Saturday, 08 October 2022 09:44

የመኮንኑ ተላላኪ

Written by  ደራሲ - ኤድሞንድ ደ አሚሲስ ትርጉም - አስቻለው ፈቀደ
Rate this item
(6 votes)

  ላለፉት 4 ዓመታት ለአፍታን´ኳ ተለያይተው አያውቁም። ታዲያ በእነዚህ ዓመታት ውስጥ አንደኛው መኮንን፤ ሌላው ደግሞ የመኮንኑ ተላላኪ መሆናቸውን ለደቂቃ አልዘነጉትም። ምንም እንኳ በመካከላቸው የዝምታ ድባብ  አጥልቶ አስቸጋሪና ፈታኝ በሆነው የውትድርና ስነ-ስርዓት ተገዥ ቢሆኑም፣ በዝምታ የተዋጡና አንዱ ለአንዱ የመተሳሰብ ጥልቅ ወዳጅነት ያላቸው ናቸው። መኮንኑ ለተላላኪው ያለውን ፍቅር የሚገልጽበት ምንም አይት መንገድ ስለሌለውና ደካማም መስሎ ላለመታየት ከንፈሩን ገጥሞ፣ እንባውን እየገፋ የግዱን ዝምታ መርጦ ማሳለፉን ተለማምዶታል።
ሁለቱም የሚግባቡት በአይናቸው ወይም ጥቂት ቃላቶችን በመጠቀም ነው።
“መቶ አለቃ-ሌላ የሚያዙን ነገር አለ?”
“የለም”
“መሄድ እችላለሁ?”
“አዎ ሂድ።”
እለቱን የሚሰነባበቱባቸው ቃላቶች እነዚሁ ናቸው። ሌላ ቃላት የለም። በቤት ውስጥ፤ በልምምድ፣ በካምፕ፣ በጦርነት፣ እየተባለ ወራት፣ ዓመታት-አራት አመታት ነጎዱ። እያደር እነሱ ያልጠረጠሩት እርስ በርስ የመተሳሰብ ፍቅር በልባቸው ትልቅ ስፍራ ያዘ። በጦር አውድማ የጠላት መድፍ በጆሯቸው ስር እያፏጨ በመቶ እርምጃ እርቀት ጎን ለጎን አብረው ተዋግተዋል። በዚህን ጊዜ ታዲያ አንደኛው በፍጥነት ዙሪያውን ይቃኝና ጓደኛውን ሲያየው “እንደገና ደግሞ ከሞት አፋፍ አመለጥን አይደል?” ብሎ እፎይታውን ተንፍሷል። በቀዝቃዛና በዶፍ ዝናብ ፊታቸው በውርጭ እየተገረፈ እግሮቻቸው ጭቃ ውስጥ ተዘፍቀው ከአንድ ምሽት በላይ አብረው ዘብ አድረዋል። ተረኛው የሌሊት ዘብ ሲመጣላቸውም “እንኳን ደስ ያለህ እንግዲህ ግዳጃችንን ፈጽመን ወደ ጦር ካምፓችን ልንመለስ ነው፤ አንተም ትንሽ ታርፋለህ” ብለው በማሰብ ፈገግታ ተለዋውጠዋል።
ከእንደዚህ ዓይነቱ የእፎይታ ነጻነት መልስ እንደገና ወደለመዱት ጥብቅ ወታደራዊ ስነስርዓት ትዕዛዝና ዝምታቸው ይመለሳሉ። ወታደሩ አለቃውን ሲያገኘውም ሆነ ሲሰናበተው አንገቱን ቀና በማድረግ አይኖቹን ትክ ብሎ እያየው የባርኔጣ ሰላምታውን መስጠቱን አንዴም እንኳ ችላ ያለበት ቀን የለም።
በዚሁ ሁኔታ  ለአራት ዓመታት አብረው ኖረዋል። አንድ ቀን መኮንኑ ወታደሩ የሚገኝበትን የጦር ክፍል እንዲያሰናብት ትዕዛዝ ስለደረሰው የዚህ ወታደር የመሰናበቻ ጊዜው ደረሰ።
የመሰናበቻው ትዕዛዝ የመጣ ቀን መኮንኑና ወታደሩ ወትሮ ከሚለዋወጡባቸው ቃላቶች ላይ በመጠኑም ቢሆን ጨማመሩበት። ልባቸው ግን ከዚያም በላይ ዘልቆ ብዙ ይናገራል።
“መቶ ዓለቃ ተጨማሪ ትዕዛዝ አለዎት?”
