Saturday, 22 October 2022 14:11

11ኛው የዶሮ ኤክስፖና 7ኛው የአፍሪካ የእንስሳት ሀብት ጉባኤ ሀሙስ ይከፈታል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ኔዘርላንድ በብሄራዊ ደረጃ ለሁለተኛ ጊዜ በአውደ ርዕዩ ትሳተፋለች

በኢትዮጵያ የንግድ ትርኢት በማዘጋጀት ቀዳሚ የሆነው “ፕራና ኢቨንትስ” መቀመጫውን ሱዳን ካደረገው አጋሩ “ኤክስፓ ቲም” ጋር ትብብር በየዓመቱ የሚያዘጋጀው  11ኛው የዶሮ ኤክስፖ (Ethiopex) እና ሰባተኛው የአፍሪካ የእንስሳት ሀብት ጉባኤ (ALEC) የፊታችን ሀሙስ ጥቅምት 17 ቀን 2015 ዓ.ም ረፋድ ላይ በኢትዮጵያ ስካይላይት ሆቴል ይከፈታል።
አዘጋጆቹ በሳምንቱ አጋማሽ ላይ በስካይላይት ሆቴል በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳስታወቁት በኤክስፖው የዶሮና የእንስሳት ሀብት ቴክኖሎጂ፣ ግብአትና መፍትሄዎች በስፋት የሚቃኝበትን ይህንን ጉባኤ  ከጥቅምት 17-19 ለሶስት ቀን ያካሂዳሉ ተብሏል።
እነዚህ ሁነቶች በወተት፣ በዶሮና የስጋ እሴት ሰንሰለቶች ልማት ላይ የገበያ ትስስር በመፍጠር፣ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በማስተዋወቅ፣ የእውቀት ሽግግርን በማምጣት፣ የኢንቨስትመንት ዕድሎችን በማስተዋወቅና የዘርፉ ዋና ዋና ተግዳሮቶች ላይ በመምከር የዘርፉን ምርታማነት ለማፋጠንና ለማሳደግ ጥሩ አጋጣሚን እንደሚፈጥሩ የሁነቶቹ አዘጋጅ የፕራና ኢቨንትስ ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ ነብዩ ለማ አብራርተዋል።
በዘንድሮ የዶሮ ኤክሰፖና የእንስሳት ሀብት ጉባኤና አውደ ርዕይ ላይ ኔዘርላንድስ በብሔራዊ ደረጃ ተሳትፎ እንደምታደርግ የተገለጸ ሲሆን፣ ከኔዘርላንድ በተጨማሪም ከ10 ሀገራት ማለትም ከኢትዮጵያ፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን ሃንጋሪ፣ ህንድ፣ ኬንያ፣ ስኮትላንድ፣ ቱርክና ዩናይትድስቴትስ የተውጣጡ ከ70 በላይ ኩባንያዎች እንደሚሳተፉም ተገልጿል። አውደ ርዕዩንና ጉባኤውን ከመላው ኢትዮጵያና ከጎረቤት ሀገራት የሚመጡ ከ4 ሺህ በላይ የዘርፉ የንግድ ባለድርሻ አካላትና ባለሙያዎች የንግድ ግንኙነት ለመፍጠር በዝግጅት ላይ መሆናቸውም ተገልጿል።
ጋዜጣዊ መግለጫው ላይ አንድ እንቁላል ከ13 ብር በላይ እየተሸጠ ባለበት ሀገር የዶሮ ኤክስፖው ምን ፋይዳ ያመጣል በሚል ከጋዜጠኞች ለተነሳው ጥያቄ በተለያዩ ምክንያቶች የእንስሳት በተለይም የዶሮ መኖ በመወደዱ የእንቁላል ዋጋ መወደዱን የገለጹት የኢትዮጵያ  የዶሮ አርቢዎች ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ ኤርሚያስ ዓለማየሁ ምርትና ምርታማነትን በማሻሻል የዶሮን ሀብት ማሳደግና የእንቁላልን ዋጋ መቀነስ ይቻላል ያሉ ሲሆን ለዚህ ደግሞ እንደዚህ አይነት ሁነቶችና መድረኮች መዘጋጀታቸው መፍትሄዎችን ለማፋጠን ይረዳል ብለዋል።
በሶስት ቀኑ አውደርዕይና ጉባኤ ከባለድርሻ አካላት፣ ከመንግስት የስራ ሃላፊዎችና ከፖሊሲ አውጪዎች ጋር የዘርፉ ችግሮች ላይ ትኩረት ያደረጉ ውይይቶችና ንግግሮች እንደሚካሄዱም ታውቋል።

Read 880 times