Saturday, 17 September 2022 13:24

አዝማሪዎቹ እስኪመለሱ

Written by  መስፍን ኃብተ ማርያም (ሰዓሊ)
Rate this item
(3 votes)

  “እትዬ ወርቄ መብራቱን ማጥፊያቸው ስለደረሰ እነ አባዬ ሲመጡ እንዳይጨልምባቸው ኩራዙን ለኩሽና እንተኛ።”
አምሳለ ኩራዙን ከለኮሰች በኋላ ተኙ። እንደተኙ የጋራ የሆነችው ለራሷ ብቻ የምታበራ የምትመስለው አምፖል ጠፋች።
 “አምሳልዬ” አለ በድሉ ከተኛበት ተንፏቆ ለመቀመጥ እየሞከረ። “ይህ ቁርበት እንዴት ይቀዘቅዛል? እንደ አንሶላ ወይም ፍራሽ አልቆ ይቀየራል እንዳይባል ጭራሽ በእኛ ወዝ እያደረ እያማረ ይሄዳል። እንዴት ይደብረኛል መሰለሽ?”
አምሳለ ግን ውበት፣ ትዕግስት፣ ጸባይም ከድህነት ጋር ፈጣሪ የለገሳት ኮረዳ ናት። ድህነት ይሞቃታል፤ እንደ በድሉ አይቀዘቅዛትም። የጎረቤት ኑሮ…ምግብ…አጓጉቷት አያውቅም። “በድሉ ስንት ጊዜ ልንገርህ? አቅምህን  አላውቅ ብለሃል። ምን ታደርግ ከሃብታም የጎረቤት ልጆች ጋር እየዋልክ”
 “አምሳልዬ ሳልነግርሽ ጠዋት ዘይት ልትገዢ  ሄደሽ ያ ልጅ መጥቶ ነበር።”
 ነፍሳት የነደፋት ያህል ብድግ ብላ የበድሉን አይን በኩራዙ እያየች
“ሳሚ…?” ካለች በኋላ የጠጠረችውን ያህል እርግብ ብላ “ለምን ወዲያው አልነገርከኝም? ምን አለህ በድሉዬ?” አለች። በበድሉ አይን ውስጥ ሳሚን እያየች። “አይ ምንም አላለኝም አምሳልዬ አለች ወይ አለኝ? የለችም አልኩት። ትንሽ ቆም ካለ በኋላ ቀስ ብሎ ደጋግሞ ወደ ኋላ እያየ ሄደ።” አምሳል ቀስ ብላ በእርጋታ በጀርባዋ ተኛች። ሳሙኤል የመጣበትን ጠዋት ስታስታውስ በዛ ጨለማ ኩራዝ ብርሃን ውስጥ ሳሚ እንደ ጠዋት ጀምበር በህሊናዋ ነጋላት- ከበድሉ ይበልጥ አየችው። ነገር ግን የናፍቆት አድማስ ስለሆነ በሃሳቧ ባየችው ቁጥር ናፍቆቷ እየጨመረ ሳሚ እየራቀባት ሄደ።
“አምሳልዬ ለምንድን ነው እሱ ልጅ የሚፈልግሽ” ብሎ አምሳለን ኩራዙ ብርሃን ውስጥ መለሳት።
በድሉ ታናሿ ቢሆንም ድህነት አፋቅሯቸዋል። አንድ ቁርበት ላይ ይተኛሉ፣ ተናጥቀው ይበላሉ። በዚህ ላይ ደግሞ የኩራዙ ብርሃን ያዋድዳቸዋል። ሀብት እኮ አንድነት የለውም። ሁሌም ለየብቻ ነው። መብላት፣ መተኛት፣ ማሰብ፣ የአንዱን ትራፊ አንዱ እንኳን አይበላም። ድህነትን የመሰለ መፋቀሪያ ጎጆ የለም። ስለዚህ አምሳለ ታናሽ ወንድሟን እንደ እኩያ ጓደኛዋ ታየዋለች።
“ወዶኝ ነዋ…!” አለችው ከትንሽ ቆይታ በኋላ። የበድሉ መውደድ ከእህቱ፣ ከአባትና ከእናቱ ባያልፍም ፍቅርን ከሚያየው ያውቀዋል።
“ታዲያ ለምን አንችስ አትወጂውም?”
