Print this page
Saturday, 15 October 2022 11:09

የመተላለቅ ፖለቲካ ወደ ድርድር ፖለቲካ መቀየር አለበት

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

    ፕ/ር መረራ በአፍሪካ ህብረት አደራዳሪነት እምነት የላቸውም
                    
        የህዝብ ተወካዮች ም/ቤትና የፌዴሬሽን ም/ቤት ሁለተኛ ዓመት የሥራ ዘመን በፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ንግግር የተከፈተ ሲሆን በንግግራቸውም የ2014 ዓ.ም የመንግስት ዕቅድ  አፈጻጸምና አዲሱን ዓመት የ2015 ዓ.ም የመንግስት የትኩረት አቅጣጫዎች አቅርበዋል።
ባለፈው ዓመት የዜጎች የጅምላ ግድያ፣ መፈናቀል፣ ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች የተፈጸመ ሲሆን በሚሊዮን የሚቆጠሩ ህጻናት በከፋ የምግብ እጥረት ለሞት አደጋ መጋለጣቸውን ፕሬዚዳንቷ ጠቁመዋል። የዚያኑ ያህል አስደማሚ ስኬቶችም መመዝገባቸውን ያነሱት ፕሬዚዳንቷ ከህዳሴ ግድብ ሶስተኛ ዙር የውሃ ሙሌት እስከ ለኤክስፖርት የሚቀርብ ስንዴ ምርት የሚደርስ ስኬት ተመዝግቧልም ብለዋል። በዚሁ የፕሬዚዳንቷ ንግግር አስተያየታቸውን የጠየቅናቸው የተቀዋሚ ፓርቲ አመራሮች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡
በሀገሪቱ የሚታየው የመተላለቅ ፖለቲካ ወደ ድርድር ፖለቲካ ካልተቀየረ፣ ዘላቂ ሰላም እንደማይመጣ የተናገሩት የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) ሊቀ መንበር ፕ/ር መረራ ጉዲና፤ አሁን በሀገሪቱ ያለው የእርስ በርስ ደም መፋሰስና እልቂት ወደ እውነተኛ ድርድር ካልተቀየረ ችግሩ እየባሰ እንጂ እየተሻሻለ እንደማይሄድ ተናግረዋል። ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ባቀረቡት ንግግር ላይ አስተያየታቸውን በስፋት የሰጡት ፕ/ር መረራ መንግስት ችግሩ አንዱንም የተናገረውን ጉዳይ በተግባር አለመፈጸሙ ነው፤ ንግግር ብቻውን ደግሞ የሚያመጣው ፋይዳ የለም ብለዋል። ውጤት የሚያመጣው ንግግር ብቻ ሳይሆን በተግባር ላይ ማዋል ነው ያሉት ፕሮፌሰሩ የኢትዮጵያ መንግስት እስካሁን የተናገረውን ተግባር ላይ በማዋል ላይ አልተሳካትም፤ ወደፊት የሚሳካለት ከሆነ አብረን እናያለን ብለዋል።
