Monday, 03 October 2022 00:00

ትናንትም፣ ዛሬም፣ ነገም፣ እነሱ አሉ!

Written by  አያሌው አስረስ
Rate this item
(2 votes)

የአገር አንድነትና ነፃነት የሚጠበቅበት መንገድ ብዙ ነው። ተሰላፊውም የመንገዱን መብዛት ያህል የበዛ ነው። ልክ እንደ ምድር አሸዋ፣ እንደ ሰማይ ከዋክብት።
የንጉሡን፣ የራሱን፣ የደጃዝማቹን ጦር ተከትለው የሚዘምቱ፤ በአማኑ ቀን ቅዳሴ የሚቀድሱ ጸሎት የሚያደርሱ። የከፋም ሲመጣ  የሟች ሰው ኑዛዜ የሚቀበሉ። ጦሩ ሊያፈገፍግ ሲዳዳው ገዝተው ወደ ውጊያው እንዲመለስ የሚያደርጉ ካህናት ዘማቾች ነበሩ።
ክራርና ማሰንቆ ተጨዋቾችና ቀረርቶና ፉከራ አዋቂዎች፣ ከጦሩ ፊትና ኋላ እየሄዱ ወኔ ቀስቃሽ ግጥም እየደረደሩ፣ ከጦሩ መካከል የጎበዝ የጎበዙን በስም እየጠሩ፣ እያወደሱ፣ ሰራዊቱ ወደ ፊት እንዲገፋ ጀርባውን ለጠላቱ እንዳይሰጥ ያደፋፍራሉ፤ ያጀግናሉ።
አንድን ሃይል መቀስቀስ ማንቃትና ማዘጋጀት ያለውን ጠቀሜታ የተረዱት ወገኖች፤ ኢጣሊያ ኢትዮጵያን ለመውረር እየተዘጋጀች ባለችበት ጊዜ፣ የኢትዮጵያ አገር ፍቅር ማህበርን መመስረታቸውን  ስናስታውስ፣ የምንረዳው የአንድ አገር  ነጻነት ለመጠበቅና  ለማስጠበቅ፣ የሚሰለፈው ወታደሩ ብቻ ሳይሆን እጅግ ብዙ ሃይል መሆኑን ነው።
የኢትዮጵያ መንግስት የሶማሌን ወራሪ ለመመከትና ወደመጣበት ለመመለስ በተነሳ ጊዜ ድርሻቸውን ተወጥተዋል። ደርግ የኢትዮጵያን አንድነት ለማስጠበቅ ከሻቢያ እና ከትህነግ ጋር በተዋጋ ጊዜ ሁሉ ማበርከት ያለባቸውን አገልግሎት አበርክተዋል።
ትሕነግ አሸናፊ ሆኖ ድል ባደረገ ቁጥር የሚይዛቸውን ንብረቶች “የኢትዮጵያ ሕዝብ ንብረት ተደርገዋል” እያለ ያውጅ ስለነበር፣ ግንቦት 20 ቀን 1983 ዓ.ም አዲስ አበባ ከገባ በኋላ “አሁን የመንግስት ሥልጣን ይዛችኋል፤ የወረሳችሁትን መኪኖች መልሱልን” የሚል ጥያቄ ያነሱ ባለቤቶች፣ አፍንጫችሁን ላሱት የሚል መልስ ተሰጥቷቸዋል። ከእነሱ በተወሰደ ንብረት ኢፈርት የተባለ ድርጅት ሲቋቋምና ሲጠበድል በአይናቸው አይተዋል።
በባድመ ጉዳይ በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ጦርነት በተከፈተ ጊዜ ትህነግ የበደላቸው በደል ከአእምሯቸው ባይጠፋም፣ በዚያ ጦርነት ወቅትም መኪኖቻቸውን ይዘው አገልግለዋል።
