Saturday, 08 October 2022 09:33

የደቡብ አፍሪካው የሰላም ድርድር መራዘሙ ተገለፀ

Written by  ናፍቆት ዩሴፍ
Rate this item
(3 votes)

   • መንግስት የሰላም ድርድሩን መቀበሉ አሸናፊነቱን ያሳያል ተብሏል
      • የኢትዮጵያን ህዝብ ቀጣይ መከራ ለማስቀረት ድርድሩ ወሳኝ ነው
      • ድርድሩ ህገ-መንግስቱን መሰረት ያደረገ መሆን አለበት - (አረና ፓርቲ)
       
       በአፍሪካ ህብረት መሪነት በኢትዮጵያ መንግስትና በህወሓት ቡድን መካከል በነገው ዕለት እሁድ ሊካሄድ ታቅዶ የነበረው የሰላም ውይይት መራዘሙ ተገለፀ። ድርድሩ የተራዘመው በሎጂስቲክ ምክንያት መሆኑን ሮይተርስ የዲፕሎማቲክ ምንጮቹን ጠቅሶ ዘግቧል።
ለ2 ዓመት ገደማ የዘለቀውን የሰሜኑን ጦርነት ለማስቆም የአፍሪካ ህብረት በደቡብ አፍሪካ ባዘጋጀው የሰላም ንግግር ላይ መንግስትንና ህውሐትን መጋበዙን ተከትሎ፤ ሁለቱም ግብዣውን የተቀበሉ ሲሆን፤ ድርድሩን በተመለከተ በምሁራንና ፖለቲከኞች ዘንድ የተለያዩ ሃሳቦች እየተንፀባረቁ ነው፡፡
አንጋፋው ፖለቲከኛ አቶ የሸዋስ አሰፋ በሰጡት አስተያየት በአገራችን “ምንጊዜም ለድርድርና ለንግግር መሽቶ አያውቅም” የሚል ወርቃማ አባባል መኖሩን  አስታውሰው፤ መንግስትም ሆነ አማፂው ሃይል ለንግግርና ለውይይት ህብረቱ ያቀረበውን ጥሪ መቀበላቸው ተገቢም አስፈላጊም ነው ብለዋል፡፡
እስከዛሬ ድረስ ከውይይትና ከንግግር ውጪ የተቋጨ ጦርነት እንደማያውቁና ለህዝቡ ደህንነት እንዲሁም ለሰላምና ለመረጋጋት ሲባል ድርድሩን መቀበል አስፈላጊ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡ “ጦርነቱ አንድ ቀን ሲቀረውም ቢሆን ለድርድር መቀመጥና ሊሞት የነበረን አንድ ክቡር ህይወት መታደግም ቀላል አይደለም ያሉት አቶ የሸዋስ ድርድሩ ግን የኢትዮጵያንና የህዝቡን ጥቅም የሚያስከብርና ጥንቃቄ የተሞላበት ሊሆን እንደሚገባው አሳስበዋል፡፡ የኢትዮጵያን ህዝብ ጥቅምና መብት ሲባል ግን የትግራይንም ህዝብና ጥቅም የሚያካትትና የትግራይን ህዝብ ለተራዘመ መከራ እንዳይዳረግ የሚያደርግ ድርድር ማለታቸውን እንደሆነ ያብራሩት ፖለቲከኛው፤ ለዚህ ደግሞ የኢትዮጵያ መንግስት ከፍተኛ ሃላፊነት ያለበት እንደመሆኑ ብልሃት የተሞላበት ድርድር ማድረግ እንደሚያስፈልግ ነው ያስገነዘቡት፡፡ “ይሄ ሁሉ መስዋዕትነት ተከፍሎ ክቡሩ የሰው ልጅ ህይወት አልፎና የሀገር ሀብት ወድሞ ከአማፂው ቡድን ጋር ለድርድር መቀመጥ አያስፈልግም ፤መፍትሄው ጦርነቱን በአሸናፊነት መቋጨት ነው የሚሉ ወገኖች አሉ፤ ይህንን እንዴት ያዩታል?” በሚል የተጠየቁት አቶ የሽዋስ ሲመልሱ፤ ጦርነቱ በኢትዮጵያ አሸናፊነት መቋጨት እንዳለበት አለበት ብለው እንደሚያምኑ  ነገር ግን አሸናፊነት የሚገኘው በጦር ሜዳ ብቻ ሳይሆን በእንደዚህ ያሉ መድረኮችም በሚደረግ ብስለት የተሞላበት ድርድር መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ምንም እንኴን በመንግስትና በአማፂው ቡድን መካከል በተካሄደው ጦርነት በርካታ ለንግግር የማይመቹ የሰብአዊና የሀብት ኪሳራዎች ቢደርሱም የድርድሩ ዓላማ ይህ መከራ እንዳይደገም በመሆኑ ድርድሩን መንግስት መቀበሉ አግባብ ነው ብለዋል፡፡ ላለፈው ግፍና መከራ ፤ ለደረሰው የሰው ልጅ ህይወት መጥፋትና የሀብት ውድመት በድርድሩ ወቅት ተጠያቂዎች ለህግ እንዲቀርቡ እንዲሁም ትጥቅ እንዲፈቱ  በመሞገት ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥቶ መደራደር ተገቢ ነው ብለዋል፡፡ “ድርድርና ንግግር ሲባል ቀድሞ ወደ አዕምሯችን መምጣት ያለበት ህዝብ መሆን አለበት” ያሉት አቶ የሺዋስ፤ እስካሁን የትግራይ ህዝብ ምን እየበላ እየጠጣና እንዴት ሆኖ እየኖረ እንደሆነ አናውቅም፣ ምን አይነት መከራ ግን እያሳለፈ እንደሆነ መገመት አያስቸግርም ፤ ለኢትዮጵያም ለትግራይ ህዝብም ሰላም ሲባልና ቀጣዩን መከራ ለማስቀረት ድርድሩና ንግግሩ ወሳኝ መሆኑን አስምረውበታል፡፡
በድርድሩ አማፂው ቡድን ከስምምነት ላይ ይደርሳል ብለው ይገምታሉ ወይ በሚል ተጠይቀውም፤ “ጉዳዩን ጊዜው ሲደርስ ነው የምናየው” ያሉት ፖለቲከኛው፤ የሆነ ሆኖ ህወሓት በጦርነቱ እየተሸነፈ መምጣቱን ተከትሎ፣ ብዙ ድጋፎቹን እያጣ በመሆኑና የህወሓት መሪዎች ህይወታቸውን ለማትረፍም ሲሉ ስምምነት ላይ ይደርሳሉ ብለው እንደሚገምቱ ገልፀዋል።  ስምምነት ላይ ባይደርሱም ግን አሸናፊዋ ኢትዮጵያ ናት ብለዋል። ምክንያታቸውን ሲያስረዱም ፤ህወሓት ከዚህ ቀደም የነበሩ የሰላም አማራጮችን ገፍቶ ወደ ጦርነት በመግባቱ ለትግራይ ህዝብ ተቆጥሮ የማያልቅ መከራ ሰጥቶታል፤ አሁንም የተሰጠውን የሰላም ዕድልና የድርድር መድረክ ቢገፋ የትግራይ ህዝብም አንቅሮ እንደሚተፋውና የዓለም አቀፉ ማህረሰብም የህወሓትን ሰላም ጠልነት የበለጠ እንዲያውቅ እድል ስለሚያገኝ በዚህ ሁሉ ኢትዮጵያ አሸናፊ ትሆናለች ብለዋል።
የአረና ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበር አቶ ጎይቶም ፀጋዬ በበኩላቸው፣ ሁለቱ ፓርቲዎች (ብልፅግናንና ህወሃትን ማለታቸው ነው) ገና ሳይካረሩና ወደ ጦርነት ሳይገቡ በፊት አፍሪካ ህብረት ለማደራደር ያቀረበውን ሃሳብ ውድቅ ማድረጋቸውን አስታውሰዋል።
በብልፅግና በኩል ያሉት አመራሮች የአፍሪካ ህብረትን የእናደራድራችሁ ጥያቄ፤ “እኛ የ3 ሺህ ዘመን ታሪክ ያለን ሀገር ሆነን ትላንት የተፈጠራችሁ አገራት ልታደራድሩን አትችሉም” በማለት ድርድሩን ገፍተዋል ያሉት አቶ ጎቶም፤ ህወሃቶችም ቢሆኑ አፍሪካ ህብረት የማደራደር አቅም የለውም ሌሎች ሀገራት ያደራድሩን በማለት ጥሪውን ውድቅ አድርገውታል ብለዋል።
በሁለቱም በኩል ድርድሩ ባለመካሄዱ ጦርነት ተጀምሮ አሁን ላለቀው ህዝብ፣ ለደረሰው መከራ ተዳርገናል ያሉት የአረና ፓርቲ ም/ሊቀመንበሩ፤ ዞሮ ዞሮ አፍሪካ ህብረት ላደራድር ቢልም አቅም የለውም ይህንን ከዚህ ቀደም በአንድ አፍሪካ አገር ሞክሮ አልተሳካለትም ይላሉ።
በአፍሪካ ህብረት አርቲክል 4/8 (four eight) የተሰኘ ችግር ሲፈጠር ጣልቃ የሚገቡበት (ሂውማኒቴሪያን ኢንተርቬንሽን) አላቸው ያሉት አቶ ጎይቶም ከዚህ ቀደም በብሩንዲ ላይ ይህን ለመፈጸም ሲሞክሩ ሀገሪቱ ስለተቃወመች ህብረቱ ጣልቃ ገብቶ ችግሩን አለመፍታቱ አቅመ-ቢስነቱን ያሳያል ብለዋል።
የሆነ ሆኖ ህብረቱ  አቅምና የማስፈጸም ብቃት ባይኖረውም፣ የራሳችን ስለሆነና በራሳችን አህጉር እንዲህ አይነት የሰላም ድርድሮችን መለማመድ ስላለብን ለድርድር መጥራቱ የሚናቅ አለመሆኑንም አብራርተዋል።
