Saturday, 24 September 2022 17:51

የመጨረሻው ምሽት

Written by  አፀደ ኪዳኔ (ቶማስ)
Rate this item
(9 votes)

 ይህቺ ጠባብ መንደራችን የምትሞቀው እግዜር ሰማይ ላይ ባንጠለጠላት  ፀሃይ ብቻ  ሳይሆን  በዚህች እንስት ሳቅም ጭምር ነው። እዚህች እንስት ነፍስ ውስጥ መለኮት ከሰውነት ጋር ተጋምዷል። የጥርሶቿ መገለጥ የንጋትን ጮራ የሚገዳደር ውበት ነበረው።  ቅላቷ ላይ ያበጡ ጉንጮቿ፣ የግራ ጉንጯ ላይ ያሉት ሶስት የማርያም ስሞሾች ለዚህ ሰፈር የደስታ ዋርካ ነበሩ። እግዜር ሰፈራችን ላይ ህይወትና ፍቅር የዘራው ከዚህች እንስት አፍ  ውስጥ  ትንፋሽ፣ ከዚህች እንስት ልብ  ላይ ደግሞ ፍቅርን ሰርቆ  ነው።  የገላዋ ናትራን የሰፈሩን ጠረን ሲለውጠው፣  እንደ ሸማኔ መቂናጥ እዚህም እዚያም የሚሉ ትልልቅ ዓይኖቿ እንደ ጨረቃ በማታ ሰፈሩ ላይ ሲበሩ፣ ድብርት የገደለውን ነፍስ በፍቅሯ ስታነቃ፣ የተራበን በእነዚያ ውብ እጆቿ ስታጎርስ አይቻለሁ። የደስታ ጣዕም በጠፋት ጊዜ እንኳን የሰዎችን የሃዘን ፅዋ ወደ ጣፋጭ የደስታ ወይን ስትለውጥ ታዝቤያለሁ። በዚህች ሴት ገላ ውስጥ የሚዘዋወረው ደም ነው ቢሉኝ እኔ አላምንም። በዚህች ሴት ገላ ውስጥ የሚዘዋወረው የፍቅር ማይ ነው።
ጉርምስናን ከዱርዬነት ጋር አምታተን፣ መማርን ከባላገርነት  ጋር አዛንቀን፣ ትዕቢትን  ልባችን ላይ አንግሰን አስፓልት መዋል እንደ ጀመርን ለመጀመሪያ ጊዜ ውበትና ደግነትን ያየሁት እዚህች ሴት ጋር ነበር። ከዚያ በፊት ሴቶች ሁሉ እንደ እንጀራ እናቴ ጠማማ ፊት ያላቸው፣ ጨቅጫቃና ምላሳም ... ይመስሉኝ  ነበር። ሰክሮ የመደባደብን ትዕቢት እንደ ፊደል ስቆጥር፣ ከዃላ ሆና የምትታዘበኝ፣ ታዝባም “አንተ ጨምላቃ...አትተውም” የምትለኝ ብቸኛ ሴት እሷ ነበረች።  ስከፋ የምፅፋቸውን ግጥሞች አንብባ “የኔ ገጣሚ” ብላ የሳመችኝ የመጀመሪያ ምናልባትም የመጨረሻ  ሴት እሷ ናት። ያ ስሞሿ ዛሬም የጉንጬን አቧራ ጠራርገው ቢፈልጉት አይጠፋም።  ለመጀመሪያ ጊዜ ስታቀፍ የፈራሁት በዚህች እንስት ክንድ ነበር። ሴት ልጅን የምሸሽ የአውሬ ልብ ያለኝ ሰው ነበርኩና።
“አንተ ጨበሬ ና እስኪ” ብላ እንደ ታናሽ ወንድሟ እቃ የምትልከኝ እኔን ነው። በእርግጥ የብዙ ጊዜ ታናሿ ነኝ።  ፍቅር አካል ኖሮት ቢገለጥ ይህቺን ሴት ይመስላል እላለሁ ለእራሴ። ኪሴን በፊቴ መዳመን ሰልላ ሆዴ ከበሮ እስኪያክል ድራፍት የጋበዘችኝ፣ በስካር ውስጥ እስከንጋት አብራኝ የደነሰች  ሴት ማን ነች? እሷ ብቻ አይደለች? ትንሽ ነው ብላ ሳትንቀኝ ከማንም በላይ ፍቅር የሰጠችኝ ሴት ማን ነች? እሷ አይደለች?  ይህቺን ሴት አለመውደድ እንዴት ይቻላል? ለጋ የጉርምስና ሰማዬ ላይ የማውቃት የፍቅር  ፀሃይ እሷን ብቻ ነበር። እናቴን እንኳን በደንብ እንዳላውቅ የተረገምኩ እድለ-ቢስ አልነበርኩ?