ግን መንግስት ይሳካለታል ብለው ይጠብቃሉ ወይ በሚል ተጠይቀውም፣ “አሁን እየተሄደበት ባለው መንገድ ብዙ የሚሳኩ ነገሮች ያሉ አይመስለኝም፤ ጦርነቱ ላይ በርትተናል፤ እሱ ከተሳካ አላውቅም ሲሉም መልሰዋል።
ፕሬዚዳንቷ  “መንግስት ሁሌም ለሰላም ድርድሩ ዝግጁ መሆኑንና ህወሓት የሰላም ድርድሩን  ከረገጠ ግን የማስታገሻ እርምጃ ይወስዳል በሚል የተናገሩትን እንዴት ያዩታል? በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ  “መንግስት ጠንካራ አቋም ላይ ተመስርቶ መናገሩ ሲሆን ህውሃት ሰላም ካልፈለገ ግን ከፍተኛ እርምጃ የመውሰድ አቅም አለኝ የሚለውን መልዕክት ለማስተላለፍ ፈልጎ የተናገረው ነው” ብለዋል። ዞሮ ዞሮ ነገሩ አዲስ አይደለም ባለፉት አራት ዓመታት ሲባል የቆየና የተለመደ አባባል ነው- ብለዋል ፖለቲከኛው።
በፕሬዚዳንቷ ንግግር ያልተዳሰሰ ወሳኝ አገራዊ ጉዳይ ይኖር እንደሆነ ጠይቀናቸውም፤ “እኔ በአብዛኛው ጉዳይ ተስፋ እየቆረጥኩ ስለመጣሁ፣ መንግስት የሚናገራቸውና የሚሰራቸው ጉዳዮችም የተገናኙ ባለመሆናቸው ቢነሳም ቢቀርም ትርጉም የለውም” ሲሉ ስሜታቸውን ገልጸዋል። ለምሳሌ ስለ ኑሮ ውድነቱና ስለ ዋጋ ግሽበቱ ብዙ ጉዳዮች የተነሱ ቢሆንም፣ ምንም የተጨበጠና የሚይታይ ለውጥ እንዳልመጣ፣ እንዲያውም በአስደንጋጭ ሁኔታ የኑሮ ውድነቱና የዋጋ ግሽበቱ ጣሪያ መንካቱን ነው የጠቆሙት፡፡ መንግስት የኑሮ ውድነቱን ለማረጋጋትና የዋጋ ግሽበቱን ለመቀነስ የሚናገረውን ያህል እየሰራም ሆነ አዳዲስ ፖሊሲዎችን ይዞ ወደፊት እየመጣ አይደለም ሲሉም ፖለቲከኛው ተችተዋል፡፡
በሌላ በኩል የሰላም ጉዳይ በፕሬዚደንቷ የተነሳ ቢሆንም የኢትዮጵያ መንግስት አሁን እየገፋ ባለበት አካሄድ የሚሳካ አይመስልም ብለዋል፡፡ “በተለይ አሁን የሰላም ጉዳይ ሲነሳ የሚነሳው ትግራይ ያለው ጦርነት ብቻ ነው” የሚሉት የኦፌኮው ሊቀመንበር፤ በአብዛኛው የሀገሪቱ ክፍል በተለይ በኦሮሚያ ግጭቶች መኖራቸውንና እሱንም ለማስተካከል የቀረቡ ጥያቄዎች መልክ አለመያዛቸውንና ምላሽ አለማግኘታቸውን ነው ፕሮፌሰሩ የገለጹት፡፡ በኦሮሚያ ፤በቤኒሻንጉል ጉሙዝ በጋምቤላና በሌሎችም አካባቢዎች ግጭቶች መኖራቸውን ያስታወሱት ፕሮፌሰሩ፤ የነዚህ  ግጭቶች ምንጭ ፖለቲካ መሆኑንና ይህንን ምንጭ የኢትዮጵያ መንግስት እየሸሸ፣ ከላይ ከላይ የሚታየው ላይ ብቻ ማተኮር ተገቢም አይደለም ዘላቂ ሰላምም አያመጣም፤ ሲሉ አሳስበዋል፡፡
