Saturday, 01 October 2022 12:27

የማዲንጎ አፈወርቅ የመጨረሻ ስንብት

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ባለፈው ማክሰኞ መስከረም 17 ቀን 2015 ዓ.ም ለህክምና በራሱ አውቶሞቢል ወደ ክሊኒክ ሄዶ በዚያው ህይወቱ ያለፈው የድምጻዊ ማዲንጎ አፈወርቅ የአሟሟት መንስኤ እስካሁን ያልታወቀ ሲሆን፤ ፖሊስ ተጨማሪ ምርመራ በማድረግ ላይ መሆኑን መግለጹ ይታወሳል፡፡ በሳምንቱ መገባደጃ በተሰማው መረጃ፤ የድምጻዊው ደም ለምርመራ ወደ ጀርመን የተላከ ሲሆን ውጤቱ ሲደርስ ለህዝብ ይፋ እንደሚደረግ ተጠቁሟል፡፡  
ይህ በዚህ እንዳለ የድምጻዊው የቀብር ስነ-ስርዓት በመንበረ ጸባኦት ቅድስተ ሥላሴ ካቴድራል ከትላንት በስቲያ በታላቅ አጀብና ክብር የተከናወነ ሲሆን በሥርዓተ-ቀብሩ ላይ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት፣ ምክትል ጠ/ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንንን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግስት ባለሥልጣናት፣የድምጻዊው ቤተሰቦች፣ ታላላቅ አርቲስቶችና የሙያ ባልደረቦች፣ እንዲሁም ወዳጆችና አድናቂዎች ተገኝተዋል።
የ17 ዓመት ሴት ልጁ ዲቦራ ማዲንጎ የአባቷን ህልፈት ተከትሎ ለመገናኛ ብዙሃን በሰጠችው ቃል፤ “ማዲንጎ አፈወርቅ ቤተሰቡን የሚወድና ለቤተሰቡ ትልቅ ፍቅርና እንክብካቤ የሚያደርግ አባት ነበር።” ብላለች።
አባቷ ለሃገሩም ይሁን ለወገኑ ትልቅ ሥራ የሰራ ሰው መሆኑን የገለጸችው ዲቦራ፤ ዘመን ተሻጋሪ ሥራ ሰርቶ በማለፉ ከማዘን ይልቅ እንደምትኮራበት ተናግራለች። “አባቴ ለሃገርና ለህዝብ መሥራትን አስተምሮኛል” ትላለች - ዲቦራ።
ከቀብር ስነ-ስርዓቱ በኋላ በመኖሪያ ቤቱ ተገኝተው ቤተሰቡንና ሃዘንተኛውን ያጽናኑት የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስትያን መምህር ምህረተአብ፣ ከማዲንጎ ጋር ቅርርብ እንዳላቸው ጠቁመው፤ በህይወት ሳለ ድሆችን በመርዳት እንደሚታወቅም ጠቆም አድርገዋል። አርቲስት  ዮሴፍ ገብሬ (ጆሲ) በበኩሉ፤ ማዲንጎ በቋሚነት የሚረዳቸው 300 ያህል ሰዎች እንዳሉ ሰሞኑን ለመገናኛ ብዙሃን ምስክርነቱን ሰጥቷል፡፡  