“ለምን አትማርም” ስትለኝ... ትምህርት አስጠልቶኝ እንደተውኩት  ስነግራት፣ እነዚያን ከንፈሮቿን ገልጣ፣ ጥርሷን እያሳየችኝ፣ “ዱርዬ” ብላኝ ነበር። ማንም ለፀጉሬ መንጨባረር ተጨንቆ አያውቅም ነበር። እሷ ግን እጄን እየጎተተች ፀጉሬን አስቆርጣኝ ትመጣለች። አባቴና እንጀራ እናቴ  እንኳን እኔን ምሳ በላህ ብለው ጠይቀውኝ አያውቁም። እሷ ግን ምሳ እንደበላሁ ማረጋገጥ የሁልጊዜ ስራዋ ነው። የእሷን ግብዣ የምወደው ጉርሻ የሚባል ፍቅር ስለሚታከልበት ጭምር  ነው።  ፍቅር ከራቀው ማዕድ፣ ፍቅር የሞላበት ረሃብ በስንት ጠዓሙ። የሴት ከንፈር የማያቃቸው ጉንጮቼ በእሷ የከንፈር ማይ ሙላት እርሰው  ያውቃሉ። ስትጠፋ ዓይኖቼ ሊያዩት ናፍቀው ያውቃሉ። ከስራ አምሽታ ስትመጣ ጨለማ ውስጥ እጠብቃት ነበር። ምን እንደምፈልግ በማላውቅበት  ህይወት ውስጥ አንድ ጋት መራመድ ሲከብደኝ ጉልበት የምዋሰው ከእሷ  ፍቅር ላይ ነበር። እሷ ወሃውን ወደ ወይን ጠጅ እንደቀየረው ክርስቶስ፣ አውሬነቴን ወደ ሰውነት የቀየረች ተዓምረኛ  ክርስቶስ  ናት።
አንድ ጊዜ እንዲህ ሆነ።
ልታገባ መሆኑን ሰማሁ። ደስ ብሎኝ ቤቷ ሄድኩ። ግን ደስታዬ ላይ ጥቁር የመከፋት ነጥብ ነበር። በዚያ ሰዓት ይሄን ነጥብ የማወቅ ንቃት አልነበረኝም። እንደ ወትሮ አቅፋ ሳመችኝ። እንደ እናት እጇን ሰዳ ፀጉሬን ዳበሰች። “አስቀያሚ ዱርዬ ነህ እኮ” እያለች ድንች ወጥ አቀረበችልኝ። በቤተሰቤቿ ሰርቪስ ቤት ነበር የምትኖረው። ሰፊ ክፍል ነበር ቤቷ። አልጋና ትንሽ የቤት እቃዎችን አቅፋ ይዛለች - ቤቷ። ቢጫ ቀለም ግድግዳው ላይ ፈሶበታል። ስገባ ቤተ- መቅደስ እንደ ሳመ ምዕመን፣ አፍንጫዬ ውስጥ ጣፋጭ ርሔ ቀርቶ ነበር።  ለእኔ ያላቸው ጥላቻ ዓይናቸው ላይ የሚነበብ እህቶች ነበሯት። ህይወት የምትፋለምህ በጠላትህ የጭካኔ ጦር እና በወዳጅህ የፍቅር ልብ ጋሻ ነው። ምን የጠላትህ የጭካኔ ጦር ቢያደማህ፣ የወዳጅህ የፍቅር  ልብ ላይ እንዴት ችለህ ዘገር ትወረውራለህ? ይሄ ተገልጦልኝ ነበር፣ የእህቶቿን ጥላቻ በዝምታ ማለፍ የጀመርኩት።
“ስታገቢ ትዘጊኛለሽ እንዴ?” አልኳት... ሳላውቀው፤ ጉሮሮዬ ውስጥ ሳግ ነበር።
የሚወዱትን የማጣት ፍርሃት፣ የሚወዱትን ከማጣት በላይ ህመም እንዳለው የገባኝ ያኔ ነበር።
“አንተን?” ብላ ... እንደማይሆን በስሞሿ ነገረችኝ።
“አስተዋውቂኝ” አልኳት...
“እሺ” ብላ ዝም አለች...
ተያይዘን ወጣን። ክለብ  ይዛኝ ገባች። ብዙ ጠጣን። ብዙ ጨፈርን። ዓለም መድረክ ላይ አበድን። በዚያ ጊዜ ሀያን ለመርገጥ ሶስት አመታት የሚቀሩት ለጋ ልጅ ነበርኩ። በዚህ መሃል እንዲህ አለችኝ፤ “አላምን ብለህ ነው እንጂ ከእኔ  ፍቅር ይዞሃል ኣ? ትልቅ ናት ብለህ ነው የምትሸሸኝ ኣ?” ብላ መሳቅ ጀመረች። ሳቋ ፀሃይ ነው - ይሞቃል። ፍቅሯ እንደ ጨረቃ የህይወትን ምሽት የሚያደምቁበት ጌጥ ነው። እቅፏ ተጠምቶ  የምንጭ ውሃን ከመጠጣት በላይ ያረካ ነበር።
የሰከረች ስለመሰለኝ መልስ አልሰጠዃትም... ግን አፈርኩ...
