩሲያ ጋር የተባበረ ‘እንቀጣለን’ በሚሉበት ጊዜ መሆኑን ማጤን ይጠቅማል፡፡ ለዚህም “Countering Malign Russian Activities in Africa Act”  በሚል የቀረበውን ህግ ማጤን ነው፡፡ ማንም እንደሚረዳው ኢትዮጵያ በገለልተኛ አቋሟና በሩሲያ ጦርነት ዙሪያ ከአሜሪካ ጎን ያልተሰለፈች ሀገር ናት፡፡ የምታንጸባርቃቸው ፋይዳዎችና የብሔረተኝነት ስሜቶችም በምዕራባውያን ዘንድ በደግ የሚታዩ አይደሉም፡፡ ከዚህ ሌላ ኢትዮጵያ በዩኤስ አሜሪካ የጦር መሳሪያ ግዢ እቀባ ተጥሎባታል፡፡ የዓለም አሰላለፍ እጅግ ተለዋዋጭ ከመሆኑ ጋር አሰላለፍን የሚያዛቡ - ካልታሰበ ጥግ የሚወረውሩ ክስተቶች ይገጥማሉ፡፡ በተለይም በዚህ ወቅት ተፅዕኖን ለማሳደርና የሀይል ሚዛንን ለማጎላበት፣ ከርዕሰ ሀያሏ ዩኤስ አሜሪካ እስከ ሪጅናል ሀይሎች ድረስ ሩጫና ግፊያ አለ፡፡ በኢትዮጵያ ያለውን ሁኔታም ለመመርኮዝና ለመግባት የሚፈልጉ - በሀገሪቱም ውስጥ ያሉ የውጭውን ጥገኝነት የሚሹበት ሁኔታም መኖሩንም ከግምት ውስጥ ማዋል ይገባል፡፡ ከዚህ አኳያ ዛሬ በተቀሰቀሰው ዳግመኛ ግጭት ውስጥ የውጭዎቹን ሚናና ፍላጎት አብሮ መመልከት ብልህነት ነው፡፡  
***
ከአዘጋጁ፡- ጸሃፊውን በኢሜይል አድራሻው፡ This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡   

Read 3683 times