ድምጻዊ ማዲንጎ ከሰይፉ ጋር በኢቢኤስ ባደረገው ቃለ-ምልልስ፤ ለሱ  ትልቅ ደረጃ መድረስ የወላጆቹ ሚና አይተኬ መሆኑን በመጠቆም፤ መኪና ከመግዛቱ በፊት የወላጆቹን ውለታ መመለስ እንዳለበት ወስኖ እንደነበር አውስቷል። ውሳኔውንም በትክክል መተግበሩን ተናግሯል።
ከዚህም ባሻገር ለታናናሽ ወንድም እህቶቹም ድጋፍ ሆኖ ለቁም-ነገር  አብቅቷቸዋል- ወላጆቹ እሱን ለቁም ነገር እንዳበቁት።
የሙዚቃ ሃያሲው ሰርፀ ፍሬ ስብሃት ስለ ድምፃዊ ማዲንጎ ተጠይቆ በሰጠው አስተያየት፤ መጀመሪያ የተዋወቁት አዲስ ነገር ጋዜጣ ላይ “ማህደረ ቅኝት ማዲንጎ አፈወርቅ” በሚል ርዕስ በጻፈው መጣጥፍ እንደነበር ያስታውሳል፡፡
“እዛ አርቲክል ውስጥ ምስጋናና አድናቆት ብቻ አልነበረም ያለው፡፡ ጥቂት ትችቶችም ነበሩት፡፡ እውነቴን ነው የምልሽ፤ ማዲንጎን ይበልጥ እንዳከብረው ያደረገኝ ደግሞ እነዛን ትችቶች የተቀበለበትና ያስተናገደበት መንገድ ነው፡፡ አየሽ ማዲንጎ ሁሉም ሰው አድናቆት የሚሰጠው ሰው ስለሆነ፤የእኔንም አድናቆት መቀበሉ አይደለም የደነቀኝ፡፡ ቢሻሻሉ ብዬ ያሰብኳቸውንና ከፕሮዳክሽን ጥራት አኳያ ያነሳኋቸውን ሀሳቦች የበለጠ ዋጋና ትኩረት ሲሰጣቸው ሳይ እጅጉን ተደነቅሁ” ብሏል፤ ሰርፀ ፍሬ ስብሃት፡፡
ማዲንጎ የሚጫወታቸው ሙዚቃዎች ያስገርሙኛል የሚለው ሰርፀ፤ በነገራችን ላይ ማዲንጎ አንድ አልበም ለመስራት እስከ 30 እና 40 ግጥሞችና ዜማዎች ነው የሚገዛው፡፡ ይህን የሚገዛው ከተለያዩ ሰዎች ሲሆን መጨረሻ ላይ ተጨምቀው 12ቱ ብቻ በአልበም ይወጣሉ፡፡ የተቀሩት በሙሉ ገንዘብ ወጥቶባቸው ይቀራሉ” ሲል የታዘበውን ተናግሯል፡፡
ድምጻዊ ማዲንጎ አፈወርቅ ሶስተኛ አልበሙን ሲያወጣ የዛሬ 7 ዓመት ግድም ከአዲስ አድማስ ጋር ባደረገው ቃለምልልስ፤ በአልበሙ ውስጥ የተካተቱት ዘፈኖች የቀደመውን የወርቃማውን ዘመን የሙዚቃ ደረጃ እንዲይዙ አድርጌ ነው የሰራሁት ብሎ ነበር። ለማዲንጎ የወርቃማው ዘመን ድምጻውያን እነ ኤፍሬም ታምሩ፣ ንዋይ ደበበ፣ ሙሉቀን መለሰ፣ ፀጋዬ እሸቱ፣ አረጋኸኝ ወራሽ የመሳሰሉት ያሉበት ዘመን ሲሆን፤”ለእኔ ወርቃማውና የምወደው ዘመን ነው” ሲል ተናግሮ ነበር። በእርግጥም ገና ታዳጊ ህፃን ሳለ ነው የእነዚህን አንጋፋ ድምጻውያን ሥራዎች በማቀንቀን ወደ ሙያው የገባው። የሴት ድምጻውያንን ዘፈኖች ሳይቀር እያስመሰለ ይዘፍን እንደነበር በአንድ ወቅት ተናግሯል። የኢቢኤሱ ሰይፉ ፋንታሁን ሰሞኑን በዩቲዩብ በለቀቀው ቪዲዮ፤ ማዲንጎ የ14 ዓመት ልጅ ሳለ መድረክ ላይ የኤፍሬም ታምሩን “እስቲ እንዴት ነሽ” የተሰኘ ዜማ ሲያቀነቅን ይታያል፤ ህዝብ በተሰበሰበበት አዳራሽ።   