ከእሷ ፍቅር ይዞኝ ነበር እንዴ? እንጃ....
ቀኑ ሲሄድ ማግባቷን የሚጠብቅ የመንደር ሰው በዛ። ሁሉም ደስታቸውን በምርቃት ይገልፁላታል። አቅፎ በመሳም ያጅቧታል።  ሰርጓን የናፈቁ ሰዎች ከየስርቻው እንደ አይጥ ተኮሎኮሉ። እሷን ያገኘ ወንድ የዓለም እድለኛ መሆኑ መወራት ጀመረ። ለምትወልዳቸው ልጆች ሳይቀር ስም ይወጣ ጀመር። የስርግ  ወጪዋን እንድትሸፍን ከየቤቱ ገንዘብ  ወደ ቦርሳዋ ጎረፈ። የምታገባውን ወንድ  ለሰፈሬው  አስተዋወቀች። እኔም አየሁት። የክርስቶስን ተዓምር እንደመመልከት ያለ አስገራሚም አስበርጋጊም ነገር ነበረው - እሱን ማየት።  እርዝመትን ከሰውነት ጋር አዳብሎ የያዘ ትንሹ ጎሊያድን  የሚያክል  ሰው ነው። እሱ ፊት የቆምኩት ደግሞ ትንሹን ዳዊት የማክል ጎረምሳ ነኝ።  እንደ እራሷ ቀይ ነው። ቀጥ  ብሎ የወረደ አፍንጫው  ቁንጅናውን ልናገር ልናገር እያለ አፍ ያወጣ ይመስላል። ጉንጩን የሞሉትን ፂሞች ሳይ፣ ፂም ባለማውጣቴ ሃፍረት ተሰማኝ። እሱን የመረጠችው በፂሙ ብቻ መሰለኝ። “ሃይ ጎረምሳው” ሲለኝማ “ሂድና ጎረምሳህን ፈልግ፣ ትልቅ ሰው ነኝ” ልለው ነበር... አባቴን የገደለ ደመኛዬ መሰለኝ። እነዚህ ንዴቶች ከውስጤ ሲቀጣጠሉ የንዴቶቼን ምንጭ ግን አላውቅም ነበር።  እሱ እሷ ብትቀርበት ብዙ እሷን የሚተኩ ሴቶች በዙሪያው ሊኖሩ ይችላሉ። እሱ እሷ ብትቀርበት ከሚወዱት መሃል አንድ ነው የሚጎለው። እኔ ግን እሷ ብትቀርብኝ ከሚወዱኝ መሃል ምንም ነው የሚቀረው። እሷን የሚነጥቀኝ መሰለኝ... ፈራሁት... አንዳንድ ክፉ ልብ መልዓክን በመሰለ መልክ ይደበቃል ብዬ የምፈራ ድንጉጥ ነኝና... ሰይጣንስ መልዓክ አልነበር?
የሰርጓን ቀን እንደ ምፅአት ቀን ፈራሁት። እነዚያ ውብ ከንፈሮቿ ዳግመኛ ጉንጬን የማይስሙ፣ ሙቀትን ከፍቅር የቀየጠ እቅፏ ላይመለስ የሚርቅ፣ ጉድፍ የማይገኝለት ፍቅሯ እንደ ጨው የሚሟሟ  መሰለኝ። እኔና እሷን ያጣበቀን የፍቅር ናጥራን ነው። ትላንታችን ፍቅርን ብቻ የመኖር፣ ንፁህ ጓደኝነትን የመሻት ገድል ነበር። ላጣት ይሆን እንዴ? በእርግጥም የሚወዱትን የማጣት ፍርሃት፣ የሚወዱትን ከማጣት በላይ ህመም ነበረው።
እንደ ነገ ሰርጓ ሊሆን እንደ ዛሬ ሰፈሩን ሸሸሁ። የሙዚቃው ጩኸት፣ የሴቶች እልልታ ለእኔ የፍርሃት  ዋሻ ብቻ ነበር። በሁለት እግሬ መቆም እስኪከብደኝ ጠጣሁ። እየተወላከፍኩ ወደ እዚያ መንደር ሄድኩ። ሙዚቃ፣ ጩኸት፣ ሽርጉድ... ያስተዋለኝ ሰው አልነበረም። ቤቴ ገብቼ ተኛሁ። ያለልማዴ የጠጣሁት እያስጓራኝ ወጣ። ሁሉም ሰዎች እንደዚህ መጠጥ ናቸው። ከህይወትህ ሆድ ውስጥ ለመውጣት ምቹ ጊዜ ነው የሚጠብቁት።
