Saturday, 24 September 2022 17:13

የህፃናቱ ግድያ ከስነልቦና አንፃር ሲታይ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 ተሳታፊዎች፡
ሃዊ ሽጉጥ-ክሊኒካል ሳይኮሎጂሰት
ብሩክ ገ/ማርያም-ዴቨሎፕመንታል ሳይኮሎጂስት
ወንድወሰን ተሾመ-ካውንስሊንግ ሳይኮሎጂሰት
መግቢያ
በየትኛውም የዓለም ማዕዘን ወላጆች የስራ ጫና ሲበዛባቸው በስራ የሚያግዛቸውን፣ ህይወታቸውን የሚያቀልላቸውን፣  እነሱን ተክቶ ልጆቻቸውን የሚንከባከብላቸውን አጋዥ ይፈልጋሉ፡፡ በዚህም ረገድ የቤት ሰራተኞች አገልግሎት ትልቁን ቦታ ይይዛል። በአብዛኛውም ጊዜ አያሌ የቤት ሰራተኞች የወላጆች እና የልጆች ደጋፊ ከመሆን አልፈው የቤተሰብ አካል እስከሚመስሉ ድረስ ግልጋሎታቸውንና ድጋፋቸውን በቅንነትና በትጋት ሲሰጡ ይስተዋለል፡፡ ነገር ግን አንዳንድ ጊዜ እነዚህ ደጋፊና አቃፊ ይሆናሉ ተብለው ቤታችን ያስገባናቸው አንዳንድ አጋዦች በተለያየ ምክንያት ተነሳስተው የወንጀልን ስራም የሚሰሩበት አጋጣሚ ሲፈጠር ይስተዋላል፡፡
የዚህ ፅሁፍ ዋና ዓላማ በቅርቡ በከተማችን በቦሌ ክፍለ ከተማ አራብሳ ኮንዶሚኒየም ውስጥ በሁለት ህፃናት ላይ በተከሰተው አስደንጋጭ ወንጀል ዙሪያ የሚያጠነጥን ሲሆን፤ ጉዳዩን ከስነልቦናና ከማህበራዊ መስተጋብር አንፃር በመቃኘት ለወላጆች፣ ለቤት ሰራተኞች፣ ለሰራተኛ አገናኝ ደላሎችና ለሌሎች ለሚመለከታቸው አካላት ዘርፈ ብዙ ሃሳቦችን በመስጠት ለማወያየት ታስቦ የተዘጋጀ ነው፡፡
ይሄ ፅሁፍ በዋናነት ሶስት ክፍሎችን የያዘ ሲሆን እነሱም፡
በቤት ሰራተኞች የተገደሉ ህፃናት ዓለም አቀፍና አገራዊ አስደንጋጭ ክስተቶች
ህፃናትን ለመግደል የሚገፋፉ ስነልቦናዊ ምልከታዎች
ችግሩን ለመፍታት ምን መደረግ አለበት
ፅሁፉ ከላይ በተጠቀሱት ሶስት ርዕሶች፣ በሶስት ክፍል በየሳምንቱ በዚሁ ጋዜጣ የሚቀርብ ይሆናል፡፡
በዛሬው ፅሁፍ በተለያዩ አገሮች የተፈፀሙ ግድያዎችን መጥነን እናቀርባለን፡፡ በዚህም መሰረት በተጠቀሱት አገራት በህፃናት ላይ የተከሰቱትን ግድያዎች ሁኔታ፣ የፍርድ ሂደት፣ በገዳዮቹ የተሰጡ ምክንያቶችና በተለያዩ አካላት የተሰጡ አስተያየቶችን እንደ መረጃዎቹ ስፋትና ጥበት ለመዳሰስ እንሞክራለን፡፡

በቤት ሰራተኞች የተገደሉ ህፃናት ዓለም አቀፍና አገራዊ አስደንጋጭ ክስተቶች
የተባበሩት አረብ ኢምሬትስ