ድምፃዊው ከሰይፉ ጋር በነበረው ቃለ-ምልልስ፤ እስከ 10 ዓመቱ ድረስ አባቱ ባወጡለት “ተገኔ” የሚል ስም ሲጠራ ቆይቶ ማዲንጎ የሚለውን ስም ወታደር ቤት እንዳወጡለትና ስሙ በቀላሉ የሚያዝ በመሆኑ በዚያው እንደጸና ይገልጻል - የሚወደው ግን አባቱ ያወጡለትን ተገኔ የሚለውን ኢትዮጵያዊ ስም መሆኑን በመጠቆም።
የመጀመሪያ አልበሜ የልጅነት ሥራዬ ነው ሲል በአዲስ አድማስ ቃለ ምልልስ የተናገረው ማዲንጎ፤ “ያኔ ጠቆር ያልኩ ነበርኩኝ፤ እንዳሁን አልፈገግኩም ነበር። አሁን እንደ እባብ ቆዳ ቀይሬአለሁ” ብሏል፤ በራሱ እየቀለደ፡፡
አፈወርቅ በአገር ወዳድነቱ አይታማም - መለያ መታወቂያው ነው። ከልጅነቱ አንስቶ በሙዚቀኛነት በወታደር ለቤት ማደጉን የሚያወሳው አርቲስቱ፤ ይህም አገሩን ወዳድና ሰውን አክባሪ እንዳደረገው በተለያየ ወቅት ባደረገው ቃለ-ምልልስ ተናግሯል። የአማፂው የህወሓት ቡድን በኢትዮጵያውያን ላይ ጦርነት መክፈቱን ተከትሎ፣ ድምፃዊው ግንባር ድረስ ሄዶ የሰራዊቱ አለኝታነቱን አስመስክሯል - የመከላከያ ሀላፊዎች እንደመሰከሩት፡፡ ለዚህም አስተዋፅኦው ከጠ/ሚኒስትር ዐቢይ እጅ የምስጋናና የዕውቅና ሰርተፊኬት ተቀብሏል።
የመከላከያ  ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተሩ ኮሎኔል ጌትነት አዳነ በማዲንጎ ስንብት ላይ ባደረጉት ንግግር “ማዲንጎ በህይወት በነበረ ጊዜ ከሄደና ከመጣው ስርዓት ጋር ጎንበስ ቀና የሚል ሳይሆን የሀገርና የህዝብ አለኝታ ከሆነው የሀገር መከላከያ ሰራዊት ጋር በመቆም ሀገሩንና ወገኑን በሀቀኝት ከልጅት እስከ እውቀት አገልግሏል” ሲሉ መስክረውለታል።
በሌላ በኩል፤ ድምፃዊው ከህልፈቱ በፊት ለሰባት ዓመታት የደከመበትና የለፋበትን አራተኛ አዲስ አልበሙን ሰርቶ ማጠናቀቁን ለማወቅ ተችሏል።
“ብሩህ ነፀብራቁ፣
ውበትና ድምፁ፣አንድነት ተሰምተው
አንድነት ቢበርቁ
የሚያውቅለት ጠፍቶ
ሚስጢሩን አካቶ
ተወርዋሪ ኮከብ፣በራሱ ነበልባል፣በራሱ
ነዲድ ላይ ተቃጥሎ የጠፋ
ተወርዋሪ ኮከብ፣በምናውቀው ሰማይ ነበረ
በይፋ፡፡”
በማለት ታላቁ ገጣሚ ዮሐንስ አድማሱ ከተቀኘላቸው ተወርዋሪ ኮከቦች መካከል ድምፃዊ ማዲንጎ አፈወርቅ አንዱ ነው ብንል ማጋነን አይሆንም፤ ይላል ከትላንት በስቲያ በሥርዓተ ቀብሩ ላይ በተዋናይና ጋዜጠኛ ተፈሪ ዓለሙ የተነበበውና በህይወት ታሪኩ ላይ የሰፈረው መግቢያ፡፡


Read 21627 times