ንጋትን በወፎች ዝማሬ ተቀበልኩት። ያለ እንቅልፍ ተኝቼ አረፈድኩ። ሰዓቱ ሲደርስ ለባብሼ ከሰፈር ሰዎች ጋር ወደ እዚያ ሰርግ ሄድኩ። አዳራሹ በሰው ተጥለቅልቋል። ገንጠል ብዬ ተቀመጥኩ። ከአፍ እንደሚወጡት የሲጋራ ጭሶች ሃሳቤ ፊቴ ላይ እየተጠቀለለ ይጠፋል። ሲለው ጀርባዬን፣  ሲለው ድብርቴን፣ ሲለው ፍርሃቴን ይዞራል። ጊዜው ቢገፋም ሙሽሮቹ ሊመጡ አልቻሉም። እንግዳው ማጉረምረም ጀመረ። እዚያው እንደተቀመጥኩ ጀንበር ጠለቀች። መጨላለም ጀመረ። በዚህ ጊዜ ነበር ከእናኑ አፍ (እናኑ ያው የሰፈራችን የወሬ ሊቀመንበር ነች)  አስደንጋጭ ነገር የሰማሁት። አዎ... ሙሽራው የውሃ ሽታ ሆኖ ጠፍቷል። በእርግጥም ከዚህ ሃዘን የሚቀምሱ ሴቶች ጥቂቶች ናቸው። ለየዋህ እንስቶች ይህቺ ዓለም ከሲኦል የምትከፋ የስቃይ በኣት ነች።
* * *
በጊዜ ንብርብር ውስጥ መቀየር ጀመረች። ቀለም የማያጣቸው ከንፈሮቿ ውሃ እንዳጣ መሬት ተሰነጣጥቀው ይታዩ ጀመር። ፀጉራ አመድ መሰለ። በጥቂት ጊዜ ውስጥ ወዟ እንደ ቅጠል ከፊቷ ላይ እረገፈ። መንደሩን የሚቀይር የገላዋ ናትራን ጠፋ። ሳቋ ደመና እንደዋጠው የፀሃይ ብርሃን ደበዘዘ። ንግግሯ  “እሺ” “አዎ” ከሚሉ አታካች ቃላት አላልፍ አለ። ከሞት በከፋ ሃዘን በተደመደመው ሰርጓ ማግስት ሳገኛት አንድ ነገር ብቻ ነበር ያለችኝ። “ከእድሉ ጋር ታግሎ ማን ነው ያሸነፈ?” ዓይኗ እንባ አርግዟል፣ ግን አያለቅስም። ድምጿ ሲቃ እያስጨነቀው ተቀይሯል። ከዚያ በዃላ ደጋግሜ ባገኛትም ልታወራኝ አትፈልግም ነበር። ብቻ እንደ ጀንበር ስታዘቀዝቅ አየሁ። ሰዎች የሃዘን ተራራ ሲወጡ እጇን ሰዳ የምትደግፍ፣ በሰዎች መከፋት ውስጥ ደስታ ሆና የምትገኝ ይህቺ ሴት በእራሷ ሃዘን ስትሰበር አየሁ። ለሰው የሚተርፉ ብዙ ሰዎች ለራሳቸው እንደማይበቁ የተረዳሁት በዚህ ጊዜ ነበር። ሃፍረት የሰውን ልጅ በዚህ ደረጃ መቀመቅ ይከታል ብዬ የማልገምት የዋህ ነበርኩና። እሷ ግን ተሸነፈች። ብቻዋን ቤቷን ዘግታ መዋል ጀመረች። በእግዜር ላይ ያላት ፅኑ እምነት፣ እንደ ጤዛ በሃዘን ፀሃይ ከሰመ። ሰዎች ተጠቋቆሙባት። እስክታቀረቅር ድረስ አሟት። የአፍረቷ እሳት ላይ ቤንዚን ጨምረው ሃዘኗን አከፉት። እህቶቿ እና ወላጆቿ ሲያፍሩባት አየሁ። እሷ ባልሰራችው ኃጢያት ከአፍረት ሲኦል እንድትገባ ሲፈረድባት ምንም ማድረግ አልቻልኩም ነበር። እኔ ማንም በሌለኝ ሰዓት ሆዴ ሲጎድል እህል፣ ልቤ ሲጎድል ፍቅር እየመገበች ሰው ያደረገችኝ ሴት ብቸኝነት ውጧት፣ ሃዘን ሲያቆስላት ዝም ብሎ ከመመልከት ውጪ የማደርግላት አንድም