Saturday, 08 October 2022 09:34

የመንግሥት እና የእነ ደብረጽዮን ድርድር

Written by  አያሌው አስረስ
Rate this item
(0 votes)


        ትሕነግ፤ የትግራይ ሕዝብ ነፃ አውጪ ግንባር ብሎ ራሱን ስለጠራ፣ የትግራይን ህዝብ ይወክላል ተብሎ መታሰብም መታመንም የለበትም። ከመንግስት የድርድሩ መሪ ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ጀምሮ ሁሉም ተደራዳሪዎች፣ ትሕነግን “የትግራይ ሕዝብ ወኪል ነው” የሚል እምነትና አስተሳሰብ ካላቸው አስቀድመው በድርድሩ ጠረጴዛ ዙሪያ ከመቀመጣቸው በፊት ይህን ሃሳባቸውን ከአእምሮአቸው ውስጥ አጥበው ማውጣት አለባቸው። ምክንያቱም ለወንበዴው ቡድን የማይገባ ዋጋ መስጠትን ያስከትላልና ነው።
ትሕነግ የትግራይ ሕዝብ ተወካይ ሳይሆን በትግራይ ሕዝብ ስም የሚነግድ የፖለቲካ ቁማርተኛ ስብስብ መሆኑን ለመገንዘብ መቻል፣ ለሚያነሳቸው ጥያቄዎች “ይህ የአንተ ጉዳይ አይደለም፤ የፌደራሉ መንግሥት ለሕዝቡ የሚያስፈልገውን ሁሉ ያደርጋል፤ ከማድረግም ወደ ኋላ አይልም” በማለት ቀንድ ቀንዱን ለመምታት ያስችላል።
ቡድኑን ትሕነግ ወይም በተለምዶ “ሕወሓት” ከማለት ይልቅ “የእነደብረ ጽዮን ቡድን” እያሉ መግለፁም አስፈላጊ ነው። መንግስት ይህን አገላለጽ ለመጠቀም በቂ ምክንያት ያለው ከመሆኑም ባሻገር፣ “ከልክህ አትለፍ” ብሎ ሥርዓት ለማስያዝም ያገለግላል።
እንኳን አደራዳሪዎች በአገር ውስጥ ያሉ አንዳንድ ወገኖች ሳይቀሩ የእነደብረጽዮን ቡድን  ጦርነት የከፈተው እሱ እንደሚያወራው ተገፍቶ የሚመስላቸው አሉ፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት ተደራዳሪዎች ለአደራዳሪዎቹ በግልጽ ሊያሳያቸውና በቂ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ሊያደርጉበት ከሚገባ ደረቅ እውነት አንዱ፤ የእነደብረ ጽዮን ቡድን የመንግስት አካል ሆኖ፣ በኢትዮጵያ መንግሥታዊ ሥልጣን ላይ ተቀምጦ፣ ከኢትዮጵያ የመከላከያ ሃይል ላይ መድፍ፣ ታንክ፣ ጸረ አይሮፕላን ወዘተ ከከባድ እስከ ቀላል መሳሪያ ሲዘርፍ፣ በየቦታው ሲያከማች የኖረ መሆኑን ነው። “የትግራይ ሕዝባዊ ሰራዊት” የሚለውን ተዋጊ በብዛት ካሰለጠነና ከአስታጠቀ በኋላ፣ ጥቅምት 23 ቀን 2013  ዓ.ም በመንግስት መከላከያ ኃይል ላይ “መብረቃዊ ጥቃት” ሰንዝሮ ወደ ጦርነት የገባ መሆኑን ማስረዳት አደራዳሪዎቹ ሀሳባቸውን ለማደራጀት እንደሚጠቅማቸው  ማሰብ ይኖርባቸዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመሩት የተደራዳሪው ቡድን አባላት፣ የእነደብረጽዮንን ቡድን ንቅናቄ ብቻ ሳይሆን የቃል አጠቃቀም ሳይቀር በክትትላቸው ውስጥ ማስገባት አለባቸው። እነደብረጽዮን “የትግራይ መንግሥት” ብለው ሲመጡ፣ “እንዲህ ተብሎ የሚጠራ አካል የኢትዮጵያ መንግሥት አያውቅም” በማለት ቀንዳቸውን ሊላቸው ይገባል፡፡
ሲጀምር  የፌደራሉ መንግስት ልዑካን እነደብረ ጽዮንን የክልሉ ገዥ አድርጎ መቀበል የለበትም። ምክንያቱም በመጀመሪያው ጦርነት እነደብረጽዮንን ከስልጣን አባርሮ ቢከዱትም  በዶ/ር ሙሉ ነጋ የሚመራ ጊዜያዊ አስተዳደር መስርቶ ስለነበርና ከዚያም በኋላ በዶ/ር አብርሃ በላይ የሚመራ አስተዳደር እንደነበር ስለሚታወቅ ነው።