ለዓመታት በኢትዮጵያ ማዕከላዊ መንግሥት ላይ ውስጥ ለውስጥ ራሱን ለጦርነት ሲያዘጋጅ የቆየው ትሕነግ፤ ትግራይ ክልል በኢትዮጵያና በኤርትራ ድንበር አካባቢ ሰፍሮ በነበረው በመከላከያ ሰራዊት ላይ “መብረቃዊ ጥቃት” በሰነዘረ ጊዜ፣ መንግስት አገር ለማዳን ወደ ጦርነት ሲገባ አሁንም በጦር ግንባሩ እየተገኙ አገልግሎታቸውን እንዲሰጡ ተደርገዋል። በሁለተኛው ዙር ውጊያ እንዳደረጉት ሁሉ አሁንም በሦስተኛው ዙር ጦርነትም በየግንባሩ እየተገኙ ከጦሩ ጋር እየወረዱ እየወጡ ናቸው።
ትናንትም በዘመነ ደርግ ከትህነግ ጋር፣ ዛሬም በአሸባሪው ትህነግና እሱ ከፈለፈላቸው ወንጀለኛ ቡድኖች ጋር በሚደረገው ትግል ውስጥ፣ ሁልጊዜ ከመከላከያው ጎን የሚሰለፉትና የማይጠፉት የሕዝብ ማመላለሻ እንዲሁም የጭነት መኪና አሽከርካሪዎችና የመኪናዎቹ ባለቤቶች ናቸው። እነሱ ሁልጊዜም አሉ።
ሹፌሮች ተሽከርካሪዎቻቸውን ይዘው ወደ ግዳጅ በተንቀሳቀሱ ቁጥር፣ ከጠላት በተተኮሰ ጥይት መቁሰል፣ ወይም የአካል ጉዳት እንደሚያጋጥማቸው ይታወቃል። አንዳንዶቹም ህይወታቸውን ሊያጡም ይችላሉ። አጥተዋልም። አምና መንግሥት ጦሩን ከትግራይ ባወጣ ጊዜ ተቆርጠው  የቀሩ በህይወት ይኑሩ ይሙቱ የማይታወቁ ብዙ ሾፌሮች መኖራቸውን አለመጥቀስ ተገቢ አይደለም፡፡
በየጦር ሜዳው ተገኝተው አገልግሎት የሰጡ የህክምና ባለሙያዎችን ያከበረውና ያመሰገነው የጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አስተዳደር የሾፌሮችንና የባለ መኪናዎችን ውለታና አገልግሎት ሊዘነጋ አይገባም።
ለመከላከያና ለሕዝባዊ ሰራዊቱ (ሚሊሻው) እንዲሁም በልዩ ልዩ መንገድ ለጦሩ ድጋፍ  ለአደረጉ  ወገኖች ምስጋናውን ያቀረበው መንግስት፤ በትራንስፖርት ዘርፍ ያገለገሉ ወገኖችንም ዕውቅናና ምስጋና ሊቸራቸው ይገባል፡፡
ለምን ቢሉ፣ ኢትዮጵያ ምንጊዜም በጦርነት ምጣድ ላይ የተጣደች አገር በመሆኗ፤ ሁልጊዜም ከዜጎች መስዋዕትነት ስለሚጠየቅና ዜጎቿ “ትናንት መስዋዕትነት ከፍለናል ዛሬስ በቃን” ቢሉ ውጤቱ ነጻነትንና ነጻ አገርን ማጣት በመሆኑ፣ ለማያቋርጠው ትግል አጋርነቱን የማይነፍገው ወገን መከበርም መወደስም ይኖርበታል፡፡  
በግዳጅ ላይ ለተሰው ገነትን፤ በህመም ላይ ለሚገኙ መዳንን፣ በአሁኑ ጊዜ ግዳጅ ላይ ላሉ ሾፌሮች ሙሉ ጤናን ከልብ እመኛለሁ።

Read 8784 times