ነገር አልነበረም። ትናፍቀኛለች... እንደ ድሮ እንድታቅፈኝ፣ እንደ ድሮ እንድትልከኝ፣ እንደ ድሮ እንድትስመኝ እፈልጋለሁ። “አላምን ብለህ ነው እንጂ እኮ ከእኔ ፍቅር ይዞሃል” እያለች የምትስቀው ነገር ናፍቆኛል። የድሮ ድምጿን መስማት ናፍቆኛል። ግራ ጉንጯ ላይ ያሉት ሶስት የማርያም ስሞሾችን እየነኩ እንደ ህፃን መጫወት ናፍቆኛል። እቅፏ ውስጥ ሆኜ መዋል ናፍቆኛል። ከእሷ ጋር እየጠጡ መደነስ ናፍቆኛል። ከእሷ ጋር አብሮ ሙዚቃ ማዳመጥ ናፍቆኛል። ጉርሻዋ ናፍቆኛል። “እናትንና” የሚል የውሸት ስድቧ ናፍቆኛል። መጥፎ ነገር አድርጌ ስታየኝ ፊቷ ላይ የሚያጠላው ኩርፊያ ናፍቆኛል። ሁሉ ነገሯ ናፍቆኛል። ስትናፍቀኝ ክፍሌን እቆልፍና ሙቅ የእንባ ፍሳሾቼን ጉንጬ ላይ አራግፍ ነበር።
ሃዘኗን  እያዩ ሁሉም እንዳላዩ ማለፍ ጀመሩ። የኛ ማህበረሰብ እንዲህ ነው። ወደ ሞት እየሄድክ ቢያይህ፣ ሆይ ሆይ ብሎ ጨፍሮ፣ ስንቅ ቋጥሮ ከሸኘኽ በዃላ ስትሞት ያለቅስልሃል። እራሱ ህመም ሆኖ ይገልህና፣ “በሽታው ሳይታወቅ ሞተ” እያለ ሰልስትህን ደግሶ ያበላልሃል። የሞትህን መንገድ እንዳልጠረገ ነፍሱን ይማረውና እያለ የሌለህን ጥሩነት ይነዛልሃል። ሲለው ሙት ወቃሽ አታድርጉኝ እና እያለ ያማሃል። እዚህ አገር ውስጥ ሞተህ እንኳን የማታመልጠው ብቸኛው ነገር ሃሜት የሚባል የሃበሻን ድንቁርና ነው።
አንድ ዕለት አዕምሮዋን ያማታል የሚል ወሬ ሰማሁ። ሃዘኔን መቆጣጠር ስለተሳነኝ፣  ሁለትም ስለናፈቀችኝ ... በዝምታ ወደ ቤቷ ሄድኩኝ። በሯ ላይ ሆኜ ስጠራት ዝም አለች። ልታወራኝ አልፈለገችም። በሯን ሳንኳኳ ብዙ ቆየሁ። እንደማልሄድ ሲገባት ነው መሰለኝ  ከፈተችልኝ። ቤቷ ጨልሟል። ቤቷም እንደ ልቧ ማቅ ለብሷል። መስኮቱ ተዘግቷል። ጣፋጭ ርሔው ጠፍቶ የሃዘን ጎፍናኝ ጠረን ባፍንጫዬ ተመላለሰ። አቀፍኳት። እንደ በድን ቀዝቅዛለች። በሁለቱ መዳፌ ጉንጯን ያዝኩት። ቅዝዝ ብላለች። እንባዬ መጣ። ከስታለች። መብራቱን አበራችው። መልኳን  አየሁት። ከቅላት ወደ መጠየም አገር ይጓዝ ነበር።
“ምን ሆነህ ነው?” አለችኝ...
“ለምንድነው እንዲህ የምትሆኚው” አልኳት..
“ምን ሆንኩኝ?”
“ከራስሽ ጠፍተሻል...ድሮ የማውቃት ሴት አይደለሽም”
“ትንሽ ደብሮኝ ነው”
“በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሁለት ዓመት ሞላሽ እኮ”
“እእ”
“የማትናፍቂኝ ይመስልሻል?”
“እኔም ትናፍቀኛለህ እኮ...” ብላ አቀፈችኝ... አገላብጣ ሳመችኝ...ከዚያም...
“ድሮ እንደማውቀው ነው ጠረንህ... አልተቀየረም! ሲገርም” አለችኝ...