በተባበሩት አረብ ኢምሬት የሻርጃህ የህዝብ አቃቤ ህግ አንዲት ኢንዶኔዢያዊ የቤት ሰራተኛ አንዲትን የዘጠኝ ወር ሴት ህፃን ልጅን በመደብደብ፣ መሬት ላይ በመጣልና ከዚያም የቤት ዝንቦችን ለመግደል በሚያገለግል የሌሊት ወፍ ማባረሪያ ጭንቅላቷን በመምታት በነፍስ ግድያ ተከሳ ፍርድ ቤት ቀርባለች። ህፃኗ ልጅ በወቅቱ በደረሰባት መደብደብ የራስ ቅል ስብራት ያገጠማት ሲሆን በኋላም በሆስፒታል ውስጥ ድጋፍ ሊደረግላት ቢሞከርም በደረሰባት የከፋ ጉዳት ምክንያት ህይወቷ አልፏል ሲል የአገሪቱ አቃቤ ህግ ተናግሯል። የፎረንሲክ ምርመራ ውጤትና ሌሎች ተጨማሪ ማስረጃዎችም ይህንኑ አረጋግጠዋል። በምርመራ ወቅት ሰራተኛዋ ሕፃኗን - ሳላማን - መሬት ላይ እንደወረወረች እና ከዚያም ብዙ ጊዜ እንደመታቻት ተረጋግጧል፡፡ ፍርድ ቤቱ የወንጀል ድርጊቱን ካረጋገጠ በኋላ ብይን ሰጥቷል። ብይኑም የሕፃኑ ወላጆች ኪሳስን (በእስልምና ህግ መሰረት የሚቀጣ ፍትህ) አይን ላጠፋ አይን (eye to eye) or (Retributive Justice) እንዲካሄድ ወስኗል፡፡   
ከፍርድ ቤቱ ብይን በኋላ የሕፃኑ አባት በእነዚህ ቀናት ሁሉ ቅዠት ውስጥ እንደነበሩ የተናገሩ ሲሆን፤ አሁን አጥፊዋ የሚገባትን በማግኘቷ እፎይታ እንዳገኙ ገልጸዋል። እስካሁንም ድረስ የልጃቸውን መጥፋት መቀበል እንደተሳናቸው በመግለፅም፤ “ለሁላችንም ልጆች ደህንነት እንጸልይ” ብለዋል።
2.  ናይጄርያ
ሁለተኛው የወንጀል ድርጊት ወደ ናይጄሪያ ይወስደናል:: የወንጀል ድርጊቱ የተፈፀመው በ16 ዓመቷ የቤት ሰራተኛ  ሲሆን የ2 አመት ህጻን ነው አንቃ የገደለችው፡፡
ተጠርጣሪዋ የ16 አመት ወጣት Hope Istifanus (ሆፕ እስቲፋነስ) ከሟች ወላጆች ጋር በሰራተኛነት ተቀጥራ ትኖር ነበር፡፡ በናይጄርያ በሰፊው የሚነበበው “ዘ ኔሽን” የተባለ ጋዜጣ እንደዘገበው፤ የ16 አመቷ የቤት ሰራተኛ Somkenechukwu (ሶምኬኔቹኩ) የተባለች የሁለት ዓመት ሴት ሕፃን ልጅን አንቃ ከገደለች በኋላ ሕፃኗን ምንም እንዳልተፈጠረባት ለማስመሰል በአልጋዋ ላይ አስተኝታት እንደነበረ፣ በዚህም ወቅት አንድ ስሙ እንዲጠቀስ ያልፈለገ ጎረቤት እንደገለፀው፣ የሟች እናት ከገበያ ስትመለስ ልጇን አልጋ ላይ ተኝታ ያየቻት መሆኑን እንደነገሩትና ሰራተኛዋም  ልጅቷን ምግብ እንዳበላቻት፣ እንዳጠበቻት እና ቤት ውስጥ ትንሽ ከሮጠች በኋላ እንደተኛች እንደነገረቻቸው የጠቆመ ሲሆን በወቅቱም እናትዬዋ  ምንም አይነት ጥርጣሬ እንዳልነበራት ገልፆ ተናግሯል።
ሆኖም እናት ህፃኗን ከአራት ሰአት በላይ ብትጠብቃትም ስላልነቃች ልትቀሰቅሳት ወስና ለመቀስቀስ ብትሞክርም  ሶምኬንቹኩን ለማንቃት ያደረገችው ጥረት ውጤት አልነበረውም፤ በሕፃኗ ላይ ምንም አይነት ትንፋሽ አልነበረም። በዚህም ተደናግጣ  እናትየዋ ህፃኗን ከሰራተኛዋ ጋር በፍጥነት ወደ ሆስፒታል ይዛት ብትሄድም ህፃኗ በህይወት እንደሌለች እና በህፃኗም ላይ የመታነቅ ምልክት እንዳለ ለእናትዬዋ ነግረዋታል ሲል ገልጧል። ከዚሀም በኋላ የሁሉም ሰው አይን በጥርጣሬ ወደ ቤት ሰራተኛዋ የዞረ ሲሆን በወቅቱ በተደረገው ምርመራም ሰራተኛዋ “ሰይጣን አስቶኝ ድርጊቱን ፈፅሜያለሁ” የሚል የዕምነት ክህደት ቃሏን መስጠቷ ተዘግቧል፡፡
