Print this page
Saturday, 20 October 2012 10:57

“ጥቁር አንበሶች”

Written by  ከበደ ደበሌ ሮቢ
Rate this item
(5 votes)

“Black Lions” በኢትየጵያውያን የሥነ ፅሁፍ ሠዎች፡- ደራሢያን፣ ገጣሚያንና ባለቅኔዎች ሠብአዊና ጥበባዊ ሠብዕና ላይ ተመሥርቶ በእንግሊዝኛ ቋንቋ የተፃፈ መፅሀፍ ነው፡፡ ይሄን ጥናታዊ መፅሀፍ የፃፉት የኖርዌይ ተወላጅ የሆኑት ፕሮፌሰር ሞልቨር ሲሆኑ ያሣተመው Red Sea publisher (ቀይ ባህር አሣታሚ) የተሠኘ ተቋም ነው፡፡
ሞልቨር ኢትዮጵያውያኑን የሥነ ፅሁፍ ባለሙያዎች “ጥቁር አንበሶች” ብለዋቸዋል፡፡ ገና እንደታተመ ሠሞን ነው ከአሥራ ስድስት ዓመታት በፊት በ1989 ዓ.ም ግድም ያነበብኩት፡፡

በአማርኛና በግዕዝ ሥነ ፅሑፍ ታሪክ በኢትዮጵያውያን ደራሢያን ጥበባዊ ሠብዕናና በኪነጥበብ ሥራዎቻቸው ላይ ተመሥርቶ በጥቁር አንበሶች መጠን በጥልቀት በአማርኛም ሆነ በእንግሊዝኛ የተፃፈ ሌላ መፅሀፍ አላየሁም፡፡ 
በዚህ ጥናታዊ መፅሀፍ ላይ ቢኖሩ የሚመረጡ ሆኖም የሌሉ ሁለት ነጥቦች አሉ፡፡ ይኸውም፡- የአንዳንድ ደራሢያን ጥበባዊም ሆነ ሠብዓዊ ሠብዕና ደብዝዞ መቅረቡ (በደንብ ያለመገለፁ)፤ በመፅሀፉ ውስጥ ሊካተቱ የሚገባቸው ኢትዮጵያውያን ደራሢያን፣ ገጣሚያንና ባለቅኔዎች በተሟላ መልኩ ያለመካተታቸው … ናቸው፡፡
ለምሣሌ፡- የህፃን ልብና የአዋቂ አእምሮ ያለው ጋሼ ሥብሀት ለአብ ገብረ እግዚአብሔር ጥበባዊ ነፍስ በጥቁር አንበሶች ውስጥ ቁልጭ ቅልብጭ … ብሎ አልታየም፤ በደንብ አልተገለፀም፡፡ ስለ ጋሼ ሥብሀት የቀረበው መወሣት በእውን የምናውቀውን ደራሢ ሥብሀት ሥሡና ግዙፍ ማንነት ወለል አድርጐ የማሣየት አቅም የለውም፡፡
ስለ ታላቁ ኢትዮጵያዊ ባለቅኔ፣ ፀሀፌ ተውኔት፣ አንትሮፖሎጂስትና አጂብቶሎጂስት፣ የዓለም ሎሪየት ፀጋዬ ገብረ መድህን ቀዌሣ የቀረበው መወሣትም እንደዚሁ ጋሼ ፀጋዬን በምልዓት ሊገልፀው የሚችል አይደለም፡፡ ጋሼ ፀጋዬ በአማርኛ፣ በኦሮምኛና በእንግሊዝኛ የሚፅፍ ብርቁ ባለቅኔ፣ ፀሀፌ ተውኔት ተርጓሚና ተመራማሪ፤ ታላቅ አፍሪቃዊ የሥነ ፅሁፍ ባለሙያና ሊቀ ጠቢብ ነው፡፡
በጥቁር አንበሶች (Black Lions) ላይ የሌለ ነገር ግን ቢኖር የሚጠቅመው ሌላው ነጥብ፡- መታከል የሚገባቸው ኢትዮጵያውያን የፅሁፍ ጥበብ ሊቃውንት ቢታከሉ የሚለው ነው፡፡ ሁሉንም ኢትየጵያውያን የሥነ ፅሁፍ ባለሙያዎች በዚህ መፅሀፍ ላይ አናገኛቸውም፡ ለምሣሌ፡- ገጣሚና ባለቅኔ፣ ፀሀፌተውኔትና ተርጓሚ፣ የዩኒቨርሢቲ ሌክቸረርና ተመራማሪ ደበበ ሠይፉ “Black Lions” ላይ የለም፡፡ ደበበ ሠይፉ “የብርሀን ፍቅር” እና ለ“ራሥ የተፃፈ ደብዳቤ” የሚሉ ሁለት ውብ የቅኔና ግጥም መድበሎች እንዲሁም ስለ ተውኔት ጥበብ መፅሀፍ የፃፈ፤ በኢትዮጵያ ሥነ ፅሁፍ ውስጥ ብልጭ ያለ ብርሀን ነው፡፡ ዮፍታሄ ንጉሤን፡- ተወርዋሪው ኮከብ ያለው እና በሌሎች ሊቃውንት ራሱ ተወርዋሪው ኮከብ የተባለው፤ ከኢትዮጵያ ተራማጅ እንቅስቃሴ መሪዎች አንዱ የሆነው የዩኒቨርሢቲ ሌክቸረር፤ ገጣሚና ባለቅኔ፣ ተርጓሚና የፅሁፍ ጥበብ ሊቅ ዮሀንስ አድማሱ “ጥቁር አንበሶች” ውስጥ አልሠፈረም፡፡ “እስኪ ተጠየቁ” በሚል የግጥም መድበሉ ውስጥ ካሉት ግጥሞች አንዱ “ተወርዋሪው ኮከብ” … የሚለው ነው፡፡