“የለም የምትሰናበትበት ትዕዛዝ ደርሷል። ስለዚህ በአስር ቀናት ውስጥ ትሄዳለህ።”
አልተያዩም። ለአፍታ ያህል ዝምታ ሰፈነ።
“መሄድ እችላለሁ?”
“ትችላለህ።”
እነዚህ ተጨማሪ ቃላቶች ወደ ፍቅራቸው የሚወስዷቸው ዋና መተላለፊያ መንገድ መሆኑን ጠቋሚ ነው። አንደኛው ጓደኛውን ከጓደኛውም በላይ የሆነውን ወንድሙን ሊያጣ ነው። ሌላው ደግሞ ያለምንም ጥርጥር ጓደኛውን ሊለይ ነው። ቢያንስ ግን ወደ ቤቱ መመለሻው ነው።
ከብዙ ዓመታት በኋላ እና ከብዙ አደጋ አፋፍ ተርፎ ቤቱ የሚመለስበት ይህ ጊዜ ለወታደሩ እፎይታ ነው። ለምን ያህል ጊዜ “በአሁኑ ሰዓት ያች ምስኪን እናቴ ምን እየሰራች ይሆን?” በማለት በጦር ካምፑ ውስጥ ሆኖ አስቦት ይሆን? እቤቱ ሲያዜመው የነበረውን ዜማ ስንት ጊዜ ሰምቶታል?! ሳያስበው ቤቱንና የትውልድ ቀየውን ተመልሶ ሊያይ የቤታቸውን ጣሪያ ደግሞ ከሩቁ አይቶ በአንድ ትንፋሽ ሮጦ ሊደርስ፣ ታናሽ እህቱ አድጋና ወንድሙ ወጣት ሆኖ ሊያገኘው እንግዲህ እቤቱ ይመለሳል! እነዚህን ነገሮች  ማሰብ በራሱ ያለፈውን ምሬቱን የሚያጠፋለትና ቁስሉንም ለማጥገግ በቂ ናቸው።
ግን ይሄ ጎበዝ የግዱን አለቃውን ትቶ የመሄዱን ሃሳብ ከራሱ ጋር ሊያስማማው ተሳነው።  አንድ ወታደር ጓደኛውን “ይቅር በለኝ” ለማለት እንደሚፈልግ ሁሉ ለዓመታት ገላውን የሸፈነውና ትራሱ ሆኖ ያለቀውን ኮቱን አንዳች ሃዘን ሳይጭርበት አያወልቀውም። በአንድ ወቅት እስር ቤት እያለ በድንገት የዘብ መኮንኑ ሲደርስበት ፒፓውን የደበቀባቸውንና አሁንም ልምድ ሆኖበት እጆቹን ሰድዶ ሲጋራ የሚፈልግባቸውን እነዚህን የደንብ ልብስ ኪሶች ከአሁን ወዲያ ሲያጣቸው ምንኛ ይበሳጫል!
መኮንኑና ወታደሩም ፊት ከሚለዋወጡበት ቃላቶች ላይ ምንም ባይጨምሩበትም ከወትሮው በተለየ መልኩ ግን “በጣም አዝነሃል ይሰማኛል” የሚሉ ይመስል ደጋግመው አይን ለአይን ይጋጫሉ። በተቻለ መጠን ወታደሩ በዓለቃው ቤት ለረጅም ቀናት መቆየት ስለፈለገ ሳይጣደፍ ስራውን ይሰራል። የወንበሮቹንና ጠረጴዛዎቹን አቧራ የሚያጸዳ ቢያስመስልም ብዙውን ጊዜ ግን መወልወያውን በአየር ላይ አድርጎ ያንቀሳቅሳል። አብዛኛውን ጊዜ በሃዘን የተሞሉ ሃሳቦች ውስጥ ይሰወራል። መኮንኑም ቀጥ ብሎ ሳይንቀሳቀስ በመቆም እጆቹን እንዳጣመረ እያንዳንዱን የወታደሩን እንቅስቃሴዎች በተመስጦ ይከታተላል።
“መቶ ዓለቃ መሄድ እንችላለን?”