በዚህ ጊዜ በዝምታ ከማልቀስ ውጪ ያደረኩት አንዳችም ነገር አልነበረም።
“ለምን ታለቅሳለህ? እኔ እኮ ደህና ነኝ...ትንሽ ድብርት ነው። እንደ ድሮ እየጠጣን እንደንሳለን እሺ። እነዚህ የሴት እጆችህ ወገቤን ይዘው እንደንሳለን... ትዝ ይልሃል ኣ? ሰው እንዳያየኝ ተደብቄ፣ ከአፍህ ነጥቄ ያጨስኳት ሲጋራ? ትዝ ይልሃል? ያ ቀውስ ሰውዬ “እናትና ልጅ እዚህ ምን ይሰራሉ?” እያለ ሲጮህ...ሃሃሃሃ... [የውሸት ሳቅ ሳቀች] ልጋብዛችሁ ብሎ አጠጥቶን የራሱን ሳይከፍል የሄደውስ ችስታ? ሃሃሃሃ....  እየኝ እስቲ... እንደ ሴት አታልቅስ እናትክንና... [ደግማ ሳመችኝ]  አንተ እኮ ብዙ ነገር ይጠብቅሃል። ቆንጆ ሚስት ታገባለህ - ግን ከእኔ በላይ እንዳትወዳት እሺ... ሃሃሃሃ...[ልታስቀኝ መልፋቷን ቀጠለች [ተደናቂ ገጣሚ ትሆናለህ። ደስተኛ ህይወት ትኖራለህ። በቀደም የአዕምሮ ሀኪም ጋር ሄጄ ነበር። አዕምሮዬ እንደታመመ ነገረኝ። ግን ቀላል ነው አያስጨንቅም። መድሃኒት ሰጥቶኛል። እድናለሁ እሺ። ስለእኔ አትጨነቅ ባክህ። አንተ ብቻ ደስተኛ ሁን...  በሰርጌ ቀን ጥሎኝ ሰለጠፋው እጮኛ ነኝ ባዩ ደደብ  ነው እንዴ የምታስበው? ገሃነብ ውረድ በለው!  ይሂድ ተወው ባክህ... በህይወትህ ውስጥ አንድ ደደብ ቢቀር ባይቀር ምን እንዳትሆን ነው? [ህመሟ እንዲቀለኝ አቃላ ትነግረኝ ጀመር] ቢመጣስ ምን ይጠቅማል? አግብቶ ልጅ መፈልፈል አንተን ከመሳም በላይ አያጓጓኝም እኮ... ና እስቲ... [ደረቷ ላይ አስተኛችኝ] ...”
“ያንቺን ሳቅ እናፍቃለሁ። ያንቺን ጤና እናፍቃለሁ። ያንቺን ደስታ እናፍቃለሁ።” ሳግ እያነቀኝ፣ ተናገርኩ...
“እናትህንና እየሳቅኩ አይደል እንዴ? አንተ እኮ ነህ የምታለቅሰው...የሰውን መጠቋቆም ሽሽት ነው እኮ ቤት የምውለው። ስራዬንም ለዚህ ነው የተውኩት። ሳትናፍቀኝ ቀርተህ ይመስልሃል? ጠልቼህ ይመስልሃል? እኔና አንተ እኮ ወንድምም፣ ጓደኛም ሁሉንም ነን። መደሰት ስፈልግ ካንተ ጋር ያሳለፍኩትን ህይወት እንደማስብ ታውቃለህ? ልብህ እኮ ማንም ያላየው የፍቅር ምንጭ ነው።”
ከሃዘኔ ብፅናናም “ወንድ ልጅ ብቻውን ነው የሚያለቅስ” የሚለውን የባለቅኔውን ስንኝ እንደ መርህ ስከተል ኖሬ፣ የምወዳት ልጅ ፊት መጫወቻውን እንደነጠቁት ህፃን ተነፋረቅሁ።
“አሁን ላይ ቤተሰቦቼ አይወዱኝም። አሁን ላይ የሰፈሩ ሰው ጠልቶኛል። ይወደኛል ያልኩት እጮኛዬም ጥላቻውን ሃፍረት በሞላው ክህደት ገልፆልኝ ሄዷል። እግዜርም ልጁ እንዳልሆንኩ በዝምታው ነግሮኛል።  እዚህ ምድር ላይ ለእኔ ሃዘን የሚያነባ ብቸኛ ሰው አንተ ነህ። እዚህም ምድር ላይ ከሚወዱኝ ሰዎች መሃል ለተዓምር የተረፈ ብቸኛ ሰው አንተ ነህ። መጀመሪያ የጉርምስናህን እሳት ለማቀዝቀዝ ነበር የቀረብኩህ። እንድትማር እንድትለወጥ፣ ብርቱ ሰው እንድትሆን ነበር የቀረብኩህ።  ስትታይ የምትገፈትር ህፃን ነበርክ። አሁን ግን ፍፁም ተለውጠህ የፍቅር ሰው ሆነሃል። ካንተ ልብ ውስጥ የክርስቶስን ፍቅር የሚገዳደር መውደድ ይወጣል ብዬ አልጠበቅሁም ነበር። ላገባ መሆኑን ስትሰማ ቅር እንዳለህ ፊትህ ላይ አንብቤያለሁ። ብቻ ሁሉም ይቅርና አቅፌ ልስምህ እንደናፈቅኩ እወቅ።”
ደረቷ ላይ ተኝቼ... ድምጿን እሰማለሁ። በህይወት ዘመኔ እግዜርን እንዲሰጠኝ ወይም እንዳይነሳኝ የጠየኩት ነገር የለም ነበር። አሁን ግን የዚህችን ልጅ እቅፍ እንዳይነሳኝ ጠየኩት። አሁን ግን የዚህችን ልጅ ፍቅር እንዳይነሳኝ ለመንኩት።
