Saturday, 24 September 2022 17:45

ኤስኦኤስ ወጣቶችን ተጠቃሚ የሚያደርግ የ95 ሚ. ብር ኘሮጀክት ይፋ አደረገ

Written by 
Rate this item
(3 votes)

ኤስኦኤስ ችልድረን ቪሌጅ  በአማራጭ ቤተሰብ ወይም ተቋም ውስጥ የሚያድጉ ወጣቶችን ተደራሽ የሚያደርግ የሶስት ዓመት ተኩል ኘሮጀክት ባለፈው ማክሰኞ መስከረም 10 በስካይላይት ሆቴል ይፋ አደረገ።
95 ሚሊየን ብር የተመደበለት ኘሮጀክቱ፤ “Leave No Youth Behind” ይሰኛል ተብሏል፡፡
በአማራጭ ቤተሰብ ወይም ተቋም ውስጥ የሚያድጉ ልጆች መሰረታዊ ፍላጎቶቻቸው የማይሟላላቸው ና በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ለአድሎአዊ አስተዳደግ የተዳረጉ በመሆናቸው ለተለያዩ ማህበራዊ ችግሮች ተጋላጭ እንደሆኑ  ተጠቅሷል።
ኘሮጀክቱ  በእነዚህ ታዳጊ ወጣቶች ላይ ትኩረት በማድረግ በአድቮኬሲ፣ በፖሊሲና በስትራቴጂ እንዲደገፉ በተጨማሪም በቀጥታ ድጋፍ እንዲያገኙ ያደርጋል ተብሏል። በዚህ ኘሮጀክት አማካይነት  2 ነጥብ 8 ሚሊዮን ወጣቶችን የፖሊሲና የስትራቴጂ አመቺነትን በማስፈን  ተጠቃሚ እንደሚደረጉ የተገለፀ ሲሆን፤ በተጨማሪም በአዲስአበባ ከተማ በ11 ወረዳዎች የሚገኙ 1 ሺህ  400 ወጣቶች በቀጥታ ተጠቃሚ የሚሆኑበት ሥራ እ.ኤ.አ ከጁላይ 2022 አንስቶ መተግበር መጀመሩ ተጠቁሟል።
ለፕሮጀክቱ ትግበራ የገንዘብ ድጋፍ የተገኘው (DANDA) ከተባለ የዴንማርክ አለም አቀፍ የተራድኦ ድርጅት ሲሆን፤ በማማከር፣ የፕሮጀክት ቀረጻና ክትትል በማድረግ ረገድ ደግሞ ኤስ.ኦ.ኤስ ዴንማርክ ትልቅ ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝ የኤስኦኤስ ችልድረን ቪሌጅ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሳህለማርያም አበበ ገልጸዋል።
እ.ኤ.አ በ2022 የሕዝብ ትንበያ መረጃ መሰረት ከኢትዮጵያ ሕዝብ 70 በመቶ ያህሉ በወጣትነት የዕድሜ ክልል የሚገኝ ነው።

Read 1474 times