1.3. ሩዋንዳ
 የሩዋንዳ የምርመራ ቢሮ (RIB) Gasabo (ጋሳቦ) በተባለ ቦታ የዘጠኝ ዓመት ወንድ ልጅ የሆነውን Davis Rudasingwa Ihirwe በመግደል የተጠረጠረችውን ሶላንጅ ኒራንጊሩዋንሳንጋ የተባለች የ37 ዓመቷ ሴት በቁጥጥር ስር ያዋለ ሲሆን ክስተቱም በጋሳቦ ወረዳ በንደራ ሴክተር በተባለ ስፍራ ውስጥ የተከሰተ ነው።  የሩዋንዳ የምርመራ ቢሮ (RIB)  ቃል አቀባይ የሆኑት ቲዬሪ ሙራንጊራ  ለኒው ታይምስ እንደተናገሩት፤ በምርመራው ሴትየዋ ተጎጂውን እንደገደለች የሚያሳዩ  ማስረጃዎች ተገኝተዋል፡፡ ወንጀለኛዋም በምርመራው ወቅት መግደሏን በሰጠችው የዕምነት ክህደት ቃል እንዳሳወቀች ተናግረዋል። ነገር ግን ልጁን ለመግደል ያነሳሳትን ምክንያት በተመለከተ ምንም መግለጫ አልሰጡም፡፡ በወቅቱም  (RIB)  ቃል አቀባይ የሆኑት ቲዬሪ ሙራንጊራ፣  ግድያ ወንጀል መሆኑን ህብረተሰቡን በማሳሰብ ወንጀሉን የፈፀመ ሁሉ ለፍርድ መቅረብ እንዳለበት እንዲሁም ሰዎች ከሰራተኞቻቸው ጋር ጥንቃቄ እንዲያደርጉ አሳስበዋል። አንድ ስሙ እንዳይጠቀስ የፈለገ የቤተሰቡ ጓደኛ እንዳለው፤ ኢሂርዌ የተገደለው እሁድ እለት እቤት ውስጥ የት/ቤት የቤት ስራውን ሲሰራ ነው። አባቱ በወቅቱ ለስፖርት ሩጫ በወጡበትና እናቱም ቤት ባልነበሩበት ወቅት ነው በማለት ሁኔታውን ገልጧል፡፡
4. ደቡብ አፍሪካ
 በደቡብ አፍሪካ Hazyview, Mpumalanga ነዋሪዎችን ከቤታቸው ነቅሎ ያስወጣ ክስተት እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በታህሳስ 3 2021 ዓ.ም.የተፈጠረ ሲሆን በወቅቱም  አንዲት Pontsho Mokgoto የተባለች ሞግዚት፣ Angel Ndlovu የተባለች የ6 ወር ህጻን ልጅን  “ደመወዝ አልተከፈለኝም” በሚል ምክንያት አስባ እና አቅዳ መግደሏ  ተዘግቧል። በወቅቱም የሕፃኗ እናት በሥራ ላይ እያለች ቀድሞ ከተዘጋጀ ወተት (ፎርሙላ ሚልክ) ጋር የዕቃ ማጠቢያ ፈሳሽ ሳሙና በመደባለቅ የሰጠቻት ሲሆን ልጅቷን በፍጥነት ወደ ሆስፒታል ለመውሰድ ቢሞከርም፣  ከወተቱ ጋር ደባልቃ በሰጠቻት ሰንላይት በተባለ የዕቃ ማጠቢያ ውህድ ምክንያት ህይወቷ እንዳለፈ እርዳታ ሲያደርጉላት የነበሩ ዶክተሮች አሳውቀዋል፡፡
የከተማው ነዋሪዎች ይህን ክስተት ከሰሙ በኋላ በከፍተኛ ንዴትና ቁጣ ወደ ጎዳናዎች በመውጣት የተሰማቸውን ሀዘንና ብስጭት መግለፃቸውንና በወቅቱ ተጠርጣሪዋ ወንጀሉን ሰርታ መሰወሯን እንዲሁም ፖሊስም ጥብቅ ክትትል እያደረገ መሆኑን በማላዊ የሚነበበው Face of Malawi የተባለ ጋዜጣ ጉዳዩን ዘግቦታል፡፡
1.5. ኬንያ