ሀኪም ቤት ስትሄድ አብሪያት እሄድ ጀመር። ቃሉን ድጋሚ እንኳን ልናገረው  የሚከብድ እንግሊዘኛ ጠርታ ህመሜ ይሄ ነው አለችኝ። የምትውጠው መድሃኒት ብዙ ነው። መልኳን ፍዝ የሞኝ ፊት አስመሰለው። ህዝባችን እብድ ብሎ እየሰደበ አግልሎ ከሚወግራቸው ታማሚዎች ውስጥ ቢያንስ ግማሹ የህመማቸው ምንጭ የዚህ ህዝብ አካል የሆነው ግለሰብ ነው። የህመማችን ንጥር የተቀመመው ስንታመም “እብድ” እያለ  ከሚያገለን አካል መሆኑ አይደንቅም?   የስቃያችን ምንጭ የፈለቀው ከወደድናቸው ነፍሶች ስር መሆኑ አያሳዝንም? የውድቀታችን መቃብር የተቆፈረው አንድ ጊዜ ወደድናችሁ  ብለው ባቀፉን ሰዎች እጅ መሆኑ አይገርምም? በግለሰብ እና በህዝብ  ስም የሚሰሩ በደሎች አሉ። ፍርድና ቅጣት የሌላቸው። ህሊና እንጂ ዳኛ እስር የማይበይንባቸው። እውነት ግን ወዴት ነሽ? እግዜር  ግን የት ነው ያለኸው?
* * *
ትንሽ እንደመሸ ወደ ቤት ልገባ መንገድ ስጀምር “አንተ ዱርዬ” የሚል ድምፅ ሰማሁ። እራሷ ናት። ያቺ ያመለኳት ጣዖት።
“የዛሬውን ምሽትህን ለእኔ ብትሰዋዉስ” አለችኝ... ከስንት ጊዜ በዃላ እውነተኛ የሚመስል ሳቋን እያሳየችኝ።
ሰው እንዳያያት ሲጨልም አንዳንዴ ትወጣ ነበር።
“እሱማ ደስታዬ ነው” አልኳት...
ተያይዘን ሄድን። አንድ ቤት ገብተን ጠጣን። ጭፈራ ቤት ገባን። ብዙ ደነስን። ደስተኛ ትመስል ነበር። ብዙ ድምፅ የሌለበት ቤት እንሂድ አለችኝ። ሄድን...
“ታፈቅረኛለህ አይደል?” አለችኝ...
“ምናይነት ማፍቀር?”
“ልታገባት እንደምትፈልጋት ሴት አይነት ማፍቀር”
“እውነት እሱን አላውቅም። የማውቀው ማፍቀር፣ መውደድ ከሚባሉ ቃላት በላይ አንቺን መውደዴን ነው።”
“ትረሳኛለህ ግን?”
“ብታጣኝ...ከዚህ በዃላ ባልኖር ካጠገብህ... ሁሉም ነገር ቢቀር የምትረሳኝ ይመስልሃል?”
ዝም አልኳት።
“እንካ ይሄን” ብላ፣ ከቦርሳዋ ውስጥ ብዙ ብር አውጥታ ሰጠችኝ።
“ምንድነው?”
“ለሰርጌ ማቋቋሚያ ይሆነኛል ያልኩት ብር ነው።”
“አውጥቼ እንዳልጥለው... ገንዘብ እንደሚያስፈልግሽ አውቃለሁ እኮ...”
“አይ ካሁን በዃላ ምንም ነገር አያስፈልገኝም”
“ማለት?”
“ተወው በቃ እሺ... ግን  ሁሌም ሲከፋህ  አንድ ነገር አስታውስ፤ እዚህ አጠገብህ የተቀመጠችዋ ሴት ከምንም በላይ ትወድሃለች። ሁሌም ስትደሰት አንድ ነገር አስታውስ፤ ይህቺ ሴት ከመጠን በላይ ታፈቅርሃለች። ብቻ አስደስተኝ። ጎበዝ ወንድ፣ ትልቅ ሰው ሁንና አኩራኝ። ጎበዝ ገጣሚ ሆነህ ነፍሴን  አስደስታት። ለእኔ የደበዘዘችው ህይወት ላንተ ስትፈካ ማየት ያስደስተኛል። ብታጣኝ እንኳን ብዙ አትዘን እሺ። ባታየኝ እንኳን ተፅናንተህ ህይወትህን ቀጥል።  ገባህ አይደል? [በዚህ መሃል ታለቅስ ነበር] በጣም ነው እሺ የምወድህ...በጣም...” ሳግ አቋረጣት እና ዝም አለች።
እኔም በዝምታዬ ፀንቼ ዝም አልኩ....ምሽታችን እንዲህ ባለ ግራ ባጋባ የወጀብ ንግግር  መሃል አለፈ።
ጠዋት ስነሳ ሰፈሩ ከበደብኝ። ሁሉም ሰው ዓይኑ ይሸሸኛል። ግራ ገብቶኝ አስፋልት ወጣሁ። የዚያች ሴት ቤት ግቢ ተከፍቷል። እናቶች ነጠላ ዘቅዝቀው ይገባሉ። የለቅሶ ጩኸት ሰማሁ። ፈዝዤ ቆምኩ። ግራ ገባኝ።  ወደ እዚያ ግቢ ቀረብኩ። ከግቢው የሚወጣ አንድ የማውቀውን ሰው አገኘሁ።
“ምንድነው?”
