Saturday, 24 September 2022 16:46

ላግዝሽ ቢሏት መጇን ደበቀች

Written by 
Rate this item
(7 votes)

 ከኢራቅ ተረቶች አንዱ የሚከተለውን ይመስላል፡-
ከዕለታት አንድ ቀን ንጉሥ በግዛቱ ዋና ከተማ ሳይታወቅ እየተዘዋወረ፣ ሕዝቡ ምን እንደሚያወራ ለማዳመጥ እየሞከረ ነበር። በአንድ መስኮት አጠገብ እያለፈ ሳለ ሶስት ሴቶች ሲያወሩ ሰማ።
አንደኛዋ፡- ንጉሡን ለማግባት ብችል ግዛቱን ሁሉ ሊሸፍን የሚችል ምንጣፍ (ስጋጃ እሰራለት ነበር) አለች።
ሁለተኛዋ፡- “እኔ ደግሞ ንጉሡን ለማግባት ብችል፤ መላ ሰራዊቱ በልቶ የማይጨርሰው ትልቅ ድፎ ዳቦ እጋግርለታለሁ” አለች።
ሦስተኛዋ፡- “እኔ ደግሞ ንጉሡን ባገባ፣ ሁለት ልጆች እወልድለታለሁ። አንደኛው ራሱ ላይ የብር ፀጉር፣ ሌላኛው ራሱ ላይ የወርቅ ፀጉር ያላቸው ይሆናሉ” አለች።
ንጉሡ በሚቀጥለው ቀን በአባቶቻቸው በኩል ሴቶቹን ልጆች አስጠርቶ ተራ በተራ እያስጠየቀ፣ በሉ ያላችሁትን ሰርታችሁ አሳዩኝ አላቸው። የመጀመሪያዋ ስጋጃውን መስራት አልቻለችም። ሁለተኛዋ ዳቦውን ለመድፋት አቃታት። የመጀመሪያዋም ስለ ጉራዋ ማድቤት ውስጥ እንድትቀመጥ  ፈረደባት። ሁለተኛዋን ደግሞ ኩሽና እንድትቀመጥ ቀጣት። ሦስተኛዋን ግን አገባት። ከዘጠኝ ወር በኋላ የብር ጌጥና የወርቅ ጸጉር ያላቸው መንትያዎች ተወለዱ። እነዚህን ሁለት ቆንጆ ቆንጆ ልጆች ያዩት ሁለቱም የንግስቲቱ እህቶች ቅናት ያዛቸውና፣ ከሞግዚቷ ተሟግተው ወስዳ ጫካ እንድትጥላቸው አስደረጓት። በቦታቸውም ሁለት አሻንጉሊቶች ተካች።
ንጉሡ የሆነውን ሲሰማ እቤቱ ፊትለፊት ንግሥቲቱ በቁሟ እስከ ጡቷ ድረስ ትቀበር አለ። መንገደኛው በድንጋይ እንዲወግራትም አስደረገ! ንጉሡ አንድ አሳ አጥማጅ አለው። የንጉሡ ዓሳ አጥማጅ ወንዝ ውስጥ አንድ ሳጥን ያገኛል፤ ሲይዘው ይከብዳል። ለሚስቱ ሄዶ ነገራት። ቤታቸው ወስደው ሲከፍቱት ምን የመሳሰሉ ባለወርቅና ባለብር ጸጉር ልጆች! ልጆች ስላልነበራቸው ሚስትየው በጣም ተደሰተችና ልታሳድጋቸው ወሰነች!