 “እኔም እወደዋለሁ። ድህነትና አባቴ አለያዩን እንጂ።”
“እንዴት?” አላት በድሉ።
“ትዝ አይልህም ባለፈው ወር ውስጥ ፈረንጇ የሸለመችህ ነው ብላ ማዘር ያመጣችውን ከፋይ የሚመስለውን ሹራብ ሰርቄ ለብሼ ስወጣ “እናገርብሻለሁ” ስትለኝ ነበር። አስታወስክ? የዛን ቀን ፊልም ከጋበዘኝ በኋላ ወደ ቤት ሲሸኘኝ አባዬ ምን እንደነካው አላውቅም በቀን ሰክሮ ከፊታችን እየተንገዳገደ በተኮለታተፈ አንደበት እንደተለመደው፡-
እኔ የአልሚዬ አባት
ሸጋው አዝማሪ
ማሲንቆ ደርዳሪ
ድምጽ ቀማሪ
ሙያውን አክባሪ…
እያለ ይሄዳል። እኔ እርምጃዬን ስቀንስ ሳሚ “ይሄ ሰውዬ ሰክሯል እንዳይመታሽ” ብሎ እጄን ይዞ አባዬን ለማለፍ ፍጥነት ጨምሮ ሲጎትተኝ፣ አባዬን ስለምወደው ሳሚ እንዳሰበው ሰካራም አድርጌ ማለፍ አቃተኝ። ድንገት እጄን ከሳሚ እጅ ውስጥ ምንጭቅ አድርጌ “አባዬ” ብዬ ሰካራሙን ሰውዬ ያዝኩት። አባዬም በስካር ብዙ ዘመን የተነፋፈቅን ያህል በሁለት እጁ እቅፍ፣ ጭምቅ እያረገኝ “አምሳልዬ… የኔ ልጅ.. የኔ ቆንጆ” ብሎ ከሳመኝ በኋላ ሳሚን የማየት እድል ሳይሰጠኝ አንገቴን አቅፎ ወደ ቤት አመጣኝ። በሳሚ እና በአባቴ መካከል የተፈጠረውን አጋጣሚ ሳስበው እንባዬ ይመጣል። ሳሚ ያን ቀን የአዝማሪ፣ የሰካራም ልጅ መሆኔን ባወቀ ጊዜ በሀፍረት እየሮጠ የሄደ ነው የሚመስለኝ። የዚያን ቀን ማታ ለመጀመሪያ ጊዜ ድህነቴ… አባቴ… ሳሚ… ተባርረው አስለቀሱኝ።” ብላ እምባዋ ቅርር አለ። በእምባዋ ውስጥ ህይወት… ፍቅር… አባት… ታማኝነት እንደ እጣ ወረቀት ተደበላለቁባት።
 የተቋጠሩትን እንባዎቿን በእጇ ጨምቃ ከጠረገች በኋላ “ዛሬ መጣ ስትለኝ አላመንኩም። በጣም ነው ደስ ያለኝ፤ እሱ ከመጣ እኔም እፈልገዋለሁ።”
 በድሉ ትንሽ ተክዞ ከቆየ በኋላ “አምሳልዬ አንቺስ ታድለሻል መልክሽ ቆንጆ ነው። ጓደኛሽ ሃብታም መሆኑ በልብሱ ያስታውቃል። እነ አባዬ አንድ ነገር ቢሆኑ እንኳን አንቺ እሱ ጋ ትሄጃለሽ” አለ የልጅነት በሚመስል ቁም ነገር።
እውነት እነሱ አንድ ነገር ቢሆኑ ምን የሚተርፈን ነገር አለ? የኩራዙን ብርሃን ተከትሎ ቢወርሱ ሊጠቅማቸው የሚችል ነገር በአይኑ መፈለግ ጀመረ።
ደሳሳ ጎጆ ነች። በቤቱ ያሉት እቃዎች ቢጫውም… ቀዩም… ሰማያዊ ቆርቆሮም ሆነ ሸክላው እርጅና… አቧራና.. የኩራዙ መብራት አመሳስሏቸዋል።