“ድርድሩንም በተመለከተ የኢትዮጵያ መንግስት የሙጥኝ ያለው አፍሪካ ህብረትን ነው” ያሉት ፕሮፌሰር መረራ፤ ይሁን እንጂ አፍሪካ ህብረትም ሆነ ከህብረቱ ቀድሞ የነበረው “አፍሪካ አንድነት ድርጅት ከተመሰረተ ከ6 አስርት ዓመታት በላይ እድሜ ቢኖረውም በነዚህ አመታት ሁሉ እዚህ ግባ የሚባል አፍሪካዊ ችግር ሲፈታ አላየንም ብለዋል። “ለአፍሪካዊ ችግር አፍሪካዊ መፍትሄ” የሚል መፈክር  በየጊዜው ከመስማት ውጭ ብለዋል። “እኔ የፖለቲካ ሳይንስ አስተማሪ እንደመሆኔ ብዙ ጉዳዮችን እከታተላለሁ ህብረቱ ይሄ ነው የሚባል የረባ ነገር ሲሰራ አይቼ አላውቅም የሚሉት ፕ/ር መረራ፤” ህብረቱ ላይ የሙጥኝ ቢባልም መፍትሄ ያመጣል በዬ አላምንም  ብለዋል።
ኮንጎ፤ ላይቤሪያ፤ ደቡብ ሱዳን፤ ሩዋንዳ፤ ሱማሊያና ሌሎችም የአፍሪካ ሀገራት በግጭትና በችግር ሲታመሱ ህብረቱ የሰራው ስራ የለም ሲሉም ለትችታቸው ማጠናከሪያ ማስረጃ አቅርበዋል።
ፈረንጆቹ ጉልበትም ቢሆን ጨምረውበት ችግሩ ከተፈታ እንጂ አፍሪካ ህብረት ላይ ሙጥኝ ማለት ችግሩ እንዲቆይ ከማድረግ ያለፈ ሌላ ፋይዳ አይኖረውም ብለዋል፡፡
“ለምሳሌ የቀድሞው የናይጄሪያ መሪ ኦሊሴንጎን ኦባሳንጆ ለምርጫው ጊዜ ኢትዮጵያ መጥተው አግኝቻቸው እንደ አንድ አዛውንት የአፍሪካ መሪ፣ የኢትዮጵያን መንግስት ብትመክር ይሻላል ምርጫው ዋጋ የሌለው ምርጫ ስለሆነ ለመታዘብ አትቸገርም” አፍሪካ ጥሩና ትክክለኛ መንገድ እንድትይዝ እንደ አንጋፋ የአፍሪካ መሪ ምከር ብለዋቸው እንደነበረ አስታውሰዋል፡፡ “አባሳንጆ ምን እንዳለ ባላውቅም በሶስተኛው ወይም በአራተኛው ቀን ምርጫው ሰላማዊና ፍትሃዊ ነው ብሎ ሚዲያ ላይ ተናግሮ ሲሄድ ብቻ አይቻለሁ” ብለዋል፡፡ የሆነ ሆኖ የድርድሩን ጉዳይ ከአፍሪካ ህብረት ቢያወጡት ጥሩ ነበር ሲሉም ምክር ለግሰዋል፡፡
ድርድሩ ከአፍሪካ ህብረት ይውጣ ካሉ በየትኛው አካል ቢካሄድ ይመርጣሉ ስንል ጠይቀናቸው “በዓለም ላይ በቂ ተሞክሮና እውቀቱ ያላቸው ትንሽም ቢሆን መግፋት የሚችሉ አገራት አሉ ያሉት ፖለቲከኛው፤” በምሳሌነት እንዲጠቅሱልን ጠይቀናቸው” የተሻሉና ገለልተኛ የሚባሉት የስካንዲኒቪያን ሀገራት ለምሳሌ እነ ኖርዌይ፤ ሲዊዲንና ኔዘርላንድ የመሳሰሉት በዴሞክራሲ ግንባታ ላይ የሚሰሩ ብሎም ለኢትዮጵያ ብዙ እርዳታና ድጋፍ የሚያደርጉ አገራት አሉ፤ ልምድም ተሞክሮዎችም በዓለም አቀፍ ደረጃ አዳብረዋል። ጉዳዩን እነሱ ቢያዩት ይሻላል ሲሉ ሀሳብ ሰጥተዋል፡፡ እነዚህ አገራት ከኋላቸው ጉልበት አለን የሚሉትን