ንጉሡ ወደ ሩቅ ሀገር ሊሄድ አስቧል። ሁለቱንም ኩሽና ያሉ ሚስቶቹን፣ “ምን ላምጣላችሁ?” አላቸው። የመጀመሪያዋ “በእንቁ የተንቆጠቆጠ ቀሚስ!” አለች። ሁለተኛዋ፣ “ከአልማዝ የተሰራ የአንገት ሀብል!” አለች። ሁለቱ እህትማማቾች ቀጥለው፤ “እባክህ እደረቷ ድረስ የተቀበረችውንም እህታችንን ምን እንደምታመጣላት ጠይቃት?” አሉት።
“አታላኛለችና ለሷ አላመጣም!” አለ።
“ግዴለህም ሚስትህ ናት፤ለእኛም እህታችን ናት። ተባበራት!” አሉት። ወተወቱት። በመጨረሻ ተስማማና፤
“እሺ ላንችስ ምን ላምጣልሽ?” አላት።
“ምንም። በሰላም ሂድ። በሰላም ተመለስ።” አለችው።
“በጭራሽ። አንድ ነገር እዘዥኝ” አላት።
“እንግዲያው “የትዕግስት አሻንጉሊት” እና “የትዕግስት ቢላዋ” አምጣልኝ!” አለችው። “የምትሄድበት ሀገር እነዚህን ሁለቱን አታጣም። ከረሳህ የምትሳፈርበት ጀልባ እሺ ብሎ አይንቀሳቀስም።” አለችው።
ንጉሡ ሩቅ ሀገር ሄደ። ንግዱን አሳካው። ነጋዴዎቹ በእንቁ የተንቆጠቆጠ ቀሚስና የአልማዝ የአንገት ሀብል እንዲገዙለት አደረገ።
ከዚያ ወደ ሀገሩ ሊመለስ መርከቡ ላይ ወጥቶ “እንሂድ” አለ። ካፒቴኑ ግን መጥቶ “ንጉሥ ሆይ! መርከቡ አልሄድም ብሎኛል” ብሎ ሪፖርት አደረገ። ንጉሡ የረሳው ነገር ትዝ አለውና “የትዕግስት አሻንጉሊት” እና “የትዕግስት ቢላዋ” አስገዛ። የሸጠለት አንጥረኛ ግን አንድ ነገር አደራ አለውና ቃል አስገባው። ይኸውም፤ “ንጉሥ ሆይ! ለሚስትህ ስጦታዋን ስትሰጣት፤ በሩ ሥር ተደብቀህ የምታደርገውን ሁሉ እይ” ንጉሡ አንጥረኛው እንዳለው አደረገ።
ለሁለቱ ሚስቶች ስጦታቸውን ከሰጠ በኋላ ግማሽ ወደተቀበረችው ሚስቱ ሄዶ ያመጣላትን ሰጥቷት ተደብቆ የምታደርገውን ያይ ጀመር። ለአሻንጉሊቷ የሚከተለውን ተናገረች። እህቶቿ ልጆቿን እንደሰረቁባትና በቦታቸው አሻንጉሊቶችን እንድታስቀምጥ ሞግዚቷን እንዳዘዟት ገለጠች። እስከ ዛሬ ድረስም ሀዘን ላይ መሆኗን እያነባች ተናገረች።
እንዲህም አለች፡- “የትዕግስት አሻንጉሊት ሆይ! አንተ ትዕግስት ነህ! እኔም ትዕግስት ነኝ! እኔ በትዕግስት ምን ያህል ስቃይ ተሸከምኩ? ምን ያህል መከራ ተቀበልኩ?!”
አሻንጉሊቱ እየገዘፈ ሄደና ፈነዳ! ይህንን ያየችው ሶስተኛዋ ሚስት “ውይ! የትዕግስት አሻንጉሊት ሆይ ልብህ ተነካ!” አለች። ከዚያም ቢላዋውን አንስታ ራሷን ልትወጋ ስትል ንጉሡ ከተሸሸገበት ዘልሎ አዳናት! ከዚያም፤ “ምነው ለአሻንጉሊቱ የነገርሽውን ለምን ለእኔ አትነግሪኝም?” ሲል ጠየቃት።
“እህቶቼን ስላጠፉት ጥፋት እንዳትጎዳቸው ፈርቼ ነው።” ስትል መለሰች። ንጉሡ ባለሟሎቹን ጠርቶ ቆፍረው እንዲያወጧት አደረገ። ሁለቱም እህቶቿን ወደ እስር ቤት ላካቸው። ቀጥሎም፤ የጠፉትን ሁለት ልጆች እንዲፈልግ ህዝቡን በአዋጅ ጠየቀ። አዋጁ በመላ ሀገሪቱ ተሰማ። ይህን የሰሙት አሳ አጥማጁና ሚስቱ፣ ተመካክረው ልጆቹን ወደ ንጉሡ አምጥተው አስረከቡ። እንደ ሽልማትም እቤተመንግስቱ አቅራቢያ መኖሪያ ቤት ሰርቶላቸው፤ ልጆቹንም በየጊዜው እያዩ ኖሩ!