የአባትና የእናታቸው ስራ ሰዓት ከሰው የተለየ ስለሆነና ቀን ቀን ስለሚተኙ ዓመት በዓል ካልሆነ በስተቀር በቤታቸው እቃ ተጠቅመው አያውቁም። ከሱቅ በሚገዛ ዳቦ… እንጀራ ነው የሚኖሩት። ቀን በቀን የሚታጠብና የሚወለወል ቢኖር የአባታቸው መሰንቆና አባታቸው የሚለብሱት የሥራ የባህል ልብስ ነው። ከዚያ ቤት የሚወጣ አይመስልም። በድሉ እንኳን በዚያች ጭል ጭል በምትል የኩራዝ ብርሃን ቀርቶ የትዬ ወርቄ አምፖል ከመንገዱ መብራት ጋር ተዳምሮ ጎጆዋ ውስጥ ቢበራም ሊወርሱ የሚችሉት ቀሪ ሀብት ሊያገኝ አልቻለም።
“አምሳልዬ እስቲ እይው ምንም ነገር የለም፣ የሀብታሞቹ ቆሻሻ ይሻላል። ሰባራ ጋን… እንጀራ የሌለው ሞሶብ… የተገነጠለ ሳጥን… በቃ ምን አለ?! አባዬ የሚኮራበት ያ የተሰቀለው ሜዳሊያ የተደረደረበት ኮት ብቻ ነው። ለምንድን ነው የሚወደው? ሜዳሊያዎቹ ወርቅ ይሆኑ እንዴ? አምሳልዬ ወታደር ነበር? ከየት አመጣው?”
አምሳለ ታናሽ ወንድሟ ያነሳውን ሃሳብ እንደታላቅነቷ አሰበችበት። ቶሎ መልስ አልሰጠችውም። የሷም አይን ከአንዱ አሮጌ ወደ ሌላኛው አሮጌ እንደወፍ በረረ ተሸከረከረ ምንም የለም፤ ሀሳቧ ውስጥ ሳሚ ብቻ ቀረ።
እንደገና በድሉ “አምሳልዬ ለምን እንደ አባዬ ማሰንቆ አልማርም? አንቺም እንደ እማዬ እስክስታ ተምረሽ እነሱ አንድ ነገር ቢሆኑ እንኳ እንደነሱ እየሰራን እንኖራለን።” አምሳለ፣ በድሉ ያመጣውን ሀሳብ የራሷ አድርጋ መሰንቆውን ከወንድሟ ቀምታ ለሳሚ ሰጠችውና አብረው ቡና ቤት ሲዘፍኑ… ዓለማቸውን ሲቀጩ… ለቅጽበት ታያት። ለመጀመሪያ  ጊዜ ወንድሟ ላይ  በሃሳቧ ጨከነችበት። ወዲያው ዘገነናት።
ለበድሉ የሚሆን መልስ በዕድሜዋ ደረጃ ስላላገኘች ድብክ ብላ ተኝታ የበድሉን ምኞትና ተስፋ እንደ ተረት መስማት ጀመረች። ከትንሽ ዝምታ በኋላ  በድሉ ከተኛበት ድንገት ተነስቶ አዲስ ቅርስ ያገኘ ይመስል “አምሳልዬ የእነ አባዬ መምጫ ስለደረሰ ያው ጨብ ብሎ ነው የሚገባው፣ ለነገ ቁርስ ለምናምን ብለሽ ደህና ፍራንክ ተቀበይና  ጧት የእንቁላል ፍርፍር ሰርተን እንብላ፣ ጥሩ ቁርስ ናፍቆኛል። ጧትም ደክሟቸው ስለሚተኙ አያዩንም።”
አምሳለ በእንቅልፍ መካከል ያለ ስስ ሳቅ ስትስቅ የወደቁበትን እንጂ የአንኳኩት የማይመስለው ብቸኛው  በራፍ ሁለቱንም ሙሉ ለሙሉ  አነቃቸው።
(አዲስ አድማስ፤ጥር 5,1993)

Read 916 times