እንደነ አውሮፓና አሜሪካ ያሉ ሀያላንን መያዝ ይችላሉም ብለዋል፡፡ “ይሁን እንጂ ጉዳያችን የራሳችን ስለሆነ መደራደርም መነጋገርም ያለብን እዚሁ አገራችን ላይ እርስ በርሳችን መሆን ነበረበት” ሲሉም ተናግረዋል። እነዚህ ከላይ የተጠቀሱት አገራት አመቻቾች ናቸው የሚሉት ፕ/ር መረራ መገዳደል አቁመን መደራደር መጀመር ያለብን  ግን እኛው እራሳችን ነን ሲሉም መክረዋል፡፡
በምዕራብ ወለጋ በአማራ ተወላጆች ላይ ኦነግ ሸኔ በሚባል አሸባሪ ቡድን የሚፈፀመውን ግድያና ጥቃት በተመለከተ በመንግስት በኩል የመፍትሄ እርምጃ አልተቀመጠም የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ በዚህ ላይ የእርሶ አስተያየት፣ ምንድን ነው ተብለው ለተጠየቁትም “በዚያ አካባቢ የተደበላለቁ ነገሮች ስላሉ እኛ ደጋግመን በገለልተኛ አካል ይጣራ፤ መንግስት እየወሰደ ያለው እርምጃ መፍትሄ አምጪ አይደለም፤ በሁለቱም በኩል ብዙ ሰዎች እንደተገደሉና አሁንም እየተገደሉ እንደሆነ እናውቃለን ግን የመጣ መፍትሄ የለም ብለን ስንጮህ ቆይተናል” ያሉት ፕ/ር መረራ ይሄ ጉዳይ ፓርላማም ላይ መነሳቱንና ነገር ግን መንግስት አካባቢው ላይ ያለውን ግድያና መፈናቀል ለማቆም በቁርጠኝነት የሚሰራቸው ስራዎች አንድ ሁለት ሶስት ተብለው እስካልተቀመጡ ድረስ ጉዳዩ በአስቸጋሪነቱ እንደሚቀጥል ነው የገለፁት።
በጉዳዩ ዙሪያ በግልፅ ቋንቋ በተደጋጋሚ እንደ መድረክ መግለጫ አውጥተናል” ያሉት ፕ/ር መረራ፤ በገልተኛ አካል ያንን ማን እንደሚሰራ ባለመጣራቱና መንግስት ባለመስራቱ አሁንም በአካባቢው ግድያና መፈናቀሉ ቀጥሏል ብለዋል። አሁንም እኔ ለሁሉም መግለፅ የምፈልገው ለዚህ ሁሉ ችግር መፍትሄ የሚሆነው የመገዳደልን ፖለቲካ ወደ መደራደር ፖለቲካ በመቀየር ነውና በአስቸኳይ ከመገዳደል ወደ መደራደር እንግባ ስል ጥሪ አቀርባለሁ ብለዋል፡፡ ይህን ማድረግ ካልቻልን ፈረንጅም መጣ አፍሪካ ህብረትም መጣ ዋጋ የለውም ብለዋል፡፡
የፓርላማ አባላት (የህዝብ እንደራሴዎች) የወከሉትን ህዝብ መብትና ነፃነት ከማስከበር አኳያ ምን አይነት ሚና ሊጫወቱ ይገባል፤ አስከዛሬስ የተጫወቱት ሚና አለ ወይ? የሚል ጥያቄም ተነስቶላቸው፤ “በዓለም ላይ ፓርላማ በሶስት ይከፈላል” በማለት ማብራራት የጀመሩት ፕሮፌሰሩ፤ አንደኛው “ጠንካራ ፓርላማ” የሚባለው ሲሆን ጥሩ ጥሩ ህጎችን የሚያወጣና እነዚያ ህጎች በትክክል ስራ ላይ መዋላቸውን ለመቆጣጠር የሚችል ነው ብለዋል፡፡