በዚህ በያዝነው የፈረንጆች ዓመት ማለት እሮብ፣ መጋቢት 02፣ 2022 – አንዲት Maureen Nyaboke የምትባል የቤት ሰራተኛ በተቀጠረች በሁለተኛው ቀን የአሰሪዋን ወንድ ህፃን ልጅ ከደበደበች በኋላ የተባረረች ሲሆን ልጁም በደረሰበት ከባድ የአካል ጉዳት በህክምና ሲረዳ ቆይቶ ከሶስት ቀናት በኋላ በውስጣዊ ደም መፍሰስ ምክንያት  እንደሞተ ኬንያን ፖስት የተባለ ድረ ገፅ የዘገበ ሲሆን፤ ማውሪን ኒያቦኬ የተባለችው የህፃኑ ገዳይ አሰቃቂውን ድርጊት ከፈፀመች በኋላ መሰወሯንም አሳውቋል።
1.6 ኢትዮጵያ
ጥቂት ደግሞ በአገራችን የተፈፀሙ ክስተቶችን ለማየት አንሞክር፡፡
ቡራዩ
በቡራዩ ከተማ ነዋሪ የሆነች እናት ወይንሸት ከበደ የዘጠኝ ዓመት ህፃን ልጇ ናሆም በልስቲ በሚያዚያ 13 ቀን 2013 ዓ.ም.  በቤት ሰራተኛዋ በሻርፕ ታንቆ መገደሉን በወቅቱም  በቤት ሰራተኛዋ ላይ የተፈረደው የሁለት ዓመት ከሶስት ወር እስራት በቂ አይደለም ብላ “በአዲስ ዘመን” ፍረዱኝ በሚል ርዕስ በፅሁፍ ቀርቦ እንደነበር የተናገረች ሲሆን፤ በወቅቱ ምንም ሰሚ አለማግኘቷን ገልጻ፣ አሁን በአራብሳው የሁለት ህፃናት ግድያ የተሰማትን ጥልቅ ሀዘን በየኛ ቲዩብ (Yegna Tube) “ፍተሻ” ለተሰኘ ፕሮግራም አሳውቃለች፡፡ ፖሊስ ጣቢያውም የቤት ሰራተኛዋን የዕምነት ክህደት ቃሏን የተቀበለ ሲሆን፤ ሰራተኛዋ ልጁን በስካርፕ አንቃ እንደገደለችው አምናለች::  በወቅቱ ለግድያው ምክንያት አድርጋ ያቀረበችው ነገር ለዓመት በዓል የተገዛ በግ  እየፈታ ስላስቸገራት እንደነበር እናቷና ጎረቤቷ በየኛ ቲዩብ (Yegna Tube) ፍተሻ ለተሰኘ ፕሮግራም በሰጡት ቃለመጠይቅ  አስረድተዋል፡፡
ቦሌ አራብሳ ኮንዶሚንየም
በአዲስ አበበባ ከተማ በለሚኩራ ክፍለከተማ ወረዳ 4 ቦሌ አራብሳ ኮንዶሚንየም ነዋሪ የሆኑትን ሰዎች እና መላው የአዲስ አበባ ነዋሪን በእንባ ያራጨውና ከፍተኛ ቁጣን የቀሰቀሰው  የአራብሳው የሁለት ህፃናት አሰቃቂ ግድያ ሲሆን፤ በህፃን ክርስቲያን መላኩ እና ወንጌላዊት መላኩ የተባሉ የሁለት አመት እና የሶስት አመት ህጻናት ላይ በቤት ሰራተኝነት ተቀጥራ በነበረ ተጠርጣሪ ግለሰብ በስለት ተወግተው ተገድለዋል።
በአጠቃላይ በአንዳንድ የቤት ሰራተኞች  በህፃናት ላይ የሚፈፀሙ ግድያዎችን በተመለከተ  ይህንን ያህል ካልን በሚቀጥለው ሳምንት የስነልቦና ምልከታውን በሰፊው እንዳስሳለን። በዚህ አጋጣሚ ልጆቻቸው በአሰቃቂ ሁኔታ ለተገደሉባቸው ወላጆች መፅናናትን እየተመኘን፣ ለሥነልቦና ድጋፍ ወደ አልታ ካውንስሊንግ ቢመጡ አልታ ካውንስሊንግ የሥነልቦና አገልግሎቱን በነፃ  እንደሚሰጣቸው ከወዲሁ እንገልፃለን፡፡
(ከአልታ ካውንስሊንግ): email: This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

Read 1427 times