“ትችላለህ።”
ተራ ወታደሩ ወጣ።
ከቤቱ ወጥቶ ሁለት እርምጃ ሳይራመድ ድንገት “አንዴ ና” ተብሎ ከክፍሉ ውስጥ ሲጠራ ሰምቶ ተመለሰ።
“ሌላ የሚያዙኝ ነገር አለ?”
“የለም የለም ግን ማለቴ የሆነ ነገር ማለት ፈልጌ ነበር፤ ግን ተወው ተወው፤ ነገ ትሰራዋለህ፤ አሁን ሂድ።”
ወታደሩ ተመልሶ እንዲመጣ መኮንኑን የጠራው ምናልባት ሊያየው ፈልጎ ይሆናል።
አይደርስ የለም በመጨረሻ ወታደሩ ተሰናብቶ የሚሄድበት ቀን ደረሰ። መኮንኑ የሚያጨሰው የሲጋራ ጭስ በአይኖቹ ላይ እምባን አቀረሩበት። በግማሽ ሰዓት ውስጥ ተላላኪው ዓለቃውን ሊሰናበት ለአንዴም ለመጨረሻም ጊዜ ይሄዳል። መኮንኑም እንደተቀመጠ በሃሳቡ “ለዚህ ስንብት እንግዲህ ራሴን ባዘጋጅ ይሻለናል።” ለመሆኑ ዘላለም ከእኔ እንዳይለይ ማድረግ እንደማልችል አላውቅም? የአገልግሎት ዘመኑስ አምስት ዓመት መሆኑን አላውቅም? ሰውየው እኮ ተወልዶ ያደገበት ቤት አለው። በሀዘንም የተለያቸው ቤተሰቦች አሉት። አሁን ደግሞ በደስታ ይቀላቀሏቸዋል። ለምንስ ታዲያ ከኔ ጋር ይቆያል? ምንስ ምስጋና ይከፈለኛል? እኔ እንደሁ ለሱ ምንጊዜም አስቸጋሪ ሰው ነበርኩ። ይሄ ደግሞ ባህሪዬ ነው። ለዚህም ምክንያቴ ይሄ ነው ብዬ በቂ ማስረጃ ማቅረብ አልችልም።  በጦሩ ውስጥ ያለ ማንኛውም ሰው ይሁን እንደነዚህ ዓይነት ነገሮችን ስፈጽም  ደፍሮኝ አያወጣቸውም። ለሱ ግን ቢያንስ ጥሩ ፊት ማሳየት ይኖርብኛል። ይኸው እንግዲህ ከብዙ ዓመት አብረው መኖር በኋላ ሊሰናበት ነው። የእኛም ህይወት እንደዚሁ ነው። አንድ ሰው እንደዚህ ዓይነቱን አጋጣሚ ከራሱ ጋር ማስታረቅና አሜን ብሎ መቀበል ግዴታው ነው። ግን ምንኛ ቅን ሰው ነው! ጠባየ ሸጋ! ጉዟችን ላይ አንዳንድ ጊዜ በድካም ዝለን፣ የጸሐዩ ሃሩር ሲያነደንና የአሸዋው አቧራ ጉሮሮአችንን ሲያንቀን የሚቀመስ ውሃ ለመጠጣት እፈልግና ቆም ብዬ ዙሪያዬን ሳማትብ ወዲያው ከጎኔ ቆሞ ኩባያውን ያስጨብጠኝና “መቶ ዓለቃ ውሃ ፈለጉ?” የሚል ድምጽ አጠገቤ ይሰማል - እሱው ነው። ተሰልፎ የሚጓዘውን ጦር ሹልክ ብሎ በመውጣት ከየት እንደሚያመጣው ሳይታወቅ ሩቅ ቦታ ሮጦ ይሄድና በድካም ላብ አዝፍቆት ይመጣና መጠጣት እስክፈልግ ድረስ ከኋላዬ በመሆን ይጠባበቃል - ምንጊዜም እሱው ነው። በካምፕ ውስጥ ከዛፍ ጥላ ስር ከተኛሁ የጸሐዩ ንዳድ ፊቴን ሲለበልበኝ ካየው ከኔ በላይ ሆኖ እጆቹ ቅርንጫፎቹን በመተላለፍ ስራቸውን ያቀላጥፋሉ። አለያም ካፖርቱን በእጆቹ ላይ በማዋል ከቃጠሎው የሚከላከልልኝ እሱ ነበር፤ ሁሌም እሱ። በካምፕ ሰንበሌጥ አምጥቶ መሬቱ ላይ ይዘረጋጋና በአንደኛው በኩል እንደ ትራስ አድርጎ ካስተካከለ በኋላ “መቶ ዓለቃ ይመቸዎታል?” ይለኛል።