ሁለተኛው አይነት ፓርላማ ደግሞ ጥሩ ጥሩ ህጎችን ማውጣት ይችላል፤ ስራ ላይ መዋላቸውን መቆጣጠር እንኳን ባይችል ለሀገር ለህዝብ የሚጠቅሙ ህጎችን ያወጣል፤ ሶስተኛው አይነት ፓርላማ ደግሞ ብዙ ጊዜ በዓለም ላይ የሚታወቀውና ፈረንጆች “talking shop” የሚሉት ነው፡፡ ያሉት ፕ/ር መረራ ይህ ፓርላማ ቢያንስ ንግግርና ጫጫታ የሚሰማበት ነው ሲሉ አብራርተዋል፡፡
ታዲያ የእኛ አገር ፓርላማ ከሶስቱ የትኛው ምድብ ላይ ይገኛል ስንል ጠይቀናቸው “ በጣም የሚያሳዝነው የሶስቱም በታች ሆኖ መገኘቱ ነው” በማለት የሀገራችንን ፓርላማ አጣጥለውታል፡፡ ምክንያታቸውንም ሲያስረዱ ቢያንስ ጫጫታውና ብሶት ማሰማቱም የለም ያሉት ፕ/ሩ እኛ ፓርላማ በነበርንበት ጊዜ ለአምስት አመት ጫጫታ ( የህዝብ ብሶት) ማሰማት ችለን ነበር በማለት የቀድሞውን ፓርላማ የተሻለ  መሆን ገልፀው፣ በአሁኑ ጊዜ ከዚያ አንሰን የኋልዮሽ ጉዞ ጀምረናል በማለት አገሪቱ ላይ ያለው ችግር ከላይ እስከታች አሳሳቢ ስለመሆኑ አስምረውበታል። ዞሮ ዞሮ ፓርላማውም የህዝብን ብዞት በማሰማት ተፅዕኖ መፍጠር አለበት መንግስት የመገዳደልን ፖለቲካ ወደመደራደር ማምጣት አለበት። ከዚህ ውጪ ያለው መፍትሄ አያመጣም ሲሉ አስተያየታቸውን ቋጭተዋል።
የፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ንግግር መንግስት በ2015 ዓ.ም ትኩረት ይሰጥባቸዋል ተብሎ የሚታሰቡ ዋና ዋና ነጥቦች ላይ ያተኮሩ ናቸው ያሉት የኢዜማ ስራ አስፈጻሚ አባል አቶ ግርማ ሰይፉ፣ ይሁን እንጂ ፕሬዚዳንቷ ቢያነሷቸው ጥሩ ነበር የሚሉ ሀሳቦችን ቀድመው እንዳይናገሩ የሚያግዳቸው እንዳለና የፓርቲያቸው የፓርላማ ተጠሪ በማሻሻያ ሞሽኑ ላይ  ያቀርበዋል ብለው እንደሚያምኑ ጠቁመው በዚህ ላይ አስተያየት ከመስጠት ተቆጥበዋል።
ፕሬዚዳንቷ ቅድሚያ ሰጥተው ያነሷቸው ሁለት ነጥቦች እንዳሉ የጠቆሙት አቶ ግርማ፣ እነዚህም ሰላም ዴሞክራሲና በተለይ አሁን በየአካባቢው ያሉ ግጭቶች በሰላም የሚፈቱበት መንገድ አንዱ ሲሆን ሁለተኛው የአገራዊ ምክክሩ ጉዳይ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