በፓርላማ አሸባሪ የተሰኘው ቡድን ትጥቅ ሳይፈታ እደራደራለሁ ማለቱን ብዙዎች በጥርጣሬ እንደሚያዩት ያነሳንላቸው ፖለቲከኛው፤ “የትኛው ፓርላማ ነው አሸባሪ ብሎ የፈረጀው? ማን ማንንስ ነው አሸባሪ የሚለው?” ሲሉ የህወሓትን በአሸባሪነት መፈረጅ ጥያቄ አንስተውበታል። ህገ-መንግስት ባልተቀየረበት ሁኔታ፣ በፊት በኢህአዴግ ውስጥ ያሉት ሰዎች አሁንም ባሉበት ሆነው  አንዱ አንዱን አሸባሪ የማለት የሞራልም ሆነ የህግ አግባብ የለውም” ሲሉ ተሟግተዋል። ከዚህ ቀደም አረና ሲታገልና ሲቃወም የነበረው ሁሉንም የግንባሩን (የኢህአዴግን አባላት) እንጂ በተናጠል አይደለም ያሉትም ሊቀመንበሩ፤ “አሁንም ጉዳዩን መንግስትና ህወሓት እያልን ከምንጠራ ህወሓትና ብልጽግና ፓርቲዎች እያልን ብንጠራ የተሻለ ነው፣ የአሁኑ ፓርላማም የትግራይ ህዝብ ውክልና የለውም “ብለዋል።
አሁን ሁለቱ ፓርቲዎች ድርድሩን መቀበላቸውና ወደ ድርድር መምጣታቸው ተገቢ ነው ያሉት አቶ ጎይቶም ፓርቲያቸው አረናም በድርድርና በንግግር የሚያምን መሆኑን ጠቁመዋል።
ሁለቱ አካላት በደቡብ አፍሪካው የድርድር መድረክ ከስምምነት ላይ ይደርሳሉ ብለው ይገምታሉ ወይም በሚል ተጠይቀውም፤ “መገመትን ምን አመጣው፤ የግድ ስምምነት ላይ መድረስ አለባቸው። ባለመስማማታቸውና ድርድር በመግፋታቸው ወጣት እያለቀ፣  አገር ኢኮኖሚዋ እየደቀቀ፣ ህዝብ እየተፈናቀለ ነው ያሉት አቶ ጎይቶም፣ በዚህ ድርድር ስምምነት ላይ ካልደረሱ የወጣቱ እልቂት፣ የህዝብ  ረሃብና መፈናቀል፣ የሀገር ኢኮኖሚ ውድቀት እንዲቀጥል ማድረግ ነው። ይህ ደግሞ አልደራደርም ብሎ ሰላም የሚገፋውን አካል በወንጀል ያስጠይቃልና፤ ሁለቱም የግድ ስምምነት ላይ መድረስ አለባቸው ሲሉ አሳስበዋል።
በድርድሩ ወቅት ቢነሱ የሀገርን ሰላም የህዝብን መብት ያስጠብቃሉ ብለው የሚያነሷቸው ሀሳቦች ምንድናቸው በሚል ላነሳንላቸው ጥያቄ፤ የመጀመሪው ጉዳይ ድርድሩ ህገ-መንግስቱን መሰረት ያደረገ መሆን አለበት፤ ምክንያቱም ሁለቱም ፓርቲዎች “መንግስት” ነን የሚሉት በህገ-መንግስቱ መሰረት ነው ብለዋል።
ሌላው ጉዳይ የመጀመሪያው የክልል ድንበር (ቴሪቴሪ) መከበር አለበት ያሉት አቶ ጎይቶም፣ የህወሓት ሃይልም ከአማራ ክልል፣ የአማራ ክልል ሃይልም ከትግራይ ድንበር መውጣ አለበት ብለዋል። “መከላከያ ሰራዊትም ቢሆን ትግራይን የመከላከልና የመጠበቅ ሃላፊነት እያለበት ከኤርትራ ሃይል አስገብቶ የትግራይን ህዝብ ማስጠቃትና ህዝቡን ማፈናቀል የለበትም” ሲሉ ተናግረዋል- የአረና ም/ሊቀመንበር።
በሎጅስቲክ ምክንያት መራዘሙ የተነገረለት የደቡብ አፍሪካው የሰላም ውይይት የሚመራው በአፍሪካ ህብረት ሲሆን የኮሚሽኑ ሊቀመንበር ሙሳፋኪ መሐመት፤ የውይይቱን አደራዳሪዎች ከትላንት በስቲያ ሃሙስ ይፋ አድርገዋል።
በዚህም መሰረት፤ ድርድሩ በአፍሪካ ህብረት የአፍሪካ ቀንድ ከፍተኛ ተወካይና የቀድሞው የናይጀሪያ ፕሬዚዳንት ኦሉሴጉን ኦባሳንጆ፣ በቀድሞው የኬኒያ ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታና በቀድው የደቡብ አፍሪካ ምክትል ፕሬዚዳንት ዶ/ር ፉምዚሌ ምላምቦ- ናግኩ የሚመራ ይሆናል ተብሏል።
Read 22072 times