እንደዚያ ሲያደርግልኝ “በእርግጥም ጥሩ ጓደኛ” ብዬ አስብና “ሂድ እረፍት ያስፈልግሃል” እለዋለሁ።
“ምናልባት ካልበቃዎት ትንሽ ላምጣና ልጨምርበት” ይላል።
“በቂ ነው ተስማምቶኛል ጊዜ አታቃጥል። ሂድና አረፍ በል” ብዬ እነግረዋለሁ።
በሌሊት ጉዟችን ላይ እንቅልፍ ከአንዱ መንገድ ወደ አንዱ መንገድ እያንጎላዠ ሲያውተረትረኝና ገደል አፋፍ ላይ ስቃረብ ክንዴ ላይ ቅልል ያለ እጅ አረፍ ያደርግና በዝግታ ወደ መሃል መንገድ ሳብ አድርጎ እየመራኝ በሚያባብል ድምጽ “መቶ ዓለቃ እሱ ጋ ገደል ስላለ እያየህ” ብሎ ሹክ የሚለኝ ምንጊዜም እሱው ነው።
“ለመሆኑ ምን አድርጌለት ነው እንደዚህ ዓይነቱን እንክብካቤና ፍቅር የሚያሳየኝ? በእውነቱ በጣም እራሴን ወዳድ ነኝ። ስለ እራሴ ብቻ ነው የማስበው። ለኔ ሲል ህይወቱን አሳልፎ እንደሰጠኝ ቅንጣት ያህል አልጠራጠርም። በዚህ ችግር ባደነደነው አካሉ ጉስቁልና በሚነበብበት ፊቱና በሻከረው እጁ ምንም ሳይማር እንደ አንድ መልካም ሚስት ቅንና ቸር ሊሆን የቻለበት ምን ምክንያት ቢኖረው ነው? ስተኛ እንኳን እንቅልፌን ላለማስተጓጎል ትንፋሹን አያሰማም። ታዲያ ከእነዚህ የደንብ ልብሶቹ ውስጥ ወታደር ያልሆነው የተቀረው የሰው ልጅ ከዚህ በፊት የማያውቀው አዲስ የሆነ ፍቅራዊ መግባባትን እንደሚማር የተረጋገጠ ነው። ብዙ ሰዎች እንደሚገምቱት እኛ ወታደሮች ምንም አይነት መተሳሰብና መፈቃቀር እንደሌለንና ቢኖርም በጦር ሜዳ ብቻ ያለ አድርገው ነው የሚያስቡት። በእውነት አያውቁንም!
የወታደር ልብ የወጣትነት ፍቅሩን እንደያዘ ነው - አያረጅም። የሰራዊቱን ፍቅር መረዳት ከፈለጋችሁ ብዙ ሌሊቶችን በጦር ሰፈር ውስጥ ማሳለፍ፣ ረዥም ጉዞ በሃሩር ጸሃይ መጓዝ፣ ፊትን በሚገርፍ ወጨፎ ዘብ መቆም ወይም ህሊናችሁን እስክትስቱ ድረስ በረሃብና በውሃ ጥም መገረፍ ይኖርባችኋል። በእነዚህ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ሁሉ አንተን ከቅዝቃዜው ሊከላከልልህ የራሱን ኮት አውልቆ የሚሰጥህ ጓደኛ ከጎንህ አለ። ታዲያ ራሱን ነፍጎ ጉሮሮ የሚያረጥብ ውሃ ወይም ኩርማን ጋሌጣ የሚሰጥህ እሱ አሽከር?  እንደዚህ ዓይነቱን ሰው አሽከር እንለዋለን? እሱን እንደዚያ ብሎ መጥራት ጭካኔ አይሆንም?” አለና መኮንናችን እጁን እያወዛወዘ አወጋ።
