Saturday, 08 October 2022 09:31

በጋምቤላ ከተማ በብሔራዊ ሰብአዊ መብቶች ተቋምና ሠራተኞች ላይ ያነጣጠረ ጥቃትን ኢሰመኮ አወገዘ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

   የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ሰኔ 7 ቀን 2014 ዓ.ም. በጋምቤላ ከተማ ላይ በኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት (በተለምዶ ኦነግ ሸኔ) እና የጋምቤላ ነጻነት ግንባር (ጋነግ) ጥቃት መፈጸማቸውን ተከትሎ በጋምቤላ ክልል የጸጥታ ኃይሎችና በታጣቂ ቡድኖቹ የተፈጸሙ የሰብአዊ መብቶች ጥሰትን አስመልክቶ ያከናወነውን የምርመራ ሪፖርት መስከረም 18 ቀን 2015 ዓ.ም ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።
በሪፖርቱ በዝርዝር እንደተመለከተው፤ ከሰኔ 7 እስከ 9 ቀን 2014 ዓ.ም. ሲቪል ሰዎች ላይ የደረሱትን ጉዳቶች አስመልክቶ ኮሚሽኑ ከክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን፣ ከክልሉ ሰላምና ጸጥታ ቢሮ፣ ከክልሉ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጽሕፈት ቤት፣ ከፌዴራል ፖሊስ የምዕራብ መምሪያ ጋምቤላ ቅርንጫፍ ሬጅመንት፣ ከከተማው ማዘጋጃ ቤትና ከጋምቤላ አጠቃላይ ሆስፒታል ስለ ጉዳዩ መረጃና ምላሽ ተቀብሏል።
የፌዴራል ፖሊስ የምዕራብ መምሪያ ጋምቤላ ቅርንጫፍ ለኮሚሽኑ በሰጠው ምላሽ፤ ሰኔ 7 ቀን 2014 ዓ.ም. ኦነግ ሸኔ እና ጋነግ ታጣቂዎች በከፈቱት ውጊያ ከመንግሥት በኩል “የፌደራል ፖሊስ፣ የክልሉ ልዩ ኃይሎችና መደበኛ ፖሊሶች መሳተፋቸውን”፤ እንዲሁም “በውጊያው ወቅት በተወሰነ መልኩ የሰው እንቅስቃሴ በከተማ ውስጥ ስለነበር፤ በበራሪ ጥይቶች የተመቱ ሲቪል ሰዎች ሊኖሩ እንደሚችሉ” ግምት የነበራቸው ቢሆንም፣ “ከውጊያው በኋላ ባደረጉት ማጣራት የክልሉ ልዩ ኃይሎች በተለይ ሰኔ 8 እና 9 ቀን 2014 ዓ.ም. በከተማው በሲቪል ሰዎች ላይ ጥቃት እንዳደረሱ መረዳታቸውን” ገልጸዋል።
አክለውም መረጃው እንደደረሳቸውም ከሚመለከተው የመንግሥት ኃላፊ ጋር በመነጋገር ድርጊቱ መቆም እንዳለበት፣ ጥቃት አድራሾችም በሕግ አግባብ መጠየቅ እንዳለባቸው፣ በድርጊቱም የተነሳ ጥቃት የደረሰባቸው ሰዎች ካሳ እንዲከፈላቸው አቅጣጫ ማስቀመጣቸውን ለኢሰመኮ አስረድተዋል። ከሰኔ 23 ቀን 2014 ዓ.ም. ጀምሮ በክልሉ ፕሬዚዳንት የሚመራ ሕዝባዊ ውይይት ከሀገር ሽማግሌዎች፣ ከክልሉ ምሁራን፣ ከከተማው ነዋሪዎችና የክልሉ የመንግሥት ኃላፊዎች ጋር መደረጋቸውንም ጨምረው አስረድተዋል፡፡
 ሆኖም የሪፖርቱን ይፋ መደረግ ተከትሎ በማኅበራዊ ትስስር ድረ-ገጾችና መገናኛ ብዙኃን የተሳሳተ፣ አነሳሽና ዛቻ ያዘሉ መረጃዎች ሲሰራጩ፤ እንዲሁም በኢሰመኮ ባልደረቦች ላይ ያነጣጠሩ የጥላቻ መልእክቶች ሲዘዋወሩ ቆይተዋል ያለው ኮሚሽኑ፤ ጉዳዩን ከሚመለከታቸው ኃላፊዎች ጋር በመነጋገር መፍታት እንደሚቻል በማመን ምላሽ ከመስጠት ተቆጥቦ እንደነበር ጠቁሟል።
ይሁን እንጂ መስከረም 25 ቀን 2015 ዓ.ም. በቡድን ሆነው የመጡ ሰዎች ወደ ኢሰመኮ ጋምቤላ ጽሕፈት ቤት በመሄድ የተለያዩ የጥፋት ድርጊቶችን የፈጸሙ ሲሆን፣ በኢሰመኮ ባልደረቦች ላይ ዛቻና ማስፈራሪያም አድርሰዋል ብሏል። በተጨማሪም፣ በከተማዋ የተለያዩ የሰብአዊ መብቶች ሥራዎችን በሚያከናውኑ ሌሎች ድርጅቶች ላይ ተመሳሳይ ጥፋት አድርሰው ድርጅቶቹ “ከከተማው ለቅቀው እንዲወጡ” ማስፈራራታቸውን ኮሚሽኑ ጠቁሟል፡፡  
ኮሚሽኑ በሕገ መንግሥት የተቋቋመ ፌዴራል የብሔራዊ ሰብአዊ መብቶች ተቋም መሆኑንና የኮሚሽኑ ሠራተኞችም በአዋጅ የልዩ መብት ጥበቃ የሚደረግላቸው መሆኑን ያስታወሱት የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ፤ “ኮሚሽኑ የክትትልና የምርመራ ሥራውን በሚያከናውንበት ወቅት የተለያዩ ተግዳሮቶች የሚገጥሙት ቢሆንም፤ ይህንን ዐይነት በብሔራዊ ሰብአዊ መብቶች ተቋምና ሠራተኞች ላይ ያነጣጠረ ጥቃት ፈጽሞ ተቀባይነት የሌለውና በክልሉ የሰብአዊ መብቶች አያያዝ ላይ ከፍተኛ አሉታዊ ምልከታ የሚጥል በመሆኑ የፌዴራልና የክልሉ መንግሥት ተባብረው በአፋጣኝ እንዲያስቆሙ ኮሚሽኑ በጥብቅ ያሳስባል” ብለዋል።
ከሰኔ 7 እስከ ሰኔ 9 ቀን 2014 ዓ.ም. በተፈጸሙ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች ተጎጂዎችና የተጎጂ ቤተሰቦች አሁንም ሟቾች የተቀበሩበትን ቦታ ለማወቅና ፍትሕ ለማግኘት በመጠባበቅ ላይ በመሆናቸው የኮሚሽኑ ምክረ ሃሳቦች በአፋጣኝ እንዲተገበሩም የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ በድጋሚ አሳስበዋል፡፡

Read 11428 times