***
ንጉሥ እናስደስታለን ብለን ያለ አቅማችን አንመኝ። የማይሆን ቃልም አንግባ። የሚጸጸት ንጉሥ አያሳጣን። ስህተቱን ሳይውል ሳያድር የሚያምንና የሚቀበል፣ ይቅርታ መጠየቅ የማያስፈራው መሪ፣ ባለስልጣን፣ ፖለቲከኛ ይስጠን። እዚህ ላይ ታዋቂውን ገጣሚ፣ አርክቴክትና መሀንዲስ አሌክሳንደር ፖፕን መጥቀስ ተገቢ ነው።
“መሳሳት የሰው፤ ይቅር ማለት ግን የመለኮት ነው!” ይለናል። (To err is Human to forgive is Divine) በየጊዜው በማናቸውም ሂደት፤ እንቅስቃሴ ውስጥና  ወቅት፣ ጥፋት መፈጠሩ እንግዳ ነገር ሊሆንብን አይገባም፡፡ ዋናውና ወሳኙ ነገር፤ ምን ያህል መሳሳታችንን ልብ ብለናል? ምን ያህልስ ያን ስህተት አምነን ተቀብለናል? ለመታረምስ ምን ያህል ዝግጁ ነን? በተለይ ያጠፋነውን ካጠፋን በኋላ፣ ጥፋቱን የያዙ ሰዎች  ህጸጹን ሲነግሩን መቆጣትና “ብቆጣም እመታሻለሁ፤ ብትቆጭም እመታሻለሁ!” ማለት አጉል መታበይ  ነው። እንዲህ ያለ አመለካከት የአምባገነንነት እኩያ ነው።
የአብዛኞቹ አምባገነኖች ዋነኛው ችግር ሰው ጤፉ መሆን ነው። ሁለተኛውና ከዚሁ ጋር በቅርብ የተሳሰረው ነገር፣ የቅራኔ አፈታት ችግር ነው። የሚታረቅና የማይታረቅ ቅራኔን በአግባቡ መለየት ነው። (Antagonistic and Non antagonistic contradiction እንዲል መጽሐፈ ዲያሌክቲክስ) በትልቁም በትንሹም፣ በሚያስፈልገውም በማያስፈልገውም፣ ፖለቲካ በሆነውም ባልሆነውም ጉዳይ መጨናነቅ ተገቢ አይደለም። በተለይ፣ “በጠብታ ውሃ ውስጥ ጉማሬ አየን” ከሚሉ ወሬ አራጋቢዎች አለመጠንቀቅ ቢያንስ የዋህነት ነው። አንዳንዴ “ጦር ከፈታው መሪ የፈታው” የሚለውን አባባል አለመዘንጋት ከብልጥነት ይልቅ በብልህነት እንፍታው ነው። “ኢትዮጵያ ለጎረቤት ሀገሮች ተርፏት አበድራለች” የሚለው ጉራ የማይጋብዘንን ያህል፤ “ኢትዮጵያ አልቆላታል! በአፍጢሟ ተደፍታለች!” የሚለውን ጨለምተኛና “ሁሉን አውድም” (Nihilistic) አስተሳሰብንም አራቱንም የአገራችንን መዓዘናት እኩል የሚነካ ፍሬ ጉዳይ አድርገን ወስደነው አስጋሪ ሊሆንብን አይገባውም! ሚዛናዊ አመለካከት ቢያንስ “በአራት ቤት ሚዛን እንዳንሸቀብ” ይረዳናል። የፖለቲካና የኢኮኖሚ ተንታኞቻችን እንደምንም የባለሱቅ ስሌት (Shopkeeper Analysis) ከሚባለው ጠለቅና መጠቅ ያለና ለነገ ታሳቢነት ያለው ሂሳብ ቢቀምሩ መልካም ነው እንላለን።
የስርአተ ማህበራችንን ነገር አንድም በሶሻል ዲሞክራሲ አንድም በሱታፌ ዲሞክራሲ (Participatory Democracy) ንፍቀ ክበብ ውስጥ ይሆነኝ ብለን እንመድበው ብንል እንኳ፤ ከነባራዊው ባህላዊው ስርዓት ርቆ ያልራቀ በመሆኑ፤ እቁብ እየከፈሉ፣ የእጅ ድንኳን እየተጋሩ፣ ጽዋ እየተጣጡ፣ ዘካና ምጸዋት እየሰጡ፤ ፈሪሃ እግዚአብሔር እንዲያድርብን ጽናቱን ይስጠን ማለቱ፤ ለጊዜው ከረሀቡም፣ ከጠብና ግጭቱም፣ ከጦርነቱም፣ እንኪያ ሰላንቲያና አርቲ ቡርቲ ይገላግለን ይሆናል!! ፓርቲዎችና ቡድኖች ዛሬም “የማይተማመን ባልንጀራ ወንዝ ለወንዝ ይማማላል” ከሚለው የተረት ማዕቀፍ ውስጥ አልወጡም፡፡ “አንድነት ለጋራ ጠላት፤ውዝግብና ንትርክ ለጓዳ ቤት!” አይነት ነው ነገረ ስራቸው። ቀና ትችት እንደሌላቸው ሁሉ፣ በሀሳዊ ውዳሴም የተሞሉ ናቸው። በዚያ ላይ ሎሬት ጸጋዬ ገ/መድህን፤ ካድሬው ሁሉ፤ “ስልጣን በሸተተው ማግስት፣ አካሄዱ ሁሉ እንደ ድመት ኮርማ ይሆናል!” ያለው፤ ዛሬ “ፋሽን” ወደመሆን አድጓል።
ከላይ የተጠቀሱትን ሁሉ ብርታቱን የሰጠው ሰው ጨክኖ ልርዳችሁ፣የአቅሜን ላዋጣ፣ ችግሩን አብረን እንፍታ አሳትፉኝ፣ ቢላቸው እንኳ ጀርባቸውን ሲሰጡ ይገኛሉ። ላግዝሽ ቢሏት፣ መጇን ደበቀች” ማለት ይሆናል! ከዚህም ይሰውረን!
እንኳን ለብርሃነ መስቀሉ አደረሳችሁ!!

Read 11677 times