“ጓደኛህ...” ብሎ ዝም አለ...
“ምን ሆነች?”
“እራሷን አጥፍታ ነው ያደረችው”
ምን እንደማደርግ ጠፋኝ። ሰማይ እንደተደፋበት ሰው በሃዘን ጎበጥኩ። ደረት መድቃት፣ አመድ ነስንሶ መቀመጥ፣  ፀጉር እየነጩ ዋኔ ማለት፣ እንባ እንደ ጀረት  ማፍሰስ ከሃዘኔ ውቅያኖስ ላይ ጠብታ ያህል ማጉደል ብቻ  ነበር። ያቺ የመጨረሻ ምሽት፣ እነዚያ ግራ የሚያጋቡ የመጨረሻ  ንግግሮች ስንብት ይሆናሉ ብዬ አልጠረጠርኩም ነበር። የህይወቷን የመጨረሻውን ምሽት ከእኔ ጋር ብቻ ነበር ማሳለፍ የፈለገችው። ያቺ በህይወቴ ውስጥ ተዓምር የሚያሰኝ ፍቅር ይዛ የመጣችው እንስት ዛሬ ላይ ሙት ብቻ ነች? በፍፁም አይደለችም።  ለመጀመሪያ ጊዜ ከሰው መወለዴን  እንዳውቅ ያደረገችኝ  ሴት ዛሬ ላይ አራት ክንድ በማይሞላ መሬት ውስጥ ዘላለም ለመኖር ወስናለች። ካሁን በዃላ ህይወቴ እንደትላንት አይደምቅም። ካሁን በዃላ የሚስሙኝ ውብ ከንፈሮች፣ የሚያቅፉኝ ትሁት ክንዶች...በስስት የሚያዩኝ  ዓይኖች የሉም።  ካሁን በዃላ የህይወትን መከፋት የምከልልበት ፍቅር የለም።  ካሁን በዃላ የደስታዬ ጀንበር ላትመለስ ጠልቃለች። በትዝታዋ ብቻ እንድኖር ፈርዳብኝ ሄደች። እንገርጉሮዬ  “ነበር” የሚል ሙትን የመታቀፍ ዜማ እንዲሆን ፈርዳብኝ ሄደች።
“ታፈቅረኛለህ አይደል” ብላኝ ነበር...
ያንን የመጨረሻ ምሽት እድሜዬን ሙሉ  እንድኖር ፈርዳብኝ ሄደች። ያንን የመጨረሻ ንግግር ዘላለም እንዳስታውስ ፈርዳብኛለች። አንዳንድ ምሽቶች እንዲህ ናቸው -  በእድሜዬህ ልኬት ውስጥ የቅፅበትን ያህል ቢያጥሩም፣ ቀሪው እድሜህን ሙሉ እንድትኖራቸው ያስገድዱሃል። አንዳንድ ቅፅበቶች ከዘላለም በላይ የሚታወሱ ናቸው።
“የማውቀው ማፍቀር፣ መወደድ ከሚባሉ ቃላት በላይ አንቺን መውደዴን ነው” ብያት ነበር...
“ብታጣኝ እንኳን ብዙ አትዘን እሺ። ባታየኝ እንኳን ተፅናንተህ ህይወትህን ቀጥል። ገባህ አይደል?” ነበር ያለችኝ...
ሳልኖረው በደመነፍስ የተረዳሁት ነገር ልክ እንዳልሆነ ገባኝ። የሚወዱትን የማጣት ፍርሃት፣ የሚወዱትን ከማጣት በላይ ህመም አልነበረውም።
“ሁሌም ሲከፋህ አንድ ነገር አስታውስ፤ እዚህ አጠገብህ የተቀመጠችዋ ሴት ከምንም በላይ ትወድሃለች” ነበር ያለችኝ...
በእርግጥም አንዳንድ ቅፅበቶች ከዘላለም በላይ የሚታወሱ ናቸው።

Read 1481 times