ድርድሩ እንዲካሄድ አጥብቀው ከሚፈልጉት አሜሪካና የአውሮፓ ኅብረት መሻት  ምግብ መድሃኒትና መሰል መገልገያዎች ወደ ክልሉ እንዲገቡ ማድረግ የመጀመሪያ እንደሚሆን ይጠበቃል። እራሱ መንግስት እንዳመነው፣ የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች እስከሚሰለች ድረስ በተደጋጋሚ እንደገቡት የዓለም የምግብ ድርጅት መኪናዎችም ሆኑ ሌሎችም እርዳታ አቅራቢ ድርጅቶች ለእነደብረጽዮን ቡድን ልዩ ልዩ መሳሪያ ሲያስተላልፉ፣ ገንዘብ ሲያዘዋውሩ ነው የኖሩት። መንግስት በቅንነት በቆረጠው ዱላ ሲደበደብ መባጀቱ ድብቅ አይደለም። ስለዚህም ወደ ትግራይ የሚገባ ማንኛውም ተሽከርካሪ፣ ሲጭን መጫን ያለበት የመንግስት ተቆጣጣሪ በተገኘበት ብቻ መሆን ይኖርበታል። በምንም ምክንያት የእነደብረጽዮን አቅምን የሚያጎለብት ሁኔታ መፈጠር የለበትም - በዚህ ረገድ መንግስት መጠንቀቅ ያስፈልገዋል።
እነደብረጽዮን መንግሥትን አብዝተው የፈተኑትና አንዳንድ ጊዜም ቀድመውት ሲሄዱ የነበረው በፕሮፓጋንዳው ትግል ነው። ድርድሩ ለፕሮፓጋንዳ የተጋለጠ እንዳይሆን አብዝቶ መጠበቅ ያስፈልጋል። መንግስት በዚህ በኩልም በብዙ እጥፍ ታጥቆ መነሳት ይኖርበታል።
መንግስት ያለውን ኃይልና አቅም ተጠቅሞ የትግራይ ሕዝብና የእነደብረጽዮን ቡድን አንድ አለመሆናቸውን፣ ለትግራይ ሕዝብ ያለውን ተቆርቋሪነት በየአጋጣሚው ማሳየት፣ ከማሳየትም በላይ የሚታመን እርምጃ በመውሰድ ማሳወቅ ቸል ሊለው የማይገባ ኃላፊነት መሆኑን መገንዘብ ይኖርበታል።
መንግስት ወደ ድርድር ለመግባት ዝግጁ መሆኑን ባሳወቀበት በዚህ ሰዓት፣ የመከላከያ ኃይሉና ጥምር ጦሩ በእነደብረጽዮን ቡድን ሰራዊት ላይ የበላይነት የያዘበት፣ የድል አድራጊነቱም መንፈስ እጅግ ከፍ ባለ ደረጃ ላይ የሚገኝበት ጊዜ ነው። በየጊዜው አዳዲስ ድል እየተመዘገበ ነው።
እነ አሜሪካና አውሮፓ ኅብረት ተኩስ አቁምን የድርድሩ ቀዳሚ አጀንዳ አድርገው እንደሚያቀርቡት ይገመታል። ግምት ብቻ ሳይሆን እንደሚያቀርቡም አያጠራጥርም። ድርድሩ የተፈለገው ለእነደብረጽዮን ቡድን ፋታ ለመስጠት፣ ከተቻለም ትጥቅ ማቅረቢያ ጊዜ ለማግኘት መሆኑ የታወቀ ነው። መንግስት አሁን ሞኝ መሆን የለበትም። የሁለት ጊዜውን ተኩስ አቁም የእነደብረጽዮን ቡድን የተጠቀሙበት ጥርሳቸውን ለመሳል፣ ጥፍራቸውን ለማሳደግ ነው። ስለዚህም መንግስት የተኩስ አቁም ስምምነት ጥያቄን ገና ከመቅረቡ ውድቅ ማድረግ አለበት። መቀበልም ከፈለገ ደግሞ አስቀድሞ እነደብረጽዮን ትጥቅ ለመፍታት ዝግጁ መሆናቸውን ማረጋገጥ አለበት።
እነደብረጽዮን ስለመገንጠል የሚያወሩት ለፖለቲካ ንግድ እንደሆነ አምናለሁ። ለድርድር ያቀርቡታል ብዬ ከምገምተው ጥያቄ ውስጥ በሕገ-መንግስቱ መሠረት፣ “የራስን ዕድል በራስ መወሰን እስከ መገንጠል ድረስ” የሚለው አንዱ ሊሆን ይችላል። ይህ በሕግ የታወቀ መብት በመሆኑ አይቻልም ብሎ መቃወም ያዳግት ይሆናል። ሆኖም ክልሉ በእነደብረጽዮን ቡድን ፕሮፓጋንዳ ስር ለብዙ ዓመታት የቆየ በመሆኑና ሕዝብ ወድዶም ሆነ ተገዶ በአሸባሪውን ቡድን አስተሳሰብ ተጽዕኖ ሥር ሊወድቅ ይችላል። አዲስ ሀሳብ ለማስተናገድና ነገሮችን ለመመርመር ጊዜ ስለሚያስፈልገው መንግስት በትግራይ ክልል የቀጥታ አስተዳደር ስርዓት አስፈላጊነትን አስረግጦ ማሳየት ይኖርበታል። በስምምነቱ ይህን መቀበሉ የማይታለፍ ጉዳይ መሆኑም ሊሰመርበት የግድ ይላል፡፡
ፈጣሪ ሰላምን ለኢትዮጵያ ሕዝብ ያውርድ!


Read 2104 times