Saturday, 15 October 2022 10:56

“አንዴ ሌባ ካሉት ቢቆርብም አያምኑት”

Written by 
Rate this item
(4 votes)


      አንድ ከተማ ውስጥ የሚኖሩ ሦስት ሌቦች ነበሩ። ሌቦቹን የሚያውቅ ሰው በግልጽ ስለማይናገር ሁሌ የመንደሩ አዛውንቶች ህዝቡን እየሰበሰቡ አውጫጭኝ ያስደርጋሉ። እውነተኞቹ ሌቦች ግን በጭራሽ ሊገኙ አልቻሉም። ሶስቱ ሌቦች ከህዝቡ ጋር እየተቀመጡ ጭራሽ አፋላጊ ሆነዋል።
ነገሩ “የሌባ ዓይነ-ደረቅ መልሶ ልብ ያድርቅ” ዓይነት መሆኑ ነው። አንድ ቀን አንድ አዛውንት ባለቅኔ በዚያው በአውጫጭኙ ላይ ተገኝተው፤ ሲፈሩ ሲቸሩ እጃቸውን አወጡ።
ሰብሳቢው፡-
 “እሺ አባቴ የሚናገሩት አለዎት?”
አዛውንቱ፡-
 “አዎ”
ሰብሳቢው ፡-
“እሺ ምንም ሳይፈሩ በግልጽ ይናገሩ”
አዛውንቱ፡-
“አሳምሬ ነው የምናገረው፤ ያውም ጥንት የቅኔ ተማሪ ቤት አስተማሪዬ የነገሩኝን ነው የምገልጸው።”
ሰብሳቢው፡-
“እኮ ቶሎ ቶሎ ይናገሩ?”
አዛውንቱ፡-
 “ጌቶቼ፤ ይሄ የአውጫጭኝ ስብሰባ እንደ እኔው የሰለቻቸው ባለቅኔ እንዲህ አሉ ይባላል።
ጎበዝ ሌባው ስማ!
ቢተው ይተው
አለዚያ ግን እኛ ጀምበር በሰረቀ ቁጥር፣ በአውጫጭኝ ስብሰባ ስንሰቃይ አንኖርም!” ብለው ደመደሙ።
በዚህ ዓይነት የሰፈሩ ሦስት አደገኛ ሌቦችን ስም ይፋ አደረጉ። እነሱም አቶ ለማ፣ አቶ ቢተው እና አቶ ጀምበር የተባሉ አገር ያሰለቹ ሌቦች መሆናቸው ታወቀና ተመንጥረው ተይዘው ወህኒ ወረዱ።
***
ያየነውን የሰማነውንና በአካባቢያችን ያለን አደገኛ ነገር አለማጋለጥ ለሁላችንም ጎጂ ባህል ነው።
ዜመኛው፤ “ያንተ ቤት ሲንኳኳ ይሰማል እኔ ቤት” ያለው ይሄንኑ አደራ ሊለን ነው። የጉርብትናችን አይነተኛ ጥቅም፤ አንዳችን ለአንዳችን ማሰባችንና መረዳዳታችን ነው። እንኳንስ በአንድ ሀገር ውስጥና በአንድ ከተማ፤ በሁለት አገሮች ያለ ጉርብትና እንኳን ክቡርና ወሳኝ ነው። ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ባህላዊ ትስስራችን ትላንትን እንደ ታሪክ፣  ዛሬን እንደ ወቅታዊ ሂደት፤ ነገን እንደ ራዕይ ጨብጠን የተሻለ ዓለም ለማየት ምንጊዜም ዝግጁ መሆን አለብን። ለሀገራችን መልካም አማራጭ የምንሆነው፡-
1ኛ/ የድል አጥቢያ አርበኞችን ስንዋጋ
2ኛ/ ልማደኛ አድር ባዮችን ገለል ስናደርግ እና
3ኛ/ ሰርግ ቤት ሲያገኙን ዘፈን አውጪ፣ ሃዘን ቤት ሲያገኙ ሙሾ አውራጅ የሚሆኑና የየዘመኑ ተራማጅ የመሆን አባዜ ከተጠናወታቸው የመንግስትም ሆነ ከመንግስት ውጭ ያሉ ሹሞች፣ ባለስልጣኖችና ዜጎችን ስንጠነቀቅ ብቻ ነው - ወደ ቀናውና ጤናማው መንገድ የምናመራው!
እንዲህ ያሉት በየትውልዱ ውስጥ ያደፈጡ ጠላቶች መሆናቸውን አንርሳ! ከእባብ እንቁላል የእርግብ ጫጩት አይፈለፈልም!? ስለሆነም ከወዲሁ አካፋን አካፋ ማለት ይገባል! (Call a spade a spade)
በየመሥሪያ ቤቱ የተሰገሰገውን መሰሪ ሸቃይ፣ አጋፋሪና አሽቃባጭ ለይቶ ማውጣት ቢያንስ ለጤናማ የነገ ውሎአችን ይበጀናል። አበው፤ “አንዴ ሌባ ካሉት ቢቆርብም አያምኑት” ያሉት ወደው አይደለም። በለመደ እጁ ምን እንደሚወስድ፣ ምን እንደሚመነትፍ አይታወቅምና! ሁሌም ቢሆን አገር ሲበዘበዝና ህዝብ ሲዘረፍ ዝም አንበል። “ዝምታ ለበግም አልበጃት” እንዲል መጽሐፉ።


Read 12692 times