በራሡ ነበልባል
በራሡ ነዲድ
ተቃጥሎ የጠፋ
ተወርዋሪው ኮከብ
በምናውቀው ሠማይ
ነበረ በይፋ …
በ“ጥቁር አንበሶች” ውስጥ ያልተካተተ ሌላው ቅድሚያ ትኩረት ሊሠጠው ይገባ የነበረው ኢትዮጵያዊ ሠሎሞን ደሬሣ ነው፡፡ ሠሎሞን ደሬሣ፡- የራሡ አስተሣሰብ ባለቤት (የራሡ ጌታ) ድንቅ ጋዜጠኛ፣ ገጣሚና ባለቅኔ፣ የዩኒቨርሢቲ ሌክቸረርና የነፍስ አስኳል አማካሪ ሲሆን፤ “ልጅነት”፡- አርባ ተኩል ግጥም እና “ዘበት እልፊቱ” የሚሉት የግጥም መድበሎቹ የኢትዮጵያ ሥነ ፅሁፍ ብርሀንማ ቅርሶች ናቸው፡፡ አሁን አሜሪካን አገር ሜኒሶታ ሜኒኦፖሊስ የሚገኘው የሠባ አምስት ወይ የሠባ ሥድስት ዓመቱ ኢትዮጵያዊ ሊቀ ጠቢብ ሠሎሞን ደሬሣ የመጨረሻ መፅሀፉን እያሠናዳ ነው፡- “ሥንብት” የሚለውን፡፡
“Black Lions” ሌሎችም በገፆቹ ያላካተታቸው ኢትዮጵያውያን የፅሁፍ ጥበብ ባለሙያዎች አሉ፡፡ በተቀረ ወርቅ ሥራ ነው፡፡ ከደራሢያን ሁሉ ለራሥ እምሩ ኃይለ ሥላሴ ሠፊ ሽፋን ሠጥቷል፡፡ ራሥ እምሩ፤ - ለሀረር ገበሬዎች ሃምሣ ጋሻ መሬት የሰጡ ሰው ናቸው፡፡ በዓለም የሥነ ጽሑፍ ታሪክ ርስቱን (መሬቱን) ለገበሬዎች የሰጠ ቢኖር እኔ የማውቀው ሩሲያዊውን ደራሲ ሊዮን ቶልስቶይን ነው፡፡ ከአንድ ዓመት በፊት ብራዚል ውስጥ አምስት መቶ ገበሬዎች መሬት ጠቦናል ብለው የቤተ መንግሥቱን አጥር ጥሰው መግባታቸው እዚህ ቢወሳ ጉዳት የለውም፡፡ ፕሮፌሰር ሞልቨር የራስ እምሩን ፖለቲካዊ ሚና ጭምር በመጽሐፋቸው ላይ አሥፍረዋል፡፡
ኢትዮጵያ በፋሺስት ኢጣሊያ ስትወረርና ንጉሠ ነገሥቱ ወደ ውጭ አገር ሲሄዱ ኢትዮጵያ አልተሸነፈችም ነገር ግን ዋና ከተማዋን ቀይራለች ብለው ኢሊባቦር (ኢሉ አባቦራ) ጐሬ ላይ የኢትዮጵያን መንግሥት ያቋቋሙ ራስ እምሩ ኃይለሥላሴ ናቸው፤ አብረዋቸው የክብር ዶክተር ደራሲ ሀዲስ ዓለማየሁ አሉ፡፡ ጐሬ ለአንድ ዓመት የኢትዮጵያ ዋና ከተማ ሆና ከዘለቀች በኋላ ራስ እምሩና ሀዲስ ዓለማየሁ ወደ ኢጣሊያ እሥር ቤት ተግዘዋል፡፡ ሀዲስ ዓለማየሁ ትግራይ ሠለክለካ ውስጥ የኢትዮጵያን አርበኞች መምራታቸውን ፕሮፌሰር ሞልቨር ጽፈዋል፡፡ የክብር ዶክተር ደራሲ ከበደ ሚካኤል ወላጅ አባት ትክክለኛው ሚካኤል ያለመሆናቸውን ያወቅሁት ከ“ጥቁር አንበሶች” ነው፡፡
ብዙ ኢትዮጵያውያን ስለ ኢትዮጵያውያን ደራሲያን የማናውቀውን ፕሮፌሰር ሞልቨር “ጥቁር አንበሶች” ላይ ጽፈውልናል፡፡
የከበረ ሰብዕና ያላቸው ራስ እምሩ ኃይለሥላሴ፤ ልጆቻቸው ከጐረቤት ልጆች ጋር ለመገናኘት እንዳይቸገሩ ቤታቸው እንኳ አጥር አልነበረውም ይሉናል ሞልቨር፡፡ ራስ እምሩ በጣም ሠአብዊ ሠው ናቸው፡፡ ከልጆቻቸው ሁለቱ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት እንደነበሩ አውቃለሁ፤ ልጅ ሚካኤል እምሩ እና አምባሣደር ዮዲት እምሩ፡፡