እነሆ ጊዜው ደርሶ ይህ ታማኝ ወዳጄ ትቶኝ ሊሄድ ነው። ከአሁኗ ደቂቃ ጀምሮ ግን  በፍጹም አላየውም! ላየውም አይቻለኝም። ነገር ግን ከሄደ እቤቱ ድረስ ሄጄ እጠይቀዋለሁ። የሚኖርበትን ስፍራ ስለማውቀው ሰፈሩንና የሚያርፍበትን የእርሻ ቦታ እጠይቃለሁ። ታዲያ እርሻው ላይ እንዳለ ስሙን ጠርቼ “ዓለቃህን አታስታውስም?” በማለት በግርምት አስደምመዋለሁ።
እሱም በተራው “ማንን ነው የማየው? መቶ ዓለቃ? እዚህ እርስዎ መጡ?!” እያለ ስሜቱ ፈንቅሎት ይናገራል።
እኔም፤ “እንዴታ! ደህንነትህን መጠየቅ አለብኛ!...ና! የኔ ወታደር! ተጠጋኝ” እለዋለሁ።
ያለምንም ማንገራገር የተናገረውን ከመፈጸም ወደኋላ እንደማይመለስ ሰው ዝግ ያለ፣ ብዙም የማይሰማውንና እየቀረበ የመጣውን የእግር ኮቴ ሲሰማ፣ በእነዚህ ሃሳቦች ውስጥ ተውጦ ነበር። ልቡን ጨብጦ የያዘው አንድ የሆነ ነገር አለ። ፊቱን አዞረ። እሱ ነበር። ተላላኪው።
ተላላኪው በጣም ስለጨነቀው አይኖቹ ቀልተዋል። ሰላምታ ሰጥቶ አንድ እርምጃ ወደፊት ሄደና በመቆም አለቃውን አስተውሎ ተመለከተው። መኮንኑ ፊቱን ወደሌላ ቦታ እንደመለሰ ነው።
“መቶ ዓለቃ መሄዴ ነው” አለ ወታደሩ።
መኮንኑ ከንፈሮቹን አንድ ላይ ነክሶ ወደ ሌላ ቦታ መመልከቱን እንደቀጠለ፤ “እስካሁን እንዳደረከው እንደ አመለ-ሸጋ ሰው ኑሮህን ቀጥል። ስራህን ስራ። ደህና ግባ። መልካም ጉዞ።”
“መቶ ዓለቃ!” በማለት በተቆራረጠ ድምጽ ተናገረና አንድ እርምጃ ወደ መኮንኑ ቀረበ።
“ሂድ ሂድ። ረፍዶብሃል አለበለዚያ ትዘገያለህ ቶሎ በል” አለና መኮንኑ እጁን ሲዘረጋለት ወታደሩ አጥብቆ ጨበጠው። “መልካም ጉዞ አትርሳኝ። አንዳንዴም ዓለቃህን አስታውሰው” አለው መኮንኑ።
ምስኪኑ ወታደር የመኮንኑን እጅ እንደያዘው ሊመልስለት ፈልጎ ነበር። ነገር ግን ከአንደበቱ አንድ ቃል ሊያወጣ ቢፈልግም ተናነቀው። እስካሁን ድረስ ፊቱን ወዳዞረው መኮንን ተመለከተና ወደፊት ቀረብ አለ።
“መቶ ዓለቃ!” ብሎ ጮኸ።
ይሄንን ብቻ ተናገረና ተፈትልኮ ወጣ።
 ሌላኛው ብቻውን ቀረ። ፊቱን አዞረና  ለደቂቃ ያህል በር በሩን አይቶ እንዳበቃ ክርኖቹን ጠረጴዛ ላይ አሳርፎ እራሱን በእጆቹ ይዞ ድፍት አለ። ሁለት ትላልቅና ክብ ዓይኖቹ እንባውን ሞልተውት ስለነበር በፍጥነት ሾልከው በጉንጮቹ ላይ ቁልቁል ወረዱ። እጁን ወደ ዓይኖቹ በመውሰድ ጠረጋቸውና ሲጋራውን ተመለከተ። ጠፍቶ ነበር።
ጭንቅላቱን በክንዶቹ ላይ አሳርፎ ራሱን ለመሪር ሃዘን ሰጠ።
(አዲስ አድማስ፤ ሚያዝያ 25 ቀን 1995 ዓ.ም)

Read 1024 times