Print this page
Saturday, 15 October 2022 11:06

መንግስትና ህውኃት ጦርነቱን በዘላቂነት ለማስቆም በቅን ልቦና ይደራደሩ ዘንድ ተጠየቁ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

 የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅትን ለማስተባበርና ለመወከል የተቋቋመው የኢትዮጵያ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ም/ቤት ፤ በሰሜን ኢትዮጵያ የሚካሄደውን ጦርነት በዘላቂነት ለማስቆም መንግስትና ህውሃት በቅን ልቦና እንዲደራደሩ ጠይቋል- በሳምንቱ መጀመሪያ ባወጣው መግለጫ፡፡
መንግስትና ህውኃት በሰላም ድርድሩ በሃገሪቱ ውስጥ ያሉ ዜጎችን ሁለንተናዊ ደህንነት የሚረጋግጥ ስምምነት ላይ ይደርሱ ዘንድ የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ ግፊት እንዲያደርጉም መክሯል-ም/ቤቱ፡፡
በሰሜኑ የሃገሪቱ ክፍል ያለው የትጥቅ ግጭት እያስከተለ ያለውን ከፍተኛ የህይወትና የአካል ጉዳት ከግምት ውስጥ በማስገባት፤ በመንግስትና በህውሐት በኩል ወደ ድርድሩ ለመመለስና ሰላምን ለማስፈን እየታየ ያለውን ተነሳሽነት ያደነቀው ም/ቤቱ፤ የአፍሪካ ህብረት የሰላም ሂደቱን በመደበኛነት ለመያዝና ለመምራት የማያደርገውን ጥረትም አመስግኗል፡፡
በሌላ በኩል፤ በምዕራብ ኦሮሚያ በሰላማዊ ዜጎች ላይ እየደረሰ ያለው ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ጥሰት፤ የጅምላ ጭፍጨፋና ሁከትን ለመግታት የተወሰደው እርምጃ በቂ አለመሆኑ እጅጉን እንደሚያሳስበው ም/ቤቱ በመግለጫው አስታውቋል፡፡ ከዚህ አንፃርም ውዱን የሰው ልጅ ህይወት ለመታደግና በአካባቢው መረጋጋትን ለማስፈን፤ መንግስት ከወትሮው በተሻለ ከፍተኛ ጥረት እንዲያደርግና የዜጎችን ደህንነት እንዲያረጋግጥ ም/ቤቱ ጥሪውን አቅርቧል፡፡
የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ም/ቤት፤ ለዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ባቀረበው ጥሪም፤ የሰላም ሂደቱን ገንቢ በሆነ መንገድ እንዲደግፍና ግጭቶችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የሚደረገውን ጥረት ከሚያሰናክሉ ማናቸውም ተግባራት እንዲታቀብ በአፅንኦት ጠይቋል፡፡
ም/ቤቱ በተጨማሪ ምሁራንና መገናኛ ብዙኃን ከፍተኛ ሚና የሚጫወቱ የማህበረሰቡ ወሳኝ ባለድርሻ አካላት መሆናቸውን ጠቁሞ፤ ሁለቱም አካላት በሰላሙ ሂደት እንዲሁም በሰብአዊ ድጋፍ  እርዳታ ላይ ገንቢ ሚና እንዲጫወቱም  ጥሪ አቅርቧል፡፡
በመጨረሻም በዚህ ወሳኝ ወቅት በትጥቅ ግጭቱ ዳግም መቀስቀስ ሳቢያ ለጉዳት ለተዳረጉ በሺዎች ለሚቆጠሩ ዜጎች ሰብአዊ እርዳታ በማድረስ ረገድ አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት የሚመለከታቸው አካላት በሙሉ እንዲረባረቡም አሳስቧል፡፡
በዚህ ረገድ ም/ቤቱ የሲቪል ማህበረሰቡን በማደራጀትና በማስተባበር፤ የሰላም ግንባታና የሰብአዊ ድጋፍ ሥራዎችን አጠናክሮ ለመቀጠል ያለውን ዝግጁነትና ቁርጠኝነት በድጋሚ እንደሚያረጋግጥም አስታውቋል-በመግለጫው፡፡
“በምዕራብ ኦሮሚያ የዜጎችን ግድያ ለማስቆም በቂ እርምጃ አለመውሰዱ ያሳስበኛል”  

Read 11560 times
Administrator

Latest from Administrator