አንቱ የተሠኙ የሥነ ጽሑፍ ሥራዎቻቸውን በጉልምሥና የእድሜ ዘመናቸው የፃፉት የክብር ዶክተር ሀዲስ ዓለማየሁ ደራሢ ብቻ ሣይሆኑ የአርበኞች መሪ ብስል ዲፕሎማት (አምባሳደር) መሆናቸውን የገለፁት ፕሮፌሰር ሞልቨር፤ እስከ ሠባተኛ ክፍል ድረስ የተማሩት ከበደ ሚካኤል እና እስከ ዘጠነኛ ክፍል የተማሩት ሀዲስ ዓለማየሁ ሁለቱም ልጅ እንደሌላቸው በመጽሐፋቸው አውስተዋል፡፡ ሁለቱም ታላላቅ ደራሲያን የክብር ዶክትሬት አግኝተዋል፡፡ “ጥቁር አንበሶች” ላይ ከቀረቡት ኢትዮጵያዊ ደራሲያን አባትና ልጅ የሆኑት የፋቡላ ደራሲ አምባሳደር ግርማቸው ተክለ ሃዋርያት እና በዳግማዊ ዓፄ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት አራት ዓመት ሩሲያ ውስጥ የወታደራዊ ሳይንስ ትምህርታቸውን የተከታተሉት ተክለ ሃዋርያት ተክለ ማርያም ይገኙበታል፡፡ ከራስ እምሩ ኃይለሥላሴ በኋላ ተክለ ሃዋርያት ተክለ ማርያም የሀረር ገዢ ነበሩ፡፡ ንጉሠ ነገሥቱ በኢጣሊያ ወረራ ምክንያት ወደ ውጪ አገር በባቡር ሲሄዱ ተክለ ሃዋርያት አላስኬድም አሉ፡፡ “ቴዎድሮስ የተሰዋ መቅደላ፤ ዮሐንስ የተሠዋ መተማ…ንጉሥ በአገሬ አይሸሽም፡፡” በማለት፡፡ በዚህ ምክንያት ይሉናል ፕሮፌሰር ሞልቨር፤ ተክለ ሃዋርያት በስደት ጅቡቲ ለመኖር ተገደዋል፤ እንዲሁም ወደ ማዳጋሥካር ተሠደው አሥራ አንድ ዓመት በማዳጋሥካር ገበሬ ሆነው ከኖሩ በኋላ፤ ልጃቸው አምባሣደር ግርማቸው ተክለ ሃዋርያት ስልጣንም ገንዘብም ስለነበራቸው ወደ አገራቸው ኢትዮጵያ እንዲመለሱ አባታቸውን ረድተዋል፡ፕሮፌሰር ሞልቨር ለዚህ ጥናታዊ መጽሐፋቸው ይሄን ርዕስ የሠጡት በሁለት ምክንያት ይመስለኛል፡ በኢትዮጵያውያን ጀግንነት በመነካት፤ ወይም በኢጣሊያ ወረራ ወቅት ህዝቡን ለነፃነቱ በድል የመሩት ኢትዮጵያውያን ጥቁር አንበሳ ወይም ጥቁር አንበሶች (Black Lions) ይባሉ ስለነበር፡፡
እንግሊዞች በሮም በጀግንነት የተሰዋውን ዘርዓይ ደረስን ወርቃማው አንበሳ ነው ያሉት “The Golden lion” የአውሮጳ ደራሲያን ከኛ ጋር ተሠልፎ (ዱር ገብቶ) ለኢትዮጵያ ነፃነት የተዋጋውን ነጭ አውሮጳዊ ፋኖ “The Red lion” ነው ያሉት፤ ቀዩ አንበሣ፡፡ ፕሮፌሰር ሞልቨር ደግሞ ኢትዮጵያውያኑን ደራሲያን ጥቁር አንበሶች አሉ፤ “Black Lions”
“Black Lions” በቅርቡ ወደ ኢትዮጵያዊ ቋንቋ ተተርጉሞ በአማርኛ እንደምናነበው ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ይሄ ጽሑፍ ሞልቨር ለኢትዮጵያ ላላቸው ፍቅርና ላሳዩት የምርምር ትጋት ለክብራቸው ይቁምልኝ፡፡
ሠላምዎ ይብዛ! በፍቅር!
Soli. Deo. Gloria!

Read 4381 times Last modified on Saturday, 20 October 2012 11:16