በሁለቱ የፕሬዚዳንቷ ንግግሮች ላይ ትኩረታቸውን ያደረጉት አቶ ግርማ፣ መንግስት ሁሌም ለሰላም እጁን እንደሚዘረጋና ችግሮችን በሰላምና በውይይት በሚፈቱበት መንገድ ላይ አጠናክሮ በመቀጠል ጠብመንጃ ያነሱ ሃይሎ ወደ ውይይት የሚመጡ ከሆነ በግራም በቀኝም  የሚሞቱ ሰዎችን ህይወት ለማትረፍ ትልቅ አጋጣሚን ይፈጥራል ብለዋል። ለነዚህ ጉዳዮች ሲባል የሰላምን እጅ መዘርጋት ጥሩ ነው ያሉት የኢዜማ አመራር ይህ ሳይሆን ቀርቶ ጉዳያችንን በጉልበት እናስፈጽማለን ከተባለ ግን መንግስት አስፈላጊውን እርምጃ መውሰዱ አይቀሬ ነው በማለት አቋማቸውን አንፀባርቀዋል፡፡
“ይሄ ማለት ግን መንግስት እጁን ሊጠመዝዙ የሚፈልጉ ሰዎችን እሹሩሩ እያለ ይኖራል ማለት አይደለም” የሚሉት አቶ ግርማ፤  ይዋል ይደር እንጂ እውነትን የያዘ ያሸንፋል። ለሌላ ጥቅም የቆሙ አካላትም ጥቅማቸው ሲቋረጥባቸው ሃሳባቸውን ይቀይሩ ይሆናል ብለዋል። በመንግስትና በህወሓት መካከል ባለው ግብግብ የትግራይ ህዝብና ድንበር አካባቢ ያለው የአማራና የአፋር ህዝብ እየተጎዳ ነው ያሉት አንጋፋው ፖለቲከኛ በመላው ኢትዮጵያ ያለ ሀይል ተንቀሳቅሶ ይህንን ለመመከት ሲል ደግሞ የህይወት የሃብትና የንብረት ኪሳራ እየደረሰ መሆኑን ገልፀዋል። “ይህንን ጥፋትና ውድመት ለአንድ ቀንም ሆነ እስከ መጨረሻው ተስማቶ ማቆም ይጠቅማል” የሚሉት የኢዜማው አመራር፣ ከዚህ አንፃር ወደ ውይይት መምጣት አማራጭ የሌለው ጉዳይ መሆኑን አስምረውበታል፡፡ ወደ ውይይት ለመምጣት ግን ቅድመ ሁኔታ ማስቀመጥ፣ መሳሪያ ይዤ እያስፈራራሁ እደራደራለሁ ማለትና መሰል ጉዳዮች ካሉ መሳሪያ ታጥቆና ሀይል አስተባሮ የአገርንና የህዝብን ሰላም የመጠበቅ መብት ያለው መንግስት ስለሆነ ይህንን ማስፈጸም አለበት ብለዋል።
አቶ ግርማ አክለውም ፤ለምንድን ነው መንግስት አቅም ካለው እስከዛሬ ጦርነቱን ያላጠናቀቀው ለተባለው “ጦርነት አቅም ስላለሽ ብቻ የምትጨርሽው ወይም አቅም ስለሌለሽ ተሸንፈሽ የምትወጪበት ሜዳ አይደለም” ሲሉ የጦርነትን ውስብስብ ባህሪ የገለፁ ሲሆን፣ መንግስት ተገድዶ የገባበትን ጦርነት ሁሉንም ደምስሼ አሸንፋለሁ ብሎ ካመነ በመሃል የሚደርሰው ኪሳራ ከባድ መሆኑንና በተለይ ህዝቡን ምሽግ አድርጎ የተነሳን አሸባሪ ለመምታት አስቸጋሪ በመሆኑ ጦርነት በታሰበውና በታቀደው ሰዓት አይጠናቀቅም ፤አቅምና ትጥቅ ስላለም ብቻ ቶሎ አይቋጭም ሲሉ ተናግረዋል።  
ስለሆነም መንግስት ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ አለበት ያሉት አቶ ግርማ “ አሳውን ለመያዝ ባህሩን ማድረቅ” የሚባለው አይነት አካሄድ አክሳሪና የማያዋጣ መሆኑን አስረግጠው የተናገሩት ፖለቲከኛው፣ ህወሃትን ለመደምሰስ በሚደረግ ውጊያ የትግራይን ህፃናት፣ አረጋውያንና ሌሎችንም የህብረተሰብ ክፍሎች ደህንነት ማረጋገጥ ያስፈልጋል ብለዋል።
የህወሓት ሃይሎችም ይህ አካሄድ እንደማያዋጣቸው አውቀው ወደ ውይይት ጠረጴዛ በመምጣት የሚቀርብላቸውን አማራጭ በመቀበል እስከዛሬ ከደረሰው የሰብአዊና ቁሳዊ ኪሳራ የበለጠ ተጨማሪ ኪሳራና ውድመት እንዳይደርስ ማድረግ ይቻላል “ይህን አማራጭ የማይቀበሉ ከሆነ ግን መንግስት ከፍተኛ ጥንቃቄ እያደረገም ቢሆን የእነዚህን ሃይሎች እጅ መያዝ አለበት” ሲሉም መክረዋል።
አገራዊ ውይይቱን በተመለከተ አቶ ግርማ ሲናሩ፣ ፕሬዚዳንቷ ካለፈው አመት የቀጠለውን ይህንን ውይይት ማንሳታቸውን አድንቀው ሌሎቻችንም በዚሁ ልክ ትኩረት ሰጥተንና የመንግስት ደጋፊ እንባላለን ከሚል መሸማቀቅ ወጥተን እንዲሁም የፖለቲካ ቁማር ከማድረግ ወጥተን ውይይቱ የተሳካ የሚሆንበትን ተሳትፎ ማድረግ አለብን ሲሉ አሳስበዋል።
በምዕራብ ወለጋ በአማራ ተወላጆች ላይ በኦነግ ሸኔ የሚደርሰውን ዘር ተኮር ግድያና ጥቃት በተመለከተ መንግስት ምን መፍትሄ እርምጃ መውሰድ አለበት በሚል ተጠይቀው “አሸባሪው ህወሓት አገርን ከመረበሽና ከማሸበር አጀንዳዎቹ አንዱ አድርጎ የፈጠረው በመሆኑ ውይይቱና ድርድሩ ከተሳካ አብሮ የሚቆም ነው” ብለዋል። ጉዳዩን ወደ ውይይትና ወደ ድርድር ማምጣት የብዙ ችግሮች መፍትሄ ሊሆን እንደሚችልም በአፅንኦት ተናግረዋል፡፡
የቀድሞውን ጠቅላይ ሚኒስትር ታምራት ላይኔንና የቀድሞውን የኢዴፓ አመራር ልደቱ አያሌውን የሰሞኑን ለህወሃት ያደረጉትን ውግንና በተመለከተ ለቀረበላቸው ጥያቄ አቶ ግርማ ሲመልሱ፣ በግድ ባርነትን የመሻትና የማስቀጠል አባዜ ስላለባቸው በዚህ ላይ ብዙ ማለት አልፈልግም  “በተለይ አቶ ልደቱ መጀመሪያ የለውጡ አራጋቢ ሆኖ የነበረ ቢሆንም ዶ/ር አቢይ የምጠላቸውን ጠራርጎ ያባርርልኛል ብሎ የጠበቀው ነገር ባለመሳካቱ ብስጭቱንና ንዴቱን ለማስታገስ ነው የሚጮኸው” ብለዋል፡፡ “እስከዛሬ ይህ ሰው ልቡን እንደሚያመው ነበር የምናውቀው፤ አሁን ግን፤ ጭንቅላቱን የታመመ ይመስለኛልም” ብለዋል፡፡ አቶ ታምራት ላይኔም ቢሆኑ የቀድሞውን በህውሃት ውስጥ የነበሩበትን ባርነት ከመናፈቅ የመጣ እንጂ ሌላ ነገር አይደለም ያሉት አቶ ግርማ፤ የሆነ ሆኖ የሁለቱ ግለሰቦች ጩኸት በኢትዮጵያ ፖለቲካ ላይ የሚያመጣው አንዳችም ለውጥ የለም ሲሉም ቋጭተዋል።




Read 12355 times Last modified on Monday, 17 October 2022 12:53